Saturday, 15 January 2022 20:24

“ዕውነት ቦት - ጫማዋን ሳታጠልቅ፤ ውሸት አለምን ዞሮ ይጨርሳል”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ከዕለታት አንድ ቀን፣አንድ ኑሮው የሞቀለት፣ይለጉመው ፈረስ፣ይጭነው አጋሰስ ያለው፤የናጠጠ ሀብታም ሰው በአንድ መንደር ይኖር ነበር፡፡ እጅግ ቆንጅዬ ወጣት ሚስትም ነበረችው፡፡ አንድ ችግር ግን ነበረበት። ይዋሻል!
ታድያ ይህ ሰው ብዙ ጊዜ ህሊናውን የሚከነክነው “መቼ ነው እኔ እውነት የምናገረው?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አንድ ቀን በጣም ከመጨነቁ የተነሳ፤ለሚስቱ እንዲህ አላት፡- “ሰማሽ ወይ የኔ ቆንጆ?”
“አቤት የኔ ጌታ?” አለች ባለቤቱ፡፡
“ኑሮዬ ተደራጅቶ ሁሉ ነገር ሞልቶልኝ ሳለ አንድ ነገር ይቆጨኛል”
“ምን?”
“ዕውነትን አለማግኘቴ”
“ዕውነት ነው ያልከኝ?”
“አዎን፡፡”
“እባክህ አትልፋ፡፡ በአገራችን ዕውነት ኖራ አታውቅም”
“አለች! እኛ መፈለግ አቅቶን ነው!”
“እንደዛ የምታምን ከሆነ ፣ቤትህ ቁጭ ብለህ ሳይሆን ዞር-ዞር ብለህ መፈለግ ነው ያለብህ!!” አለችው፡፡
ባልየውም፤
“ካልሽስ የዛሬ ማለዳ ዕቅዴ በጠዋት ወጥቼ ዕውነትን ፍለጋ መዞር ነው፡፡”
“ይቅናህ፡፡ ስታገኛት ግን ከኔ ልታገናኛት ቃል ግባልኝ” አለችው ሚስቱ፡፡
ባል ሊያገናኛት ቃል ገብቶ ንብረቱን ሁሉ አውርሷት ከቤቱ ወጣ፡፡
በየመንገዱ ከለማኝ ጀምሮ ይጠይቅ ጀመር፡፡ ተራሮች ላይ ወጥቶ ዕውነትን ለማግኘት ሞከረ፡፡ ዕውነትን አላገኛትም፡፡ ሸለቆዎች ውስጥ እየገባ በረበረ፡፡ ትናንሽ መንደሮችንና ከተሞችን አሰሰ፡፡ የለችም፡፡ ባህሮችንና የባህር-ዳርቻዎችንም መረመረ፡፡ ጨለማና ብርሃንን አጤነ፡፡ የቆሸሹ ቦታዎችንና በአበባ የተሞሉ ጽዱ ቦታዎችን እየገባ አጣራ፡፡ ዕውነት እዚያም የለችም፡፡ ቀንና ሌሊቶችን አጠና፡፡ ሳምንታትን፣ ወራትንና ዓመታትን ውስጣቸውን ፈተሸ፡፡ አሁንም እውነት አልተገኘችም፡፡
   አንድ ቀን በተራራ ግርጌ ባለ አንድ ዋሻ ውስጥ ዕውነት ተሸሽጋ እንደምትኖር ሰዎች በጠቆሙት መሰረት ወደዚያው ሄደ፡፡ እዚያ ያየው አስገረመው፡-
ለካ፤ዕውነት አንድ የጃጀች አሮጊት ነች!ብልህ ናት፡፡ አስተዋይ ናት፡፡ ማዳመጥ እንጂ መናገር አትወድም። በመላ ድዷ ላይ የምትታየው እንዲት ጥርስ ብቻ ናት፡፡  እሷ ግን የወርቅ ጥርስ ናት፡፡ ፀጉሯ ሽበት ብቻ ነው። እሱንም ሽሩባ  ተሰርታዋለች! የፊቷ ቆዳ የደረቀና የተጨማደደ ፤የዱሮ ብራና ይመስላል! ይህ ሁሉ ሆኖ የአሞራ ኩምቢ የመሰለ የእጅ ጣቷን እያወናጨፈች መናገር ታውቅበታለች፡፡ ድምጿ የሚያምር፣የተቃና ፣ለስላሳና ጣፋጭ ናት፡፡
ሰውየውም ለማጣራት ፡-
“ዕውነት፣ዕውነት አንቺ ነሽን?”ብሎ ጠየቃት፡፡
ዕውነት አሮጊቷም፤
“አዎን ነኝ” አለችው፡፡
አብሯት አንድ አመት በመቆየት ትምህርት ከጥበቧ ሊቀስም ወሰነ፡፡ ሀሳቡን ተቀብላው አብረው ከኖሩ በኋላ፤በመጨረሻ እንዲህ አለችው፤
ከእንግዲህ በየመንገዱ ላይ እግኝቶ ለሚጠይቅህ ለማንኛውም ሰው፤”ከየት መጣህ? “ሲልህ ከዕውነት ቤት መመለስህን ንገረው፡፡ ምን መሳይ ናት ካለህ፡-“ወጣት፣ፀጉሯ ጥቁር-ዞማ የመሰለ፣ ዐይኖቿ ጎላ ጎላ ያሉ፤የእጅ-ጣቶቿ ቀጥ ቀጥ ያሉ የሚያማምሩና ፤ቆዳዋ የልጅ ቆዳ የሚመስል ናት ብለህ ንገር” አለችው፡፡
ሰውየውም እየተደሰተ፤
“ለአገሩ ሁሉ ያልሽኝን እነግራለሁ” ብሎ እየሮጠ ሄደ፡፡ ዕውነትም እያየችው በትዝብት ሳቀችበት!
ሰዎች ራሳቸው ያልሆኑትን ነገር ሲነግሩን ለመቀበል ከመቸኮላችን የተነሳ በአይናችን የምናየውን እንኳ ለማመዛዘን ያቅተናል፡፡ ያም ሆኖ አንድ ነገር ውል ይለናል፡፡ ከእውነት ይልቅ በእጅጉ ዓለምን የሞላት ውሸት መሆኑ! ከተጨባጩ ነገር ይልቅ የተጭበረበረው ፍሬ ጉዳይ ውሃ እንደሚያነሳ እናስተውላለን፡፡ ይባስ ብለን ደግሞ ያንኑ ውሸት በሴራ እንተበትበዋለን!
ይኸንን እንዲያፀኸይልን ህንዳዊው ፈላስፋ ካውቲላ የሚለንን እንስማ፡-
“በዓላሚ ቀስተኛ፤የተሰደደ ቀስት
ሁለት ዕድል አለው፤መግደል ወይም መሳት፡፡
ግን በስል ጭንቅላት፣ሴራ ከተሳለ
ህፃንም ይገድላል፣እናት ሆድ ውስጥ ያለ!”     
      ይህ ግጥም ሴረኞችን እንከላከል ዘንድ የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ አደገኛነቱን እንድናጤንም የሚያሳስብ ነው፡፡ እንደእኛ ያለ ከአያት ቅድመ አያት ጀምሮ፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ፣ቂም በቀልና የውርዴ ያህል ተንኮል የተጠናወተውን ማህበረሰብ አዝሎ የሚጓዝ “ሊቅ- አዋቂ” ያለው፣መከረኛ ህዝብ፤ ሁሌ ለአሮጌውም ይሁን ለአዲሱ ሹም እጅ-እየነሳ እየኖረ ነው፡፡  ያ ባይሆን ኖሮ፡-
“ለመቶ አምሳ ጌታ፣ ስታሰር ስፈታ ነጠላዬ፤ አለቀ በላዬ….
ለምስለኔው ሙክት ለጭቃው ወጠጤ
እንዲህ ሆኜ ነው ወይ፣በአገር መቀመጤ! እያለ እያንጎራጎረም ነበር፡፡
ያም ሆኖ እጅግ የከፋው እለትም፡-
ገዴ ዞራ ዞራ በዕንቁላሉ ላይ….(“ይ” ይጠብቃል)
“ጊዜ እሚጠብቅ ሰው ጅል ሊባል ነወይ?
…አ.ረ ምረር ምረር፣ ምረር  እንደቅል
አልመርም ብሎ ነው፣ዱባ እሚቀቀል!”
ይላል፡፡
የሃገራችን ዴሞክራሲ ደጋግመን እንዳየነው፤ ወይ የይስሙላ ዲሞክራሲ (pseudo- democratey) ነው አሊያም ባንድ ስሙ ኢ-ዲሞክራሲ ወይም ፀረ ዲሞክራሲ ነው፡፡ አንድነትም፣የፓርቲዎች ጋብቻንም፣ ተፈጥረው ሳይጨርሱ በየቡድኑ ገብተው ጠብ የሚያጫጭሩትንም “የትልቁ ዓሳ ትንሹን አሳ ይውጣል” ፖለቲካንም “ፍየል ፈጁን አውሬ ፍየል አርደህ ያዘው” ባዩንም፣የዕድል-አጥቢያው አርበኛውንም፣ከኔ ካልሆንክ የዚያኛው ነህ ባይ  ወዶ ገባው ኮርማውን፣ አዲስ ግልብጡንም ወዘተ ወዘተ ፈሪውንም ከላይ ባየንበት ፖለቲካዊ መነፅር ለማየት አዳጋች አይደለም፡፡ አሰቃቂው ነገር ግን ሁሉም በህዝብና በአገር ስም መማል፣መገዘቱ ነው! ከዚህ ይሰውረን፡፡ በዚህ ላይ ስደት ለወሬ ይመቻልን ስንጨምርበት እጅግ የከፋ ሁኔታ ውስጥ ይከትተናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሐዘን ቤት ሙሾ አውራጆች፣ሠርግ ቤት ዘፈን አውጪዎች የሆኑት የየዘመኑ አድርባዮች የሚያደርሱት ጥፋት ፍጹም አደገኛ ነው፡፡ የጥንቱ የሩሲያ ፖለቲካ መሪ ቭላዲሚር ሌኒን the PENDULUM OF OPPORTUNITY  NEVER STOPS OSCILATING ይላል (የፔንዱለም እጅ ዕድሜ ልኩን መወዛወዙን በጭራሽ አያቆምም፣ አንደማለት ነው፡፡)  እጅግ ከጉዳዮች  ሁሉ ባስፈሪ ሁኔታ ዛሬ አሳሳቢ   የሆነው ግን በየሰበቡ፣ወይም በየሽፋኑ የሚጫረው የሃይማኖት ግጭት ነው! ከሁሉም  ይሰውረን!! ዛሬ በሀገራችን ብዙ ድርጅቶች፣ፓርቲዎች የፖለቲካ ብሔራዊ እንቅስቃሴዎች መፍጠራቸው ይነገራል፡፡ መፈጠራቸው ባልከፋ!  “የአንተ  እውነት ውሸት ነው፡፡ ትክክለኛው ዕውነት የእኔ ነው፡፡ እኔ ብቻ  ነኝ ሀቀኛ” ካሉ ነው ጣጣ እሚመጣው፡፡ ምን ያህል ህዝብ በዚህ ዓይነት ቅስቀሳ ይወናበዳል? ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ፣ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት እጃቸውን ሲያስገቡበት ምን ያህል የተወዛገበ ሂደት ውስጥ እንደሚገባ እናጢን፡፡ “ዕውነት ቦት ጫማውን ሳታጠልቅ፤ ውሸት ዓለምን ዞሮ  ይጨርሳል” የሚለው ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡፡
ለክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የጥምቀት በዓል!
ለሁላችንም ሁነኛ የአመለካከት ጥምቀት ይስጠን!

Read 9438 times