Print this page
Tuesday, 11 January 2022 07:13

አሁንና እኛ

Written by  ፉአድ ተሾመ
Rate this item
(3 votes)

«አዬ  እድል!  አዬ   እጣ!
ምን   ቢያምሩ   ባል  አይመጣ።»
እንድትል   አኳኋኑ  አላምራት  ቢል  ጊዜና  ነው!  ያለ  ወጉ   መቸ  ይሰምራልና።  ወግ  ማጣት  ለፍላፊም  ያደርጋል።  ሀገር  ምድሩ  የሚጠመድበት  ወሬ   አለማጣቱ  ያስደሰተው  ይመስላል።  የወሬ   ሱስ  ቶሎ   የማይለቅ  የድብርት  አለቃ  ኾኗል።  የባለጊዜዎችም  መፈንጫ  ነው።  
«የሌሊቱ  ዝናም  ምንም  አላ‘ረገኝ፣
  ቀን  የጣለው  ነው  የደበደበኝ።»  እንዲል።
«ጦርነት   ሲኖር   ፖለቲከኞች   ታላላቅ   ሰዎች  ይኾናሉ። …  ጦርነትም  ሁኔታዎችን   ይፈጥራሉ። ሰዎች ጨቋኝና መሪዎች   እንዲኾኑ ሁኔታዎችን ያመቻቻል።» ይላል  ኦሾ። ሰዉ ሁሉ  ፖለቲከኛ  አዋቂ፣  ፖለቲከኞች ደሞ የመሪዎች ቁንጮ  ኾነው  በዚህ  ጊዜ ይታያሉ። ሁሉም አዋቂ  ኾኖ  ያወራል፤ ይተነትናል። መደማመጥ   የጎደለው ወሬ። ስለምን ማውራት እንደሚፈልጉ  ግን  ማስተዋል  አለመኖሩን  መገንዘብ  ይቻላል።  አብዛኛው ተንታኝነትን መላበስ እንጂ  ከዚያ  ባሻገር  ስላለው  ጥልቅ  ነገር  መረዳት  የለውም።
“ነገርን ከስሩ ውኃን ከጥሩ” የሚል  ብሒል ከተዘነጋ አንድ ትውልድ  የተሻገረ  ይመስለኛል።  ወሬዎች  በሙሉ  አሰልቺዎችና  ፍሬከርስኪ   የኾኑ   ነገሮች  ስብስብ   ናቸው።  ሁሉም   አዋቂ፣  ሁሉም  መሪ፣  ሁሉም  ተንታኝ፣  ሁሉም  ጠበቃ፣  ሁሉም   አንቂ …  በሆነበት  ሐገር   ሰላም  ይሰፍናል  ማለት  ዘበትነት  ነው።  “ላም   አለኝ   በሰማይ…»  ይሉት  ተረት  ያስተርታል።  ደራሲው   እንዳለው፤  እንዴት   ሰው   ጆሮ   መኾን  ይከብደዋል።  ሁሉም  እንደ “አፍ” ይሰራዋል።  ከተማው   የተረበሸው  በጫጫታ ነው።  ፍርሃት   ፍርሃት  የሚሰማኝ ሁሉም  አውቃለሁ  ማለት  ሲጀምር  ነው።  የሕብረተሰቡ   መግባቢያ   ቋንቋ  ፖለቲካ   መኾኑ  በራሱ  ያስደነግጣል።
አንድነትን   ማጥበቅ   የምንችለው   በፍቅር   እንጂ   በጦርነት   አይመስለኝም።  ጦርነት   መንገድ  ሲኾን  እንጂ  መዳረሻ  ሲኾን   ታሪክ  አያስረዳንም።  ጦርነት   ያናንቃል።  በጦርነት  ትርፉ  ጥላቻና   ቂም  በቀልነትን  በሕዝብ   ላይ  ማስረፅ  ነው።  
«ክፉ  ጊዜ   የተኛውን  ሕሊናና  ያንቀላፋውን  አዕምሮ  የሚቀሰቅስ  ነው»  ይላሉ  ፕ/ር  መስፍን    ወ/ማርያም  በአንዱ   መፅሐፋቸው።  ነገር   ግን   በዚህ   ጊዜ  የነቃውን  ሕሊና  እና  አዕምሮ  ማግኘት  ይቸግራል።  
"ኩርፊያ   የሸፈነው  ፈገግታ"   መፅሐፍ  ላይ  ደራሲ  ሥዩም  ወልዴ  እንዲህ   ይላል፡- «ከተገነዘብኳቸው  ነገሮች  አንዱ  በራስ  የመተማመናችንን  ሁኔታ   ነው።  ገፅታችን  ላይ  ሲታይ  ኢትዮጵያዊያን  ሁሉ  ኩሩነት፣  ብልህነት፣  ቀናነት፣  ትጉህነት፣  ታታሪነት፣ ደግነት፣ ሥልጡንነት፣ ተግባቢነት፣  አትንኩኝ፡  ባይነት፣  ነፃነት ወዳድነትና  ለክፉ  ጊዜ  ደራሽነት  ወዘተ… የመሳሰሉት  በጎ  ባህርያት  የተላበስን  ስንመስል  በውስጣችን   ግን  ተጠራጣሪነት  ፈሪነት፣  መስሎ   አዳሪነት፣  ደበኝነት፣  እወደድ  ባይነት፣  ድብቅነት፣  ግብዝነት፣  አሳችነት፡  ወዘተ… የመሳሰሉት  ባህርያት  ይዘን  እንገኛለን።
«በዚህ  በኋለኞቹ   ምክንያት   የሌሉንን   የፊተኞችን  ፀጋዎች  አሏችሁ  እንድንባል  ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ   አንልም። ግላዊነት፣  ማኅበራዊነት   ያላቸውን  ተቀራራቢነት «ውስጤን    ማን   ያውቀዋል?  በአፌ መስዬ ብኖር   የሚያዋጣኝ   አማራጭ    ነው?» የምንል ብዙዎች  ነን።  እንዲህ   ያለው   ባህርይ  በተለይ በአገር  ጉዳይ  ማንፀባረቅ  መሞከር  እንዴት  ያለ  ከፍተኛ ወንጀል  እንደሆነ  አይሰማንም።  አንዳንዴ  ከፍርሃት ሲመስለኝ፣  አንዳንዴ   ከምን  እንደመነጨ  ለማወቅ ያዳግተኛል።»  ይላል።  በዚህ  መንገድ ዛሬ   ላይ   ስንቱ   በወንጀል  ተዘፍቆ  እንደሚኖር  በቂ   ማሳያ   ነው።  
«በዚህ ጊዜ ጠንካራና  ብርቱ   ኢትዮጵያዊ   ዜጋ ምን አይነት መኾን  አለበት?»  ለሚለው   ጥያቄ   እያንዳንዱ   ዜጋ   አስቦ  ስለዚህ  ጥያቄ  መልስ  የመፈለግ   ግዴታ  ያለበትም  ይመስለኛል። የሰው ልጅ  እንደኾነ   ሁልጊዜ   ያደረገው ነገር ትክክል  ሥለመኾኑ  ምክንያት  ሲፈልግ  የሚደክም ፍጡር   ነው።  አዕምሮን   ደግሞ   በምክንያት  እያጠሩና   እየመገቡ   መደለል   ከሕሊና   ፍጥጫ    እንደማያስጥሉ  ይዘነጉታል።
እናም   የአንዲት  የወሎን   እናት  ምርቃት   ለኢትዮጵያ   ጀባ  ልበል።  
ቢስሚላህ
አላህ  ፡  ይውደድሽ፣
አላህ  ፡  ያጋድሽ፣
ልጆችሽን  ፡  ለገነት፣
አንቺንም  ፡  ለክብረት፣
ወልዶ  ፡  መሳሙን፣
ዘርቶ  ፡  መቃሙን፣
የአላህን  ፡  እርዳታ፣
የነቢን  ፡  ጉማታ፣
           ለአንቺ  ፡  አላህ  ፡  ያ‘ርገው!
ያው
የ‘ርሜሽንማ  ፡  እንደምንገድ  ፡  ያ‘ርገው!
እንዲህ  ፡  ያለም  ፡  የለ!
           ደግ  ፡  እድል  ፡  ጀባ፣
           ደግ  ፡  ተምኪን  ፡  ጀባ፣
ተጎሳ  ፡  ፍቅሩን፣
ተዳኛ  ፡  ምክሩን፣
             ለአንቺ  ፡  አላህ  ፡  ያ‘ርገው!
ዘበን  ፡  ይግጠምሽ፣
ወራት  ፡  ይግጠምሽ፣
የወለድሽው  ፡  ይደግ፣
የዘራሽው  ፡  ያፍራ፣
ታመት  ፡  ዓመቱ፣
ተወር  ፡  ሳምንቱ፣
               መድረሱን  ፡  ለአንቺ!
እንዲህ  ፡  ያለም  ፡  የለ!
          አላህ  ፡  ያ‘ርገው፣
          አላህ  ፡  ይደግፍሽ፣
          አላህ  ፡  ዘመድ  ፡  ይሁንሽ፣
          አላህ  ፡  ወኪል  ፡  ይሁንሽ ፣
        አላህ  ፡  ገደፋ  ፣  ወረፋ  ፡  ይሁንሽ ።
አሜን!!!
አላሁመሶሊ ፡  ወሰሊ ፡  መዓላ ፡  ሰይዲና  ፡  መሐመድ! …]


Read 409 times