Thursday, 13 January 2022 05:43

ቅጽበትና ዘለዓለም በጊዜ አረዳድ ውስጥ

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(1 Vote)

 --የሆነስ ሆነና ጊዜ ግን ምንድን ነው? ጊዜ ምንምን ያልተደገፈ፣ በማንምና ምንም ላይ ጥገኛ ያልሆነ፣ለማንም የማይገዛ፣ በመሬት ስበት የማይፈተን ሁነት እንዴት ሊሆን ቻለ?  ቅጽበት ዘለዓለም የሆነችባት ያች ነጥብ መቼ ነበረች? መጠየቅን የሙጥኝ ካልኩ ወዲህ ጊዜን ለመረዳት ያላደረግኩት ጥረት የለም፡፡ ሆኖም አሁንም በምናልባት አፅቅ ከታጠሩ ጥቂት ጥርጣሬዎች በስተቀር ይህ ነው የምለው የጠጠረ መረዳት የለኝም፡፡-"


   የ17ኛው ክፍለዘመን ዘመን ጳጳስ ጀምስ አሸር (James Ussher 1581-1656 እ.ኤ.አ) አንድ ቀን ድንገት ተነሳና ‹‹ከአዳም ጀምሮ የተፈራረቁ ትውልዶችን ዕድሜ በሚገባ አጥንቻለሁ፡፡ በግኝቴም መሠረት እግዚአብሔር ከክርስቶስ ልደት 4004 ዓመታት በፊት እሁድ ጥቅምት 26 ልክ ከምሽቱ በ12 ሰዓት ከዜሮ ዜሮ ምድርን ፈጠራት፡፡›› ብሎ አወጀ፡፡ ሰበከ፡፡
‹‹ኸረ ተው ጥቂት ሴከንዶች እንኳን የሉትም?›› ተብሎ ሲጠየቅ
‹‹ወይ ምናምኒት!›› ሆነች መልሱ፡፡ እንደ ጳጳሱ አባባል፤ ጊዜ ምድር ከመፈጠሯም በፊት ጊዜ ነበር ማለት ይሆን? ወይስ ጊዜ እሁድ ጥቅምት 26 ከምሽቱ አስራ ሁለት  ሰዓት ድንገት ተጀመረ? ስለ ጊዜ ማንም ከመላምት ያለፈ መልስ የለውም። በአጠቃላይ በእኔ እምነት መጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ላይ የሚሰበከው ሀቲት ‹‹አምላክ የማይስማማውን ምግብ በልቶ ሆዱን በጠና ታሞ ይህችን ምድር አስታወካት›› ከሚለው የምዕራብ አፍሪካ ተረት ለይቼ አላየውም፡፡ አንዳንዶች አምላክ ምድርን ለመፍጠር የወሰደበት ሰባት ቀናት የእግዚአብሔር ቀናት ናቸው፤ ወደ ሰውኛ የጊዜ አረዳድ ብንቀይራቸው ቢሊዮን ሚሊዮን ዓመታት ሊወጣቸው ይችላል ይላሉ፡፡ ይሄኛው ትንሽ ስሜት የሚሰጥ ይመስላል፡፡  
የሆነስ ሆነና ጊዜ ግን ምንድን ነው? ጊዜ ምንምን ያልተደገፈ፣ በማንምና ምንም ላይ ጥገኛ ያልሆነ፣ ለማንም የማይገዛ፣ በመሬት ስበት የማይፈተን ሁነት እንዴት ሊሆን ቻለ?  ቅጽበት ዘለዓለም የሆነችባት ያች ነጥብ መቼ ነበረች? መጠየቅን የሙጥኝ ካልኩ ወዲህ ጊዜን ለመረዳት ያላደረግኩት ጥረት የለም። ሆኖም አሁንም በምናልባት አፅቅ ከታጠሩ ጥቂት ጥርጣሬዎች በስተቀር ይህ ነው የምለው የጠጠረ መረዳት የለኝም፡፡
ሰር አይዛክ ኒውተን ከጳጳሱ ጀምስ አንድ ክፍለዘመን በኋላ ብቅ ያለ እንግሊዛዊ ጠቢብ ነው፡፡ ‹‹እኔ እኔን የሆንኩት በእነ ጋሊሊዮ ትከሻ ላይ ቆሜ ነው፡፡›› የምትል ትህትናውን አስቀድሞ ስለ ጊዜ አዲስ እይታውን ፈነጠቀ። ለኒውተን ጊዜ absolute ነው፡፡ እኔ እና እናንተ፣ ምድራችን፣ ኸረ እንዲያውም መላው ዩኒቨርስ ኖርንም አልኖርም ጊዜ ግን ይኖራል፡፡ ኒውተን ይቀጥላል፡፡ ‹‹ጊዜ እኛ እንደሚገባን በጨረቃ መወለድና መሰወር፣ በጸሐይ መውጣትና መግባት ብቻ የሚለካ የሚፈተን ተሰባሪ ሁነት አይደለም፡፡ ጊዜ ፍጹማዊ ነው፡፡ ሆኖም ጊዜን በሂሳባዊ ቀመሮች መለካት ይቻላል፡፡››
ሌላ አንድ ክፍለዘመን አለፈና የሆነ ነገሩ አቦይ ስብሀትን የሚመስለኝ አንስታይን ተከሰተ፡፡ ‹‹ኒውተን ሆይ እባክህ ‹አፉ› በለኝ›› የምትል መግቢያውን አስቀድሞ የኒውተንን የጊዜ አረዳድ እርቃኑን የሚያስቀረውን relativity theory አስተዋወቀን፡፡ እንደ ሪላቲቪቲ ቲወሪ ከሆነ አንድ ሰው ለብርሃን ፍጥነት (186000 ማይል በሴከንድ) በቀረበ ሽምጠጣ በጠፈር ውስጥ ለመቶ ሺህ ዓመታት ቢጓዝ አፍታም የምታክል ጊዜ ያለፈችም ላይመስለው ይችላል፡፡ ወደ ምድር ድንገት ቢመለስ እንደ የመጽሐፍ ቅዱሱ 66 ዓመታት ያንቀላፈው አቤሜሌክ ግራ በመጋባት መደናበሩ እኮ ነው፡፡ ሲያሳዝን! አንተ ግን በብርሃን ፍጥነት መጓዝ ብትችል ቅጽበትና ዘለዓለም ሲሳሳሙ ልትመለከት ትችላለህ፡፡
ግልጽ እኮ ነው፤ ልክ በብርሃን ፍጥነት መጓዝ የጀመርክ ጊዜ፣  ያኔ ‹ጊዜ› በስመዓብ እንዳሉት ሰይጣን እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ እብስ ይላል፡፡ ጊዜ የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ሆኖም እንደገና እንደ ሪላቲቪቲ ቲወሪ ከሆነ በጠፈር ውስጥ የትኛውም አካል በብርሃን ፍጥነት ሊጓዝ አይችልም፡፡ ምክኒያቱም በዚያ ፍጥነት በሚጓዝበት አጋጣሚ መጠነ ግዝፈቱ የትየለሌ ስለሚሆን፡፡ ተጨማሪ ጉልበት ብታውልበትም ግዝፈቱ ይጨምራል እንጂ ፍጥነቱን ማሳደግ አትችልም፡፡ ለሪላቲቪቲ ቲወሪ ብቸኛው አንጻራዊነትን ያመለጠ ፍጹማዊ ነገር የብርሃን ፍጥነት ብቻ ነው። ብርሃንም ቢሆን እየተምዘገዘገ ሄዶ ወደ የጽልመት እምጥ (black hole) የስበት ንፍቀ ክበብ ከገባ ወገቡን እንደተመታ እባብ ይጥመለመላታል እንጂ ተመልሶ አይወጣም፡፡ እዚያ የፊዚክስ ህግ ጂኒጃንካ ብሎ ነገር አይሰራም ጓዴ! አንተም ቢሆን እየተጠነቀቅክ! ዋ እንዳትጠጋ!
እኔ ግን እላለሁ ጊዜ የሚከፋፈል አይደለም፡፡ ጥልቀቱ ሲቸግረን በሚገባን ልክ የከፋፈልነው እኛ ነን፡፡ የሁላችንም ከልጅነት ወደ ወጣትነትና እርጅና ጉዞ እንደህልም ያለ ብዥታ የበዛበት ነው፡፡ በቅጽበት ውስጥ ዘለዓለም አለ፡፡ ከፈለክ በቅጽበት ውስጥ ቅጽበት ብቻም አለ፡፡ በቅጡ ከተረዳሃቸው ቅጽበትና ዘለዓለም አይበላለጡም፡፡ ጊዜና ወንዝ ደግሞ እጅጉን ይመሳሰላሉ፡፡ ሁለቱም በአንድ ጊዜ ሁሉም ቦታ ይገኛሉ። ማንም ተመሳሳዩን የወራጁን ወንዝ ውኃ ደግሞ መንካት አይቻለውም፡፡ ልክ ማንም የትኛዋንም ቅጽበት ደግሞ መኖር እንደማይችል ሁሉ፡፡ በሕይወትህ ውስጥ ቅጽበት ዘለዓለምን የምታክልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ወሳኙ የአንተ የተሀዝቦ ንቃት ብቻ ነው፡፡ የስነ ተረት(Myth) ሊቁ ጆሴፍ ካምቤል እንዲህ ይላል፤ ‹‹eternity isn’t some later time. Eternity isn’t even a long time. eternity has nothing to do with time. eternity is a dimension of here and now… if you don’t get it here, you won’t get it anywhere.›› የካምቤል ሐሳብ በአብዛኛው ከሂንዱ አስተምህሮ የተቀዳ የሚመስል ቀለም አለው፡፡
አወዛጋቢው ፈላስፋ ኦሾ በበኩሉ ጊዜን ለመለካት መሞከር ጅልነት ነው ይላል። ይቀጥልናም ‹‹It is our arbitrary method to measure time, which is immeasurable. Time has always been at stop. since the very beginning it has been at stop. It has never moved.››
እያንዳንዱ ህልው የሆነ ነገር ወይም ሁነት ወይም ሌላ በዝንተዓለም የጊዜ ልኬት ውስጥ አስቀድሞ ነበረ፡፡ ለምሳሌ እኔ ጊዜ በማይቆጠርበት የጊዜ ልኬት (timeless time) በምልዓተ ዓለሙ ውስጥ ብናኝ፣ ደቃቅ ህዋስ፣ ቃል ወይም ሌላ ብቻ አንዱን ሁነት ሆኜ ነበርኩ፡፡ ዘመኑ ሆኖ ገፁ ሲገለጥ ካንቀላፋሁበት የኦናነት ገደል ባንኜ በግዝፈተ አካል ስቀዝፍ አያችሁኝ፡፡ ዘመኑ ሆኖ ገፁ ሲታጠፍም ወደ ደቃቅ አሸዋ ወይም ወደ ትንኝ ተቀይሬ መኖሬ ይቀጥላል፡፡
በምልዓተ ዓለሙ ውስጥ ሁሉም ነገር እንዲህ ተመጋጋቢ ሠንሰለትን ይከተላል፡፡ በዚያኛው የጊዜ ጽንፍ አስቀድሞ ያልነበረ ወደፊት የሚሆን ምንም ነገር የለም፡፡ የሆነ (being) ብቻ እንጂ… ሆኖም ይህችን ዓለም ከሚያሾሯት ፈርጣማ ክንዶች እጅግ ብርቱው ጊዜ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። ጨካኙ ሞት እንኳን ቦቅቧቃ ሆነን ካልተረዳነው በስተቀር በዚህ ዓለም ላይ የጊዜን ያህል ወሳኝነት የለውም፡፡ እኛ በጊዜ የማይጨበጥ ሐዲድ ላይ ከትናንት እስከ ዛሬ በተሰመረ ምናባዊ መስመር ላይ ታይተን የምንጠፋ ጥላዎች ነን፡፡ ጊዜ ደግሞ ህልውና (existence) ሚዛኑን ጠብቆ የቆመበት ፅኑ መሰረት ይመስላል፡፡
ጊዜን ክብ፣ ንቅናቄ አልባ፣ በምልዓት የተያዘ ሁነት እንደሆነ መናገር የበለጠ ስሜት የሚሰጥ አይመስላችሁም? ጊዜ ባዶ ኦና ፍጹም ኦና ሂደት ነው፡፡ የጊዜ የኦናነት ልኬት ልክ እኛ እንደምንኖርበት ምልዓተ ዓለም (universe) ዳርቻው አይታወቅም፡፡ በአንድ ሰው ግንባር ላይ በኩራት የምትጀነን ቅማል ሰውየው እየተራመደ መሆኑን መረዳት እንደሚቸግራት ሁሉ እኛም የጊዜን ጥቅል ጽንፍ የለሽ ኦናነት እንዲህ ነው ብለን ለመበየን አቅም ያንሰናል፡፡
እኔ ግን ቅዱስ አውገስቲን ጊዜ ምንድን ነው ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ የሰጣትን ገራሚ መልስ አስነብቤያችሁ ነገሬን ልጠቅልል፡፡ ‹‹What, then, is time? If no one asks me, I know; if I wish to explain to him who asks, I know not.››


Read 4452 times