Print this page
Sunday, 23 January 2022 00:00

የሃይማኖት ፍልስፍና

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(0 votes)

   (ክፍል-5 ነገረ እኩይና ሌሎችም ትችቶች)
                
          በክፍል-4 ፅሁፌ እግዚአብሔር መኖሩን የሚያስረዱ መከራከሪያዎች ላይ የተሰነዘሩትን ትችቶች ተመልክተናል። በዛሬው ፅሁፌም  ተጨማሪ ትችቶችን እንመለከታለን፡፡
ከዚህ በፊት እንዳነሳነው እግዚአብሔር መኖሩን ከሚያስረዱ መከራከሪያዎች መካከል አንደኛው የሥነ ዲዛይን መከራከሪያ ነው፡፡ ይህ መከራከሪያ ልክ የእጅ ሰዓታችንን ወይም ሞባይል ስልካችንን አይተን ‹‹ሰዓቱንና ሞባይሉን የሰራ አዋቂ ሰው አለ›› እንደምንለው ሁሉ፣ የዩኒቨርሱን ህግና ሥርዓት ተመልክተንም ‹‹ዩኒቨርሱን በዕውቀት የሰራ ኃይል አለ›› ማለት እንችላለን የሚል ሐሳብ አለው፡፡
እዚህ መከራከሪያ ላይ እንደ ካንት፣ ዴቪድ ሂዩምና በርትራንድ ረስል ያሉ ፈላስፋዎች ትችቶችን አቅርበዋል፡፡
ኢማኑኤል ካንት ‹‹በሥነ ዲዛይን መከራከሪያ›› ላይ ሁለት ትችቶችን ሰንዝሯል። የመጀመሪያው፣ ‹‹የሥነ ዲዛይን መከራከሪያ ትክክል ነው ብለን ብንሄድ እንኳ፣ መከራከሪያው የሚያስረዳን ዩኒቨርሱ ጥሩ አርክቴክት እንዳለው እንጂ ፈጣሪ መኖሩን አይደለም፡፡ ምክንያቱም፣ ዩኒቨርሱ በራሱ መንገድ ከተፈጠረ በኋላ አርኪቴክቱ (የኪነ ህንፃ ባለሙያው) ዩኒቨርሱ የሚመራበትን ህግና ሥርዓት ሰርቶለት ሊሆን ይችላልና፡፡
ሁለተኛ የካንት ትችት፣ ‹‹የሥነ ዲዛይን መከራከሪያ በዩኒቨርሱና በሰው ልጅ አእምሮ መካከል ያለውን መስተጋብር የማያውቅ ነው›› የሚል ነው፡፡ እንደ ካንት አመለካከት የሥነ ዲዛይን ተከራካሪዎች ዩኒቨርሱ በህግና በሥርዓት እንደሚመራ ማሰባቸው ትክክል አይደለም፡፡
ዩኒቨርሱ በተለያዩ ኤሌክትሮ-ማግኔቲክ ሞገዶች፣ በተለያዩ ድምፆችና እንቅስቃሴዎች፣ በተለያዩ ቀለሞችና ቅርፆች፣ በተለያዮ ጣዕሞችና ሽታዎች ትርምስምስ ያለ ዓለም ነው፡፡ እናም ዩኒቨርሱ ከዚህ ሁሉ ትርምስ የተነሳ ህግና ሥርዓት የለውም። ይሄንን ትርምስምስ ያለ ዓለም በመልክ በመልኩ እያደረገ የሚያደራጀው አእምሯችን ነው፡፡ አእምሯችን ይሄንን የሚያደርግበት ደግሞ የራሱ ሶፍትዌር አለው፡፡
ነገሩን ከኮምፒዩተር ጋር አገናኝተን ማየት እንችላለን፡፡ የኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ ትርጉም በሌላቸው በዜሮና በአንድ ቁጥሮች ብቻ የተሞላ ነው፡፡ ሆኖም ግን ዜሮና አንድን በተለያየ መንገድ እያደራጀ ወደ ፊደሎች፣ ቁጥሮች፣ ምስሎችና እንቅስቃሴዎች የሚቀይራቸው የኮምፒዩተሩ ሶፍትዌሮች ናቸው፡፡ አእምሮም ትርምስምስ ያለውን ዓለም በመልክ በመልክ እያደራጀ ልክ ዩኒቨርሱ ህግና ሥርዓት እንዳለው አድርጎ ያሳየናል፡፡ በመሆኑም፣ ለዩኒቨርሱ ህግና ሥርዓት የሰጠው እግዚአብሔር ሳይሆን የሰው ልጅ አእምሮ ነው፡፡
ዴቪድ ሂዩም በሥነ ዲዛይን መከራከሪያ ላይ የሚሰነዝረው ትችት ደግሞ፣ ‹‹ይህ መከራከሪያ በሥነ አመክንዮ ‹‹The Fallacy of Composition›› የሚባለውን ግድፈት ፈፅሟል›› የሚል ነው፡፡ ይሄ ሥነ አመክንዮአዊ ግድፈት በአንድ ነገር በጥቅሉና ጥቅሉን በሰሩት ክፍሎች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ነው፡፡
ለምሳሌ፣ ብረት የተሰራበት የመጨረሻዎቹ ቅንጣቶች አተሞች ናቸው፤ አተሞች ግን አይታዩም፡፡ ‹‹አተሞች ስለማይታዩ፣ ከአተሞች የተሰራው ብረትም አይታይም›› የሚል ሰው ‹‹The Fallacy of Composition›› የሚባለውን ግድፈት ፈፅሟል፤ የአተሙን ያለመታየት ባህሪ ወደ ብረቱ ያለ አግባብ ወስዶታልና፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የተለያዩ የዩኒቨርሱ ክፍሎች (ህንፃዎች፣ ድልድዮች፣ ኮምፒዩተሮች…) ፈጣሪ ስላላቸው ብቻ ይሄንን የፈጣሪነት ባህሪ ለጥቅሉ ዩኒቨርስም መስጠት አግባብ አይደለም፡፡
በዴቪድ ሂዩም አመለካከት የሥነ ዲዛይን መከራከሪያ የሚፈፅመው የሥነ አመክኖያዊ ግድፈት ‹‹The Fallacy of Composition›› ብቻ ሳይሆን ‹‹Weak Analogy (ደካማ ተመሳስሎሽ)›› የሚባለውን ግድፈትም ጭምር እንጂ፡፡
እንደ ሂዩም አመለካከት ‹‹የእጅ ሰዓታችን ወይም የሞባይል ስልካችን ፈጣሪ ስላለው ብቻ፣ ዩኒቨርሱም ፈጣሪ አለው›› ብሎ መከራከር Weak Analogy ነው፡፡ እንዴት ለእጅ ሰዓታችን የሰጠነውን መደምደሚያ ለዩኒቨርሱ እንሰጠዋለን? ሁለት ዓለሞች ቢኖሩ፣ ‹‹አንዱ ዓለም ፈጣሪ አለው፤ ስለዚህ ሁለተኛውም ዓለም ፈጣሪ አለው›› ብንል ማመሳሰሉ ትርጉም ይኖረው ነበር። ሰዓትን፣ ቤትንና ዩኒቨርስን ስናመሳስል ግን ተመሳስሎሹ አያስኬድም፤ ደካማ ይሆንብናል፡፡
የሥነ ዲዛይን መከራከሪያ ላይ ትችት የሰነዘረው ሌላኛው ፈላስፋ እንግሊዛዊው በርትራንድ ረስል ነው፡፡ ረስል በዚህ መከራከሪያ ላይ ሁለት ትችቶችን ይሰነዝራል፡፡ የመጀመሪያው ትችት በጥያቄ የታጀበ ነው፣ ሁሉን ቻይ፣ ፍፁም የሆነና ዝንተ ዓለም የነበረ አምላክ እንደዚህ ዓይነት በግድፈት የተሞላ ዓለም እንዴት ሊፈጥር ቻለ? እኔ ይሄንን ነገር ከእሱ አልጠብቅም!! እናንተ ሁሉን ቻይ፣ ፍፁም ብትሆኑና ይሄንን ዓለም ፍፁም ለማድረግ ሚሊዮን ዓመታት ቢሰጣችሁ፣ እንደዚህ ዓይነት በሰቆቃና በእልቂት የተሞላ ዓለም ነው ወይ የምትፈጥሩት?
ሁለተኛው የረስል ትችት ከቻርለስ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ህልዮት የሚነሳ ነው፡፡ ፍጥረታት ረጅምና አዝጋሚ በሆነ ሂደት እንዴት ራሳቸውን ከአካባቢያቸው ጋር እያስማሙ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ እንደደረሱ የዳርዊን ህልዮት ግልፅ አድርጎታል፡፡
ይሄም የሚያሳየን ዩኒቨርሱ በአንድ ጊዜ ጥንቅቅ ተደርጎ የተፈጠረ ሳይሆን በሂደት ራሱን ከሁኔታዎች ጋር እያስማማና እየለወጠ መሄዱን ነው፡፡
ነገረ እኩይ (The Problem of Evil)
የነገረ እኩይ ፅንሰ ሐሳብ በፍልስፍናም ሆነ በሥነ መለኮት ትምህርት ውስጥ በጣም የቆየ ነው፤ የአስተምህሮቱ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሐሳብም ‹‹ሁሉን ቻይና ፍፁም የሆነ አምላክ እያለ እንዴት በዓለም ላይ እኩይ ሊኖር ቻለ?›› የሚል ነው፡፡ እዚህ ሐሳብ ላይ የሥነ መለኮት መምህራን ትኩረት እንዲያደርጉበት ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት፣ ሐሳቡ ‹‹እግዚአብሔር የለም›› ብለው ለሚከራከሩ ሰዎች ጠንካራ የሐሳብ ስንቅ የሚያቀብላቸው መሆኑ ነው፡፡
ነገረ እኩይ አብዝቶ ሲያስጨንቃቸው ከነበሩ ቀደምት የሥነ መለኮት ፈላስፎች ውስጥ ቀዳሚው ቅዱስ ኦገስቲን ነው። ‹‹ሁሉን ቻይና ፍፁም የሆነ አምላክ እያለ እንዴት በዓለም ላይ እኩይ ሊኖር ቻለ?›› ለሚለው የነገረ እኩይ ጥያቄ፣ ቅዱስ ኦገስቲን በስተመጨረሻ የደረሰበት ድምዳሜ ‹‹እኩይ የመልካም ነገር አለመኖር እንጂ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ህልውና ያለው ነገር አይደለም (Evil doesn’t have any existence, but it’s the absence of good)›› የሚል ነው፡፡
ልክ ጨለማ፣ በብርሃን አለመኖር ምክንያት የሚመጣ ነገር እንጂ በራሱ ህልው የሆነ ነገር እንዳልሆነው ሁሉ፣ እኩይም የመልካም ነገር አለመኖር ያመጣው ክስተት እንጂ ፍጡር አይደለም፡፡
ይሄ የኦገስቲን ሐሳብ ለበርካታ የሥነ መለኮት ሊቃውንት እፎይታን የሰጠ ነበር። ለፈላስፎች ግን ይሄ የኦገስቲን ሐሳብ የሚያረካቸው አልሆነም፡፡ ለዚህም ነው ከቅዱስ ኦገስቲን ቀደም ብሎ የነበረው ኢ-አማኒው ፈላስፋ ግሪካዊው ኤፒኩረስ ያነሳውን የነገረ እኩይ ሐሳብ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ዴቪድ ሂዩም እንደገና የተነሳው፡፡
ሂዩም ኤፒኩረስን በመጥቀስ ከፍፁማዊው አምላክ ጎን ለጎን እንዴት እኩይ አብሮት ሊኖር እንደቻለና ማጥፋት እንዳልቻለ በሦስት ምናልባቶች ያስቀምጠዋል፤ የመጀመሪያው፣ ምናልባት፣ እግዚአብሔር  እኩይን ማጥፋት እየፈለገ ነገር ግን ካልቻለ፣ እግዚአብሔር  አቅመቢስ ነው ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው፣ እግዚአብሔር እኩይን ማጥፋት እየቻለ ግን ማጥፋት ካልፈለገ፣ እግዚአብሔር ክፉ ነው ማለት ነው፡፡ ሦስተኛ፣ እግዚአብሔር እኩይን ማጥፋት እየቻለም እየፈለገም ሆኖም ግን ካላጠፋው፣ እግዚአብሔር የለም ማለት ነው፡፡
በሦስቱም ምናልባቶች ብንሄድ ነገረ እኩይ የእግዚአብሔር ህልውና መከራከሪያዎች ላይ ጠንካራ ተግዳሮት ያስከትላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡Read 353 times