Tuesday, 25 January 2022 10:18

ሥነ-ህይወት እና ሣይንስ

Written by  አብዲ መሃመድ
Rate this item
(0 votes)

(ማንይንገረው.. ምን ነገረን?)
                           
              (ክፍል አንድ)
መጀመሪያ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ እያለሁ አብዝተው የትምህርት ገበታ ላይ ከማይገኙ “ወመኔ” ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ አብዝቼ ክላስ እቀጣለሁ፡፡ (አጥር በመዝለል- በድብድብ) ተደጋጋሚ ፋውል እሰራለሁ፤ ወላጅ በማምጣት ነጥብ አስቆጥሬያለሁ፡፡ እንደ “ሀሙራቢ” የማይደፈር ህግ እጥሳለሁ፤ ደንብ እተላለፋለሁ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሙሉ ጊዜ ተማሪ አይደለሁም፡፡ ስድስት ክፍለ ጊዜ ሙሉ መታደም እሚሆንልኝ አልነበረም። እደበራለሁ፣ እሰለቻለሁ፡፡ ትምህርት ላይ ከማጠፋው ጊዜ ይልቅ ከጓደኞቼ ጋር (በተረብና ብሽሽቅ) የማሳልፈው ህይወት ይበልጥብኛል፡፡ የሚያቅበጠብጥ ደስታ ይፈጥርልኛል፡፡ ታዲያ በማይገባኝ ምክንያት ለ“ለአማርኛ” እና “ባዮሎጂ” ትምህርቶች ግን ልዩ ፍቅር ነበረኝ፤ አዎ በነዚህ የትምህርት ክፍለ- ጊዜዎች ክፍል ያጠመደ አያጣኝም፡፡ ያው አልፎ - አልፎ ለአቴንዳስ ስል ግዴታ ሆኖ ልገኝ ብችልም መጨረሻ ወንበር ተሸሽጌ በደብተሬ መሀል የታላቅ ወንድሜን ያረጁ የብርሃኑ ዘሪሁን (የማእበሉ .. ዋዜማ፣ ማግስት፣ መባቻ.. እንዲሁም የፍቅረ ማርቆስ ደስታ (ከቡስካው በስተጀርባ፣ የዘርሴዎች ፍቅር፣ አቻሜ.. የመሳሰሉ በጊዜው ተወዳጅ እና ተነባቢ የነበሩ ልቦለዶችን ወሻሽቄ አበጥራለሁ፡፡ ከሚታክተኝ ሁሉ ብቸኛው ማምለጫዬ ንባብ ነበር፡፡)
በዚህ መነሻነት ከሰሞኑ በአብዛኛው የንባብ ትኩረቴን በሰው ዘር አመጣጥ (ጂኦግራፊ) እና በስነ - ህይወት አፈጣጠር (ባዮሎጂ) ላይ ስላደረጉ ጥናቶችን እያሰስኩ - እያግበሰበስኩ ሳገላብጥ ሰነበትኩ፡፡ ስለ ሁለቱም ሰፊና ጥልቅ አለማት የሚያጠና የእውቀት ዘርፍ ሣይንስ እንደሆነ ማንም አያጣውም፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በዚህ ጉዳይ ላይ እያሳተመ ያሰራጫቸው ስራዎች በቀላሉ የሚገኙ አይደሉም፡፡ ቁጥራቸውም ሲበዛ ውስን ነው፡፡ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የሳይንስ መጻህፍት በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ (ይህን ስል በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ለማስተማሪያነት የሚያገለግሉ የሳይንስ መጻሕፍትን እንደማይጨምር ይሰመርልኝ) ለማግኘትም ቢሆን አድካሚ ነው፡፡ በመጨረሻም ዋናው ቅጥር ጊቢ የ6 ኪሎን በር አንኳኩቼ ተሳክቶልኛል። አለም ዛሬ የደረሰችበትን የሳይንስ ልቀት በመፈተሽ አለም- አቀፍ እውቅና የተቸረው እስራኤላዊው ምሁርና ተመራማሪ “ዩቫል ኖህ ሃራሪ” የሰው ልጅ ያለፈ እና መጭውን መጻኢ - ጊዜ የፈተሸባቸው ስራዎቹ “ሆሞ-ሳፒያንስ” እና “ሆሞ-ዲዩስ” እዚህ መጥቀስ የተገባ ነው፡፡ በአንድ ወቅት… ሃራሪ በማልስማማባቸው ጉዳዮች ላይ ተደምሜ እንዳነበው የሚያስገድደኝ ፀሀፊ ነው.. ሲል ምስክርነቱን የሰጠው ቢሊየነሩ ቢልጌትስ ነበር፡፡ በሀገራችንም ቢሆን ቢዘገይም እውቅና እያገኘ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ የእምነትና የሃይማኖት መልክዐ-ምድር በሚፈታተነው የሀገራችን ባህል የሳይንስ እውቀትና ግንዛቤ አንጻር ሀራሪ በስፋት ቢነበብ ሊኖረው የሚችለው አይነተኛ አስተዋጾ በቀላሉ ሊገመት አይችልም፡፡ ይህን ሀገራዊ ፋይዳ ቀድመው ተረድተውት ይመስላል የሳይንስን እውቀት በአማርኛ ዘግበው በመጻህፍት መልክ በተከታታይ በማቅረብ የላቀ አስተዋጽኦ ካደረጉልን ግለሰቦች መካከል የባዮሎጂ ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር የሆኑት የኛው ሽብሩ ተድላን አለመጥቀስም- አለማመስገንም አይቻለንም። ፕሮፌሰሩም የሃራሪን ሁለት ስራዎች በመግቢያቸው እውቅና ሰጥተው ለኛ እንዲመች በሀገር በቀል ቋንቋ ባዘጋጇቸው ትኩረታቸውን ዝግመተ - ለውጥ ላይ ባደረጉት ሁለት መጻህፍቶቻቸው (ከየት ወደ የት፣ የሰው ዘር አመጣጥ) ሳይንሳዊ አስተሳሰባችን እንዲዳብር የላቀ አስተዋጽኦ አድርገውልናል፡፡
ሳይንሳዊ እውቀትን ህዝባዊ በማድረግ በሀገር ቤት ቋንቋ ማዳረስ ይቻላል የሚሉን ሽብሩ፤ አያይዘው … ተመልከቱ ገበያ ላይ የሚታዩ አንድ ወጥ ሆነው፤በአንድ ግለሰብ እይታ ላይ የተመሰረቱ መጻህፍት ናቸው። ያን አይነት ጽሁፍ ደግሞ ግራና ቀኝ ለማየት ለመዳሰስ አይመችም፡፡ በተለይም ሳይንስ ነክ የሆኑ እና ይዘታቸው በሀገር በግለሰብ ሣይገታ ስለ ሰው ልጅ ጠቅለል ባለ መልክ የሚተቹ መጻህፍት በአካባቢያችን ብዙም አይታዩም። ቢኖሩም የእውቀት መገበያያ መድረኮችን ያበረክታል፡፡ ሀሳብ ማንሸራሸርን ይጭራል፡፡ ስለ ታሪክ ስለ ባህል የበለጠ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያስችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በሀገራችንም የሚደረሱት መጻህፍት በሂደት፣ ይዘቶቻቸው እየጠሩ፣ የሚቀርቡትን አስተያየቶች እየጠለሉ-እየዳበሩ እንደሚሄዱ ተስፋ አደርጋለሁ። (ቀዳሚ-ቃል) ሲሉ በዘርፉ የሚደረሱ ሳይንስ-ነክ ሙከራዎችን ውስንነት ጠቁመዋል፡፡
ቀደም-ባሉት ጊዜያት በታሪክ ውስጥ ከተጻፉት የሳይንስ መጻህፍት መለስ ብለን ስንመለከት፤ በትርጉም መልክ የተዘጋጁት በጣም ጥቂት እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ በ1920 ገደማ በፊታውራሪ ተክለ-ሐዋርያት ተክለ-ማርያም እና በባላምባራስ  ማህተመ-ስላሴ ስለ ግብርና፤እንዲሁም ኋላ ላይ በዶ/ር ፍስሃ ሃይለ መስቀል “የባህሪ አወራረስ” እና “የኢትዮጵያ ታላላቅ አራዊት” በሚሉ ርዕሶች ስር መጻህፍት ተዘጋጅተው ለአንባቢያን እንደቀረቡ ዋቢዎች ያመለክታሉ፡፡
ወደ ቅርብ ጊዜዎቹ ስንፈታትሽ አዲስ ፈር-ቀዳጅ የሆነው ዶ/ር ሰለሞን ይርጋ ሲሆን፤ ያዘጋጃቸውም መጻህፍት የቻርልስ ዳርዊን #የብቸኛ ዝርያዎች መንስኤ; (ትርጉም) እና "አጥቢዎች" የተሰኙ ሁለት ስራዎች ናቸው፡፡
መምህሩ ነው.. ሰለሞን ይርጋ፡፡ ተማሪው ደግሞ ማን ይንገረው ሸንቁጥ፡፡ በአጥቢዎቹ ተምሮ የአስተማሪውን ፈር ተከትሎ፤ እነሆ (ባለ አከርካሪዎችና ከደስታ ባለፈ) የተሰኙ ሁለት መጻህፍት ለማዘጋጀት በቅቷል፡፡ እኔም ለዛሬ ቅኝት አብይ ትኩረቴ እነዚህን ሁለት ስራዎች መቃኘት ይሆናል፡፡
በሥነ-ህይወት ጥናት ህይወት ካላቸው ፍጥረታት ውስጥ ከእጽዋትና ባክቴሪያ በተለየ በጥልቅ ሁኔታ ሲታዩ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ይኸውም ባለ-አከራካሪዎችና አከራካሪ የሌላቸው በሚል.. ማን ይንገረው የበኩር  ስራውን “ባለ-አከርካሪዎች” በሚል ከአመታት በፊት ነበር ሰፋ ያለ-ጥናት አድርጎ ለንባብ ጀባ ያለን፡፡ ባለ-አከራካሪዎች የሚባሉት በተለምዶ የጀርባ አጥንት የሌላቸው ማለትም… አሣዎች፣ እንቁራሪቶች፣ ገበሎች አዕዋፋትን አጥቢዎችን ያጠቃልላሉ።
እነዚህ እንስሳት በቁጥር ብዙ ባይሆኑም የሰውን ልጅ ትኩረት ግን የሚስቡ ናቸው። ለዚህም ምክንያቱ በቀላሉ ለመታየት የሚችሉ በመሆናቸው፣ ከሰው ልጅ ጋር የቅርብ ግንኙነት ስላላቸው፤ የሰው ልጅ በነዚህ ጥቅል ቡድኖች ውስጥ ተጠቃሎ በመገኘቱና በዚህም - ከነዚህ ቡድኖች ጋር ስነ-ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ታሪካዊ ትስስር በማዳበሩ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በስነ-ህይወት ትምህርት ጥናት ውስጥ እንደ ሰው ልጅ ሁሉ አሣዎች መጀመሪያ.. ቀጥሎ እንቁራሪት አስተኔዎች፣ ከዚያ አዕዋፍና በስተመጨረሻም አጥቢዎች እያሉ የ500 ሚሊዮን አመት አዝጋሚ  የለውጥ ሂደት አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ  ሊያደርሳቸው መቻሉ ደራሲው በመጽሐፉ አስፍሮት እናነባለን፡፡ ይህን ብቻ አይደለም፤ የአዝጋሚ ለውጥ ሂደት  ምክንያትም የእርስ በእርስ ዝምድና እንዳላቸው በማስረጃ ይገልፃል። ለምሳሌ ከነዚህ ፍጥረታት በዝርያ ብዛት ካየናቸው አጥቢዎች አነስተኛውን  ማለት 5 ሺህ ያህል ብቻ ይዘው ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ 5 ሺህ ያህል ከሚሆኑት የአጥቢ ዝርያዎችም አንዱ “ሰው” ነው፡፡ ማን ይንገረው በመጽሐፉ በአመዛኙ ለሰው ቅርብ የሆኑና ሰውን የሚያጠቃልሉ የእንስሳት ቡድኖች ገድል በጥቂቱም-በአይነቱም ይተርክልናል። ለትረካው ማጣፈጫ ያደረገውም ሰውን ሊስቡና - ሊያስደንቁ የሚችሉ የእንስሳት ገድሎችን በማጣቀስ ስለ እንስሳት ግንዛቤ በማስጨበጥ ላይ በአያሌው ተግቷል፡፡ በተለይ በአዋቂዎችም ሆነ ለታዳጊ ወጣቶች፣ እነዚህ እንስሳት እንዴት ያለ የተለያየ አኗኗር ባህሪይና ዕድገት እንዳላቸው ተገርመንም ሆነ ተደንቀን የበለጠ ለማወቅ እንድንነሣሣ ያደርገናል፡፡
መጽሐፉ በአዝጋሚ ለውጥ ሂደት ቀድመው ከጀመሩት “አሣዎች” ጀምሮ … የሚናደፉ፣የሚሰደዱስ፣የሚያታልሉስ? በራሪዎችስ? ባለሣምባዎችስ? እያለ ይዘረዝራል፡፡ ከሌሎችም የእንስሳት ዝርያ ምድብ ይወስደንና ዝላይና ዘፈናቸውን፣ ምላስን እንደ እጅ አጠቃቀማቸውን፣ ጀርባን ለእንቁላል መፈልፈያነት መጠቀማቸውን ይገልጻል፡፡ እባብን ከመርዛሙ እንዴት ይለያል? እንዴት ይራመዳሉ? በምናቸው ይናደፋሉ? እንሽላሊቶችም ይበራሉ? ውኃ ላይ ይሮጣሉ? እያለ እየጠየቀና እየመለሰ የአዞንና የኤሊ ዘመድን በተመሣሣይ መልኩ ያስቃኘናል፡፡ በመጨረሻም ለእኛ ከሁሉም መደቦች የተሻለ ቅርብ የሆኑትን አጥቢዎች ይዳስሳል፡፡ ስለእነዚህ መደቦች ብዙ የተጠና ነገር እንዳለ እሙን ነው፡፡ ከብዙ በጥቂቱ እየጨለፈ ለየት ያለ ባህሪና አስገራሚ ተፈጥሮ ያላቸውን ዝርያዎቻቸውን ይገልጻል፡፡ ስለ-ዕንቁላል ጣዮቹ፣ ጥሩር ለባሾቹ፣ በረኽኞቹ፣ ባለከረጢቶቹ፣ በራሪዎቹ፣ ባለ ብዙ ሚስቶቹ፣ አልምጦቹ … ሌላም - ሌላም ትንግርቶችን እየገለጠልን፣ እያስገረመን፣ የበለጠ ለመረዳት እያነሳሳን ይጓዛል፡፡
ጸሀፊው ሥነ-ህይወትና ሣይንሳዊ እውቀትን በግልጽና በቀላሉ ለመረዳት በሚቻል መንገድ በመጽሐፉ ለማስፈር ተሳክቶለታል ለማለት ያስደፍራል፡፡ ማንኛውም አንባቢ በኢትዮጵያ የሚገኙ ባለ አከርካሪዎችን ስም ይረዳ ዘንድ በተቻለ መጠን በአካባቢ ሰዎች የተሰጣቸውን ስም ከእንግሊዝኛ ስሞች ጋርም ለማገናዘብ በብርቱ ሞክሮአል፡፡
ለዚህም ነው ሽብሩ በቀዳሚ ቃል ሀተታቸው…. ሣይንስና-የሣይንስ እውቀት ውጤት የሆነው ቴክኖሎጂ፤ ለሰው ልጅ የኑሮ መሻሻል፣ ለኢኮኖሚ እድገትና ለብልጽግና እንደ ዋና መሣርያና ሞተር ይቆጠራሉ፡፡ ስለሆነም ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን የሚሻ ህብረተሰብ ሁሉ ስለ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ግንዛቤ ማዳበር ይጠበቅበታል የሚሉን፡፡
የትኛውም አመለካከት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚዳብረው ያንን አስተሳሰብ ሊያሰርጹ የሚችሉ ጽሁፎች፣ ስዕሎች፣ ፊልሞችና ሌሎች የማስተማርያ ዘዴዎች ሲዘጋጁና ወደ ህብረተሰቡ ሲሰርጹ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ በመሆኑም የአገራችንና በአጠቃላይ የአለማችን የተፈጥሮ ሀብት ችግር ላይ እንደ መሆኑም ከዚህ አንፃር ይህች “ባለ-አከርካሪዎች” መጽሐፉ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የራሷን ውስን አስተዋጽኦ ታበረክታለች የሚል እምነት አለኝ፡፡ የደራሲውን ሌላ መጽሐፍ (ከደስታ ባለፈ) በመጪው ሣምንት ይዤ እመለሳለሁ፡፡   

Read 1196 times