Saturday, 22 January 2022 00:00

በሶማሌና ኦሮሚያ የተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እያስከተለ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ከ270 ሺ በላይ ከብቶች በድርቁ ሞተዋል
                 
              ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለከፋ ችግር የዳረገው በሶማሌና ኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ድርቅ፣ በ40 ዓመታት ታሪክ ውስጥ እጅግ የከፋው መሆኑን አለማቀፍ የረድኤት ተቋማት ገለፁ፡፡
የአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስ ኤዩ) እና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ባወጡት መረጃ፤ የተከሰተው ድርቅ በ40 ዓመታት ታሪክ ውስጥ እጅግ የከፋ መሆኑን ጠቁመው፣ ነዋሪዎች ወደተለያዩ አካባቢዎች እየተሰደዱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች አርብቶ አደሮች መሆናቸውንና የኑሮ መሰረታቸው የሆኑት ከብቶቻቸው ምግብና ውሃ በማጣት በየእለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ እየሞቱ መሆኑንም የተቋማቱ  ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በሶማሌና በኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች በወቅቱ ይጠበቅ የነበረው ዝናብ አለመዝነቡንና አካባቢዎቹ ዝናብ ካገኙ ረጅም ጊዜ  መሆኑን ተከትሎ የድርቁ ሁኔታ በቀጣይም የከፋ ችግር ያስከትላል የሚል ስጋት እንዳለ ሪፖርቱ ያሳስባል፡፡
በተለይ በሶማሌ ክልል ፋፋን እና ሲቲ ዞን ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ ይጠበቅ የነበረው ዝናብ አለመዝነቡን ተከትሎ፣ ከፍተኛ የሆነ ድርቅ መከሰቱንና በአካባቢው ለከብቶች የሚሆን ምንም አይነት ግጦሽ አለመኖሩን እንዲሁም ለሰው ምግብነት ይመረቱ የነበሩ ሠብሎች ደርቀው መቅረታቸውን አመልክቷል-ሪፖርቱ
በዚህ ድርቅ ሳቢያ በሶማሌ ክልል በአመቱ ይጠበቅ ከነበረው የማሽላና የበቆሎ ምርት 70 በመቶ እንዲሁም ይጠበቅ ከነበረ የማሽላና የበቆሎ ምርት 70 በመቶ እንዲሁም ስንዴ ምርት 30 በመቶ መታጣቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በደቡብ ኦሮሚያ በተመሳሳይ 70 ከመቶ የሚሆነው ምርት መታጣቱን አመልክቷል፡፡
በሁለቱ ክልሎች እስካሁን መኖና ውሃ በማጣት ከ270 ሺህ በላይ ከብቶች መሞታቸውን፣ አሁንም ቁጥራቸው ከሞቱት የላቀ ከብቶች ለተመሳሳይ አደጋ መጋለጣቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ሰዎችም በድርቁ ምክንያት የተሻሉ ወደ ሚሏቸው የክልሎች አካባቢዎች ከብቶቻቸውን ይዘው እየተሰደዱ መሆኑም በሪፖርቱ ተመልክቷል።


Read 3459 times