Tuesday, 25 January 2022 08:00

የዛሬ 57 ዓመት ለፊልም ሥራ ገንዘብ ያበደረው ባንክ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ባለፈው ሳምንት “ሂሩት አባቷ ማነው?” የተሰኘው የዛሬ 57 ዓመት የተሰራ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፊልም በሸራተን አዲስ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርቋል፡፡
 በጣም የገረመኝ ታዲያ በጭብጡም ሆነ በፊልም አሰራር ቴክኒኩ ከፍተኛ ልህቀትና ርቀት  የተነሳ፣ ፊልሙን በዚህ ዘመን በድጋሚ መስራት አለመቻሉ በባለሙያ መገለፁ ነው። በአንድ በኩል የወቅቱን የጥበብ ባለሙያዎች ልዩ አቅምና ብቃት ብናደንቅም፤ ከ57 ዓመት በኋላ ያንኑ መሥራት ወይም መድገም አለመቻል ግን ከፍተኛ ውድቀትና ድቀት ነው። እንዴት ወደፊት  መራመድ ባይሆንልን እንኳን ኋላ መመለስ አቃተን?!
ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ ምን መሰላችሁ? የዛሬ 57 ዓመት ፊልሙ የተሰራው ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተገኘ የ40ሺ ብር ብድር  መሆኑ ነው። በዚያን ዘመን ባንኩ ለፊልም ስክሪፕት  ገንዘብ ማበደሩ በእጅጉ የሚደንቅ ነው። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የዛሬ 57 ዓመት ፣ ምን ታይቶት ይሆን ለፊልም ሥራ ገንዘብ ያበደረው?
በነገራችን ላይ ገንዘቡን የተበደረው የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን፣ ብድሩን በወቅቱ መክፈል ባለመቻሉ፣ ከ40 ዓመት በላይ ፊልሙ  በልማት ባንክ ይዞታ  ስር መቆየቱ ታውቋል። በመጨረሻ ግን ባንኩ፣ የአገር ሃብትና ቅርስ ነው በሚል፣ ፊልሙን ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስረክቧል-ብድሩን ሙሉ በሙሉ በመሰረዝ።
በ40ሺ ብር የተሰራው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊው ፊልም “ሂሩት አባቷ ማነው”፤ ወደ 350 ሺ ብር ገደማ ወጥቶበት ዲጂታላይዝድ መደረጉም ተገልጿል። ይህም ፊልሙ  ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ለትውልድ እንዲተላለፍ ያስችላል ተብሏል፡፡
ዛሬ በአንጻሩ ከ30 የማያንሱ ትርፋማ የግል ባንኮች ቢኖሩንም፣ ለሃሳብና ለእውቀት ወይም ለጥበብ ስራ ዋጋ ሰጥቶ ገንዘብ የሚያበድር አንድም ባንክ እንኳን አለመኖሩ፣ ያሳዝናል፡፡ ምነው ጉዞአችን እንዲህ ቁልቁል ሆነ ያሰኛልም፡፡ አሁንም ቢሆን የአስተሳሰብና አመለካከት ለውጥ ማምጣት ከመንግስት ፖሊሲ አውጭዎች፣ ከባንክ ባለሙያዎችና አመራሮች በእጅጉ ይጠበቃል።
እስከዚያው ግን የዛሬ 57 ዓመት  “ሂሩት አባቷ ማነው” ለተሰኘው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፊልም መስሪያ የ40 ሺ ብር ብድር የሰጠውንና ፈር ቀዳጁን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደጋግመን ልናመሰግነውና ዕውቅና ልንቸረው ይገባናል- ለተራማጅ አስተሳሰቡና አሰራሩ፡፡ የዘመናችን ባንኮችንም እንደሚያነቃቃ ተስፋ እናደርጋለን!!
ጆሲ ከአምባሳደር


Read 1286 times