Tuesday, 25 January 2022 07:52

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ዝም የምንልበት ዘመን ይሁን ..
                          ዘውድአለም ታደሠ


            አንዱ አጠገቤ ተቀምጦ ብቻውን እያወራ ነው። ምኑም እብድ አይመስልም’ኮ። «አንተ ውጣ ከዚህ። አይነስብህን ነው ማጠፋው!» ምናምን እያለ ይበሳጫል። ይሄን እንደ ታምሩ ብርሃኑ ቃጥላ ማሪያም ነው መውሰድ እያልኩኝ ሳስብ፣ ከፊት ለፊቱ የተቀመጠ ስልክ አየሁ። ለካ አክቲቪስት ነው። በዩቲዩብ ላይቭ ገብቶ ነው ከማያውቃቸው ሰዎች ጋር እሚጣላው።
ዘንድሮ መቼስ እግዜር በዩቲዩበርና በአክቲቪስት ባርኮናል። ወጣቱ በሙሉ ካሜራ ይዞ እየዞረ ፕራንክ ያደርጋል። ያው የኛ ሐገር ፕራንክ የተመታ ነው። ህዝቤም ከጃንሆይ ጀምሮ መንግስት በየቀኑ ፕራንክ ሲያደርገው ስለኖረ ፕራንክ ብሎ ነገር ስልችት ብሎታል። ባለፈው አንድ ዩቲዩበር አባቱን በስተርጅና ፕራንክ አድርጎ አስደንግጧቸው፣ በማግስቱ የመግደል ሙከራ ነው ብለው ፍርድ ቤት በመሄድ ከውርስ ነቀሉት አሉ፡፡
ቲክቶካውያንማ ሌላ አለም ውስጥ ገብተዋል። ቅንጡ ኑሮ ትጠላለህ። አንዳንዶቹ እዚህ ቁጭ ብለው ካናዳ ነው የሚኖሩት። ፖለቲካ ሃይማኖት ምናምን የሚያውቁልህ ነገር የለም። አንዳንዶቹ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከስልጣን መውረዱንም አልሰሙም።
በነገራችን ላይ ቲክቶክ ደሃ ላይ ያስጠላል። ፕላትፎርሙ ራሱ የተዘጋጀው ለሞጃ ልጆች ነው። አሁን አሁን ግን ጠዋት ጠዋት እንደ ምስጥ ከፈራረሰ አፈር ውስጥ የሚወጡ አመድማ ልጆች፣ ቲክቶክ እየሰሩ ያስደብሩን ይዘዋል። ማይ ብራዘር እንደኔ ችስታ ከሆንክ፣ ቲክቶክ ላይ ከሃብታም ልጆች ጋር እየተጋፋህ ራስህን በሞራል አትጉዳ። ወደ እናት አለም ፌስቡክ መጥተህ አማርር። አለቃቅስ። መንግስትን ውቀስ። በሃይማኖት ተጣላ። ብዙ ቲክቶከሮች፣ ቲክቶክ የሚያግዳችሁ ምንም ማለባበስ አያስፈልግም፤ የደሃ ወሬ ስለምታወሩ ነው። ቀልዳችሁ ራሱ የደሃ ነው። አባዬ አንዳንድ ቲክቶከሮች ቤትኮ የሐገር ቅርስ ሁሉ አይተናል። አሁን ሞአ አንበሳ ትሪና የንኬሉ ኩባያ ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ራሱ ይኖራል? እንደው ከእነ በላይነህ ክንዴና ወርቁ አይተነው ልጆች ጋር እየተጋፋህ፣ ቪዲዮ ሰርተህ መንግስት ቢያስርህ ራሱ ይፈረድበታል?
ለማንኛውም እንኳን አደረሰን። አሁን አሁን በአል በመጣ ቁጥር ሃይማኖቶች በመሬት ሲጣሉ ማየት የተለመደ ሆኗል። በሚያስገርም ሁኔታ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ጎዳና ላይ የሚኖር ህዝብ አለ። የከተማዋን መሬት በብዛት አጥረው የያዙት ግን የሃይማኖት ድርጅቶች ናቸው። ያም ሆኖ እንደ ነገረኛ ጎረቤት አጥሬን ገፋህ እየተባባሉ የሚጣሉት እነሱው ናቸው። ህዝቡን ያስታርቃሉ ተብለው ተስፋ የሚደረጉ ሃይማኖቶች፣ ራሳቸው መታረቅ አቅቷቸው ጉዳያቸው ፍርድ ቤት እየታየ ነው።
አሁን ከዚህ ፅሁፍ ስር እንኳ ሃይማኖቱን ወክሎ በኮመንት የሚሳደበውን ሰው ማየት በቂ ነው። መጭው ዘመን ሃይማኖተኞች፣ ከብሔርተኞች ብሰው ብሔርተኞቹ ጋር ለግልግል የሚሄዱ ይመስለኛል። አውርተን አልሆነልንም። መጭው ዘመን ዝም የምንልበት ይሁንልን።

_____________________________________


                       ዳያስፖራ ሆይ አትቅበጥ!
                            ዘውድአለም ታደሠ

                 ሰሞኑን የሆኑ ነጭ ቱታ ምናምን የለበሱ ዳያስፖራዎች በተደጋጋሚ እየተሰበሰቡ «መንግስት እንዴት ሳያማክረን እስረኛ ፈታ» አይነት ብሶት እያወሩ ሲነጫነጩ አየሁ። አንዳንዶቹማ ትንሽ ፓራስታሞልና  የቁስል ፕላስተር ለመከላከያ ስላዋጡ እሹሩሩ በሉን ማለት ነው የቀራቸው። ማኛዬ፤ ነጮቹ እነ ካርል ሃይስ በም እንኳ ያን ሁሉ ትምህርት ቤት ሰርተው፣ ያን ሁሉ የውሃ ጉድጓድ አስቆፍረው special እንክብካቤ አልፈለጉም።
እነ ዶክተር ሃምሊን እንኳ 50 አመት ሙሉ አፈር እስኪቀምሱ ድረስ የተቀናጣ ኑሯቸውን ትተው እልፍ አእላፍ ምስኪን ሴቶችን ከፌስቱላ አክመው ከስቃይ ሲገላግሉ ኖረው ለአንዲት ቀን እንኳ እንዲህ አልተቀናጡብንም። ቆይ በምን አግባብና ስሌት ነው ሐገር ውስጥ ከሚኖረው ዜጋ በተለየ መንግስት ውሳኔ ሲወስን እናንተን የሚያማክራችሁ? አንተዋወቅም እንዴ አለቃዬ? ሐገር እንዲህ በዶላር ጠኔ እየተሰቃየች ከመቶ ዶላር አቅም በባንክ መላክ ሰስተህ በብላክ ማርኬት እየላክ፣ ጥቁር ገበያውን ስታደራው የኖርከው አንተ አይደለህ እንዴ? ምን ይላል ይሄ?!
ጎበዝ፤ አናታችን ላይ በመቶ ሰማኒያ ነዳህ እኮ! በገብርኤል ይዘንሃል ፍሬን ያዝ! ... እንኳን ነገር ሲረጋጋ ቤተሰብህን ልታይ የመጣኸው አንተ ይቅርና፣ ወያኔ ሸዋሮቢት ደረሰች ሲሉት ማቄን ጨርቄን ሳይል የመጣው ምንጊዜም የማከብረው ታማኝ በየነ እንኳ እንዳንተ እዘሉኝ አላለም! መምጣትህ ደስ ይላል። ሐገርህ መምጣትህን እንደ ውለታ ከቆጠርከው ግን በማርሽ ባንድ አጅበን ወደመጣህበት ልንሸኝህ ዝግጁ ነን!

_________________________________________

                            ክብና ሞላላ ጠረጴዛ
                               ጌታሁን ሔራሞ

                 እ.ኤ.አ. ከ1969-2004 የፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት (PLO) መሪ የነበረው ዕውቁ ያሲር አረፋት በሙያው ሲቪል ኢንጂኒየር ነበር። በአንድ ወቅት አሜሪካ እስራኤልንና ፍልስጤምን ለማደራደር የሶስቱም ሀገራት ተወካዮች ወደ ውይይቱ ክፍል ከገቡ በኋላ ክርክሩ የተጀመረው በጠረጴዛው ቅርፅ ላይ ነበር። ነገሩ እንደዚህ ነው፦ ያሲር አረፋት ወደ ክፍሉ እንደገባ ዓይኖቹ ያረፉት በጠረጴዛው ቅርፅ ላይ ነበር፤ ሞላላ (Oval) ነበር። በዚሁ ሞላላ ጠረጴዛ ሁለቱ ጫፍ ላይ የተሰየሙት የአሜሪካና የእስራኤል ዋና ተወካዮች ናቸው፤ የፍልስጤም ተወካዮች ያሲር አረፋትን ጨምሮ በጎን ወዳሉት መቀመጫዎች ተገፍትረዋል። ከጠረጴዛው ሞላላ ቅርፅ የተነሳ የውይይቱ ኢነርጂና የበላይነት ወደ ሁለቱም ሞላላ ጫፎች እንደሚያመዝን (Hierarchical vibe of the negotiation) የገባው ሲቪል ኢንጂነሩ ያሲር አረፋት፤ ሞላላው ጠረጴዛ በክብ ጠረጴዛ ካልተቀየረ በቀር ውይይቱን መጀመር የማይታሰብ መሆኑን ለአሜሪካ አሳወቀ። ምክንያቱም በክብ ጠረጴዛ ሁሉም ተደራዳሪዎች ከመኸሉ እኩል ርቀት ስለሚኖራቸው ማንም ገዥ ቦታውን መቆጣጠር አይችልም። እናም የያሲር አረፋት ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ሞላላ ጠረጴዛው በክብ ተቀየረ፤ ውይይቱም ቀጠለ። ታዲያ ሞላላ ጠረጴዛ የሚያስፈልግበት የውይይት ዓይነት የለም እያልኩ እንዳልሆነ አስምሩልኝ። ለምሣሌ ስብሰባው የሥልጠና (Training) ከሆነ ሞላላው ጠረጴዛ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል።
ብዙውን ጊዜ ትኩረት የምንሰጠው ንቁ (Conscious) ለሆንንባቸው ጫናዎች ብቻ ነው፤ በአንጎላችን ከፊል ንቁ (Subconscious) እና ኢ-ንቁ (Unconscious) ደረጃ የሚደርሱብንን ጫናዎች ለይቶ መከላከል ግን ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው፤ ያለ እኛ ይፋዊ ዕውቅናና ፈቃድ አካባቢያችን በአንጎላችን ላይ አልፎ ተርፎም በባሕሪያችንና በስሜታችን ላይ የሚያስከትለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ልክ እንደ ያሲር አረፋት አነፍንፈን “discover” የምናደርግ ስንቶቻችን እንሆን? That is why I am in love with Environmental & Architectural Psychology disciplines! Both disciplines help us to bring the unconscious/subconscious world to the conscious realm for our proper preemptive response!

_________________________________________


                       ስንኞች
                           በእውቀቱ ስዩም

በብዙ ጭንቅና በብዙ መከራ
አቁሜ ሲጃራ
እጠነቀቅ ብየ፤ ለሳምባ ለልቤ
በትምባሆ ምትክ ፤ንፉግ አየር ስቤ
ከሱስ ጸዳሁ ልበል?
መኖርን የሚያክል ሱስ ተከናንቤ
* * *
ከገነት ጋር ጠፍቶ ፤የጤና ትርጉሙ
የተሻለው ሕመም፤ ጤንነት ነው ስሙ፡፡
(ከ’ስብስብ ግጥሞች)

___________________________________________

                      በየት በኩል!
                         በእውቀቱ ስዩም


             በነገራችን ላይ ዩቲዩብ  ውስጥ ለተከታታይ ሁለት ሰአት ያክል ከተርመሰመስሁ፣ ዩቲዩብ ራሱ የኔ ነገር ያሳስበዋል፡፡ ዛሬ በውቄን ደብሮታል ወይም ቦዘኔ ነው ብሎ ስለሚያስብ  "ይቺን ነገር ብታያት" እያለ ይለቅብኛል፡፡ በቀደም አልጋዬ ላይ ለአራት ሰአት መገላበጤን ሰልሎ ሲያበቃ የሆነ የአማርኛ ሞቲቬሽን ንግግር ሪኮመንድ አደረገኝ:: ኪሊክ አደረግሁ! አንዱ ሱፉን ግጥም አድርጎ፣ ተከርክሞ ጸጉሩን" "የሚከተሉትን ሀያ ስድስት ነገሮች ቢያደርጉ ህይወትዎ ይለወጣል፤" ብሎ ጀመረ፤ እኔ፥ “ሀያ ስድስት አልበዛም ጋሼ? ትንሽ ቀንስልኝ! ደንበኛ እንሆናለን” እያልኩ መገላበጤን ቀጠልኩ፤ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ ከሰውየው ንግግር አዕምሮዬ  ላይ የቀረው “ላይክ፤ ሼር፤ ሰብስከራይብ አድርጉ” የሚለው ተማጽኖ ብቻ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሰባኪዎችና አነቃቂ ንግግር አቅራቢዎች ድምጻቸውን በወርድ በቁመቱ ለጥጥው የሚናገሩበት ምክንያት አይገባኝም፥ አንዳንዴማ ማይኩ ራሱ "አቦ አትጩህብኛ" ብሎ ጆሮውን ይይዛል! ጥበቡ ይገለጥልህ እንጂ በሹክሹክታም መምከር ይቻላልኮ ጀለስ! አንድ ባልንጀራ አለኝ፤ በሙያው ኤሌክትሪሽያን ነበር፤ ከፈረንጅ መካሪዎች የተውጣጣ ምክር ተርጉሞ “ስኬት” የሚል መጽሐፍ ጽፎ ይሸቅላል፤ ከሶኬት ወደ ስኬት የተሻጋገረበት ጥበብ ሲገርመኝ ይኖራል፤ እና እንደ ቡና ሱስ ሆኖበታል፡፡ አንድ ቀን በእግረኛ መንገድ ስወዛወዝ፣ ከሚፈጥን አውቶብስ ወርዶ፤ አባርሮ ደረሰብኝ፥
“የደበረህ ትመስላለህ”
“የደበረኝ እንደሆን ምን ልታደርግ ነው?”
“አንድ ሁለት አነቃቂ ጥቅስ ልልቀቅብህ”
“የንቃት ችግር የለብኝም! የሚያስተኛ ጥቅስ ካለህ ወዲህ በል”
ገና ባፍላነቴ የself-help መጽሐፍ እጨመጭም ነበር፤ ኬኔዲ ላይብረሪ ገብቼ አንድ ምእራፍ እንደጨረስኩ በቃ የህይወትን ምስጢር መፍቻ ቁልፍ የጨበጥሁ ይመስለኛል፤ እንዲያውም ቁልፉን አስቀርጬ ለወዳጆቼ ለመበትን ሁሉ ያምረኛል ግን ምን ዋጋ አለው! ከቤተመጽሐፍ ወጥቼ ገና ከግቢው በር ላይ አንድ ወያላ በኮሌታዬ እየጎተተ ባልጠራሁት ሚኒባስ ውስጥ ሲዶለኝ፣ ያ ሁሉ ያነበብኩት የፈረንጅ ምክር ፍርክስክሱ ይወጣል፤ እና ትዝ እሚለኝ የወንድሜ የሞሴ ገጠመኝ ነው።
ወንድሜ ሞሴ ገና በጣም ብላቴና እያለ የሻረግ እምትባል የጎረቤት ልጅ ጋራ ይጋጫል ፤ የሻረግ ሞሴን ቢያንስ በሶስት አመት ትበልጠዋለች፤ እና አብረው ትንሽ ሲጫወቱ ይቆዩና ድንገት ትተነኩሰዋለች፤ በዛሬ አነጋገር ቡሊ ታረገዋለች፤ ትግስቱ ሲያልቅ ግብግብ ይገጥማታል፤ የሻረግ ከቦኖ በጀሪካን ውሃ ማመላለስ፤ የዳበረ ክንድ አላት፤ የሞሴ ሁለት እግር ተከክቶ ቢደለዝ የሻረግን ክንድ አያክልም፤ ግብግቡ ሲጀመር የሞሴን ማጅራት አፈፍ አድርጋ እንደ ሰጋጅ ካስጎነበሰችው በሁዋላ በክርን ትሰልቀዋለች፤ ደሞ ክንዷ ሲነሳ ለመፈክር እንጂ ለክርን አይመስልም!
አንድ ቀን በታላቅ ወንድምነት መከርኩት፥
“ከፊትለፊት ስትመጣብህ ወደ ሁዋላ አራት ርምጃ ተንደርደር፤ ከዚያ እግሯን አፈፍ አድርገህ ገርስሰህ ጣላት፤ ከመጣልህ በፊት ግን በምትወድቅበት አቅጣጫ ድንጋይ አለመኖሩን አረጋግጥ፤ በእጅህ ብትጠፋ እዳው የቤተሰብ ነው”
ይህን ከመከርኩት ከሁለት ሰአት በሁዋላ የሺሀረግ ወጣች፤ መጀመርያ ለጨዋታ ከዚያ ለጠብ ጋበዘችው፤ እኔም የአጥራችን በር ላይ ቆሜ፥ ሰነፍ ቆሎ እየበላሁ ሁኔታውን መከታተል ጀመርኩ፤ ገና ግብግቡ እንደተጀመረ፤ የሺ የሞሴን ቁንጮ ጨምድዳ ያዘችና ጭንቅላቱን እንደ ነሀስ ቃጭል ነቀነቀችው፤ እንኳን እሱ እኔም ተመልካቹ ዞረብኝ፤ በመጨረሻ ሞሴ፥ በውጭ ነፍስና ግቢ ነፍስ መሀል ሆኖ እንዲህ ሲል ሰማሁት፥
“በውቄ! እግሯ በየት በኩል ነው?”

___________________________________________

                    ሦስት ዓይነት አማራነት
                           እዮብ ምህረትአብ ዮሐንስ


         [በግርድፉ ከከፈልነው ሶስት አይነት አማራ አለ]
(1)
ሸገር ላይ የሚኖር/የተወለደ፣ አክሰንቱም የአማራነት ስሜትም የሌለው፣ የናትና አባቴ አገር ማርቆስ ነው- ቡልጋ ነው ምናምን የሚልህ፣ ወይንም በናቴ እንትን ነኝ በአባቴ አማራ የሚልህ። ወይንም ከሌላ ዘር አግብቶ ድብልቅ ልጆች የወለደ። ትምህርት ቀመስ። ካልሆነም ኑሮውን ያቸነፈ። አማራነት የዘመዶቹ አገር የሆነበት። ዘመዶቹ ስለሆኑ የሚወዳቸው። በአማራነቱ አያፍር አይኮራ። ግን አማራነቱ ትዝ የማይለው። ከብሄሩ አዲስ አበቤነት የሚቀድመው። ራሱን ኢትዮጵያ በተሰኘው በትልቁ ማእቀፍ (The Bigger Picture) ውስጥ አኑሮ Defined መሆን የሚመርጥ። አምሃራይዝድ የሆኑ ከተሜዎች Livelihoodዳቸው ላይ ያዋሃዱት፣ አማራው የሰጠን ቋንቋ፣ ባህል፣ ትውፊት፣ ታሪክ፣ የአገር ፍቅር ስሜት፣ የኢትዮጵያዊነት Narration የሚመቸው። የሚያኮራው።
(2)
አማራ ክልል የሚኖር አማራ። ጎንደሬነቱ ወሎዬነቱ የሚቀድምበት። Thick Accent ያለው። አክሰንቱን ለማጥፋትና፣ እንደ ሸገር ሰው ለማውራት የሚታገል። ሄለን እንደ ጫልቱን በፍትፍቴ እንደ ፌቪ ፖስቴ የሠራ። ወይንም የገጠር አርሷደር። በአዝማሪ የአርበኛ ግጥምና ‘አንተ እኮ ኩሩ ጎንደሬ ነህ፣ የጠራህ ቡልጋ ነህ’ አይነት የዳበሩ ግየዳዎች (Established Myths) እና እንደ ቅመም ቆንጠር በተደረጉ ጢኒጥዬ የታሪክ ማስረጃዎች ቀና ብሎ፣ የበታችነት ሳይሰማው፣ ከሰው በላይ ነኝ ብሎ አምኖ የሚኖር።
 የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን መልአክቶች ናቸው የገነቧቸው ብሎ ገግሞ የሚያምን። በኑሮ ቺስታ፣ በስልጣኔ ባላገር፣ በአስተሳሰብ አድማስ Narrow። (Made in ብአዴን በለው)
(3)
የአማራ ብሄርተኛ። በቀደም አማራ የሆነ፣ አዲስ በጥባጭ። ‘’አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ’’ Type። ‘ . . . በረራ የኛ ነች፣ ቀይ ባህር የኛ ነው። አዳም ጎጃሜ ነው። የኖህ መርከብ ጣና ላይ አርፋ ነበረ’ ብሎ የሚያምን። የስሙኒ መገፋትን የሰባት ሺህ ብር አድርጎ የሚያጋንን። Conspiracyን ከምቀኝነትና ከደብተራ ባህል ጋራ አዋህዶ የተላበሰ። ሁሌ ሴራ እየተጎነጎነብን ነው ብሎ ፓራኖያ የሚጠበጥበው። እንደ ማንኛውም ፌዴራሊስት ብሄርተኛ፣ ስቅስቅቅቅ ብሎ በማልቀስ ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከአለም ሶስተኛ የሚወጣ። ከራሱ ብሄርተኛ አማራ ጋራ እርስ በራስ የሚጠላለፍ፣ የሚመታታ፣ የሚጣጣል። መሠሪነት፣ ሸረኛነት Brand መገለጫው የሆነ። በአመት ሰባ ጊዜ Black Profile Picture የሚለጥፍ። ፌስቡክ ላይ በፍጥነት Unfriend የምታደርገው።Read 1108 times