Saturday, 22 January 2022 00:00

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ግፊት ሲደረግ ነበር ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የኮቪድ መስፋፋትን ምክንያት በማድረግ የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ከፍተኛ ግፊት ሲደረግ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ “የተለያዩ ስውር እጆች በአዲስ አበባ ኮቪድ ተስፋፍቷል፤ በሃገሪቱም ሠላም የለም፤ የፀጥታ መደፍረስ አጋጥሟል” በሚል በየዓመቱ በአዲስ አበባ ብቻ የሚካሄደውን የመሪዎች ጉባኤ፣ በሌላ ሃገር እንዲካሄድ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
ይሄን ስውር ተልዕኮ ለማክሸፍም በርካታ እልህ አስጨራሽ የዲፕሎማሲ ጥረት መደረጉን የገለፁት ቃል አቀባዩ፣ “በመጨረሻም በርካታ የማግባባት  ስራዎች ተሰርቶ ጉባኤው ከአዲስ አበባ እንዳይወጣ የማድረጉ ጥረቱ ተሳክቷል” ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጉዳዩን አስመልክተው በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “አፍሪካዊ ወንድማማችነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር በሚያስፈልገን በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት መሪዎች ተስማምተው የህብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡” ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልዕክትም፤ “የጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄድ ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ ሰላማችንና ደህንነታችን የምናስመሰክርበት፤ ለአፍሪካ ጉዳዮች ያለንን አቋም በድጋሚ የምናስመሰክርበት፣ የኢትዮጵያን መልካም ሁኔታ ለአፍሪካውያን ወገኖቻችን በተግባር የምናሳይበት፤ከዚያም አልፎ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የምናገኝበት ጉበኤ ነው፡፡ ስለዚህም ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ከሁላችንም ብዙ ይጠበቃል፡፡” ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በመጪው ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡




Read 3903 times