Tuesday, 25 January 2022 10:12

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 አንዴ ስማኝ
መኖሪያህ ጠፍቶብን እኛ
መድረሻ ቦታ ስናጣ፤
ደማችን ፈሶ ጨቅይቶ
በዲያብሎስ አፍ ሲጠጣ፤
ወንድም ወንድሙን ገሎ
በደስታ በሚዘልበት፤
እናት በልጇ ሀዘን
ቤት ዘግታ በምትሞትበት፤
ረሀብ ቸነፈር ወርዶ
ምድር አለሙ ሲቸገር፤
ቀባሪ ያጣ የሰው ነፍስ
ጌታዬ እያለ ሲያማርር፤
እንዴት ተቻለህ አንተ
እንዳላዪ ዞሮ መሄድ፤
ካላጣኸው ከሞላልህ
ለምን ጠፋህ አንድ መንገድ፤
ኧረ ባክህ አንዴ ስማኝ
ካለህበት ከመንበርህ፤
ታምር ስራ ለሀገሬ
አለ ብዬም ልቀበልህ፤
አለዚያም ዝም ካልከኝ
ከቶ ምንም አልልህም፤
ክብር ዙፋኑን አውልቀዉ
እሱ ሳይሻል አይቀርም፤
እኔም ገነት ሲኦል አልል
አያስፈራኝም መቀፀፌ፤
ለሚአምኑህ ካልታመንክማ
አለማመን ይሁን ትርፌ።
*   *   *
የሰከንዶች ህይወት
ፅልመት በሸፈነው ሰማይ ወረት በወረሰው ተስፋ፤
በምሽት የወጣች ብርሀን ደርሷት የእርሷ ወረፋ፤
ተራው የኔ ነው እያለች አጥሮባት መቆያ ጊዜው፤
በዛ ጨለማ ድቅድቁ በማይታወቅ መድረሻው፤
ተወርዋሪ ኮከብ ሆና የመብረቅ ብርሀን ብልጭታ፤
ላፍታ ላንድ ጊዜ ብቻ ፍካቷን አውጥታ ታይታ፤
ጊዜ በማይሰጡ በአጫጭር ሰከንዶች፤
ሁሌ ስትታየኝ በሰማይ የኖረች።
 አለች.....
ምክር አላት ለኔ፣ ድምጿ ይሰማኛል
እርሷን ተከትሎም፣ ልቤ እንዲህ ይለኛል፦
"እስኪ ልብ ብለህ፣ እያት ተመልከታት
 ባይረዳት ማንም፣ ትልቅ ትርጉም አላት
 በሰጠችህ ጊዜ፣ ህይወት ምን ብታጥር
 ለሰው ብርሀን ሆነህ፣ ድንቅ አለምን ፍጠር
አውቃለሁ
 አንተን የሚሰማህ....
 በመምጣቷ ደስታ፣በመሄዷም ሀዘን
 ሁሌ የማይለካ፣ሁሌ የማይመዘን
ግን.....
 እርሷን ባየህበት፣ በሰከንዶቹ ውስጥ
 አለ ብዙ ምክር ፣ አለ ብዙ ተስፋ
 ከኖርከው የሚበልጥ;
ልቤ እንዲህ ይለኛል
ምክር አላት ለኔ ፣ ድምጿ ይሰማኛል
ለካስ...
ለካስ ሰው ይማራል ፣ በሰኮንድ እይታ
በኮከብ ብርሀን ፣ በመብረቅ ብልጭታ
በቅፅበት ውስጥ ታይተው
ቢሄዱም በቅፅበት፤
ሰርክ ያስተምራሉ ፣ ሳያወጡ አንደበት።
ከሳሚ አንተነህ



Read 1641 times