Tuesday, 11 January 2022 07:03

የሥነጽሁፍ ዳሰሳውን ለመዳሰስ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ የጥበብ ዓይናችንን ልንገልጥ የረዳን፣ ሌሎችም ብዙ ቡቃያዎች አብበው ፍሬ  አዝለው ላገር ያካፈሉበት ማዕድ ነው፡፡ ስለዚህም እኔ የቀዳሚዎቻችን እግር ተከትለን መዓዛቸውን ናፍቀን፤ ጉርሻቸውን ተቀብለን ድክ ድክ ብለንበት ቆመን ሄደናል …ዛሬም ወደፊትም ይኸው መንገድ፣ ይኸው ፋና ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ፡፡
እኔ በግሌ ብዙ ዝንባሌዬ ወደ ጥበቡ ስለሆነ የጥበብ አምዶችን ለንባብና ፅሑፍ አዘወትራለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ማኅበረሰብንና ፖለቲካን ዘልዬ የማልፍበትም አንጀት የለኝም፡፡ በተለይ ሀገሬ ጫንቃዋ ጎብጦ እንባ በጉንጮቿ በሚዝረበረብባቸው ቀናት፣ ድንኳኗ በጣር ተሞልቶ ልቧ በትዕቢተኞች ሲረገጥ፣ ሠፈሬም ባይሆን ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ ለመፃፍ ሞክሬያለሁ፡፡… ግን ዋናው ሠፈሬ ጥበቡ ነው፡፡
የዛሬ ፅሑፌም እዚሁ ጥበብ ሠፈር ነው።…. መነሻዬም የታህሳስ 9 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ የሳሙኤል በለጠ ፅሑፍ ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ የሚያትተው፣ ስለ ስንቅነህ እሸቱ ድርሰትም ስለ ኢምፕሬሽኒዝምም ነው፡፡ ጠበቅ ያለው ጉዳዬ ፀሐፊው ከነስብሃት ጀምሮ የቀድሞ ደራስያንን አንስቶ ታላላቆቻችን ካላቸው በኋላ ‹‹ሌሎች ሥራቸውን ያልመረመረላቸው ታላቅ ደራሲዎች›› ብሎ፣እሸቱ (አታሞ ፑልቶ) ሌሊሳ ግርማ፣ዮሀንስ ሀብተ ማሪያም፣ዮናስ ኪዳኔ የመሳሰሉ…ይለናል። ለኔ መጣጥፉ በጥሩ ሁኔታ የተጻፈ፤ፍሰቱ ደስ የሚል፣ብዕሩ የዳሰሳቸው ሀሳቦችም ተገቢ ናቸው፡፡ የልብ ቅንነትና ጥበብ ወዳድነትም፣ፍትፍት ብለው ይነበቡበታል። ይሁንና ጥንቃቄም የሚያሻቸው ጉዳዮች እንዳሉበት አስተውያለሁ፡፡ እናም ጥንቃቄዎችን በየተራ ማየት የዛሬ ዓላማዬ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ቀጥታ ያለምክንያትና ማሳያ ‹‹ታላቅ›› ባይልም፣አብደላ እዝራ ደማቅ አድርጎ በስም ለሚያስቀምጣቸው ገጣምያን መመዘኛ እንዲያስቀምጥልኝ በዚሁ ጋዜጣ ላይ በጽሑፍ ጠይቄው ነበር፡፡ ምክንያቱም የሚመጣው ጣጣና በትውልድ ላይ የሚፈጥረው ስህተት ቀላል አይደለምና!
ስለዚህ መቸም ቢሆን “ታላላቅ” ስንል፣ ላልናቸው ደራስያን በቂ ማስረጃዎችና ማሳመኛዎች ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
ለምሳሌ፡-
በቅርጽ ከሆነ የዶክተር ኃይሉ አርአያን ማሳያ እንኳ ብናይ፡
የቦታ፣የይዘት ክልል፣ዋህድነት(Organic unity)……፣ጥልቀት፣(complexity…ለውጥ (varaiety)፣ አንድ ወጥ ዕድገት (Evolutionary development)፣ ሚዛናዊነት (Balance) ወዘተ ማየት ግድ ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ድርሰቶቹ የተፃፉበት ዘውግ፣ዘውጉ የሚፈጥረው ውበትና የይዘት ልዩነት መፈተሽ፤ለምሳሌ..
ግጥም ቢሆን ታላቅ ገጣሚ ለመባል ያበቃው ምኑ ነው?... ንዑስ ዘውጎችስ እነማን ናቸው፡፡ በየዘውጉ የቃላት አጠቃቀም Rhythmical language፣ የስሜት ከፍታና ዝቅታ፣ የተራኪው አንጻር ምርጫ (በአብዛኛው) ስለሚለያዩ.. (ተራኪ ግጥም እንደ ሌሪክ በዜማና በዘይቤያዊ ቃላት መነከር አይጠበቅበትም) ስለዚህ ምክንያቱን ከዘውጉ ጋር አያይዞ ማሳየት ይጠይቃል፡፡
ግጥም በዚህ ዘመን በአብዛኛዎቻችን ዘንድ እንደሚታሰበው፣ ሀሳብ ብቻ ያለመሆኑ ማጤንና፣ የግጥም ስያሜ መነሻ ሳይቀር ምክንያቱ ዜማ በመሆኑ በዜማና በአሰራ… የውበት መግለጫዎችንና -አደራጃጀቶችን ሳይቀር መወሰንና የምዘናውን ውጤት በምክንያት ማስቀመጥ፡፡ ማለትም ከድምፅ ጀምሮ ቃል፣ ስንኝ፣ ዐርኬ ድረስ ሄዶ፣ የገጣሚውን ልክ - በመረጃ ማሳየት፡፡
በቤት ዓመታት፤ ቤት ዓመታቱ ለዓይን-ይሁን ለጆሮ፣ አሊያም-ልብ፤ መመዘን፤ ‹‹የሀሀ ሀሀ›› ቤት ነው፤ (ይህ ፍዝ ወይም ተደጋጋሚነቱ አሰልቺ ነው) የ‹‹ሀለ ሀለ›› ቤት ነው? ይህ ጉራማይሌ በመሆኑ ስሜት ያነቃቃል፤ ሙዚቃው ልብ ይሰርቃል፡፡ እናም እነዚህ በግጥም ውስጥ ዋጋ አላቸው፡፡
ወደ ስነ - ልሳናዊ ጉዳዮች ከገባን- የአናባቢዎችን የድምፅ ከፍታ፤ ድምቀትና ፍዘት፤ በቤት መምቻ ላይ የከፊል አንባቢዎች ምርጫና፣ የግጥሙን ከፍታ መለካት። ይህ ጉዳይ ከሀገር ሀገር የሚለያይ ነው፡፡ እንግሊዝ ከጣልያንና ከፈረንሳይ ግጥሞች የምትለየውም በዚሁ ሰበብ ነው። እኛ አገር ስንመጣ ፍንጽቆችንም ግምት ውስጥ ማስገባት ይጠይቃል፡፡ ..በተጨማሪም አንጓዊ መዋቅሩን፣ የስንኞች መጠን፣ በቤት ዓመታት፣ በምጣኔ ስልት፣በአዝማች አቀማመጥ ወዘተ ልናየው ይገባል፡፡ የጎንዮሽና የወርዳዊ ግጥምሞሽን፣ ስሜት፣ በዐርኬዎች መካከል የሚኖረው መሸጋገሪያ ለጊዜ፣ ለሃሳብ ፋታ ሰጪ መሆኑን መገንዘብ። (በአጠቃላይ - አሰነኛኘቱ ምን ያህል ተሳክቷል” ብሎ የቤት ዐመታት ድንጋጌን በማየት የገጣሚውን ርምጃ መለካት)
ተናባቢ ድምጾች ለግጥም ቤት መምቻ ትርጉም እንዳላቸው መርሳት የለብንም፤ እነርሱም በሶስት ተከፍለው እግድ ወይም ፈንጂ፤ ሹልክልክ፤ ከፊል አናባቢ በመባል ተለይተው በተግባራቸው ልዩነት ያመጣሉ።
እግድ፣ አየር በምላስና በድድ፣ በምላስና በጥርስ፤ በምላስና በትናጋ ታፍኖ ሲለቀቅ፤ ከንፈር ተጋጥሞ ሲለቀቅ የሚፈጠሩ ሀይለኛ ድምጾች ናቸው፡፡
ሹልክልክ የሚባሉት፣ በአንድ ቦታ ታግዶ የነበረው አየር ቀስ በቀስ እየለቀቀ ሲወጣ የሚፈጠሩ ድምጾች ናቸው፡፡
ከፊል አናባቢዎች ደግሞ በአናባቢና በተናባቢ መካከል ያሉ ድምጾች ሲሆኑ፣ በዙሪያቸው ባሉ አናባቢዎች ተጽዕኖ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡
እንግዲህ በግጥም ዜማ ላይ እነዚህም ተጽዕኖ አላቸው ማለት ነው፡፡
ሌላው፣ በግጥም ባህሪያት ውስጥ የትኞቹን - ተጠቅሟል?... በየትኞቹ ተሳክቶለታል? ሙዚቃዊነቱ፣ ድድርነቱ፣ ምናባዊነቱ፣ ተጨባጭነቱን ማሰብ! ማመዛዘን፤ ባብዛኛው እንደሚታወቀው፤ ቃላት አጠቃቀሙና ገለፃው፤ ‹‹ከቃል መርጦ ለኪነት›› ለግጥም መጣኝ ነው ወይ?.. የሚለውን ማየት ማነጻጸር፤የቱን የቱን ዘይቤ ተጠቅሟል፡፡ በዚያስ ገለፃና ቃላት ምሰላው ምን ያህል-ወደ ስሜት ሕዋሳታችን-ዘልቋል?...
ከዚያ በኋላ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ባህሪያትና አላባውያን የገጣሚውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ምን ያህል ተሳክቶላቸዋል?... ብለን ከለየን በኋላ “እገሌ በዚህ ምክንያት” ታላቅ ገጣሚ ነው ብንል አሳማኝ ነው። ስለዚህ ሳሙኤል በለጠ “ታላቅ ገጣሚ” ሲል በየትኛው መመዘኛ እንደሆነ ማሳየት ለሁላችንም ይጠቅማል፡፡…. ደስ ያለን ግጥም ሁሉ ታላቅ ግጥም የማይሆነውም ለዚህ ነው፡፡
ዛሬ እነዚህ ማንሳት የፈለግሁት ለሳሚ ጽሑፍ መልስ ለመስጠት አይደለም፤ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ (እጅግ ጥቂቶች ካልሆኑ በቀር) ስለ ዘውጉ ያለን ዕውቀት መሰረቱን የለቀቀ ሆኖ ስለሚታይ ነው፡፡ አንዳንዴም ስለ ግጥም ሙዚቃ ሲነሳ፤ ስለ free verse` እያወሩ በዚህ ቋት ሊከትቱ የሚሞክሩ ብዙ ስላሉ ነው፡፡ …እናም ብቻ የግጥምን ቀሚስ ገልበን፤ ውበቱን ገፍፈን ብናሳንሰው አላውያን መሆናችን ነውና በወጉ ብንመዝን እመርጣለሁ፡፡
ስለ ድፍንፍን ኂሳችን ስንጸጸት የቀደመው የአማርኛ ስነ ግጥም ልምዳችንን የጥንቱ የግዕዝ ስነጽሑፍ የሚከነዳው ይመስለኛል። በተለይ ከስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ እንደ አዲስ ብቅ ያለው መንፈሳዊው ስነ ጽሁፍ ከአምስቱ ዘውጎች አንዱ የሆነው ቅኔ የተሻለ ነበረ፡፡
በዘመኑ ገድላትን፣ መዝሙራትን፣ ተዐምራትን መኄስ የተለመደ ባይሆንም ቅኔ በቋንቋ ቅርጽ ላይ፣ በዘረፋና በነገራ ጊዜ፣ ዜማ በመስበር፣ ተነሺና ወዳቂውን በመለየት፣ አሊያም የሃሳብ ስርቆት ወይም ፕላጃሪዝምን ይተቻል፡፡ በአንድምታ ኂስ ብዙም ያልተለመደ ቢሆንም ከታወቁት ጠበብት ከዮሃንስ አፈወርቅና ቄርሎስና አትናቴዎስ መስመር ፈካሪ ከሆነ እንደሚተች ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ …ይህ ግን ሰለጠነ ባልነው ዘመን አይታይም፡፡
አንዳንዴ ልክ እንደግጥሙ የዚህ ዘመን ስካርና አንድ መስመር ብቻ ይዞ መንጎድ የፈጠረው ብዥታ ያለ ይመስለኛል። ይህን ብዥታ በአጫጭርና ረዣዥም ልቦለዶቻችን ምዘና ብዙ ጊዜ ታዝቤዋለሁ። እንዳስተዋልኩትም ፍልስፍናና ስነ-ልቦናዊ ጥያቄ አዘል ድርሰቶች ሁሉ እንደ ቁንጮ ድርሰት ተደርገው ይወሰዳሉ። ደራሲዎቻቸውም እንደ ፈላስፋና ታላቅ ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ ይሁንና ይህ የግለሰቦች ስሜትና የዘመን መንፈስ ብቻ ነው፡፡ የዘመን መንፈስ ከቀደመው ስነ ፅሑፋዊ መሰረት ሥሩን ያበቀለበት የታሪክም አጋጣሚ የለም፡፡ ሃያሲው ቲ ኤስ ኢሊየትና መሰሎቹ እንደሚሉት፤ ሁሉም ድርሰት መሰረቱ የቀደመውን ሥራ ነው፡፡ ዛሬ ሌላው ዓለም  ያገኘው፣  በእኛም ሀገር አንገቱን ብቅ ያደረገው ድኅረ ዘመናይ ስነ-ፅሑፍ እንኳ የበቀለው ዘመናዊነት ላይ ነው። ስለዚህ በዚህ ዘመን የሚፃፉ ድርሰቶችም የሚመዘኑት በየተፃፉበት ዘውግና ዐውድ ነው፡፡
ለምሳሌ ታሪካዊ-ልቦለድ ድርሰት ስንፅፍ፤ ያንን ድርሰት የምንመዝንባቸው መመዘኛዎች አሉ፡፡ አለዚያ የኛ ስሜት ፍልስፍና ስላማረው፤ ወይም ዝንባሌያችንም እርሱ ስለሆነ “ይህ ድርሰት አይረባም!›› ልንል አንችልም፡፡ ይልቅስ የኛ ድርሻ ዘውጉ የሚጠይቀውን አሟልቷል ወይ ብለን መጠየቅ ነው፡፡ ታሪካዊ ልቦለድ ሲፃፍ፤ በታሪክ ውስጥ የነበሩ ሁነቶች ሲከወኑ ተዋናይ የነበሩና በታሪክ ውስጥ የኖሩ ገፀባህሪያትንና የጊዜውን አጠቃላይ ዐውድ፣ ስነ ልቦና ባህል የቃላት አጠቃቀም፣ ልብ ሰቀላ ወዘተ ከማየት በቀር አንዳች ውስብስብ ፍልስፍና አንጠብቅም፡፡ እንደዚያ ከሆነ ደግሞ በቅርብ ዐመታት እየሰፋና እየበዛ የመጣውን ስነጽሑፍን ከተለያዩ ዲስፕሊኖች ጋር የማጣመር ሂደት ወስደን አንድ ስርቻ ልንወሽቀው ነው፡፡ ግን አይሆንም!
ድርሰታችን ታሪክ ቀመስ ልብወለድ ከሆነም በተመሳሳይ የራሱ መመዘኛ አለው። እነዚህ ድርሰቶች ያለፉ-ሁነቶችን በፈጠራ ምናብ አጣፍጠውና አጣጥመው - እንደ ተንቀሳቃሽ ስዕል በልባችንም ይኖሩታል። ደግሞም ጆን - ሔርሴይ--- እንደሚሉት ታሪክ አጥቃሽ ናቸው፤ አይረሴም፡፡
 “Most of us know what little we do of the Napoleonic wars, not from histories, but from Tolstoy war and peace of the American civil war, not from Tolstoy’s war and tray commentaries on that to military. War, but from carnies the red badge of courage and the stories of Ambrose Bierce and Margaret Mitchell’s Gone with the Wind;
ወደ እኛ ሀገር ስናመጣው የ1960ዎቹን የወሎ ድርቅና ረሀብ፤ የአብዮቱን ፍንዳታ ዋዜማና ማግስት ከታሪክ መፃሕፍት ከማንበብ ይልቅ የብርሃኑ ዘርይሁን “ማዕበል” በሦስት ጥራዝ ማንበብ የተሻለ ትውስታ ትዝታና ጣዕም ይኖረዋል፡፡
ታዲያ ብርሃኑን የምንመዝነው በምንድን ነው?... በታሪካዊ ሁነቱ፤ በታሪኩ መቼት፤ በገጸባህሪያት አሳሳሉ፣ በዘመኑ መንፈስና ዐውድ፣ በፖለቲካዊና ማህበራዊ ገፅታው አቀራረብ?... እነዚህ መፃሕፍት ውስጥ ደራሲው ገብቶ ፍሬድሪክ ኒችን፣ ጆን ሎክን፣ ጆን ሮዊ፤ ወይም ፕሌቶና አርስቶትል፤ አሊያም ዲበ አካላዊነት፣ ስነ ዕውቀት፤ ስነ ፋይዳ ሥነ - አመክንዮ አጣቅሶና ፈትሎ እንዲያቀርብልን አንጠብቅም፡፡… ፍልስፍና ራሱን የቻለ፣ ልክ እንደ ስነ ልቦና ሳይንስ ከሌላ ሳይንስ (ስነመለኮት) የተወለደ ዲስፕሊን ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ድርሰት በፍልስፍና ስለታመቀ፣ ድርሰቱ ታላቅ ሊባል አይችልም፡፡ ድርሰቱን ታላቅ የሚያሰኘው በራሱ መታገጊያ ውስጥ በሚኖረው የተዋጣ ስራና ምናብ ነው፡፡
በግጥም ዘውግም ውስጥ-ፍልስፍና ለሚጠማን ራሱን ችሎ ‹‹ዲበ - አካላዊ ግጥም›› ስላለን ያንን ንዑስ ዘውግ መርጠን ጥማችንን ልንቆርጥ እንችላለን፡፡ በሁለንተና ባንስማማም ፍልስፍና ውስጥ ገብተው ሆድ በሚያባባና በሚስረቀረቅ ድምጸትና ጥያቄን በሚፈትል ግሩም ፈለግ፣ ኤፍሬም ስዩምና ዳዊት ጸጋዬ  ነፍስ የሚያማልል በገና አላቸው፡፡ ስነ መለኮታውያን እንደሚሉት ነፍስ ያለችው እዚህ ስፍራ ነው፡፡
 ፍልስፍና ለሀገራችን አዲስ እንዳይሆን አድርጎ የሰራው የአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ተጠባቢ ዘርዐ ያዕቆብ  ነው፡፡…
አለዚያ ፍልስፍና የስነፅሑፋችን ሁሉ ጌታ ከሆነ ዐለም ላይ እነ ጆን ሚልተን የነገሱበት “EPIC” ግጥሞችን ፍልስፍና የላቸውም ብለን ልናሽቀነጥራቸው ነው። ስለዚህ ድርሰት ታላቅና ምርጥ የሚያሰኘው ፍልስፍና መያዙ አይደለም፤ ሁለንተናዊ ተዋጽኦው እንጂ!  በዚህ ዓይነት ሃሳቦች ላይ ብቻ ተንጠልጣይ ከሆንን ፈረንጆቹ (message hunter) ብለው የሚያስጥቷቸውን ዓይነት መሆናችን ነው፡፡
መነሻ አድርጌ የተነሳሁት የሳሙኤል በለጠ ዳሰሳ ፣ የከያኒ ዳሰሳ  ሀዲድ አይደለም። በጥቂቱ የስነ-ጽሁፍ መምህራንን አይነት መዋጮና፣ ከፊል የፍልስፍና ምሁራንን መንገድ የያዘ ነው። ስለዚህም አንድ ቦታ ስለ ስንቅነህ እሸቱ ፍልስፍና አንስቶ ሌላ ቦታ ወደ ውስጥ ሳይገባ የደራስያኑን ሀሳቦች ይጠቃቅሳል። ከላይ “ታላቅ ደራሲዎች” ካላቸው በስተቀር በይፋ ዳኝነት የሰጠበት ቦታ የለም። ከጋዜጣ ገጽ ውስንነት አንጻር ወይም ከዓላማ አንጻር በቂ  ነው። (ምናልባት ይዞት ስለተነሳው ደራሲ በቂ ማሳያ ሳይሰጥ በሌሎች ገጣምያንና ደራስያ ስራ ---- ዓላማውን ከግብ እንዳይደርስ ቢገዳደረውም፣ የተነሳበትን ስነጽሁፋዊ የፍልስፍና ዘርፍ ሊያሳይ ሞክሯል። በተለይ ኢምፕሬሽኒዝምን  መልክ አድርጎ ማሳየቱ ከሌላ ዲስፕሊን ጋር ያጠላዋል። ይልቅስ ኢምፕሬሽኒዝም “ደራሲው የተሰማውን ስሜት በጥሬ ሳይገርዘው እንደሚያቀርበው መናገሩ ትክክል ነው። በግለሰቡ ፍላጎትና የስሜት ግለት ላይ የተመሰረተ ነውና!
እንዳለውም መነሻውም  የጣሊያን ሰፈር ነው። ክላውድ ሞኔት፣ ማኔት፣ ዴጋስ፣ ሬይኖር… በዘመኑ የነበሩ ላይ አምጸው ብቅ ያሉ ናቸው። ዋነኛ ዓላማቸው ግን በስዕል ስራቸው ስለሚኖረው የብርሃን አጠቃቀም ነው። ከአተያይ ይልቅ ድባብ ላይ ትኩረት ያደርጉም ነበር። ዛፉን ከመሳል ይልቅ የተጣለው የፈጠረውን ስሜትና ውጤት የሚል ፍልስፍና ነበራቸው። ይህ ነው ወደ ስነ-ጽሁፍ ሰፈር የመጣው።
ስነ-ጽሁፍ ሰፈር ከመጣ በኋላ ወደ ቨርጂኒያ ወልፍ ሰፈር ገብቶ የነሲግመንድ ፍሮይድን ሳይኮ አናሊሲስ አጥቅሷል። እነ አድለር፣ ዩንግና እነዚህ ገመዳቸው ሲሳብ Stream of conciousness ውስጥ ይገባሉ። እዚህ ውስጥ ያሉ ባህርያት ደግሞ ለድርሰቱ ሴራ ግድ የላቸውም፤ ምክንያታዊነት አያውቁም፣ ይልቁኑስ እንደ ደመና ይበታተናሉ። ውስጣዊ መነባንብንም ያዘወትራሉ። ይህም ማለት በክብ ገጸባህርያቱ ውስጣዊ ሕይወት ላይ ያተኩራሉ። ገጣምያኑ የፈረንሳይ የተምሳሌት ፈርጦች የእንግሊዙ ኦስካር ዋይልድ፣ አርተር ሲሞን ከዚህ ገበታ ይቆርሳል።
ታዲያ ይህ የስነ-ጽሁፋዊ ፍልስፍና ስለመጣ እውነታዊነት የስነጽሁፍ ፈርጅ በዚህ ዘመን ተጥሏል ማለት ነው?... አይደለም!
ሳሚ የጠቀሰው የደራሲው ሀሳብ እንዲህ ይላል “… ልብ ወለድ የሰውን ልጅ ዘወትራዊ የህይወት ስንክሳር ከነግብስብሱ የመከተብ ተግባር” (reporting) ሳይሆን ላቅ ያለ ፍስፍናዊ ይህ ግን በእውነታዊነት ስነጽሑፍ ሲታይ ግጭት አለው፤ዘውጉ ሌላ ሚዛን አለውና፡፡
ርዕሰ ጉዳይን በተዋበ ቋንቋ ሰንዶ የማቅረብ ተግባር ነው። ይህ ደግሞ ከእውነታዊነት ጋር ይጋጫል፡፡ ዘውጉ ሌላ ነዋ!
What this audience most desired, interestingly, were not fanciful works that would take them away from their daily concerns.
As newly awakened, increasingly powerful social force, they wanted to study themselves. Art became, for a time, a kind of looking glass held up to the world.
እንግዲህ እውነታዊነት ዐውዱና ምርጫው እንጂ ፍልስፍናው አይወስነውም።
ይህ ሃሳብ የሳሙኤል በለጠ አይደለም። ስለዚህ ሙግቴ በሳሙኤል ሳይሆን ሳሙኤል ከጠቀሰው ፀሐፊ ሀሳብ ጋር ነው። ልብ ወለድ የግድ የጦዘ ፍልስፍና ሊኖረው አይገባም። ታሪክ ቀመስ፣ እውነታዊነት፣ ታሪካዊ ወንጀል ነክ፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል። የተለያዩ ቅርጻዊና ጭብጣዊ ዘውግ ሊጻፍ ይችላልና… መደምደሚያ መስጠቱ ተገቢ አይመስለኝም፤ አይደለምም!
ዘመናዊ ስነ-ጽሁፍ የድህረ ዘመናዊነት መሰረት ሆኖ የበቀለው በሃያኛው ክፍለ ዘመን ማለዳ ነው። ሲነሳ ደግሞ ያን ለውጥ የፈጠሩ ዓለማቀፋዊ ሰበቦች ነበሩት። ከነዚህም ውስጥ በምዕራቡ ዓለም የተነሳው የኢንዱስትሪ አብዮትም ንቅናቄው የተፈጠረው ጠንካራ የኢኮኖሚ ውድድርና የአፍሪካና የእስያን ጥሬ ሃብት የመቀራመት ፍትጊያ፣ በ1905 ዓ.ም ተሞክሮ የከሸፈው የሩስያ አብዮት ያኖረው ቁስል የአውስትሮ ሀንጋሪ ብሔርን መሰረት ያደረገ ግጭትና ግጭቱ ያመጣው ቀውስ መወሳሰብ፣… ቀደም ሲል “እግዚአብሔር ሞቷል!” የሚለው የፍሬዴሪክ ኒች ፍልስፍና፣ የዘመኑን አዲስ አስተሳሰብ በህብረተሰቡ መካከል መዝራቱ የሰው ልጆች የራሳችን ችግር ፈቺዎች ራሳችን ነን ብለው ብቻቸውን መቆማቸው ይጠቀሳል። አንድ ደራሲ እንዲህ  እንደጻፉት፤ “ We could no longer look to God for solace and sense of meaning that we must henceforth accept that we are alone on the earth!”
እና በዘመኑ ማቴሪያሊዝምና ራሽናሊዝም መስፈኑና ከዚያ በኋላ፣ የሰው ልጅ እውቀቱን ምርኩዙ አድርጎ ዓለሙን ለመዋጀት ራሱን እንደሰንደል ለኩሶ መጤስ መርጧል። ለጥቆም፣ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ መጥቶ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲከሰት እውቀቱ ሳያድነው ቀረና ዓይኖቹን ወደ ሌሎች አማራጮች ማንሳት ቃጣው፤ ድልድዩ ፈርሶ፣ ድልድይ ተገነባ… እናም ሌላ ቀን መጣ፣ ሌላ ፍልስፍና፤ ቀደም ያለው እውነታዊነትም የራሱ ሰበብና መልክ አለው።

Read 755 times