Tuesday, 11 January 2022 07:01

ወጣቷ ጀግና፤ ከጭልጋ እስከ ጣርማበር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

"እስከመጨረሻው ድረስ ለሀገራችን እንፋለማለን"

ወታደር  እርጥቤ በውቀታው ትባላለች። የ18 ዓመት ወጣትና የአማራ ልዩ ሃይል አባል ናት። ዘንድሮ ጥቅምት 29 ቀን 2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ የነበረች ቢሆንም፣ አገሬ በጠላት ተወርራ የምን ፈተና ነው በማለት ከጭልጋ እስከ ጣርማበር ተፋልማለች፡፡ ይህቺ ወጣት ጀግና ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር በጎንደር ከተማ ተገናኝተው የጦር ሜዳ ውሎዋን፣ ቁጭትና ምኞቷን አውግታታለች። እነሆ፡-

የት ነው ተወልደሽ ያደግሽው?
በጎንደር አካባቢ አርባያ በለሳ ወጣ ብላ በምትገኝና ሮቢት በምትባል ትንሽ የገጠር ከተማ ውስጥ ነው ተወልጄ ያደግሁት።
መቼ ነው ልዩ ሀይልን የተቀላቀልሽው?
ሐምሌ ውስጥ ነው የተቀላቀልኩት፡፡ ከነሐሴ ጀምሮ የልዩ ሀይሉ አባል ሆኜ ስዋጋ ነው  የቆየሁት።
እንዴት ልዩ ሃይሉን ልትቀላቀይ ቻልሽ?
ልዩ ሀይሉን የተቀላቀልኩት የአገር ጉዳይ በመሆኑ ነው። ወንድሞቻችን በወጡበት ሲቀሩ፣ እናቶቻችን በዋልድባ ሲገደሉና በህዝቡ ላይ በደልና ግፍ ሲፈጸም ስመለከት፣ ከፍተኛ ቁጭት አድሮብኝ ነው፣ ህዝብና አገሬን ልታደግ ብዬ የገባሁበት።
ተማሪ ነበርሽ አይደል?
አዎ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩኝ፤ ጥቅምት 29 ማትሪክ መፈተን ነበረብኝ። ነገር ግን በዕለቱ ውጊያ ላይ ስለነበርኩኝ ፈቃድም አልጠየቅኳቸውም። ሰላም ሲሆን እፈተናለሁ እንጂ እንዴት ውጊያ አቁሜ እፈተናለሁ በማለት ነው ፈቃድ ያልጠየቅኩት። ሮቢት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር የምማረው።
ለወላጆችሽ  ስንተኛ ልጅ ነሽ?
ለእናቴ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ። ለአባቴ ሶስተኛ ልጅ ነኝ። ሁለት ታላላቅ እህቶች አሉኝ። ከኔ በታች ደግሞ ሁለት ወንድሞችና ሁለት እህቶች አሉኝ፡፡
እንደሚታወቀው ወላጅ ልጆቹ ተምረው ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ ነው የሚፈልገው። አንቺ ቤተሰቦችሽ ፈቅደውልሽ ነው  ወይስ በራስሽ ፈቃድ ነው ወደ ውትድርና የገባሽው?
መጀመሪያ ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጦርነቱ ተጀምሮ ለልዩ ሀይል አባልነት ልመዘገብ ስሄድ ቁመትሽ አጭር ነው ብለው መልሰውኝ ነበር። እድሜዬም 18 አልሞላም ነበር።  በሁለተኛው ዙር ደግሞ ሀምሌ ውስጥ አባቴን "ልሄድ ነው እዘምታለሁ" ስለው "ዝመቺ የአገር ጉዳይ ነው እኔም እከተልሻለሁ" ብሎ አበረታታኝ። እናቴ ግን ደስ አላላትም ነበር፤ እየከፋት እያለቀሰች ግድ ሆኖባት ነው የሸኘችኝ። ከዚያ በኋላ አባቴ ሚሊሻ ሆኖ ተከትሎኝ መጣ። አባቴ በውቀታው እንዳለው ይባላል። በላሊበላ ግንባር ነበር የዘመተው። አሁን እሱ ወደ ቤት ተመልሷል።
መጀመሪያ የት ግንባር ነበር የዘመትሽው?
መጀመሪያ ላይ ጎንደር ጭልጋ ውስጥ ከቅማንት ጋር ነበር የተዋጋነው። ከዚያ በኋላ ከጭልጋ ሀይቅ ወረባቦ ጊራና ተንታና መቅደላን ይዘን፣ በሰሜን ሸዋ ዞረን፣ ጣርማ በር፣ ደብረሲና ከተማ እየተዋጋን ጠላትን እየጠረግን በመሄድ፣ ቆቦና አላማጣ ደርሰናል፡፡
እንዴት ከአላማጣ ግንባር እዚህ ጎንደር ተገኘሽ?
እንደሚታወቀው የገና በዓል ደርሷል። እናቴም ናፍቀሽኛል እያለች እያለቀሰች ነው። ይህን ለአለቆቼ ነግሬ ፈቃድ ስጠይቃቸው፣ ለአንድ ሳምንት ፈቃድ ሰጥተውኝ ነው የመጣሁት። በዓሉን ከእናት አባቴ፣ ከእህት ወንድሞቼ ጋር ካከበርኩ በኋላ ወደ አላማጣ ተመልሼ ከጓዶቼ ጋር እቀላቀላለሁ።
የአጼ ቴዎድሮስ የቁንዳላ (ጸጉር) አቀባበል ስነ-ስርዓት እንዳለ አውቀሽ ነው በበዓሉ ላይ የተገኘሽው ወይስ በአጋጣሚ ነው?
ከራያ ቆቦ ተነስቼ ስመጣ ለአርበኛ ተሾመ አየለ (ባላገሩ) ደወልኩለት፡፡ በሰሜን ሸዋው ውጊያ ላይ ተገናኝተን ተዋውቀን ነበር። እሱም "የአፄ ቴዎድሮስን ቁንዳላ አጅቤ ጎንደር እሄዳለሁ" ሲለኝ፣ እኔም በዚህ አጋጣሚ የዚህ ታሪክ ተካፋይ ልሁን ብዬ፣ የቁንዳላው አቀባበል ላይ  ተገኘሁ። በጣም ነው ደስ ያለኝ። ተሾመ ባላገሩ ዛሬ በጠዋት (ሰኞ) ወደ አዲስ አበባ በረራ ነበረው። እኔን ከዚህ ወደ ቤተሰቤ ለመሸኘት ነው በረራውን ያራዘመው። በጣም አመሰግነዋለሁ።
እንደነገርሽኝ ከአሸባሪው ህውኃት ጋር በተደረጉ የተለያዩ ውጊያዎች ላይ ተሳትፈሻል፡፡ አውደ ውጊያው ምን ይመስል ነበር?
በየአውደ ውጊያው ያለው ነገር ደስታም ሀዘንም የተቀላቀለበት ነው።
እንዴት? እስኪ ንገሪኝ?
በየግንባሩ ብዙ ድል አስመዝግበናል፤ ብዙ የአሸባሪውን ህውኃት አባላት ደምስሰናል። ከብዙ ቦታዎችም ጠራርገን ገርፈን አስወጥተነዋል። ይሄ የሚያስደስተኝ ቢሆንም በዚያው ልክ ጓዶቻችንን አጥተናል። እኔም ጓደኞቼን አጥቼ ልቤ ደምቷል። ቢሆንም ህይወት ካልተሰዋ፣ መስዋዕትነት ካልተከፈለና ደም ካልፈሰሰ ድል አይመጣምና ጓደኞቼ ጠላታቸውን ገድለው በክብር ነው የተሰውት፤ የክብር ህልፈት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ያጽናናኛል። እኛ ደግሞ እንደ ዕድል ሆኖ ተርፈናል፤ ነገ ልንሰዋ እንችላለን። ብንሰዋም ለሀገራችንና ለህዝባችን ደስ እያለን በኩራት ነው የምንሰዋው። እኛ ስንሰዋ እኛን የሚተካ ትውልድ ሀገሩን ይጠብቃል።
በዚህ ሁሉ ግንባር ስትዋጊ ተመትተሽ ታውቂያለሽ?
የቦንብ ፍንጣሪ መትቶኛል፡፡ ይሄን የደንብ ልብሴን በስቶ ያለፈ ጥይት ስቶኛል (የተነደለ የደንብ ልብሷን እያሳየችኝ) ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከመማረክ ሮጬ አምልጫሁ። #ከነነፍሷ ይዘህ አምጣት፤ ያዛት ያዛት; እያሉ አሯሩጠውኛል። ግን አመለጥኳቸው፡፡
የት አካባቢ ነው ይህ የሆነው?
አንዱ መቅደላ ግንባር ነው። መሳሪያዬን 31 አጉርሼ ዝናር ወገቤ ላይ ታጥቄ ኩላሊቴን ሁሉ ይዞኝ በደንብ አላራምድ ብሎኝ ነበር፤ እና ለመሳሪያዬም ብለው መሰለኝ ሊይዙኝ የነበረው፤ ያንን ጫና ተቋቁሜ እየሮጥኩ እንደገና እየተኮስኩ አመለጥኳቸው። ሌላው ደብረሲና ላይ ነው፤ ከፍተኛ ውጊያ ነበር፤ አንዷ ጓደኛዬ አጠገቤ ተሰዋች። እኔን ሊይዙኝ ሞክረው አመለጥኩና ቦታ ይዤ የገደልኩትን ገድዬና አቁስዬ አመለጥኳቸው። ብቻ ብዙ ዓይነት ነገር ያጋጥማል። እንደ እድል ትተርፊያለሽ እንጂ ያው ጦርነት መግደል መሞት ነው።
ውጊያ ለወንድም ለሴትም ፈተና መሆኑ ይታወቃል። በተለይ ለሴት ደግሞ ይበልጥ ፈታኝ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ በውጊያ ላይ ለሴቶች በጣም ፈታኝ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው?
ውጊያ ላይ ሴት ከወንድ ያነሰ ሚና አይኖራትም። ነገር ግን ለሴት ፈታኝ የሚሆነው ጫካ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ብዙ ነገር ያስፈልገናል። ከሞዴስ ጀምሮ በርካታ ነገር ያስፈልገናል፤ ነገር ግን ህዝባችን ሁሉንም የሚያስፈልገንን ነገር ሲያቀርብልን ነበር። ሞዴስ ሳሙና፣ ቅባት፣ ፓንት፣ ቁምጣ፣ ካልሲና በርካታ ለሴት ልጅ የሚያስፈልግ ነገር በሙሉ ሲቀርብልን ነበር። ህዝቡ ይህን ከማቅረብ በተጨማሪ ግንባር ድረስ እየመጣ ልብሳችንን እያጠቡ፣ ጫማችንን እየጠረጉ፣ ጸጉራችንን ሁሉ እየሰሩና እያስተካከሉ፣ አይዟችሁ እያሉ እያበረታቱና እያጀገኑን አብረውን ተዋግተዋል ማለት ይቻላል። ለደብረ ብርሃን ህዝብ በተለይ ታላቅ አክብሮት አለን። ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ነው የደገፈን። በህዝብ ድጋፍና አበረታችነት እኛም ይበልጥ ጀግነን አሸባሪው ህውኃትን ጠርገን፣ አማራና አፋር ክልልን አስለቅቀናል። ከዚህ በኋላ አገር ሰላም ይሆናል ብለን እናስባለን። ሰላም ካልሆነም እስከመጨረሻው ድረስ ለሀገራችን እንፋለማለን።
እስካሁን ከነበርሽባቸው ግንባሮች የወራሪው ሃይሎች በየትኛው ቦታ ላይ ነው የሚቆጭሽን ጥፋት ያደረሱት?
እነሱ በሁሉም ግንባር ከጥፋት ውጪ የሚያውቁት ነገር የለም። ወረባቦ ጊራና አካባቢ ያደረሱትን ጥፋት አይቻለሁ። ነገር ግን መጨረሻ ላይ ያለ የሌለ ሃይላቸውን ተጠቅመው ሊጎዱንና አዲስ አበባ ሊገቡ ጣርማ በር ላይ ገጥመውን ነበር። ይሁን እንጂ በሰላ ድንጋይም ሆነ በሁሉም አቅጣጫ ሲያዝባቸው መውጣት አልቻሉም። በእኛም በኩል ብዙ መስዋዕትነትና ተጋድሎ ተደርጎ ድል አድርገናል። ደብረ ሲና ላይ ምሽግ ሰርተው ሙሉ ቀን ሲዋጉበት የነበረውን ሰብረን ገብተን ልክ አስገብተናቸዋል። የምንማርካቸውን  እየማረክን፣ እጅ የማይሰጡትን እየደመሰስን ድል በድል ሆነናል።
ስትማርኳቸው ለምን መጣን ይሏችኋል?
"እኛ መዋጋት ፈልገን አይደለም ተገደን ነው፤ ከየቤቱ ግዴታ አንድ ሰው መዝመት አለበት ብለው  እያስገድዱን ነው የመጣነው" ነው የሚሉት። አንድ ጊዜ አንዱን ስጠይቀው “እየተገደድን ከቤት ታንቀን እየወጣን ነው እንጂ ተዋግተን አገር እንደማንገዛ እናውቀዋለን ተውን፤ አትግደሉን; አለኝ። እንደዛም ሆኖ ያጠፉትን ጥፋት እያየሁ ስለቆየሁ አያሳዝኑኝም። እነሱ የእኛን ከማረኩ ያሰቃዩዋቸዋል፤ ይገድሏቸዋል። እኛ ግን ማርከናቸው ምናልባት ትምህርት ቢሆናቸው እያልን ምግብ እንሰጣቸዋለን፤ ውሃ እናቀርባለን፤ ይበላሉ ይጠጣሉ። እንደነሱ የተማረከ ወታደር በፓትሮል አስፋልት ለአስፋልት እየጎተትን ነውር አንሰራም።
አንቺ የኛ ወታደሮች በህውኃት ተማርከው በአስፓልት ሲጎተቱ በአይንሽ አይተሻል?
አይቻለሁ፡፡ ተማርከው ያመለጡና ደግመው ወደ እኛ  የተቀላቀሉ ጓዶቼም ነግረውኛል። ምንም ርህራሄና ስነምግባር የላቸውም። በጣም አስቀያሚና አጸያፊ ድርጊት ነው የሚፈጽሙት። አንድ ሰው ከተማረከና መሳሪያውን ከፈታ በኋላ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳናደርስ በስልጠና ጊዜ በተደጋጋሚ ተነግሮናል። በውጊያ ላይ የማረክናቸውን ወስደን ለጦር መሪዎቻችን አስረክበን ነው ወደ ውጊያችን የምንመለሰው።
ምን ያህል ጠላት ገድለሻል?
በጣም ብዙ ገድያለሁ። በተለይ ጊራና መቅደላ ላይ እግረኛ ውስጥ ሆኜ ብዙዎችን ጠላቶቼን ጥያለሁ። ተሰልፈው ይመጣሉ፤ ያኔ ቦታ ይዤ ብዙ የሀገሬን ጠላቶች እየመታሁ ሲወድቁ አይቻለሁ፡፡ አሁን ገና ነው አጃቢ የገባሁት። አጃቢ ከገባሁ ገና አንድ ወር ነው የሆነኝ፡፡ በእግረኛ ውስጥ እያለሁ በብዙ ግንባር ተሰልፌ ተዋግቻለሁ።
ልዩ ሃይልን ከመቀላቀልሽ በፊት ስለ ውትድርና የነበረሽ አመለካከትና ከገባሽበት በኋላ ያለው ሁኔታ  ምን ይመስላል?
በፊት ልጅ ሆኜም  ፖሊሶች የሚሊተሪ ልብስ ለብሰው ስመለከት፣ ሴቷ መሳሪያ ታጥቃ ሳያት እቀና ነበር። አሁን ላይ አባል ሆኜ መሳሪያውን ይዤው፣ መያዝ ብቻ ሳይሆን ተፋልሜበት በተግባር ሳየው ደስ ይለኛል። ሁለተኛ ደግሞ የአገር ጉዳይ ነው። በሶስተኛ ደረጃ ሚሊተሪው ያለውስ ክብር ብትይ፣ የስንቱ ጀግና ደም ነውኮ የሚፈስበት። ሲቀጥል ሚሊተሪ የደንብ ልብስሽን ለብሰሽ ስትሄጂ፣ ህዝብ የሚያሳይሽ ክብር፣ ፍቅርና አድናቆት ያኮራል። እኔ ገና የ18 ዓመት ልጅ ነኝ፤ ግን ህዝቡ ለኔ ያለው ክብር ልክ እንደ ትልቅ ሰው ነው። ይህን ሁሉ ስመለከት እንኳንም ወታደር ሆንኩ፤ እንኳንም ተዋጋሁ፤ ለህዝቤ ለአገሬ ብሞትም ክብር ነው እያልኩ እደሰታለሁ።
በውጊያው ጓደኞቼን አጥቻሁ፤ ልቤ ተሰብሮ ነበር ብለሻል፡፡ የቅርብ ጓደኛ የምትይው ሰው ከጎንሽ ተሰውቶብሻል?
አዎ ጓደኞቼን አጥቻለሁ። በተለይ በወታደራዊ ስልጠናው አብረውኝ የነበሩና አብረውኝ የተመረቁ ነበሩ። ሌላ ሻለቃ ደርሷቸው የተለያየ ግንባር ላይ ነበርን። ስጠይቅ #እከሌ ሞቷል እከሌ ቆስሏል; ይሉኛል ፤አብረዋቸው የነበሩት። ተመርቄ ከወጣሁ በኋላ ያወቅኳቸው ጓደኞቼ አብረውኝ የነበሩትም ተሰውተዋል። ከነዚህ ውስጥ አንድ ሴት ጓደኛዬ ብቻ ናት የተሰዋችው፤ ሌሎቹ  ወንዶች ናቸው።
ሴቶች በብዛት አይሞቱም ማለት ነው እንዴ?
በእርግጥ ይሞታሉ፤ ግን ለመማረክም ለመተናነቅም ወንዶች ጓዶቻችን ይፈጥናሉ ይሮጣሉ። እኛ ሴቶች ግን አንዴ ቦታና ምሽግ ከያዝን አይተን ነው የምንተኩሰው፤ ብዙ አንሯሯጥም። ወንዶቹ ይበልጥ ስሜታዊ ይሆናሉ፤ እልህ ይይዛቸዋል፤ ገድለው ለመሞት ወደፊት ነው የሚሉት። ከዚህ በተጨማሪ ወንዶቹ እኛ ሴቶቹ እንዳንመታ ደረታቸውን ለጥይት እየሰጡ ይከልሉናል። እንዴት እንደሚጠነቀቁልን ብታይ። እኛን ወደ ኋላ ወደ ኋላ እየተው፣ እነሱ ወደፊት ይሄዳሉ። ጫና ከበረታ እኛም ወደፊት ከማለት አንመለስም፤ አብረናቸው ፊት ለፊት ነው የምንፋለመው። ወደ ኋላ ሁኑ ቢሉንም እሺ አንልም። በዚህ ምክንያት የሚመቱ ሴቶችም ቁጥር ቀላል አይደለም። ብዙ ባልተዋወቃቸውም የተመቱ አሉ። አንዷ የቅርብ ጓደኛዬ ተሰውታብኝ በእጅጉ አዝኜ ነበር። ባንቺ ትባላለች፤ የጎጃም ልጅ ናት። በጣም ነበር የምወዳት፤ ደብረሲና ላይ ተሰዋችብኝ።
እሷ ስትሰዋ ተስፋ አልቆረጥሽም?
እንኳን ተስፋ ልቆርጥ የባስ እልህና ቁጭት በዝቶ፣ ብዙ ጠላቶቼን አርግፌ አርግፌ ጥያለሁ። በዚያ ውጊያ እንደሷ ለመሰዋትና ለሀገርና ለህዝብ ክብር ነፍሴን ላለመሰሰት ወስኜ ፊት ለፊት ተፋልሜያለሁ። እንደ እድል ሆኖ እንደሆነ አላውቅም፣ ይሄው በህይወት አለሁ። አሁንም ቁጭት አለኝ። ምክንያቱም የከተማው እናቶች ሲያገኙንና ያሳለፉትን ስቃይ  ሲነግሩን የባሰ የቁጭት እሳት ነው የሚለቅብኝ፡፡ በተለይ የኮምቦልቻ እናቶች ስቃይ አላቅሶናል። እና አሁንም የህውኃትን አሸባሪ ቡድን ገጥሜ የእናቶቼን ስቃይ መበቀል ነው የምፈልገው። በተለይ በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሱት ግፍና መከራ፣ ርህራሄዬን አማጦ ነው የወሰደብኝ። ይሄ ሁሉ እንኳን ተስፋ ሊያስቆርጥ፣ ሄጄ ግንባር ላይ ልሙት ነው የሚያሰኝሽ።
ከሳምንት በኋላ ወደ አላማጣ ተመልሰሽ ልዩ ሃይሉን ትቀላቀያለሽ?
አዎ ለስምንት ቀን ነው የተፈቀደልኝ። ከዛ በኋላ አጃቢ ላይ ከተመደብኩ አንድ ወር ሞልቶኛል ብዬሽ የለ፤ወደዛ ሥራዬ እመለሳለሁ፡፡
እስኪ ለሀገርሽና ለህዝብሽ ያለሽን ምኞት ግለጪ?
ለአገሬና  ለህዝቤ ሰላምን እመኛለሁ። የተሟላ ሰላም እስኪመጣ ድረስ ያለ የሌለ ሀይሌን ተጠቅሜ እፋለማለሁ። ለሀገሬና ለህዝቤ ህይወቴን እስከመስጠት ድረስ የምሰስተው ነገር የለም።
ትምህርትሽ አገር ሰላም እስኪሆን ድረስ አይቀጥልም ማለት ነው?
አዎ፡፡ በእርግጥ ዶክሜንትሽን ይጻፉልሽና ጥቅምት 29 ፈተና ያልወሰዱ እንደ ደሴና ኮምቦልቻ ያሉ ከተሞች ተማሪዎች በወረራው ሳቢያ ስላልተፈተኑ፣ አንዱ ቦታ ትፈተኛለሽ ብውኝ ነበር። ነገር ግን የአገር ሰላም ሲረጋገጥ እደርሳለሁ። ያኔ እፈተናለሁ። አገር ሰላም ሳይሆንና ሳይረጋጋ ብፈተንም ብማርም ዋጋ የለውም።
በመጨረሻ ምን ትያለሽ?
ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋሁ። በውጊያ ጊዜ አንድም የጎደለብን ነገር የለም። በአጠቃላይ ህዝቡ ጦርነቱን በተለያየ መልኩ ተዋግቷል ማለት እችላለሁ።
ለእኛ ለሴት ወታደሮች የተለየ ክብርና እንክብካቤ ተደርጎልናል፡፡ እጅግ አመሰግናለሁ፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም የገና በዓል እንዲሆንላቸው እመኛለሁ፤ እወዳችኋለሁ።

Read 4080 times