Sunday, 09 January 2022 00:00

አራት ማእዘኑም በቦታው፣ ክቡም በቦታው

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁ!

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“አጅሬው፣ ወደ ውጭ ወጥተህ ነበር እንዴ!”
“ኸረ እኔ የትም አልሄድኩም፡፡”
“ምነው ታዲያ ሰሞኑን አላየሁህ፡፡”
“ሰሞኑን ስቱዲዮ ውስጥ ሥራ በዝቶብኝ ነበር፡፡”
“ስቱድዮ! የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሆንክ እንዴ!”
“እንደሱ አይደለም፡፡ በሚቀጥለው ወር የሚለቀቅ ሲንግል ስላለኝ ስቱድዮ እየተቀረጽኩ ነበር፡፡”
ይሄኔ ጭጭ ነው...በድንጋጤ! ልክ ነዋ...ያለንበት ዘመን ማንም ሰው ምንም አይነት ነገር ማድረግ የሚችለበት ነዋ! ማናችንም ምንም መሆን የምንችልበት ዘመን ነዋ! እናማ... ስለሆነ ቀጥተኛ ጥያቄ፣ መስቀለኛ ጥያቄ ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ እናንተ ናችኋ እንትን ሰፈር ግሮሰሪ አፕሬቲቭን አራቷን ቀንድቦ “እዩዋት ስትናፍቀኝን ‘በትሬንታ ኳትሮ‘ ሞተር ድምጽ ካልዘፈንኩ ያለ ጊዜ፣ “አንተ እንዲህ አይነት የዘፈን ችሎታ ኖሮህ እስከዛሬ ምንም ሳትነግረን!” ምናምን ብላችሁ የማይሆን እጸፋሪስ አቅምሳችሁ እዚህ ያደረሳችሁት!
“ስማ... ያ ሰውዬ፣ ያ እንኳን ማይክል ጃክሰን ...”
“እሱ ሰውዬ ማይክል ጃክሰን የሚለውን ስም በፍርድ ቤት አስጸደቀ እንዴ! በእውነተኛ ስሙ የሚጠራው ጠፋ እኮ!”
“ለመደብና...”
“እናንተ ናችሁ እኮ በባዶ ሜዳ ማይክል ጃክሰን፣ ማይክል ጃክሰን እያላችሁ ጭንቅላታችን ላይ ኳስ ካልተጫወትኩበት እያለን ያለው፡፡”
“አሁንማ ቁርጥህን እወቀው፣ ኳስ ብቻ ሳይሆን የፈረስ ጉግስ ልጫወትበት ማለቱ አይቀርም፡፡”
“አልገባኝም፡፡”
“ሰውየው ሲንግል ሊለቅልህ ነው፡፡” 
“የምን ሲንግል...”
“የምን ልበልህ... የጂን ሲንግል? ዘፈን ሊለቅ ነው እያልኩህ ነው፡፡”
“ምን! እሱ ሲንግል ካወጣ ምን እንደማደርግ ልንገርህ? በአንድ ሳምንት ውስጥ ሞንጎሊያ በረሀ መሀል ቁጭ ነው፡፡ ምን አለ በለኝ እዛ ድረስ በእግሬ ባላቀጥነው! በእሱ ሰበብ የመጣ መቅሰፍት እኮ ለእኛም ነው የሚተርፈው!”” ቂ...ቂ...ቂ...
እናማ... አራት ማእዘኑም በቦታው፣ ክቡም በቦታው ይሁኑ ለማለት ያህል ነው!
እኔ የምለው የምር ግን... አንዳንድ ‘ሲንግል’ ተብለው የሚለቀቁ ሥራዎችን ስንሰማ...አለ አይደል...ግራ የሚገባን ነገር አለ፡፡ አሀ... ሲንግል ለመቀረጽ ሲገቡ ደብል ምናምን ገጫጭተው የሚገቡ እየመሰለን ተቸገርና! አሀ...በዘመናዊ መሣሪያዎች የተሞላ ስቱድዮ ሊያስተካክለው ባልቻለው ድምጽ ጆሯችን ላይ የጅምላ ጥቃት ይፈጸምብናል እንዴ! (ግን እኮ ስሙኝማ...ስደት ለወሬ ይመቻል የሚባል ነገር አለ አይደል! አንድ ሲንግል ከለቀቁ በኋላ የዛሬ አስር ዓመትም፣ አሥራ አምስት ዓመትም...
“ያኔ ሲንግል የለቀቅሁ ጊዜ ትዝ አይልህም...”
“ሲንግሌ በወጣ በአራተኛው ወይም በአምስተኛው ሳምንት አካባቢ ይመስለኛል...”
“ሲንግሌን ለቅቄ ብዙም ሳልቆይ ነው...
የእኔ ቢጤው ከተወሰኑ የአማርኛ ፊደላት ጋር የማይታረቅ ቅራኔ ያለው ሁሉ ካልዘፈንኩ እያለ ደማችን እየረጋ ተቸገርን እኮ!
እኔ የምለው...‘ድምጻዊ’ እና ‘ዘፋኝ’ ልዩነት አለው እንዴ! አሀ...ሁሉም ነገር በቦታው ይሁና! ሁለቱን ቃላት ለአንዱ ሰው እያፈራረቅን ስንጠቀም የትርጉም መዛባት እንዳይፈጥር ብለን ነው፡፡ (ወይም... አሽሙር እንዳይመስልብን!) “እሱ ግን ሥራው ምንድነው?” ስንባል “ድምጻዊ ነው...” እንላለን፡፡ “ታዲያ ለምንድነው ብዙ ጊዜ የማናየው?” ስንባል ምን እንላለን መሰላችሁ... “እረፍት የለውም፣ ቀንም ሌትም እንደዘፈነ ነው፡፡” እናላችሁ... ችግሩ ምን መሰላችሁ... እኛ ደግሞ  “እሷ ግን መዝፈን አይደክማትም!” ስለ ሰርግ ቤት ወይም ስለ ‘ናይት ክለብ’ እያወራን አይደለም፡፡ የወጣቶቹን ቋንቋ ለመጠቀም “ቶክ ታበዛለች” ማለታችን ነው፡፡
እናላችሁ... ሙዚቃ አፋችን ላይ ስለመጣ ነው እንጂ...ሁሉም ነገር ላይ ችግር ነው፡፡ ምን መሰላችሁ፣ “እሱ ካኮረፈ ስለማይመለስ እንዳይቀየመን!” “አንዴ ነክሳ ከያዘች ስለማትለቅ ቂም እንዳትይዝብን!” እያልን የማይሆን አስተያየት እንሰጥና እኛም በሰማይ ቤት ‘ብላክ ሊስት’ ውስጥ እንገባለን። ሰዎቹም በቃ ራሳቸው ላይ ዘውድ ይደፉና ‘ሰው ጤፉ’ ሆነው ቁጭ!
“እኔ እንዳንተ አይነት ወርቅ ድምጽ ቢኖረኝ ኖሮ አይደለም ሀገርንና አፍሪካን ድፍን ዓለምን በአውራ ጣቷ ነበር የማቆማት!” ታዲያላችሁ... አይደለም ዘፈን እችላለሁ ብሎ ቀና፣ ቀና የሚለው የእኛ አይነቱ አንዲቱን ዓረፍተ ነገር ሦስት፣ አራቴ ሳይሰባብር መጨረስ የማይችለውስ የዝሆን  ጫንቃ ያወጣ ቢመስለው ምን ይገርማል!
“እዪው፣ እንዲህ የምትለው ጓደኛዬ ስለሆነች ነው አትበይኝና መዝፈን ትችያለሽ ማለት ብቻ ሳይሆን ድምጸ መረዋ ማለት አንቺ ነሽ!” ስሚኝማ እንትናዬ... ይህን ካልሽ በኋላ...በሁለተኛ ወሩ “ድሮ አቅፋ አገላብጣ ስማኝ እንኳን የማትጠግበው ሴትዮ አሁን እጄን ለመጨበጥ እየተጠየፈች ነው!” ምናምን የሚል አቤቱታ እንዳንሰማ!
እናላችሁ...ሰውና ሥራ አልገናኝ እያለ፣ ፈረንጅ እንደሚለው አራት ማእዘኑን እንጨት ክቡ ቀዳዳ ውስጥ ለማስገባት እየተሞከረ ስንት በተለያዩ ዘርፎች ሊዳብር የሚችል ችሎታ ያላቸው ሰዎች፣ በተለይም ወጣቶች፣ በመንገድ ላይ ቀርተዋል፡፡ ክፋቱ ምን መሰላችሁ፣ ወዳጅ ዘመድ ነዋ!...አሀ፣ “አንተን የመሰለ ዘፋኝ የት ተገኝቶ!” “እዚህ ሀገር በአሁኑ ሰዓት አንቺን የመሰለች ገጣሚ የለችም!” እየተባለ ብዙ ነገር ተበላሽቷል፡፡
እናማ... አራት ማእዘኑም በቦታው፣ ክቡም በቦታው ይሁኑ ለማለት ያህል ነው!
ስሙኝማ... አለ አይደል... በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሰዋችን እንደ ዜጋ አስተያየት ሲሰጥ መስማት ደስ የሚል ነገር ነው፡፡ (እነ እንትና፣ ሁልጊዜ የመስመር ዳኛ መሆን አይሰለቻችሁም! አሀ...እንደምንም መሀል ዳኛ ለመሆን ሞክሩዋ! ዘዴውን! ዘዴውማ ደገምገም አድርጋችሁ ቲቪ ላይ መታየት ነው፡፡ ከዛ በኋላ ምን ችግር አለ...“አንድ ስሙን የማላስታውሰው ፈላስፋ በአንድ ወቅት እንዳለው፣” ምናምን ማለት ነው። ምን አለ በሉኝ...በማግስቱ ጠዋት ከአስር መገናኛ ብዙሀን የቃለ መጠይቅ ግብዣ ባይደርሳችሁ! በነገራችን ላይ... መሀል ዳኛ የተባለው ግን በቀደም የአርሴን ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ያበሳጩት አይነት ማለታችን አይደለም፡፡ ፌስቡክ ላይ “የማን ሲቲ ‘ማን ኦፍ ዘ ማች’ መሀል ዳኛው ናቸው፣” የሚል ነገር አንብበናል፡፡
እናላችሁ....እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አይደለም የቡድኖች አባላትን አሳምኖ ሊያቀራርብ ይቅርና ከሚስቱ ጋር አንዲት ሰላማዊ ምሽት አሳልፎ የማያውቅ ሰው አለ እንበል፡፡ (ለ‘ትህትና’ ያክል “እንበል” አልን እንጂ መአት እንደዛ አይነት ሰው አለላችሁ፣ የደጅ ብስጭቱን ሁሉ ቤተሰቡ ላይ የሚወጣ፡፡)  አለ አይደል... መሸት ሲል ከእሱ ቤት አካባቢ የሆነ ጮክ ያለ ድምጽ ሲሰማ...“ደሞ መከራዋን ሊያበላት ነው...” የሚባልልት አይነት ቤተሰብ ያለው ሰው ማለት ነው፡፡ ታዲያማ... አንድ ምሽት ሀገር ሰላም ብላችሁ ቴሌቪዥን ዜና ምናምን እየተከታተላችሁ ሳላችሁ ምን ቢፈጠር ጥሩ ነው...የአጅሬው መልክ የቴሌቪዥኑን ስክሪን አይሞላውም!
መጀመሪያ ላይ እማወራዋ “ይቺ ብቻ ነች የተረፈችው...” ብላ ያቀመሰቻችሁ ዳግም አረቄ ሥራዋን መሥራት የጀመረች ይመስላችኋል፡፡ እና ጋዜጠኛው ያስተዋውቃል... “የዛሬው እንግዳችን በቅርቡ የተቋቋመው ‘የሰላምና አብሮ መኖር’ ምግባረ ሰናይ ድርጀት ዋና ዳይሬክተር አቶ....” በቃ፣ ምን አለፋችሁ...የመስሚያ ህዋሳቶቻችሁ በሙሉ ላለመተባበር ያምጻሉ፡፡ የሰላምና አብሮ መኖር! ሰውየው እኮ አይደለም እሱ ራሱ በሰላም አብሮ ሊኖር ገሚስ መንደሩ በሰላም እንዳይኖር ዋናው በጥባጭ ነው! (ስማ፣ ጋሼ ዳይሬክተር፣ እስቲ መጀመሪያ በየምሽቱ አሳሯን ለምታበላት ሚስትህ ሰላሟን ስጣት!) የምር ግን በየወፍራም ወንበሩ ላይ እንዲህ አይነት መአት ሰዎች ባይገኙ ነው!
መድረክ ላይ “በእውነቱ የድርጅቱ ሠራተኞች በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ሥራ አክባሪዎች፣ ድርጅቱን ለማሳደግ በትጋት የሚሠሩ...” ምናምን እያለ ሲክብ ቆይቶ ቢሮው ሲገባ... “ምድረ አልማጭ ተሰብስቦ ድርጅቱን በኪሳራ ሊያዘጉት ነው እኮ!” የሚል አለቃ ሲበዛ የምር አስቸጋሪ ነው። መድረክ ላይ የሚባሉ ነገሮችን አብዛኛውን ጊዜ “አናምንም!” ስንል በምክንያት ነው ለማለት ያህል ነው፡፡
እናማ... አራት ማእዘኑም በቦታው፣ ክቡም በቦታው ይሁኑ ለማለት ያህል ነው!
መልካም የገና በዓል ሰሞን ይሁንላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1679 times