Saturday, 08 January 2022 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የጌታቸው ረዳ የ”R2P” ትርጓሜ ግትርነት


   ጌታቸው ረዳ “The African Report” ላይ በዲሴምበር 21 2021 “Ethiopia: UN Commission is a Victory for the Cause of Justice and Accountability” ከሚለው ርዕስ ሥር ያሰፈረውን ፅሁፍ አንብቤው ነበር። ፅሁፉ በአብዛኛው የሳንቲምን አንዱን ገፅታ ብቻ የሚያመላክት ነው ማለት ይቻላል። ለዛሬ የሚከተለውን ላንሳ።
በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአውሮፓ ሕብረት (EU) ጎትጓችነት በጦርነቱ ተፈፅመዋል በሚባሉ ወንጀሎች ዙሪያ ምርመራ እንዲካሄድ ውሳኔን ማሳለፉ ይታወሳል። ታዲያ ውሳኔው በድጋፍ ብቻ የታጀበ አልነበረም፤ 21 ሀገራት ቢደግፉም ቻይናንና ራሺያን ጨምሮ 15 ሀገራት ተቃውመዋል፣ 11 ደግሞ በድምፀ-ተአቅቦ አልፈውታል። ታዲያ ጌታቸው ረዳ በተለይም 15ቱን ሀገራት በፅሁፉ ወርፎአቸዋል (በቁጥሩ መደናገጡን ጌቾ አልሸሸገም..Disturbing numbers... ብሎታል)። አልፎ ተርፎም ውሳኔውን ተቃውመው ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ ሀገራት ከዓለም ወቅታዊ ፖለቲካ የዕሳቤ እርከን ሸርተት እንዳሉ ያለ አቅሙ ለማስገንዘብ ሞክሯል። ጌታቸው ረዳ ሀገራቱን ለመውቀስ በዋናነት የተጠቀመው የR2P ፅንሰ ሐሳብን ነው።
R2P..Responsibility to Protect...የተባበሩት መንግስታት በሰው ልጆች ላይ የዘር ፍጅት፣ ጄኖሳይድ፣ የጦር ወንጀሎችና የሰብዓዊ ቀውሶች ጥቃቶች በሚፈፀሙበት ወቅት ተጠቂዎቹን እስከ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በሚደርስ እርምጃ የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት የሚያስገነዝብ መርህ ነው። ታዲያ የ”R2P” መርህ ተፈፃሚ በሚሆንበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ቻርተር ዘብ የሚቆምለትን የሉዓላዊነት አጥር እስከመጣስ ይደረሳል። ይህ መርህ በተባበሩት መንግስታት የፀደቀው እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም. ነው።
በጌታቸው ረዳ ዕይታ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑን የተቃወሙት ሀገራት ምክንያታቸው በሉዓላዊነት ፅንሰ ሐሳብ ላይ ኋላ ቀር አስተሳሰብን በመያዛቸው ነው። በጌታቸው አባባል በሉዓላዊነት ላይ የነበረው ግትር አቋም ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ በተለይም ከ”R2P” መርህ መዋቀር ወዲህ ለዘብ እንዳለ የገለፀበት የፅሁፉ ክፍል ይህን ይመስላል፦
“Those that objected to the resolution couched their objection in terms of its inconsistency with the principle of state sovereignty. In reality, the invocation of sovereignty cannot serve as an all-purpose defense against external scrutiny of a state’s actions within its domestic jurisdiction.
This rigid interpretation of sovereignty is radically at odds with normative shifts that have taken place in the international system over the past 3 decades, particularly with regards to the principle of responsibility to protect (R2P).”
ጌታቸው ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ በሉዓላዊነት ላይ የነበረው ትርጓሜ “shift” እንዳደረገ በግልፅ አስምሯል፣ ለዚህም የሉዓላዊነት ትርጓሜ “Shift” ማድረግ በዋናነት የጠቀሰው የ”R2P” መርህን ነው። ስለዚህም እነ ራሺያና ቻይና በሉዓላዊነት ላይ ያላቸው ግንዛቤ ከ30 ዓመታት በፊት የነበረ ነው፣ ያረጀና ያፈጀ ቆሞ-ቀር አስተሳሰብ ነው። መቼም ጌቾ እንደ ልቡ ነው፤ የፈለገውን ቢል ማን ይከሰዋል? በሀገር ውስጥ ፖለቲካ እንደፈለገ ከአመክንዮ በተጣረሰ ትንታኔ ማብራሪያ መስጠቱ አንሶት የዓለም ፖለቲካ ዳይናሚዝምን ለእነ ራሺያና ቻይና ሊያስተምራቸው ይጥራል። ጥረቱ በማስረጃ የተደገፈ ምሉዕ ትንታኔ ቢሆን ኖሮ ማን በተቃወመው?
የምር ግን የ”R2P” ፅንሰ ሐሳብ ብቅ ማለት የሉዓላዊነትን ትርጉም ጌታቸው በገለፀው መጠን “Shift” አድርጎታል? ወይስ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ከሚያሳድረው እጅ-አዙር ተፅዕኖው የተነሳ “shift” የተደረገው የR2P ትርጓሜ ነው?
“R2P” በተባበሩት መንግሰታት እ.ኤ.አ በ2005 ከፀደቀ በኋላ በሁለት ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የመርሁ አቅም ተፈትሾ ተግባራዊነቱ ፈተና ላይ ወድቋል (One can call such assessment...pragmatic evaluation of R2P principle)። የመጀመሪያው የሊቢያ የ2011 (እኤአ) የኔቶ ወረራ ሲሆን ሁለተኛው የሶሪያው የ2012 (እኤአ) የእርስ በእርስ ዕልቂትና ስደት ነው። የተባበሩት መንግስታት ኔቶ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝና በፈረንሳይ አጋፋሪነት ሊቢያን እንዲወራት የይለፍ ፈቃዱን የሰጠው በ”R2P” መርህ ነው። እናም የወቅቱ የአሜሪካ መሪ ባራክ ኦቦማ፣ ሂላሪ ክሊንተንና የኔቶ መሪ ካናዳዊው ሻርል ቡሻር ሊቢያን በአየር ድብደባ ዶግ አመድ ከማድረጋቸው በፊት የጣልቃ ገብነታቸው ብቸኛው ሰበብ “Responsiblity to Protect” የሚል ነበር። ከላይ ስማቸውን የጠቀስኳቸው የአሜሪካና የኔቶ ባለሥልጣናት ከ”R2P” ግብና ዓላማ ውጭ የመንግስት ግልበጣና የሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ላይ እጃቸው እንደማይኖር መተማመኛ እስከመስጠት ደርሰው ነበር። ነገር ግን በገሃድ የሆነው ኔቶ በሊቢያ ከ”R2P” መርህም በዘለለ ጋዳፊን ከሥልጣን የማስወገድ ድብቅ ዓላማ እንደነበረው ያሳበቀ ነበር። የአሜሪካና የእንግሊዝ ወታደሮች ለአማፂያን ወታደራዊ ሥልጠና ከመስጠትና የጦር መሳሪያን ከማስታጠቅ ባለፈ በውጊያውም ተሳታፊ እንደነበሩ የሚያመላክቱ አያሌ መረጃዎች ነበሩ፤ የማታ ማታም የሊቢያ ሉዓላዊነት መቀመቅ ወርዶ በጥቂቱም በሊቢያ የውስጥ ጉዳይ ከ12 ሀገራት በላይ እጃቸውን ለመክተት በቁ (በዚህ ጉዳይ ቀደም ሲል ዘርዘር ያለ ፅሁፍ ማካፈሌን አስታውሳለሁ።) ይህ ሁሉ የሆነው ግን በስመ “R2P” ነው። እናም ኦባማ ዋሽቷል፣ ሂላሪ ክሊንተንም ዋሽታለች፤ ሌተናል ጄኔራል ቡሻርም ዋሽቷል። ከነዚህ ውስጥ ቢያንስ ኦቦማ ከሥልጣኑ በወረደ ማግስት በሊቢያ ላይ በወሰነው ውሳኔ ተፀፅቷል። በ”R2P” ሰበብ የተጀመረው ጦርነት የሊቢያን ሉዓላዊነት በማፈራረስ በመጠናቀቁ ነው ኦባማ በውሳኔው የተቆጨው።
በእርግጥ ከውሳኔው ጀርባ ከሂላሪ ክሊንተን በተጨማሪ የሱዛን ራይስና የሳማንታ ፓወር ስውር እጆች እንደነበሩ ይነገራል። እናም ጌቾ እነ ቻይናና ራሺያ በስመ “R2P” እነ አሜሪካ የሚፈፅሙትን ደባ ቢቃወሙ "..30 ዓመታት ያህል ወደ ኋላ ቀርታችኋል.." በማለት መውቀሱ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት ያለው አይደለም። እነርሱ ጣልቃ ገብነቱን መቃወማቸው የሚጠቅመው ኢትዮጵያን ነው፤ ቢያንስ ውሳኔአቸው ኢትዮጵያ እንደ ሊቢያ እንዳትፈራርስ ያግዛታል። በእርግጥ ይህ ኢትዮጵያን ከመፈራረስ መታደጉ ቀደም ሲል...."እስከ ሲዖልም ድረስ ወርደን ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን"... ይሉን ለነበሩ መልካም ዜና አይደለም። የነጌታቸው ዓላማ ኢትዮጵያን ማፈራረስ እስከሆነ ድረስ አፈራረሷ እንደ ሊቢያ በአሜሪካ ጣልቃ ገብነትም ሆነ በኔቶ እነርሱ ግድ አይሰጣቸውም።
ያም ሆነ ይህ የሊቢያው ወረራ የ”R2P” መርህን ገደል ውስጥ ከከተቱት ዓለም አቀፍ ሁነቶች አንዱ መሆኑ ይሰመርልን። ይህንኑ የሊቢያን ቀውስ ከግምት በማስገባት ብራዚል ለተባበሩት መንግስታት በR2P ላይ አንድ የማሻሻያ ሐሳብ እንዳቀረበች ይነገራል፤ ይኸውም R2P ወደ RwP ይቀየርልን የሚል ነበር...ማለትም ወደ “Responsibility while Protecting!” በነገራችን ላይ አሜሪካ በስመ ሰብዓዊ ጣልቃ ገብነት በሲ አይ ኤ አማካይነት በታሪክ ውስጥ በብዙ ሀገራት ላይ (በተለይም በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ) የፈፀመችውን ሽፍጥ በማጋለጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች አሜሪካዊያን የፖለቲካና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሐያሲያን ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ዊሊያም ብሉም፣ ሐዋርድ ዚንና ኖኣሚ ቾምሲኪ ተጠቃሽ ናቸው። ከሶስቱም ፀሐፍት የዊሊያም ብሉምን “Killing Hope U.S. Military and CIA Interventions Since World War II, 2004” መፅሐፍ ማንበብ አሜሪካ በስመ ሰብዓዊ ጣልቃ ገብነትና ዲሞክራሲ ከ50 በላይ በሚሆኑ ሀገራት ላይ የሸረበችውን ሴራና በውስጥ ጉዳይ ጓዳ ድረስ ዘልቃ የፈበረከችውን መርዝ ስፋትና ጥልቀት ባለው መልኩ ለመገንዘብ ይረዳል።
“R2P” ወገቤን ያለበት ሌላው ዓለም አቀፍ ሁነት የሶሪያው ጦርነት ነው። የሚገርመው በሶሪያ ጦርነት፣ የጦርነት ወንጀሎችና ሰብዓዊ ቀውሶች ቢስተዋሉም “R2P” በተባበሩት መንግስታት አልተተገበረም። ብዙ አጥኚዎች ዘግይቶ የገባቸው የ”R2P” መርህ የሚሰራው እንደ ሊቢያ ላሉ ደካማ ሀገራት መሆኑን ነው። “R2P”ን ፈርጣማ ወታደራዊ ጡንቻና በልዕለ ኃያላን መካከል አሻሚ ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎት ባላቸው ሀገራት ላይ መተግበር የሚታሰብ አይደለም። በሶሪያም ጦርነት “R2P” የገጠመው ፈተና ይኸው ነው። ሶሪያ እንደ ሊቢያ ዘው ተብሎ የሚገባባት ሀገር አይደለችም። ይህ እውነት ለአውስትራሊያው የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦብ ካር ገብቶት ነበር፤ እንደዚህ ነበር ያለው፦
“This is (Syria) militarily strong regime. There isn’t an appetite, and not a budget, in the western world for the sort of intervention that would be involved here.”
ለምን ቦብ ካር ብቻ! የR2P ፅንሰ ሐሳብ ቀማሚ እንደሆነ የሚነገርለት ጋሬት ኤቬንስም R2Pን ሶሪያ ላይ መሞከር አደጋ እንዳለው አስምሯል፦
“”Syria has a ...a very different geopolitical environment ...no Arab League unanimity is in favour of tough action; a long Russian commitment to the Assad regime , and strong Syrian armed forces with a credible air defense system, meaning that any intervention would be difficult and bloody...it is too much now for such renewed consensus to help much now in Syria.”
የኦቱዋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፈሰሩ ኤሮል ሜንጅስ ደግሞ እንደዚህ ይላል፦
“Syria is a very hard case for current R2P intervention, due to the tri-level proxy war unfolding there.”
ከሶሪያ ጦርነት አንፃር የ”R2P” መርህን የሚተቹ አጥኚዎቹ የመርሁን ወጥ ያለመሆንን (Inconsistency) በጉልህ ያሳምራሉ። እስቲ አስቡት፦ ለምሣሌ ቻይና ላይ “R2P”ን እንዴት መተግበር ይቻላል? ኔቶም ሆነ አሜሪካ ሊቢያ ገብተው ጋዳፊ ላይ የፈፀሙትን ቻይና ላይ መፈፀም ይችላሉ? ወይም ራሺያ ላይ መተግበር ይችሉ ይሆን? እንኳንስ እነሱ ላይ ሶሪያም ላይ አልሞከሩትም። ሲጠቀለል R2P የሚተገበረው በሚሊተሪና በኢኮኖሚ አንፃራዊ ዝቅተኛ አቅም ባላቸው ሀገራት ላይ ነው።
እናም ጌታቸው ረዳ ማወቅ ያለበት ከሉዓላዊነት ፅንሰ ሐሳብ ይልቅ የ”R2P” ፅንሰ ሐሳብ “Shift” ማድረጉን ነው። “R2P” ከላይ እንደተመለከትነው ኃያላን ሀገራት የታዳጊ ሀገራትን ሉዓላዊነት ለመግፈፍ ሰበብ መሆኑንና ወጥነትን ባለማስተናገዱ ከየአቅጣጫው ሂሶችን ማስተናገድ ከጀመረ አሥር ዓመታት ያህል አልፈዋል።
በመጨረሻም አንድ እውነት ላስቀምጥ፦ በየትኛውም ሀገር ሰብዓዊ ጥቃትና የዘር ፍጅት እንዳይፈፀም ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ የሚደገፍ ነው፤ ሌላ ስውር የጂኦፖለቲካ ዓላማን በጉያው እስካልሸጎጠ ድረስ “R2P”ን የሚቃወም የለም። ከዚህ አንፃር ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ አየርላንድ ፣ የአውሮፓ ሕብረት ግጭቱ በሕወሓት ጠብ ጫሪነት ከተከሰተ ጀምሮ የሚያሳዩት ምልክቶች ዓላማቸውን ለጥርጣሬ አጋልጦ የሚሰጥ ነው። ለምሣሌ ቀደም ሲል የተባበሩት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (OHRC) እና በዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (EHRC) በጣምራ ባደረጉት ምርመራ፣ የጄኖሳይድን ማስረጃዎችና ምልክቶች ያገኙት በትግራይ ውስጥ ሳይሆን በኢትዮጵያ እንደ ማይካድራ ባሉ አካባቢዎች ነበር። ትግራይ ውስጥ ጄኖሳይድ ስለመፈፀሙ ምንም ማስረጃ እንዳላገኙ ይፋ ከማድረጋቸውም ባለፈ ሪፖርቱ በነአሜሪካ ሳይቀር ተቀባይነትን አግኝቶ ነበር። በእርግጥ ወቅቱ የትህነግ ሠራዊት ወደ አዲስ አበባ እየተቃረበ ስለነበር ምዕራባውያን በወያኔ ድል አይሉት የዕውር ድንብር ተሳክረው ለሪፖርቱ ብዙም ትኩረት አልሰጡም ነበር። ይህ የትህነግ ጉዞ በኢትዮጵያ ጣምራ ጦር የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ተገትቶ የወያኔ ሠራዊት ጀርባውን ለአዲስ አበባ ፊቱን ግን ለመቀሌ ሰጥቶ መፈርጠጥ ሲጀምር ምዕራባውያኑ ከስካራቸው ነቅተው፣ የተውትን የጄኖሳይድ ዜማን “ሪሚክስ” አድርገው ማቀንቀን ጀመሩ...ግልፅ ወገንተኝነትና ኢ-ፍትሐዊነት ዳግም አንሰራራ። ጌታቸው ረዳም በፅሁፉ፣ በዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሚመራውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን(EHRC) እንደ በቀቀን የዶ/ር አብይ መንግሥት የሚለውን ከመድገም ባለፈ ሌላ ሚና እንደሌለው አድርጎ መሳለቅ ጀመረ። እንደዚህ በማለት፦
“The EHRC’s involvement in the joint investigation team (JIT) had seriously undermined the integrity of the investigative process and the credibility of the findings. Indeed, the EHRC’s parroting of the Abiy regime’s prepackaged talking points confirmed the peril of involving a state-appointed entity in the investigation of crimes allegedly committed by the appointing state.
ታዲያ ጌታቸው “EHRC”ን በኢ-ሚዛናዊነት ከከሰሰው በእጥፍ አስበልጠን እኛም አሜሪካን፣ የአውሮፓ ሕብረትን፣ እንግሊዝን፣ አየርላንድን ጦርነቱ በወያኔ ከተጫረበት ጊዜ ጀምሮ ባሳዩአቸው ይፋዊ ምልክቶች ተንደርድረን በወገንተኝነት የመክሰስ መብታችን የተጠበቀ መሆኑን ጌቾ ሙሉ በሙሉ የዘነጋው ይመስላል። እሱ የ”EHRC”ን ሚዛናዊነት ከጠረጠረበት ልክ በላይ እኛም በዘረዘርኳቸው ሀገራት የሚዘወረውን የ”OHRC”ን ፍትሐዊነት እንጠራጠራለን። እሱ የሉዓላዊነት ትርጓሜ ግትርነትን ባወሳበት መጠን እኛም የ” R2P”ን ትርጓሜ ግትርነትን ለዚያውም ታሪካዊ ማጣቀሻዎች እያነሳን እንሞግታለን። ጌታቸው ረዳ ሌሎች ሀገራትን በሉዓላዊነት ትርጓሜ ግትርነት በከሰሰበት የክስ ወጥመድ እሱ ራሱም የR2P ትርጓሜ ላይ በያዘው ግትር ትርጉም ተይዟል። ቢያንስ በ”R2P” ሰበብ ሉዓላዊነት እንዴት እንደሚገረሰስ ማሳየት አልፈለገም፣ ባለማወቅ ወይም ሆን ብሎ...By ignorance or by omission! ማለትም ሳንቲሙ ሌላ ገፅታ እንዳለው ከነአካቴውም አያውቀውም፤ አሊያም ሌላ ገፅታ እንዳለው አውቆ ግን ለመሰወር ይሞክራል። And we call such fallacy Half-Truth fallacy and commonly it is believed that:
Half Truth = Lie
ማሳሰቢያ፦ የዚህ ፅሁፍ የእንግሊዝኛ ትርጉም በቀጥታ ለ”The Africa Report” ሊላክ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል።
=============================================


ኢኮኖሚው ከጦርነቱ ያልተናነሰ ፈተና  ይሆንብናል


ለበርካታ መቶ ዓመታት ጠንክሮ ሰርቶ ወረት ማጠራቀምን በሚነቅፍና ለእለታዊ ፍላጎት መትጋትን በሚያበረታታ ባህልና ልማድ ተጽእኖ ስር በመውደቃችን፣ ሀገራዊ ሀብት የመፍጠርያ ጊዜያችንን አባክነናል፡፡ ለማደግ ብንጥርም ወደታች የሚጎትቱን ውስጣዊና ውጫዊ ማነቆዎች ስለገነገኑ፣ ኢኮኖሚያችን ከስር ፈንቅሎ መውጣት የማይችልና እንደ ካሮት ወደ ታች የሚያድግ ደካማ ሆኗል፡፡
ጦርነት የሚያስከትለውን ፈተና ቢያንስ ባለበት ለማቆም የሚያግዘን ቅድመ ዝግጅት ስለመኖሩ መረጃ የለኝም። ነገር ግን ለዘመናት የተቆለሉብን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ማነቆዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ኢኮኖሚው ያለ እቅድና ቅድመ ዝግጅት ከተመራ ከባድ ውጥንቅጥ ያስከትላል የሚል እምነት  አለኝ፡፡  በተለይ ጦርነቱን በቅጡ ስንመረምረው አስፈሪ በሆነ ደረጃ የሰው ሃይል፣ ማምረቻ፣ ምርት፣ የመሰረተ ልማት ውድመትና ስነ ልቦናዊ ቀውስ ያስከተለ ስለሆነ የፈተናውንን ክብደት በቅጡ የምንረዳው ይመስለኛል ።
እንደ አለመታደል ሆኖ ጦርነቱ የደቀነብንን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ለመታደግ የሚረዳ ካፒታል፣ ነዳጅ ወይም ማዕድናት የለንም። አዲሱ በጀትም ቢሆን ከሚቀጥለው ዓመት የምንበደረው፣ እሴት ያልፈጠረውና ካልተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ አቅም የመነጨ ነው። በጀቱ የሚሸፈንበት መንገድም በቅጡ ካልታሰበበት ለግሽበት እንደሚዳርገን ግልጽ ነው፡፡ ወገባችንን ጠበቅ ካላደረግንም፣ በምርት እጥረትና መስተጓጎል ምክንያት የዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሬ እጥረቱም ሌላ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የብዙዎቻችን ጥያቄ ከዚህ ውጥንቅጥ መውጣት ይቻላል ወይ ? ከተቻለስ እንዴትና ስንት ዓመት ይፈጃል የሚል ነው? ለዚህ ጥልቅ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የጊዜና የቦታ እጥረት ስላለ ለውይይት መነሻ እንዲሆን ይህንን አጋርቻለሁ። ኢኮኖሚው ከጦርነቱ ያልተናነሰ ፈተና መሆኑ ስለማይቀር  መነሻው ላይ እንወያይበት።
የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት በሚል ስያሜ የሚጠራ ድርጅት (OECD) አንድ ሃገር በጦርነት ውስጥ ሲሆን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቱና እድገቱ በ1.6 በመቶ እንደሚያሽቆለቆል ይገልጻል፡፡ ጦርነቱ ከቆመ ከአንድ ዓመት በኋላም ምርታማነቱ  አንድ በመቶ ይጨምራል። በዚህ አካሄድ ወደ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመሸጋገር ከ15 እስከ 22 ዓመት ሊፈጅበት እንደሚችል ያትታል፡፡
ጥናቱ ይህን ቢያቀርብም ከጦርነት ተጽእኖ በፍጥነት አገግመው በመውጣት ወደ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት የተሸጋገሩ ሀገራት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አውሮፓውያን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነትበኋላ ከጦርነቱ ተጽእኖ ለመውጣት የፈጀባቸው 5 ዓመት ነው።  ጃፓን 8 ዓመት፣ ኮርያ 8 ዓመት፣ ከአፍሪካ ሴራሊዮን 10 ዓመት ወዘተ... መጥቀስ ይቻላል ፡፡    
እንደ አብዛኛው በማደግ ላይ ያሉ አገሮች፣ ሀገራችን አስተማማኝ የካፒታል አቅምና እንደ ነዳጅ ያለ ወሳኝ የተፈጥሮ ሀብት ስለሌላት ልናተኩርበት የሚገባው አቅማችን የሰው ኃይላችን፣ የመሬትና የውሃ ሃብታችን ነው። በወርልድ ባንክ የሀገራት ተቋማዊ የፖሊሲ  ምዘና (CPAI) መሰረት፤ የፖሊሲ ለውጦችን ማድረግ ለፈጣን ሽግግር ሌላው አስፈላጊ ነገር እንደሆነ ያትታል፡፡  ከእነዚህም ውስጥ:-
1. ቀጣይነት ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ተሃድሶ ማድረግ (Macroeconomic Management and Sustainability Reforms)
2. ዘለቄታ ላለውና ፍትሀዊ/ሚዛናው ለሆነ እድገት መዋቅራዊ የፖለሲ ሽግግር ማድረግ (Structural Policies for Sustainable and Equitable Growth)
3. ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ማህበራዊ ፖሊሲ መቅረጽ (Policies for Social Inclusiveness)
4. ለፐብሊክ ዘርፉ አስተዳደር ፖለሲ መንድፍ ናቸው፡፡ (Public Sector Management policy)
የበርካታ ሀገሮች ልምድ እንደሚያመላክተው፣ እስከ አሁን በመጣንበት መንገድ እርዳታ ላይ ብቻ መንጠላጠል የትም እንደማያደርሰን ጥናቶች ያመላክታሉ። በወርልድ ባንክ ተመሳሳይ ጥናት መሰረት፤ ያለ ፖሊሲ ማሻሻያ ተጨማሪ አንድ በመቶ እርዳታ መቀበል፣ በኢኮኖሚው ላይ ከ0.005 እስከ 0.1 በመቶ ብቻ የእድገት ሕዳግ አለው። በእርምትና በተሀድሶ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ አቅጣጫን በመቀየስና ያገኘነውን እርዳታ ከምርት ምክንያቶች ጋር በማቀናጀት የስራ ሃይላችንን ዲሲፕሊንድ ካደረግን፣ ሀገራዊ ሀብታችንን ከውድቀት በመታደግ፣ ወደ ተሻለ አቅማችን ለመመለስ ሰፊ እድል አለን፡፡
በስፋት ወደ ፊት የምመለስበት ቢሆንም ሌላውና ወሳኝ ነገር፤ የስራ ባህላችንን የሚመለከት ነው፡፡ ምርታማነትና የሥራ ባህል ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡ እንደ ኤዢያ ታይገር ባሉ በርካታ ሀገሮችም ተመስክሯል። ከእለት ፍጆታው እጅግ የላቀ ተረፈ ምርት ለማምረት ጉጉቱና ተነሳሽነቱ ያለውና ዲሲፕሊንድ የሆነ የስራ ሃይል ለራሱ ከሚፈጥረው ሀብት ባሻገር ሀገራዊ ሀብትን በማጎልበት እሴት የመፍጠር አቅሙና እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ማህበረሰባችንን በዚህ መልክ ከቀረጽነው በጦርነትና በተጓዳኝ ችግሮች የባከነውንና የሚባክነውን የምርታማነት ጊዜ በጥንካሬ በመተካት ተፈጥሮአዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ፈታናዎችን ተቋቁመን ያለመንገጫገጭ በአጭር ጊዜ ወደ ሃዲዳችን ለመመለስ እንችላለን።


=================================

መጭውን ጠበቅሁት
በእውቀቱ ስዩም

ከማዶ ሚመጣው፥ ዘመድ ነው እንግዳ
ከላይ የተለጋው፥ ኳስ ነው ወይስ ናዳ
ብየ መች ጠየቅሁኝ
መጭውን ጠበቅሁት
ድንጋይ ላይ ቁጭ ብየ፤ ጸሀይ እየሞቅሁኝ፥
መከራም አላጣም፥ ተድላም አልጎደለኝ
ደንታ ነው የሌለኝ፥
ባካል በስሜትም፥ ታሞ ላገገመ
ወድቆ ለተነሳ ፥ እየደጋገመ
ከገዛ ጉድጓዱ ፥አጽሙን ለሚለቅም
ሞትም ብርቅ አይደለም፥ ትንሳኤም አይደንቅም::


Read 723 times