Print this page
Saturday, 29 January 2022 00:00

"ሰለፊ-ውሀቢያዎች" እና “የድምፃችን ይሰማ” ትግል (ታሪካዊ ቅኝት)

Written by  በአብዱልከሪም ተመስገን (በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር)
Rate this item
(2 votes)


                  የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የትግል እንቅስቃሴ ወይም በአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ህዝበ ሙስሊም ዘንድ “ድምፃችን ይሰማ” በሚል የሚታወቀው ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ትግል፣ በዘመነ ህወሓት/ኢሕአዴግ ከተከሰቱ ህዝባዊ ትግሎችና አመፆች፣ በሥርዓቱ ላይ ባሳደረው ከፍተኛ ጫናና በትግሉ እርዝማኔ (ከ2004 - 2010)፣ በመጀመሪያ ተርታ ከሚመደቡት ውስጥ አንዱ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ምንም እንኳን የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች በመጀመሪያዎቼ የትግል ጊዜያት የመብትና የነፃነት ቢሆኑም፤ ትግሉ እየጠነከረና የህዝብ ተሳትፎ እንደ ማዕበል እየጎረፈ ሲመጣ፣ በትግሉ ውስጥ የመሸጉና ድብቅ አላማ ያነገቡ የሰለፊ-ውሀቢያ አስተምህሮ ተከታዮችና ደጋፊዎች፣ የትግሉን ዓላማ በመጥለፍ የራሳቸው ድብቅ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ እኩይ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የፅሁፌ ዓላማም  የዚህ አስተምህሮ ተከታዮችና ደጋፊዎች ያላቸውን የገንዘብ፣ የመዋቅርና ጥብቅ የውጭ ግንኙነት በመጠቀም በህዝበ ሙስሊሙ ኪሳራ ሊያስፈፅሟቸው አስበዋቸው የነበሩ ድብቅ አላማዎችን ማሳየት  ነው፡፡ በቀጥታ ወደ ርዕሱ ከመግባታችን በፊት ግን ስለ ጉዳዩ ምልዑ ምልከታ ለመያዝ ታሪካዊ ዳራ አስፈላጊ በመሆኑ፤ በመጀመሪያ ሰለፊያ ማለት ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ መቼና በየት ገባ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡  
ሰለፊያ ማለት ምን ማለት ነው?
ሰለፊያ ማለት በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ካሉ በርካታ አስተምህሮቶች  አንዱ ነው፡፡ “ሰለፊያ” የሚለው ስያሜ የመጣው ከአረብኛው “አሳ-ሊፊ አሳ-ሳአሊህ” የሚል ሃረግ ሲሆን ትርጉሙም “ጻድቆቹ ቀደምት የነብዩ መሐመድ ወዳጆች” ማለት ነው፡፡ አንድ አንባቢ ሊረዳው የሚገባው ዕውነት ቢኖር፣ ሌሎች የእስልምና አስተምህሮቶች ራሳቸውን ሰለፊያዎች ነን ብለው ይገልፃሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በተለምዶ የሰለፊ አስተምህሮት ተከታዮች ‘’ወሀቢያ’’ የሚለውን ስያሜ እንደ ትችት ወይም በእንግሊዝኛው pejorative  ይመለከቱታል። በዚህም ምክንያት በዚህ ፅሑፍ ውስጥ በምገልፃቸው የአስተምህሮት ፅንሰ-ሃሳቦች የሚያምኑና የሚደግፉ፣ ራሳቸውን ሰለፊያ ብለው የሚጠሩትን “ሰለፊያ-ውሀቢያ” በሚል ስያሜ ለመለየት ተገድጃለሁ፡፡
የሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምሮ የነብስ አባት ተደርጎ የሚቆጠረው ኢብን ታይሚያአ (Ibn Taymiyya) ነው፡፡ ኢቢን ታይሚያአ በአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የሙስሊም ሊሂቅ ሲሆን፤ ለሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮ እርሾውን ያዘጋጀ እና ከሱ በኋላ ለመጡት የሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮት መስራች ተደርገው ለሚቆጠሩት የአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ የእስልምና ሊቅ ሙሐመድ ኢቢን አብዱልወሀብ ከፍተኛ የተነሳሽነት ስሜት ያስተላለፈ እንደሆነ በብዙ ድርሳናት ተሰድሮ እናገኘዋለን፡፡ እንግዲህ “ውሀቢያ” የሚለው ስያሜ የመጣው የአስተምህሮቱ ፈጣሪ ተደርገው የሚቆጠሩትን የአብዱልወሀብን አስተምህሮት ተከታዮች ለመጥቀስ ነው፡፡
ወደ አስተምህሮቱ ዋና ዋና ፅንሰ ሃሳቦች ስንገባ፡- እውቁ የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም የኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ተመራማሪ የሆነው ሀጋይ ኢሪሊች (Haggai Erlich) ከባልደረባው ሙስጠፋ ካባህ (Mustafa Kabha) ጋር በጋራ “Al-Ahbash and Wahhabiyya፡ Interpretations of Islam” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም ባሳተሙት አርቲክል ስለ ሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮቶች የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች ዘርዝረዋል፡-
ውሀቢያዎች ፈጣሪንም ወይም የአላህን ልዩ መሆንን፤ ብቸኛው አምላክ መሆኑን እና ምን የማይሳነው መሆኑን ወይም በአረብኛው ሲጠቃለሉ ተውሂድን አጥብቀው ይከተላሉ፡፡
ቅዱስ ቁርአን እና በውስጡ የያዛቸው ቃሎች ዘላለማዊ ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡
በውሀቢያ አስተምህሮ ለአውሊያዎች ወይም ለተቀደሱ ሰዎች የሚደረግ ዚያራ ወይም ጉብኝት ፈፅሞ የተከለከለና እንደ ሽርክ ወይም አህዛብነት የሚያስቆጥር ነው ብለው ያምናሉ፡፡
ሌላኛውና ዋነኛው የውሀቢያ አስተምህሮ ሃይማኖት፣ ሀገርና ፖለቲካ የማይነጣጠሉና የማይለያዩ ናቸው የሚለው ነው፡፡ በዚህም ውሀቢያዎች ከሀገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነቶች በሁለት ጎራዎች ከፍለው ይመለከቱታል። እነሱም፤ ሙስሊሞች በከፍተኛ ቁጥር ብዙሀን ከሆኑበት ሀገራት ጋር የሚኖር ግንኙነትና ሙስሊሞች አናሳ ወይም ብዙሀን ካልሆኑባቸው ሀገራት  ጋር የሚደረግ ናቸው፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች አብላጫውን ቁጥር በያዙባቸው ሀገራት ሃይማኖትና መንግስት (በአጠቃላይ ሀገር) አንድ መሆን አለባቸው ብለው ያምናሉ። የመንግስትም አስተዳደር በሼሪያ ህግ ላይ የተመሰረተ ይሆናል፡፡ ሙስሊሞች ዳሀጣን በሆኑባቸው ሀገራት ደግሞ የእምነቱ ተከታዮች በሃይማኖታቸው እንዲሰባሰቡና እንዲደራጁ በማድረግ የእስልምናን ድል እናመጣለን ብለው ያስባሉ፡፡
ሰለፊያ-ውሀቢያ ወደ ኢትዮጵያ እንዴትና መቼ ገባ?
ከላይ ለማስቀመጥ እንደተሞከረው፣ የሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮ ትውልዱ በሳውዲ አረቢያ ሆኖ፣ ከፍጥረቱ በኋላ ባሉ ሁለት ከመንፈቅ ምዕተ-ዓመታት ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ዋና ዋና አስተምህሮቶችና ሌሎችንም የአስተምህሮቱን መንፈሳዊ ህልዮት  ይዞ በመላው ዓለም ለመስፋፋት ችሏል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም የዚህ አስተምህሮት መዳረሻ ከሆኑ ሀገራ መካከል አንዷ ናት፡፡ የሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮ ወደ ኢትዮጵያ በትክክል መቼ እንደገባ አይታወቅም፡፡ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ የታሪክ አጥኚዎች በተለይም ቀደም ሲል ከላይ የተጠቀሰው ሀጋይ ኢርሊች፣ እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም ባሳተመው “Saudi Arabia and Ethiopia: Islam, Christianity and Politics Entwined” በሚለው መፅሐፉ፤ ሰለፊያ-ውሀቢያ በኢትዮጵያ ውስጥ እግሩን የተከለው በጣሊያን ወረራ ጊዜ ሀጅ ሄደው በተመለሱ ኢትዮጵያውያን እንደሆነ ይገልፃል፡፡ በተለይም ሼክ ዩሱፍ አብዱልረህማን አል ሐረሪ የተባሉ የሐረሪ ተወላጅ፣ አስተምህሮቱ በግንባር ቀደምትነት በሐረርና በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን አፅንዖት ሰጥቶ ከትቧል፡፡ ሌላኛው በሰለፊያ-ውሀቢያ ላይ በተለይም ደግሞ በባሌ ስለነበረው ታሪክ ጥናት ያደረገው ቴርዤ ኦስቴቦ (Terje Østebo) “Localizing Salafism: Religious Change among Oromo Muslims in Bale, Ethiopia” በሚለው ድርሳኑ፤ የኢርሊችን መከራከሪያ ሃሳብ ጠንካራነት ተቀብሎ፤ የጫት ንግድ በሐረርጌ መስፋፋት በዙሪያው የሚኖሩ ኦሮሞዎችን ከፍተኛ ገቢ እንዳስገኘላቸውና በዚህም ምክንያት ሀጅ ለማድረግ የሚያስችል አቅም መቀዳጀታቸውን፣ ይህም ሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮ ከሀጅ በተመለሱ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ በምስራቅ ኢትዮጵያ እንዲንሰራፋ እንዳደረገው ያወሳል፡፡ በተጨማሪ በ1960ዎቹ አካባቢ ከሳውዲ አረቢያ ከትምህርት የተመለሱ የባሌና የአርሲ ተወላጅ ተማሪዎች አስተምህሮቱ በዚሁ በምስራቁ ክፍል በተለይም በትውልድ አካባቢያቸው ባሌና አርሲ ማስፋፋታቸውን ኦስቴቦ ከትቧል፡፡
እንግዲህ የሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮ መሰስ ብሎ ከገባባቸው የምስራቁ የሀገሪቷ ክፍሎች ወደ ተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ተዛምቷል፤ ምንም እንኳን በቆየው የኢትዮጵያ እስልምና በሱፊ ትውፊት ቢገታና ቢደናቀፍም፡፡ ኦስቴቦ፤ "The Question of Becoming: Islamic Reform-Movements in Contemporary Ethiopia” በሚለው ጽሁፉ፤ ለአስራ ሰባት ዓመታት የቆየው የወታደራዊው ስርዓት የሰለፊያ-ውሀቢያን እንቅስቃሴ ለመግታት ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ እንቅስቃሴው በነበረው ያልተማከለ ባህርይ ጨርሶውኑ ሊገታው እንዳልቻለ ሰንዷል፡፡ ኦስቴቦ በዚሁ መጣጥፉ፤ ህወሐት መራሹ ኢሕአዴግ የሐገሪቱን በትረ-ስልጣን በጨበጠ ወቅትና ሀገሪቷን ባስተዳደረበት ወቅት የሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮ ወደ ጅማ፣ ወሎ እንዲሁም ወደ መዲናችን አዲስ አበባ መስፋፋት እንደቻለ ዘግቧል፡፡ እንግዲህ የአስተምህሮቱን ታሪካዊ ዳራና ዋና ዋና ፅንሰ-ሃሳቦችን በምናባችን እንያዛቸውና ወደ ዋናው ፅሑፍ አውድ እንግባ፡፡
ሰለፊያ-ውሀቢያ  እና “ድምፃችን ይሰማ”
ቀደም ሲል ከላይ በጠቀስኩት በኢርሊችና በሙስጠፋ በተፃፈው ጽሁፍ፤ ሰለፊያ-ውሀቢያዎች ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ስለሚያዩበት መንገድ የሚከተለው ሀሳብ ሰፍሯል፡- “The founders of the Wahhabiyya in their writings mostly ignored Islam’s positive concepts of Ethiopia and Ethiopians.” ወደ አማርኛ ስንመልሰው፤ “የውሀቢያ መስራቾች በጽሑፎቻቸው እስልምና ሃይማኖት ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያለውን አዎንታዊ አመለካከቶች ችላ ወይም ገሸሽ አድርገዋል።" በዚሁ መጣጥፍ የማጠቃለያ ክፍል፣ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ፣ ሰለፊያ-ውሀቢያዎች ማሳካት ስለሚፈልጉት ዓላማ የሚከተለው  ተፅፎ እናገኘዋለን፡- “The Muslims in today’s Ethiopia are in fact quite divided in coping with their own new momentum. The majority continue to conceive themselves as Ethiopians first. They aspire to an Ethiopia of open dialogue on equal footing…..The more activist cells, popular known as Wahhabiyya, aspire and work toward Islamic victory” ትርጉሙም፡- “በአሁኗ ኢትዮጵያ ያሉ ሙስሊሞች የራሳቸውን በሃይማኖታቸው ላይ ያላቸውን አዲስ ተነሳሽነትን መፍትሔ በመስጠት ጉዳይ ዙሪያ ተከፋፍለዋል። አብዛኛዎቹ ራሳቸውን በቅድሚያ ኢትዮጵያዊ አድርገው በማሰብ ቀጥለዋል። የነዚህ ሙስሊሞች መሻት በዕኩልነት ላይ የቆመ ክፍት ውይይት የሚደረግባት ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡ በአብዛኛው ዋልታ የረገጡ ክፍሎች ወይም በገሀድ  ውሀቢያ ተብለው የሚታወቁት፣ የእስልምና አሸናፊነትን ለማምጣት ይፈልጋሉ፤ ለዛም ግብ መሳካት ይሰራሉ፡፡”
እነዚህን ሁለት ሃሳቦችን ያነሳሁት እንዲሁ ያለምክንያት አይደለም፡፡ የሰለፊያ-ውሀቢያ ተከታዮች ይህንን አመለካከትና ዓላማ ይዘው ነው እንግዲህ እጃቸውን በ”ድምፃችን ይሰማ” እንቅስቃሴ ውስጥ የሰደዱት፡፡ እስቲ የድምፃችን ይሰማን እንቅስቃሴ ዋነኛ መታገያ ሀሳቦችን በዝርዝር እንመልከት፡፡
የ”ድምፃችን ይሰማ” እንቅስቃሴ ዋነኛ ጥያቄ ከነበሩት መካከል የመብት ጥያቄ አንዱ ነው፡፡ ይሄ የመብት ጥያቄ በአብዛኛው የሚያጠነጥነው፣ ህዝበ ሙስሊሙ በመረጣቸውና በፈቀዳቸው ሰዎች መጅሊሱ መመራት አለበት በሚለውና በጊዜው የነበረው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት፣ ከህገ-መንግስቱ በተጻራሪ በሃይማኖቱ ውስጥ እያደረገ ያለውን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ነበር፡፡ ሁለተኛው የትግሉ ጥያቄ ደግሞ  ከዚሁ ጋር ተያያዥት ያለው በአል-ሀበሽ (Al-Ahbash) አስተምህሮ ዙሪያ የተነሳው ንትርክና ግጭት ነው። እንግዲህ ስናጠቃልለው የ”ድምፃችን ይሰማ” እንቅስቃሴ ዋነኛ ጥያቄዎች ተብለው የሚነሱት እነዚህ ሁለት ነጥቦች ናቸው፡፡ ከዚህ በመቀጠል በዚህ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የመሸጉትና የትግሉ መሪና ተሳታፊ ሆነው የተንቀሳቀሱት ሰለፊያ-ውሀቢያዎች፣ እነዚህን ሁለት የ”ድምፃችን ይሰማ” የህዝበ ሙስሊም ጥያቄዎች፣ እንዴት ለራሳቸው ዓላማ ማስፈፀሚያ እንደተጠቀሙበት እንቃኛለን፡፡
ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ሁለቱ የ“ድምፃችን ይሰማ” ጥያቄዎች ተያያዥነትና ትስስር አላቸው፡፡ በመንግስት ጣልቃ ገብነትና በመጀሊሱ አመቻችነት ከሌብነን ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል የተባለው የ”አል-ሀበሽ” (በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ “ሀባሽ” ተብሎ የሚጠራው ማለት ነው፡፡) አስተምህሮ፣ በዛም ምክንያት የተነሳው ህዝባዊ አመፅ እኩይ አላማ ባላቸው በሳዉዲ አረቢያ በሚደገፈው አወሊያ ትምህርት ቤት ለተሰባሰቡና ለተደራጁ የሰለፊያ-ወሀቢያ ተከታዮች ዓላማ ማስፈፀሚያ ይሄ ነው የማይባል ከፍተኛ ሽፋን ሰጥቷቸዋል። በኢትዮጵያ እስልምና ታሪክ ላይ ብዙ ጥናታዊ ፅሁፎችን ያሰናዳው ፈረንሳዊው ኤልዋ ፊክ (Eloi Ficquet) “The Ethiopian Muslims: Historical Processes  and Ongoing Controversies” በሚል ርዕስ በፃፈው መጣጥፍ፣ ይህንኑ ሀሳብ በሚያጠናክር መልኩ የሚከተለውን አስፍሮ እናገኛለን፡- “Actually, the feelings of confusion and discontent raised by the controversy {over Al-Ahbash} were present among the Muslim population as a whole, and not just its radical and militant elements, but the developments provided a context that Salafi militants could exploit,, by defending, quite paradoxically, the liberal principles of secularism in order to reach a wider audience.” ትጉሙም፡- “በዓል-ሀባሽ ንትርክ የተቀሰቀሰው የመደናገርና የቅሬታ ስሜቶች በአክራሪና በአመፀኛ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን በመላው የሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ የተስተዋሉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ክንውኖቹ ለሰለፌያ አመፀኞች ከነሱ ሀሳብ በተፃራሪ የሆነውን የነፃ አለማዊ መርህን በመደገፍ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህብረተሰብን ለመድረስ የሚያስችል ምክንያት የሰጠ ነበር፡፡”
ፊክ በዚሁ መጣጥፍ በአወሊያ ትምህርት ቤት በኩል የተሰባሰቡ የሰለፌያ-ውሀቢያ ቁንጮዎች የአል-ሀባሹን ውዝግብ እንዴት እንደተጠቀሙበት ይነግረናል። ፌክ ይጽፋል፡- “Thus, behind the theological dispute on al-ahbash there was a fundamental conflict over the legitimacy and representativeness of religious institutions in a still partially settled legal framework. For the “Aweliyya network” formed by that school`s faculty, students and alumni, the al-ahbash controversy offered an opportunity to reaffirm their influence and legitimacy as the moral and political authority of the Majlis.” ወደ አማኛ ስንመልሰው፡- “በአል-ሀበሽ ምክንያት ከተነሳው ስነ-መለኮታዊ ንትርክ ጀርባ መሰረታዊ የሆነ የሐይማኖት ተቋማትን ቅቡልነትና ወካይነት ላይ ያነጣጠረ ግጭት ነበር፡፡ በአወሊያ ፋኩዩሊቲ፣ ተማሪዎችና ተመራቂዎች ለተመሰረተው የ”አወሊያ ኔትወርክ” የአል-ሀበሽ ንትርክ የመጅሊሱን የሞራልና የፖለቲካ ልዕልና በመገዳደር በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ ተፅኖአቸውንና ቅቡልነታቸውን ዳግም ለማረጋገጥ የተሰጠ እድል ተደርጎ ተቆጥሮ ነበር፡፡
ከላይ በተብራራው መልኩ እንግዲህ ሰለፊያ-ውሀቢያዎች እንዴት የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ ለራሳቸው አላማ ማስፈፀሚያ እንደተጠቀሙበት አይተናል፡፡ ነገሩ ግን በዚህ አያበቃም፡፡ ከአል-ሀባሽ ንትርክ ጋር በተያያዘ ሰለፊያ-ዉሀቢያዎች ግርግሩን ለድብቅ መሻታቸው ከመጠቀማቸውም በተጨማሪ ከአስተምህሮቱ ጋር ያላቸው ግጭትና ፉክክር አስተምህሮቱን ህዝበ ሙስሊሙ እንደ ባዕድ እምነት እንዲያየውና እንዲቃወመው ገፍተዋል ብለን በድፍረት መናገር እንችላለን፡፡ በሀጋይ ኢሪሊች እና በሙስጠፋ ካእባህ በተከተበው መጣጥፍ እንደተጠቆመው፤ የአል-ሀበሽና የሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮቶች ፉክክር ስረ-መሰረቱ የሚጀምረው በምስራቅ ኢትዮጵያ በምትገኘው ጥንታዊቷ የእስልምና መዲና ሐረር ነው፡፡ በፋሺስት ወረራ ጊዜ ወደ መካ ለሀጅ የሄዱ ጥቂት  የሐረሪ ተወላጆች በዛው በሳውዲ አረቢያ በርካታ ተከታይ ባለው የውሀቢያ-ሰለፊያ አስተምህሮ ተነደፉም ተጠመቁም፡፡ እነዚህ ከአዲስ አስተምህሮት ጋር ወደ ቀያቸው የተመለሱ ቡድኖች፣ ሐረርን ከኢትዮጵያ ለመገንጠልና ሙስሊሞችን ብቻ የያዘች ነፃ የሐረር መንግስት ለመመስረት ከፋሺስት ወረራ በኋላ ባሉት ስምንት አመታት ያለመታከት ጥረዋል፡፡  ረጅም ጊዜ ከፈጀ ትግል በኋላ የእነዚህ ተገንጣይ አክራሪ የሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮ ተከታዮች ዓላማ፣ በጊዜው በነበረው የንጉሰ ነገስቱ መንግስትና ከዚህ እኩይ አላማ በተቃራኒ በቆሙ አገር ወዳድ የሐረሪ ተወላጆች ትብብር ሊከሽፍና አቀንቃኞቹም ወደ ተለያዩ ሀገራት ሊበተኑና ሊሰደዱ ችለዋል፡፡
የእነዚህ አክራሪ ሰለፊ-ወሀቢያ መሪ የነበረው ሼክ ዩሱፍ አብዱልረህማን አል-ሐረሪ፣ ቀደም ሲል ትምህርቱን ወደ ተከታተለበት ሳዑዲ አረቢያ እንዲመለስ ተገድዶም ነበር፡፡ በሐረር በተለይና በኢትዮጵያ ባጠቃላይ የአብዱልረህማን ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበረው የአል-ሀባሹ አስተምህሮ መሪ የሆነው ኢትዮጵያዊው የሐረሪ ተወላጅ ሼክ አብደላ ኢብን ሙሀመድ ኢብን ዩሱፍ ኢብን አል-ሐረሪ ነበር፡፡ እንደነ ኢርሊች አገላለፅ ከሆነ፣ ሼክ አብደላ በኢትዮጵያ እስልምናና ክርስትና አብሮ መኖርና መቻቻል ላይ ከፍተኛ እምነት ነበራቸው፡፡ እነ ኢርሊች ሲፅፉ፤ “Reportedly born in 1910, he received an Islamic education in Ethiopia and grew to be a firm believer in Ethiopian Islamic Christian coexistence.” ወደ አማርኛ ስንመልሰው፡- “እ.ኤ.አ በ1910 ዓ.ም እንደተወለደ የሚነገርለት ሼክ አብደላ፣ እስላማዊ ትምህርትን በኢትዮጵያ እንደተማረና በኢትዮጵያ እስልምና እና ክርስትና አብሮ-መኖር ጥልቅ እምነት ያለው ሆኖ እንዳደገ ተዘግቧል፡፡” በዚህም ምክንያት ይላሉ እነ ኢርሊች፣ በጊዜው በሰለፊያ-ወሀቢያ አክራሪ ተገንጣዮችና እነሱን በሚገዳደሩት መካከል በነበረው ትግል ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ። አክራሪዎቹ የሰለፊያ-ወሀቢያ ተከታዮች ሼክ አብደላንና ተከታዮቻቸውን በጊዜው በሁለት ምክንያቶች ያብጠለጥሏቸው ነበር፡፡ የመጀመሪያው እ.ኤ.አ በ1941 ዓ.ም በሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮቶች መሰረት በሐረሪ ውስጥ ያሉትን ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች ለማዋቀር ተደርጎ በከሸፈው ሙከራ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እነዚሁ አክራሪዎች ከሱማሊያ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ አቀንቃኞች ጋር በመተባበር ሐረርን ከኢትዮጵያ ለመገንጠልና የሙስሊሟ ሶማሊያ አካል ለማድረግ ከተደረገው ሙከራ ጋር በተገናኘ ነበር፡፡ ሰለፊያ-ውሀቢያዎቹ ሼክ አብደላንና ተከታዮቻቸውን #ከማዕከላዊ መንግስት ጋር ሆናችሁ አጥቅታችሁናል፤ አላማችንንም አጨናግፋችኋል; በማለት ነበር የሚከሷቸው፡፡
ይሄ ሁሉ ከሆነ በኋላ እንግዲህ ሼህ አብደላ ከሀገር ተሰደው በመካ፣ እየሩሳሌምና ደማስቆ ከቆዩ በኋላ እ.ኤ.አ በ1950 ወደ ቤሩት ሌብነን አመሩ። ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በሌብነንም የእስልምና እና የክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች አብሮ መኖርንና መቻቻልን እየሰበኩ ቆዩ፡፡ ይህም የለዘብተኛና አቃፊ አቋማቸው ብዙ ደጋፊዎችንና ተከታዮችን አፈራላቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1983 ዓ.ም የእስልምና  ግብረ-ሰናይ ፕሮጀክቶች ማህበር ወይም በእንግሊዘኛው Association of Islamic Philanthropic መሪ ሆኑ፡፡ ማህበሩ እሳቸው መሪ ከሆኑ በኋላ “አህባሽ” እየተባለ መጠራት ጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ ከ1983 ጀምሮ ሼክ አብደላ በአለም አቀፍ ደረጃ ዝናን አተረፉ፡፡ የተለያዩ ወደ ሀያ የሚጠጉ ከአስተምህሮአቸው ጋር የተዛመዱ መጽሐፍትን ፃፉ። እነ ኢርሊች፣ ”Al-Ahbash and Wahhabiyya: Interpretations of Islam” በሚለው ቀደም ሲል በተጠቀሰው መጣጥፋቸው፤ የሼህኩ ዋነኛ መልዕክት ከተወለዱበት ሀገር ኢትዮጵያ ይዘውት የመጡት የክርስትና እና እስልምና አብሮ መኖርን የሚያንጸባርቅ ነበር ይላሉ፡፡ የሚመሩት ማህበር በሁሉም አህጉራት ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ በአውሮፓ ዋነኛ ማዕከላቸውን በጀርመን ላይ ከፍተዋል፣ በምዕራብ አውሮፓም እንዲሁ፡፡ በተጨማሪም በኢንዶኔዥያ፣ በማሌዥያ፣ በህንድ፣ በፓኪስታን፣ በታጃኪስታን፣ በሶሪያ፣ በጆርዳን፣ በግብፅ፣ በካናዳ፣ በሰዊዘርላንድ፣ በፈረንሳይ፣ በዩክሬን፣ በሆላንድ፣ በስዊድን፣ በአውስትራሊያና በአሜሪካ ከፍተው ነበር፡፡ የአሜሪካና የምዕራብ መንግስታት በተለይ ሼህኩንና አስተምህሮታቸውን እጃቸውን ዘርግተው ተቀብለዋቸዋል፤ እንደ ጉድ እየተንሰራፋ የመጣውን አክራሪውን የሰለፊያ-ውሀቢያ አስተምህሮ ለመግታት በማለም፡፡
እንግዲህ በዚህ ታሪካዊ ፉክክርና መቆራቆዝ ውስጥ ነው የአል-ሀበሽ አስተምህሮ ወደ ኢትዮጵያ ዳግም ተመልሶ የመጣው፡፡ እናም የአል-ሀበሽ ለዘብተኛ አካሄድና በሙስሊም እና ክርስቲያን ወንድማማቾች መካከል ያለውን አብሮነት ማጉላት፤ይህም በአለም ላይ አስተምህሮቱን በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ እንዳደረገው የተገነዘቡ በ”ድምፃችን ይሰማ“ ትግል ውስጥ የመሸጉት የሰለፊያ-ውሀቢያ አክራሪ መሪዎችና ደጋፊዎች፣ ይህንን አይነተኛ አጋጣሚ በመጠቀም ስለ አስተምህሮቱም ሆነ ስለታሪኩ ብዙም ግንዛቤ የሌላቸውን ወጣቶች አስተምህሮቱ የባዕድ እንደሆነና በመንግስት ጣልቃ ገብነት ህዝበ ሙስሊሙ ላይ ለመጫን እየተደረገ እንደሆነ በማስገንዘብ፤ አጋጣሚውን በአንድ በኩል የኢትዮጵያ እስልምና ሞተር የሆነውን መጅሊሱን ለመቆጣጠር በሌላ በኩል ደግሞ ታሪካዊና በጊዜውም ከፍተኛ ተቀናቃኛቸው የሆነውን የአል-ሀበሽ አስተምህሮትን ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት ተጠቅመውበታል፡፡ ይሄ ነው እንግዲህ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታት!!!

Read 1754 times