Thursday, 27 January 2022 00:00

በአለማችን 207 ሚ. ሰዎች ለስራ አጥነት እንደሚዳረጉ ይጠበቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ከታሊባን ወዲህ በአፍጋኒስታን ግማሽ ሚ. ሰዎች ስራ አጥ ሆነዋል

            በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2022 በመላው አለም የሚገኙ 207 ሚሊዮን ሰዎች ከስራ ገበታቸው በመፈናቀል ለስራ አጥነት ይዳረጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተባበሩት መንግስታት የስራ ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በ2020 የፈረንጆች አመት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አለማቀፉ የስራ አጥነት መጠን 6.6 በመቶ መድረሱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ባለፈው አመት ወደ 6.2 በመቶ ዝቅ ማለቱንና በተያዘው አዲስ አመት ደግሞ 5.9 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም  አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ታሊባን አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ ወዲህ ባሉት አራት ወራት ያህል ጊዜያት ብቻ በአገሪቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለስራ አጥነት መዳረጋቸውን ተመድ አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስራ ድርጅት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠሩን ተከትሎ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ ቀውስ ውስጥ የገባ ሲሆን በዚህም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከስራ ገበታቸው ውጭ ለመሆን ተገድደዋል፡
በአገሪቱ የስራ አጦች ቁጥር እስከ መጪዎቹ አራት ወራት ድረስ 900 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል የጠቆመው ድርጅቱ፤ ታሊባን ሴቶችን ከስራ ገበታቸው በብዛት ከማገዱ የተነሳ የስራ አጥነት ሰለባ የሆኑት በአብዛኛው ሴቶች መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡ሰራተኞች በብዛት ከተፈናቀሉባቸው መስኮች መካከል ግብርና፣ ኮንስትራክሽንና ሲቪል ሰርቪስ እንደሚገኙበት የተነገረ ሲሆን፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደመወዛቸው ሳይከፈላቸው ከስራ ገበታቸው እንደተፈናቀሉም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ወታደሮች፣ የጤና ባለሙያዎችና መምህራንም ከተጎጂዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

Read 2245 times