Tuesday, 25 January 2022 08:01

ቁጥሩ ሳይሆን ከቁጥሩ ጀርባ ያለው ስዕል

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 "--ከነገሩ ሁሉ በካሜሩኑ ጨዋታ ምነው ግማሽ መንገድ ላይ ደከሙ? ምነው በመጀመሪያው ግማሽ ያሳዩትን የጨዋታ እንቅስቃሴ በሁለተኛው መድገም አቃታቸው? ምነው ‘ፋይቲንግ ስፒሪት’ የሚሉት ነገር አነሳቸው? ምነው እልህ የሚባለው ነገር ሌሎቹ ቡድኖች ላይ የምናየውን ያህል ልናይ አልቻልንም? አይነት ጥያቄዎች መጠየቅ ይቻላል፡፡--"
           
           እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ስማ፣ ምን ሆነሀል? ፊትህን በመስታወት አይተኸዋል? ዘፍዝፈው ያሳደሩት ነው እኮ የሚመስለው!”
“ምን እባክሀ፣ እንደልማዳቸው አይሸነፉ መሰለህ!”
“እነማን?”
“ይሄ ደግሞ... እነማን እንድልህ ነው! እነቼልሲ! ብሄራዊ ቡድናችን አራት ለአንድ ተሸነፈ አይደል እንዴ!”
“የት ተጫውቶ?”
“ለአፍሪካ ዋንጫ ከካሜሩን ጋር ተጫውቶ አራት አያቅሙን መሰለህ!”
“ብሄራዊ ቡድናችን ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈ እንዳትለኝ!”
መቼም ጨጓራችንን የምንልጥበት ምክንያት አናጣም አይደል...ብዙ ሰው እኮ እዛ መድረሳችንን እንኳን በማያውቀው ወይም በጣም ዘግይቶ በሰማው ውድድር ሳይሳካልን ቀርቶ በጠፋ አሞክስሊን ጨጓራችን ሲበግን ሰነበተላችሁ...ከአንድ ሺህ የመብገኛ ምክንያቶች አንድ ሺህ አንደኛው ማለት ነው!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... በዚህ የቡድናችን የአራት ለአንድ ውጤት ብዙዎቻችን ተበሳጨንሳ! እኔ የምለው...እንደው ገብስ ገብሷን እናውራና ምን አይነት ውጤት ነው የጠበቅነው! ደግሞስ ካሜሩንን ከሚያህል ቡድን፣ ከችሎታ ባለፈ በአካል ግንዲላ፣ ግንዲላ ከሚያካክሉ ጋር ተጫውተን! (እኔ የምለው፣ ኸረ ‘ፊዚካል’ የሚባለው ነገር ይታሰብበት። አሀ...ቀጫጭኖቹ ምናምን ለዚህ ዘመን ኳስ አይሆንማ! ነካ ሲያደርጉን እንደፌንጣ እየተስፈነጠርን... በስንቱ እንስፈንጠር! ወይ ሜሲን መሆን ነው፣ አለበለዛ ትከሻ ማውጣት ነው፡፡) እናላችሁ... አራት ያቃሙን አብዛኞቹ እኮ በአውሮፓ ታላላቅ  ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው!
ደግሞላችሁ...ኮሚክ እኮ ነው፡፡ እዚህ ሀገር እኮ እግር ኳስ ልክ  ዕቃ፣ ዕቃ የሚባለው አይነት የልጆች ጨዋታ ብቻ የሚመስለን አሁንም መአት ነን፡፡ (እግረ መንገድ...የዕቃ ዕቃ ዘመን በቆርኪ ሰርግ የሚደገስበት የተባረከ ዕድሜ! እናላችሁ...ለታሪክ ሰነድነት ያህል አሁን “ቀይ መስመር፣ ቀይ መስመር” የሚባለው ነገር የዚህ ዘመን አዲስ ‘ክሬቲቪቲ’ ምናምን ሳይሆን ያኔ በቆርኪ ሰርግ ጊዜ ነው  የተጀመረው! ቂ...ቂ...ቂ...)  
“ምነው ዛሬ ቤቱ ጭር አለ...ያ ጎረምሳሽ የት ሄዶ ነው?”
“እባካሽ፣ አሁንስ የእሱ ነገር ስልችት ነው ያለኝ፡፡ እዛው ከጓደኞቹ ጋር ኳስ ሊራገጥ በጠዋት የወጣ ነው!”
“ብቻ ኳስ ሲራገጥ አንድ ነገር እንዳይሆንና ጦስ እንዳያመጣብሽ! አሁን እንደው ማን ይሙት፣ የተሻለ ጨዋታ የጠፋ ይመስል ኳስ ማሳደድ ጤንነት ነው!” (እኔ የምለው አንድ ጊዜ “ለሀያ ሁለት ሰዎች አንድ ኳስ ሰጥተው ከሚያራግጧቸው ምናለ አንድ፣ አንድ ኳስ ቢሰጧቸው!” አሉ የተባሉት ሰው ዩቲዩብ ቻነል የማይከፍቱትሳ! አሀ...ሀሳባቸው የኳስ ውጤት ችግራችንን ይፈታልን ይሆናላ!)
እናላችሁ... አራት አጠጡን ብለን ስንበግን ከረምናት ነው የምላችሁ! መቼም እንግዲህ አሉን ከምናላቸው ተጫዋቾች የተሻሉ የተባሉት ናቸው... በአመራረጥ በኩል ብዙ ሰበር ዜና የሚባል ደረጃ የደረሱ አይነት ማጉረምረሞች ስላልሰማን ነው፡፡፡
(የሚያሳዝነው ምን መሰላችሁ... አራት ለአንድ በመሸነፋችን አንዳንዶቻችን የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች መሆናቸውን ተውነውና ከዚህ ዘር፣ ከዛ ዘር የሚሉት ትርክት መጣ! እንደው ምን ይሻለናል!)
ከነገሩ ሁሉ በካሜሩኑ ጨዋታ ምነው ግማሽ መንገድ ላይ ደከሙ? ምነው በመጀመሪያው ግማሽ ያሳዩትን የጨዋታ እንቅስቃሴ በሁለተኛው መድገም አቃታቸው? ምነው ‘ፋይቲንግ ስፒሪት’ የሚሉት ነገር አነሳቸው? ምነው እልህ የሚባለው ነገር ሌሎቹ ቡድኖች ላይ የምናየውን ያህል ልናይ አልቻልንም? አይነት ጥያቄዎች መጠየቅ ይቻላል። ምን መሰላችሁ... በእግር ኳሳችን ስለ ችሎታና ብቃት ከማውራት ይልቅ ሌላ፣ ሌላው ‘ወከባ’ በዛና እውነተኛውን ስዕል ሳያበላሽብን አልቀረም፡፡  
እንዴ፣ አንድ ሰሞን የኳስ ተጫዋቾች ደሞዝ በወር በመቶ ሺዎች ውስጥ ገብቶ “ጉድ!” ስንባባል ከርመን የለ እንዴ! ያው እንደ አብዛኛው ነገራችን በኳሱም ‘ፈረንካዋ’ ነች የበጠበጠችን...በአደባባይም፣ ከመጋረጃ ጀርባም “ከኬኩ ድርሻዬ ይገባኛል፣; ባይ በዛና! አንድ ሰሞን እኮ የአንድ ቡድን ተጫዋች ሆኖ ለሦስት፣ አራት ዓመታት የገቡትን ውል ስለማክበር ሳይሆን በተፈረመ በወራት ውስጥ ስለማፍረስ ነበር ትልቁ ዜና። “ኢትስ ቢዝነስ፣ ደሚ!” እንዲል ፈረንጅ ‘ቢዝነሷ’ አሪፍ ስለነበረች ውል አክብሮ አንድ ቡድን ውስጥ ከመቆየት ውል አፍርሶ ወደ ሌላ መሄዱ የኳሳችን የዘወትር ዜና ነበር። እናላችሁ፣ ለረጅም ጊዜ አቅዶ ስፖርቱን ከማሳደግ ይልቅ ተጫዋቾችን አየር በአየር እንደምንለው ንግድ አይነት ዛሬ በአንዱ ማሊያ፣ ከጥቂት ወራት በኋላ በሌላ ማሊያ ማየት የተለመደ ነበርና፣ ችሎታንና ክህሎትን ማሳደጉ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ወረዱና  ያልተዘጋጀንበትን፣ ያልሠራንበትን ውጤት መመኘት መጀመሪያም ልክ አይደለም፡፡
እናላችሁ.. ኳስ እንደ አንድ ትልቅ ኢንደስትሪ አይነት ነገር ከመታየት ይልቅ  በየዝግጅቱ የበዓል ማድመቂያ አይነት ይሆናል... “ከሚቀርቡት ዝግጅቶች አንዱ በጋዜጠኞችና በአርቲስቶች መሀል የሚደረግ አዝናኝ የእግር ኳስ ጨዋታ ነው...” እንደሚባለው አይነት፡፡ ልክ ግጥምን የመሰለ ታላቅ የሥነጥበብ ዘርፍ ላይ እንደሚታየው ማለት ነው...  “ስማ... እስቲ በዓል ላይ ሰዉ እንዳይደበር ግጥም የሚያነቡ አንድ፣ ሁለት ልጆች ፈልግልን...” እንደሚባለው፡፡
እናማ...ኳሳችን በመአት ችግር ውስጥ ያለ ስለሆነ በእሱ ምክንያት ጨጓራችን ወንፊት የሚሆንበት ምክንያት የለም ለማለት ነው። አለ አይደል...በብዙ ዘርፎች የዓለም አቀፍ ደረጃ ምናምን የሚባለውን አይደለም መድረስ፣ ቀረብ ማለት እንኳን ያልቻልነው የማይሆነውን ስንጠብቅ፣ ያልሆነውን ለመሆን ስንሞክር ነው፡፡ እናማ...ለኳሳችን አካባቢው እንኳን ዝር ያላለበትን ደረጃ መስጠት ስንት ነገር ባነፈረው ጨጓራችን ላይ እንደገና ፍል ውሀ መቸለስ ነው የሚሆነው ለማለት ነው፡፡ 
ስሙኝማ...እንግዲሀ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ብዙ ነገር ላይ የምንጠብቀውና የሚሆነው እየተለያየብን ግራ የሚገባን መጀመሪያም የምናይበት ‘መነጥር’... አለ አይደል....ኦሪጂናል ስላልሆነ ነው...ኳሳችንን አንድ፣ ‘ቦተሊካችንን’ ሁለት በሉልኝማ!  
ለምሳሌ የሆነ አክቲቪስት አንድ ሰሞን በቃ ቴሌቪዥኑንም፣ ሬድዮኑንም፣ ማህበራዊ ሚዲያውንም፣ ብቻ ምን አለፋችሁ፣ ሚዲያውን ሁሉ ይሞላዋል፡፡ እኛ ደግሞ ቶሎ ‘ክርብት’ ማለት እንችልበት የለ...ጋሽዬ አክቲቪስት ነገሩን ሲተረትረው ብርቅ ይሆንብንና “እንዴት አይነት ድንቅ ሰው መሰለህ! ልክ ልካቸውን ነው እኮ የነገራቸው፣” እናባባላለን፡፡ (በጥናት ባይረጋገጥም እዚህ ሀገር ‘ቦተሊከኞች’ እና አክቲቪስት የሚባሉት ቲፎዞ መሰብሰቢያ ምናልባትም ዋነኛ ‘ስትራቴጂያቸው’፣ ያኛውን ወገን ልክ ልኩን መንገር ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡)
እናላችሁ...“ሲያወራ ብትሰማው እኮ...  እንደው ምን ሲያደርግ ይሄን ሁሉ እውቀት ሰበሰበው!” ስንለው የነበረው ሰው ይከርም ይከርምና ድንገት ፍሬቻ የለ፤ የኋላ ማርሽ መብራት ብሎ ነገር የለ...ብቻ ድንገት እጥፍ ብሎ ቁጭ፡፡ ደግሞላችሁ...“ልክ ልካቸውን ነገራቸው...” ስንለው የነበርነው ሰውዬ እኛኑ ልክ ልካችንን መንገር፣ “የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ ፖለቲካ ስለማይገባው ነው...” ምናምን እያለ እስከ ዶቃ ማሰሪያችን ማጠጣት ሲጀምር እኛ ምን ብንል ጥሩ ነው...“ከመሳደብ ሌላ ምንም የማያውቅ ለካስ ባዶ ቀፎ ነው!” እናላችሁ...ወጣቶቹ እንደሚሉት “ሙድ ይይዝብናል።” (‘ሙድ መያዝ’ የሚሉት ቋንቋ የወጣቶች ብቻ መሆኑ መቅረቱን ለማሳወቅ ያህል ነው፡፡)
የምር ግን...አለ አይደል... የሆነ ዜማ ነገር ስላለው፣ ደግሞ ስልችት፣ ስልችትችት ካሉን የፖለቲካ ‘ክሊሼዎች’ ስለሚያተርፈን መደበኛ አጠቃቀም ውስጥ የማናስገባውሳ!  
“አሁን የመናገር ዕድሉን ለአቶ እከሌ እንሰጣለን፡፡”
አቶ እከሌ ማይኩን ይይዙና፣ በቃ ለአንዳንድ ተሰብሳቢዎች የማይመቹ ነገሮች ይጨማምሩና ጥቂት ነርቮችን ይነካካሉ፡፡ ይሄኔ እጅ እያወጡ “ሀሳብ አለኝ!” “ተቃውሞ አለኝ!” ምናምን ይባል የለ፣ ሰብሳቢ ደግሞ “ቆይ እሳቸው ሀሳባቸውን ይጨርሱ፣” ምናምን ነገር ይላል፡፡ ይሄኔ አንዱ ብድግ ብሎ ታዲያ “እዚህ ተቀምጠን ህግ አለባት በምትባል ሀገር ሙድ ይያዝብናል እንዴ!” ቢል ያለ አንጃ ግራንጃ ሀሳብ ተላለፈ ማለት አይደል!
ለክፉም ለደጉም ዋናው ነገር አራት ለአንድ ቁጥሩ ሳይሆን፣ ከቁጥሩ ጀርባ ያለው ስዕል ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1211 times