Saturday, 22 January 2022 00:00

የስነተዋልዶ ጤና----በግጭት አካባቢ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የስነ ተዋልዶ ጤና ሰፋ ያሉ ጉዳዮችን የሚመለከት ነው፡፡ እርግዝናና ልጅ መውለድ፤ የሴ ቶች፤ የህጻናት፤ የታዳጊዎችና የወንዶች ጤንነት ከስነልቡና…. ከአካል… ከወሲባዊ ጥቃት መከላከል እና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ማድረግ፤ ያልተጠበቀ እርግዝናን እና ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥን መከላከል፤ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ፤ የምክር እና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግን ሁሉ ይመለከታል። የስነተዋልዶ ጤና ኤችአይቪ ኤይድስን ጨምሮ  በወሲባዊ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፉ በሽታዎችን መከላከልና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስወገድን ይጨምራል፡፡
የስነተዋልዶ ጤናን ለመጠበቅ የሚሰጠው አገልግሎት በሰዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች በተለይም ለሴቶች የተለየ ትኩረት የሰጠ መሆን አለበት፡፡ የህብረ ተሰቡን ማህበራዊና ባህላዊ ገጽታዎች ያገናዘበ እና ያከበረ መሆን አለበት፡፡
ግጭት በተከሰተባቸው እና ከአካባቢያቸው በተሰደዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የደረሰ ችግር ቢኖር የስነተዋልዶ ጤና አገል ግሎቱ የሰው ልጆችን መብት ባከበረ መልኩ መሰረታዊ የሆኑ ፍላጎቶችን ለምሳሌም መጠለያ፤ ምግብ፤ ውሀ እና የጽዳት አገልግሎትን ባካተተ መልክ ቢሆን ትክክለኛው አሰራር ይሆናል፡፡   
የአለም የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ 2000
The open public journal 2020 እንዳስነበበው በአለም አቀፍ ደረጃ ሊባል በሚችል ሁኔታ በተለያዩ ጊዜያት ወታደራዊ ግጭቶች ከውጭና ከውስጥ (እርስ በእርስ) በሚባል ደረጃ ተከስ ተዋል፡፡ በኤሽያ፤ ሲሪያ፤ አፍጋኒስታን እና ኢራቅ በቅርብ ጊዜ በጣም አስከፊ በሆነ ደረጃ የተ ከሰቱ ግጭቶች ነበሩ፡፡ በአፍሪካም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ ደቡብ ሱዳን እና መካከ ለኛው አፍሪካ እንዲሁ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በአሜሪካም ሜክሲኮ በተመሳሳይ ግጭቶች እና የወንጀል ድርጊቶች ስለነበሩ የእናቶችና የህጻናትን ሞትና አካል ጉዳት ለመከላከል የተ ሰሩ በጎ ስራዎችን እጅግ ወደሁዋላ እንደጎተቱና ምንም ጥረት እንዳልተደረገ የሚያስቆጥር ውጤት እንዳስከተሉ እውን ነው፡፡ ይህንን በተለይ ከአፍሪካ አንጻር ለሚመለከተው ከፍተኛ ድህነትና ደካማ የሆነ የጤና አገልግሎት ባለበት ሁኔታ ችግሩን የበለጠ እንደሚያገዝፈው አይጠረጠርም፡፡ ሰዎች ግጭት በሚነሳባቸው አካባቢዎች ሁሉ በተለይም ሴቶችና ህጻናት አካባቢያቸውን ለቀው እንደሚሰደዱና ከስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ስደት ባለበት ሁኔታ በቂ የህክምና ባለሙያና መድሀኒት እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶች እጥረት እንደሚከሰት መረጃው ይገልጻል፡፡
በግጭት ወቅት በህክምናው ዘርፍ በሚኖረው በጣም የተዳከመ የህክምና አገልግሎት አሰ ጣጥ ምክንያት ሊከላከሉዋቸው የሚቻልና ለጉዳት የማያደርሱ ሕመሞች ሁሉ ሰዎችን የሚጎዱ ሲሆን የውሀ እጦትና የጽዳት ማጣት ለመመረዝ ስለሚያበቃ በተለይም በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ከፍተኛ ችግር ይከተላል፡፡ በእርግጥ እንደ ወባ፤ታይፎይድ የመሳሰሉት ሁሉ የወታደራዊ ግጭትን በመሸሽ ለሚሰደዱ ሰዎች አስከፊ ሕመሞች ናቸው፡፡
ወታደራዊ ግጭት በሚደረግባቸው አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችን መረጃው እንደሚከተለው ያስነብባል፡፡
ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት አንዱ ነው፡፡ ምንም እንኩዋን የተቻለውን ያህል ድጋፍ ይደረጋል ቢባልም ሰዎች በቤታቸው ውስጥ እንደሚኖሩበት ሁኔታ ሊሟላ አይችልም፡፡ ምናልባትም በድህነት የሚኖሩ እንኩዋን ቢሆኑ በመኖሪያ ቤታቸው እንደአቅም በለመዱት ሁኔታ መኖር ለሰዎች ተስማሚ ነው፡፡
በእርግዝና ላይ ላሉ ሴቶች፤ ለህጻናት፤ ለሽማግሌዎች፤ ለታመሙ ሰዎች አስፈላጊውን ለማሟላት የሚያስችል አቅም ካለመኖሩም በላይ ቢኖር እንኩዋን ወደ ገበያ ሄዶ ተፈላጊውን ነገር ማግኘት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሊገበያዩ የሚችሉባቸው ቦታዎች ስለሌሉ ነው፡፡
በስደት ወቅት በሰዎች ላይ የሚደርስ ሕመም እንኩዋን ቢኖር ለማሳከም የሚቻልበት የህክምና ቦታ አለመኖሩ በስደት ላይ ላሉ ሰዎች እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
በስደት ወቅት ህጻናቱን፤ ሽማግሌዎችን፤ እርጉዝ ሴቶችን እና የታመሙ ሰዎችን በቤት ውስጥ በመንከባከቡ ረገድ የሴቶችና ልጃገረዶች ሚና እጅግ በጣም ውስንና አስቸጋሪ ነው፡፡ ወደ ገበያ መሄድ፤ ምግብ ማብሰል፤ ጽዳትን መጠበቅ፤ ልብስን ገላን የመሳሰሉ ነገሮችን ማጠብ ውሀ በተለመደው መንገድ ቀድቶ ማቅረብ የመሳሰሉት ነገሮች እጅግ ከባድ ናቸው፡፡ ሴቶች በስደት ወቅት ቤተሰብን የመንከባከብ ተግባር ለመፈጸም በቀን ውስጥ እስከ 11 ሰአት ድረስ እንደሚያጠፉ ተመልክቶአል፡፡ በግጭት ምክንያት በሚፈጠረው ስደት የተነሳ ሴቶች የስነተዋልዶ ጤናቸውን ካለመንከባከብ በተጨማሪ ልፋታቸው ከባድ እና ከንቱ ነው፡፡
በግጭት ወቅት ሌላው የሚያጋጥመው ነገር ሀብትን ማጣት ነው፡፡ አብዛኞቹ ለስደት የሚዳረጉ ቤተሰቦች ቤታቸውን፤ የሚያርሱትን መሬት፤ ሰብላቸውን፤ ገንዘባቸውንና ያፈሩትን ሀብት ትተው ወደማያውቁት አዲስ ስፍራ እንዲሰደዱ ግድ ይሆንባቸዋል፡፡  
መጠለያ ማግኘት በስደት ላይ ላሉ ሰዎች አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይም በእርግዝና ላይ ላሉ ሴቶች፤ ጨቅላ ህጻን ለያዙ ወይንም በቅርብ ጊዜ ለወለዱ፤ ለህጻናት እና ለመሳሰሉ ሁሉ መጠለያ አለማግኘት ከባድ ነው። ምናልባትም በሰፊ አዳራሽ ወይንም ከሸራ፤ ከቆርቆሮ በመሳሰሉት በተሰሩት መጋዘኖች በእምነት ቦታዎች እና በመሳሰሉት ስፍራዎች በብዛት ሆነው ሊሰፍሩ ይችላሉ፡፡ ለጊዜው እንቅልፍን ሸለብ ለማድረግ ያህል ካልሆነ በስተቀር ለመኖሪያነት እጅግ አስቸጋሪ ነው። ከልክ በላይ በተጨናነቀና ከለላ ወይንም ለጥበቃ በማያመች ሁኔታ ውስጥ መኖራቸው ሊያደርስ ከሚችለው ጉዳት መካከል ሴቶችና ልጃገረዶች ተገድዶ ለመደፈር አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡  
ለስደት የተዳረጉ ልጃገረዶችና ሴቶች ተገዶ የመደፈር አደጋ ሲገጥማቸው ምናልባት ያልተ ፈለገ እርግዝና ቢገጥማቸው፤ ደህንነቱ ያልተጠባ ጽንስ ማቋረጥን ቢሞክሩ፤ ወይንም በግብረ ስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፈው ሕመም ወይንም ለኤችአይቪ ኤይድስ ቢጋለጡ እራሳቸውን በአስቸኩዋይ ሊከላከሉበት የሚችሉት የህክምና አገልግሎት በቅርብ ማግኘት ስለማይችሉ በወቅቱም ይሁን በወደፊት ሕይወታቸው ለችግር ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
በግጭት ምክንያት የሚሰደዱ ቤተሰቦች ከሚያጡአቸው ጥቅሞች መካከል ምግብ ነክ ያል ሆኑ ቀላል የሚመስሉ ግን ቀላል ያልሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌም …ፍራሽ፤ ብርድልብስ፤ ትራስ፤ የውሀ ማጠራቀሚያ (ጀዲካን)፤ የማብሰያ እቃዎች፤ የጽዳት መጠበቂያ፤ ሳሙና እና የሚለብሱት ልብስ በነበሩበት ቦታ ተትተው የሚቀሩ ወይንም እንደልብ መሸመት የማይቻል በመሆኑ በስደት ጊዜ ለማግኘት አስቸጋሪ ከሚሆንባቸው መካከል ይመደባል፡፡
በግጭት ወቅት ከጥቅም ውጭ ከሚሆኑ አገልግሎት መስጫዎች መካከል የመጠጥ ውሃ ቦኖዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ውሀ የሚቀዳባቸው ቦታዎች እና መጸዳጃዎች በግጭቱ ምክንያት አደጋ ስለሚደርስባቸው ግጭቱን በመፍራት የሚሰደዱ ሰዎች በደረሱበት ቦታ ይህንን የንጹህ ውሀ አገልግሎት ለማግኘት ይሳናቸዋል፡፡
በስደት ላይ ያሉ ሰዎች ለመጠጥም ይሁን ለጽዳት የሚያውሉት ውሀ ማጣታቸው በመጠ ጥም ይሁን በጽዳቱ በኩል ለውሀ ወለድ በሽታዎች እና ለኢንፌክሽን ሊያጋልጣቸው  ይች ላል፡፡ በሌላም በኩል ውሀውን ለማግኘት እርቀው መጉዋዛቸው ግድ ስለሚሆን በዚህ ሳቢያ ለጥቃት ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
ሴቶች ወይንም ልጃገረዶች የሽንት ቤት መጸዳጃዎችንም ሆነ የወር አበባ መቀበያን በተገቢው ሊያገኙ ስለማይችሉ ለኢንፌክሽን ሊጋለጡ ይችላሉ።
በግጭት ምክንያት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሴቶች እና ወንዶች የተለያየ የመጸዳጃ ቦታ ዎች ስለማይኖራቸውና እንዲያውም ራቅ ብለው በመሄድ ክፍት በሆኑ ሜዳዎች ለመጠቀም ስለሚገደዱ ሴቶችና ልጃገረዶች ክብራቸውን፤ ጤንነታቸውን በመንከባከብ ረገድ ከፍተኛ የሆነ ችግር ይገጥማቸዋል The open public journal 2020 እንዳስነበበው፡፡
ግጭት በሚኖርባቸው አካባቢዎች የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም። የእናቶችና ጨቅላ ልጆቻቸውን ደህንነት በሚመለከት አገልግሎት መስጠት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ እና አደገኛ የሆኑ የወሲብ ባህርይዎችን መከላከል ከባድ ይሆናል፡፡ የስነተዋልዶ ጤናን እንዲጠበቅ ማድረግ በተለይም ለሴቶች የሰብአዊ መብትን ከማክበር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህንን መብት አለምአቀፍ አካላት የተቀበሉትና በአለምአቀፍ ግብ እንዲሟላ ስምምነት የተደረሰበት እንዲሁም የሚተገብሩት ሆኖ ሳለ ነገር ግን በሚነሱ ግጭቶች ሳቢያ ሲሸራረፉ ይታያል። ይህንን ለማስተካከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን በጠቅላላ ባንመለከትም የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከሌሎች አካላት ጋር በመተባር በማድረግ ላይ ያለውን በሚቀጥለው እትም ለንባብ እንላለን፡፡Read 3747 times