Monday, 24 January 2022 00:00

"በቀኝ አውለኝ!"

Written by  ነፃነት አምሳሉ አፈወርቅ
Rate this item
(1 Vote)


               "ቀኝ መዋል ለራስ ህልውና ብቻ ማሰብ ሳይሆን ለሌሎችም በጎነትን በገዛ ተነሳሽነት ማድረግን ያካትታል፡፡ የራስን ዓለም ብቻ ፈጥሮ ምቾትና ድሎትን ማግበስበስ ስግብግብነት ነው፡፡ የእኛ ደስታ ሙሉ የሚሆነው ከሌሎች ጋር ባለው ቀና መስተጋብር ነው፡፡ በጎነትን ስንሰጥ ከኛ የሚቀነስ ነገር የለም፡፡ ለሌሎች ግን ሌላ የህይወት ገጽ ሊከፍት ወይም የእድገት መሰላል ሊሆን ይችላል፡፡"
                 
            ብሂለ አበው ንጋሬያችን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወራረሱ፣ የሕይወታችን ትርጉም ሰጪ ፍቺዎች ሆነው ዘልቀዋል። ቁምነገርን በሳቅና በጨዋታ አዋዝቶ ብልህን ለመምራት፣ ዝንጉን ለማንቃት፣ ሰነፍን ለመምከር፣ ክፉን ለመገሰጽ እንደየ ይትብሃላችን የቋንቋ ደርዝ እያመሳጠርንና እያፍታታን፣ ኑሮአችንን ቀሊል ለማድረግ በመላና በዘዴ የምንጋራቸው ምሳሌያዊ ንግግሮቻችን የጋራ ሀብቶቻችን ሆነው ቀጥለዋል፡፡
የሰው ልጅ “ሀ ብሎ ከፊደል፣ ዋ ብሎ ከመከራ” ይማራል፡፡ ማለዳውን ሲጀምርም ቀኝ አውለኝ ብሎ ከቤቱ ይወጣል፡፡ የአባባሉ ምንጭም የእለት ተእለት ኑሯችን ነጸብራቅ  ነው፡፡ ጉዳዩ የመንገድ መመላለሻ አቅጣጫዎችን ይዞ የመጓዝ ሳይሆን የበጎነትን ሃሳብ የመሻት፤ የመቀበል፤ የማሳደግ፤ ከመልካም ነገር ጋር የመተባበር ጽኑ ምኞት ነው፡፡ ይህ ምኞት ምንም እንኳን በተማጽኖ የሚቀርብ ቢሆንም፣ እንዲያው በሰማይ ላይ ተበትኖ እንደቀረ ደመና ብላሽ ሆኖ እንዳይቀር በተግባር መደገፍ ይኖርበታል፡፡  
ሰው የሚያጭደው ያንኑ የዘራውን እንደሆነ ሁሉ የምስራችን ለመስማት ከመርዶ ነጋሪነት መውጣት አለበት፡፡ የቀና እሳቤ ባለቤት መሆን የግድ ይላል። መልካምነትን ከሰዎች ከመጠበቅ ይልቅ አስቀድሞ መልካም ማድረግን ይጠይቃል። በጎነትን ከሶስተኛ ወገን ከመፈለግ ይልቅ ራስን አርአያ አድርጎ ሰርቶ ማሳየትንና ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ የቀኝ መዋል እሳቤው ከዚህ እውነት ጋር መጋመድ ይኖርበታል፡፡
ፍቅር ድሮ ቀረ፤ ዘንድሮ ምን ሰው አለ፤ መዋደድማ ታሪክ ሆነ፤ የሚሉ ልብ ሰባሪና መንፈስ አድካሚ ንግግሮች የክብር ቦታ እያገኙ፣ ተስፋ ሰጪና አበረታች አባባሎች ምንጩ እንደ ደረቅ ዥረት እየከሰሙ የመጡት ለምንድነው ብለን እኛነታችንን በጠራ መስታወት ላይ ብንመለከት፣ ችግሩ እኛ ሰዎች መልካም የማንሆነው መልካም መሆን አቅቶን ሳይሆን መልካም መሆን ስለማንፈልግ መሆኑ ይገለጥልናል። የሰው ልጅ ድርጊቱ በልቡ ውስጥ ሞልቶ ከፈሰሰው ሃሳብ የፈለቀ እውነት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡  አስቀድሞ መስረቅ የፈለገ ሰው ቀን አጋጣሚ ቦታና ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ካደፈጠበት ጎሬ ብቅ ብሎ የልቡን አድርሶ ይመለሳል፡፡ እጄ የሰረቀው እኔ ሳልፈልግ ነው የሚል ሰው የለም፡፡ እግሬ የተራገጠው እኔ ሳላዝዘው ነው ማለትም አይችልም። ክፉ ቃል የተናገርኩት አስቤበት ሳይሆን አንዳች ነገር ከአፌ አፈትልኮ ነው ማለት የራስን ሞኝነት በአደባባይ እውቅና መስጠት ነው፡፡ የፍቅርም ሆነ የጥላቻ መነሻ መስመሩ ልባችን ውስጥ ያለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህን አስተሳሰብ ገርቶ ወደ ፍቅር መመለስ እንጂ ለሰራነው ጥፋት ማስተባበያ እንዲሆነን ሽማግሌዎች ፊት ጉንጭ አልፋ ክርክር ማድረጉ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
ያልሰጠነውን ፍቅር አናጭድም፤ ያልዘራነውን በጎነት አንሰበስብም፤ ያልወቃነውን ደግነት በጎተራ አንከትም፤ ያልተከልነውን አብሮነት ከየትም አምጥተን አናሳድግም፡፡ ሰው የተባልንበት እውነት ከሌሎች ፍጥረታት ጋር ስንተያይ ተወዳዳሪ በሌለው ክብር በመፈጠራችን በእለት ኑሯችን ላይ የራሳችን ይሁንታ÷ ድርሻ÷ ውሳኔና ፈቃድ እንዳለን ብንዘነጋና ነገሩን ሁሉ በምንግዴ ብንፈጽመው በቸልተኝነታችን እንጠየቅበታለን እንጂ አንታለፍበትም፡፡
ቀኝ መዋል ስንል ከፈጣሪ በታች የራሳችንን እለታዊ ኑሮ ስንኖር፣ በገዛ አካሄዳችን ላይ እኛ ራሳችን ወሳኝ አካል መሆናችንን ታሳቢ እንድናደርግ እድል ይሰጠናል፡፡ ከፍጥረታችን አንስቶ የምንመረምርበት÷ የምንፈትሽበት÷ የምናመዛዝንበት አእምሮ የተሰጠን ለምንሰራው እያንዳንዱ ነገር በኃላፊነት እንድንወጣው ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም ቀኝ አውለኝ እያልን የፍቅር ሰው የመሆን ሰፊ እድል ተሰጥቶናል፡፡ በዚህ ጉልበትም የሚጠቅመንን ከማይጠቀምን÷ የሚረባንን ከማይረባን÷ የሚጎዳንን ከማይጎዳን እንደ ወርቅ አንጥረን ለመለየት እንችላለን፡፡ ይህ ችሎታችን የተገኘው ከሰው መሆን ጸጋ ነው። ይህ ጸጋ አዲስ እውቀት የሚጨምር÷ አስተሳሰብ የሚያንጽ÷ አመለካከት የሚያስተካክል ስጦታ ነው፡፡ ከውስጣችን የሚመነጨው ኃይል የመስጠት÷ የማካፈል÷ የማጋራት ኃይል መሆኑን ለማወቅ ከራሳችን ጋር የአርምሞ ጊዜ ወስደን መመርመር ይገባናል፡፡ ሰይጣን አሳሳተኝ በሚል ስንፍና የራስን ,ድብቅ ፍላጎት በሌላ ማመካኘት፣ የቀኝ አውለኝ ጸሎት የህይወት መመርያ አይሆንም፡፡
ክፋትን እየፈጸምን ቤተሰብ ስንበትን÷ አመጻን እየዘራን ጎረቤት ስናጣላ÷ ተንኮልን እያስተማርን ማህበረሰቡን በጥርጣሬ እየሞላን÷ ሴራ እየደወርን በጠልፎ መጣል ስሌት ሀገርን እያናጋን አንድም ለህዝብ አንድም ለገዛ ራሳችን ሰላም እያጣን፣ ለይምሰል ብቻ ቀን አውለኝ ማለት ፋይዳ አይኖረውም፡፡ እሳት እንዲሚያቃጥለን ለማወቅ የግድ ጣታችንን እሳት መሐል እንደማንጨምር፣ ውኃ ዋና ሳንችል በውቅያኖሱ ውበት ተመስጠን ዘልለን ውኃ ውስጥ እንደማንገባ ሁሉ ወደ ጥፋት እልቂት ፍጅትና ትርምስም ከመግባታችን በፊት መንገድ እንደሚያቋርጥ እግረኛ ቆም ብለን ግራና ቀኛችንን ማየት ብልህነት ይሆናል፡፡ አለበለዚያ ነገር ዓለሙ ሁሉ በቀኝ አውለኝ ብሎ በግራ እንደመዋል ይሆንብናል፡፡ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ!
ቀኝ መዋል ለራስ ህልውና ብቻ ማሰብ ሳይሆን ለሌሎችም በጎነትን በገዛ ተነሳሽነት ማድረግን ያካትታል፡፡ የራስን ዓለም ብቻ ፈጥሮ ምቾትና ድሎትን ማግበስበስ ስግብግብነት ነው፡፡ የእኛ ደስታ ሙሉ የሚሆነው ከሌሎች ጋር ባለው ቀና መስተጋብር ነው፡፡ በጎነትን ስንሰጥ ከኛ የሚቀነስ ነገር የለም፡፡ ለሌሎች ግን ሌላ የህይወት ገጽ ሊከፍት ወይም የእድገት መሰላል ሊሆን ይችላል፡፡
ከማህበረሰብ አንጻር ካየነውም ህዝባችን የመልካምነት ቋሚ ደጋፊ ቢሆንም ቅሉ ዘመናዊነት በሚባል ህመም አጥንቱ እየተበላ ወደ ግላዊነት በማዘንበሉ፣ እኛ ከሚለው የወል ጥቅም ይልቅ እኔ ወደሚለው ጠባብነት ማዘቅዘቁ፣ ቀኝ አውለኝ ብለው የተነሱትን በግራ እያዋለ ተቃርኗችንን አግዝፎታል፤ በዚህም የደግ ሳምራዊዎችን ቁጥር አሳንሶብናል፡፡ የእጅ በእጅ ጨዋታውም “ያለው ከሌለው ጋር” ሳይሆን “ያለው ካለው ጋር” ወደሚል ገፊ እሳቤ በማዝመሙና የመደብ ልዩነት እየተፈጠረ በመሄዱ ምክንያት “ከሌለህ የለህም” የሚለውን የጋሽ ጥላሁን ገሰሰን ዘፈን ደጋግመን እንድንሰማ አስገድዶናል፡፡ ቀኝ አውለኝ ብለን በግራ እየዋልን በመቸገራችንም የአብሮነት ትዝታችን በሸክላ እንደተቀረጸ የድሮ ዘፈን በፍለጋ የሚገኝ ትዝታ እየሆነብን ይገኛል፡፡
ከሀገራችን አንጻር ካየነውም ያለንበትን መራር እውነት ለመዋጥ ተቸግረን ለቀባሪው አረዱት እንደሚባለው ካልሆነብን በስተቀር ሊደርስ የመጣውን ልቅሶ ድንኳኑ ጋር ሲደርስ አልሰማሁም እኮ እያለ እንደሚያለቅስ ልቅሶ ደራሽ ውጥንቅጦሻችንን አላየሁም አልሰማሁም የሚል ዜጋ አለ ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ እየኖርነው ያለነውን ኑሮ እንኳን እኛ ቀርተን የዓለም ህዝብና መንግስት በራስጌ የዜና ንግርቱ ላይ እያስቀደመ መክረሙን መካድ አይቻልም፡፡ ዜናዎቹም ከአርእስቱ አንስቶ ጦርነት ነው፡፡ ጦርነት ውስጥ ደግሞ የዓባይ ፏፏቴ የውኃ ፍንጣቂ ሳይሆን የጥይት አረር ይንተከተክበታል፡፡ ውጊያ ውስጥ ጥቅጥቅ ካለ ጫካ ውስጥ የሚሰማ የወፎች ዝማሬ ሳይሆን የሟቾች እሪታ ይደመጥበታል። ወታደሮች እንደ ወጡ የማይመለሱበት ብሎም አካለ ጎደሎ የሚሆኑበት፤ ንጹህ ዜጋ ከቀዬው የሚፈናቀልበት፤ ሴቶች በጅምላ የሚደፈሩበት አቅመ ደካሞች ሌላ አቅም የሚያጡበት፤ ስደት ወርቃማ ምርጫ የሚሆንበት፤ መፈናቀል የማያስገርምበት፤ ንብረት እንደ ቅዳሴ ጧፍ የሚነድበት፤ ቅርሶች የአመድ ክምር የሚሆኑበት ወቅት ነው፡፡ ያለፍንበትን ጦርነት እንደ ጣፍጭ የፍቅር ፊልም ይደገም እያሉ ሊመለከቱ የሚችሉት ጥይት ሻጮቹ ብቻ ናቸው። እንደ ሀገር በቀኝ ለመዋል ብዙ እቅድ አቅደን፤ በጀት መድበን፤ ቁሳቁስ ገዝተን፤ የሰው ኃይል አሰማርተን ብንነሳም ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ በግራ ውለናል፡፡
ቀኝ አውለኝ ስንል የሀገርን ህመም መረዳት፤ ቁስልዋን መቁሰልና ስብራቷን መጠገን መቻል ነው፡፡ በፈረሰች ከተማ ላይ ሠርግ የሚደግስ እንደሌለ ሁሉ በተጎሳቆለች ሀገር ላይ ምንም መስራት ስለማይቻል፣ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ለሰላም መፍትሄ የስብሰባ አዳራሽን መምረጥ የሆደሰፊነት ምልክት ነው፡፡
ቀኝ አውለኝነት ለኔ ብጤ ለመመጽወት ሃይማኖትን አይጠይቅም፤ ጎዳና ላይ የወደቀውን ለማንሳት ብሔሩን አያጣራም፤ ማህበረሰቡን ለማስተማር የሀገሬ ልጅ በማለት ወንዝና ተራራን  አይቆጥርም፡፡ ሀገሩን ለማበልጸግ መንግስት የሚሰጠውን የማበረታቻ ድጋፎችን ሲያጠና እድሜውን አይፈጅም፡፡ ደግ ቀን ሲመጣ መናፈሻዎችን ሲያጣብብ፣ ክፉ ቀን ሲመጣ የቅድሚያ ትኬት ለመቁረጥ አውሮፕላን ጣቢያን አያጨናንቅም፡፡ ወገኑን ይታደጋል፤ ያጽናናል፤ ያክማል፤ ያጎርሳል፤ ያለብሳል፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን በቀኝ አውለኝ ብሎ በግራ እንደመዋል ነው፡፡
ቀኝ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የበጎነትና የህብረት ነጸብራቅ ነው፡፡ በቀኝ ለመዋል የግድ ሃይማኖተኛ መሆን ሳይሆን ሰው ሆኖ መገኘት ብቻ ይጠይቃል። ከሰውነት የሚገኘው በረከት ደግሞ በጭቃነት የሚገለጥ ፈራሽነት ሳይሆን በመንፈስ ከፍታ የሚገለጥ የንጽህና፣ የቅድስና፣ የልዕልና፣ የአስተማሪነት፣ የአርያአነት፣ የለጋስነት፣ የጠባቂነትና ለበጎች እራስን ሰጥቶ ታማኝ እረኝነትን የማስከበር ጥግ ነው፡፡ ቀኝ ቢመታ ያደቃል፤ ቢይዝ ይጨፈልቃል፤ ቢወረውር ያርቃል፤ ቀኝ ሀሳብም እንዲሁ ቢናገር ያጽናናል፤ ቢገስጽ ይመልሳል፤ ቢያስተምር ያበረታል፤ ቢመራ ያሸንፋል፡፡ በግራ አስተሳሰብ ላይ ቆሞ በቀኝ ምኞት መመሰጥ ግን ለግልም ለህዝብም ለሀገርም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡
የህዝብን መከራና ስቃይ እንደ ባዳ ሆነው እያዩ “ሀገሬ ናፈቀችኝ” በሚል ለስላሳ ዜማ ናይት ክለብ ውስጥ ተቃቅፎ በእንባ መራጨት የቀኝ አውለኝ ሰዎች መገለጫ አይደለም፡፡ ሀገር ላይ የሚደርሰውን መከራ በሰበር ዜና ሰምቶ በማህበራዊ ሚዲያ ሼር በማድረግ፣ የዩቲዩብ ገቢ መሰብሰቢያ ለማድረግ መጣደፍም የዜግነት ተቆርቋሪነትን አያሳይም፡፡
“ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፡ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም’’ እንደተባለው የገጣሚው ምክረ ሃሳብ፤ ቀኝ አውለኝነት በየትኛውም ልኬት ከራስ ደስታ በላይ ለሌሎች ደስታ ቅድሚያ የሚሰጥ እውነት ነው፡፡ ሰጪ የሚሰጠው ከተሰጠው ላይ ቆርሶ እንጂ ያለውን አሟጦ አይደለም። የሰጠ ደግሞ ስለ በጎነቱ ብድራት በሌላ ጊዜ ከሌላ አካል ይቀበላል፡፡ መካፈል ውስጥ መብዛት እንጂ ማነስ የለም፤ መተጋገዝ ውስጥ መጽናት እንጂ ውድቀት አይታሰብም፤ መመካከር ውስጥ የመውጫ መንገድ እንጂ መጠላለፍ አይኖርም፡፡
ለተራበ አብልቶ ለተጠማ አጠጥቶ፣ ለተራቆተ አልብሶ የወደቀ አንስቶ የሞተ ቀብሮ፣ ጤናማ እሳቤውን ወንዝ ዳር እንደተተከለች ተክል በህዝብ ልብ ላይ አብቅሎ መገኘት የቀኝ አውለኝ ጸሎት ሌላኛው ትሩፋት ነው፡፡ ግለሰቦች በቀኝ ሲውሉ ማህበረሰቡ ተረጋግቶ ይኖራል፤ ማህበረሰብ በቀኝ ሲውል ሀገር ሰላም ታገኛለች፤ ሀገር በሰላም ስትኖር መንግስት ከቀልቡ ሆኖ ሕዝብን ይመራል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚመጣው ተጎታች ፉርጎ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ልማትና ብልጽግና ይሆናል! እናም ለራሳችን ለህዝባችንና ለሀገራችን በቀኝ እንዋል! ሻሎም!Read 2384 times