Saturday, 29 January 2022 00:00

ምክክር ለምን? በምን ጉዳይ ላይ? እንዴት?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 1. በቅዠትና በስካር ፉክክር የጦዘ ዘመን።

ለመመካከርና ለመግባባት ምን ያስፈልጋል? 1ኛ. መካበበር፣ 2ኛ. የወደፊት አላማ ላይ ማነጣጠር፣ 3ኛ. ዋና ዋና ቁምነገሮች ላይ ማተኮር፣…
በእውቀትና በጥበብ፣ በቅንነትና በልኩ፣ በጨዋነትና በስርዓት ማከናወን ከተቻለ፣ “ምክክር”፣ ጠቃሚና ውጤታማ ሊሆን ይችላል - በጥረትና በፅናት።
ግን፣ ብዙ ችግሮችና እንቅፋቶች መኖራቸውን አንርሳ። ደግሞስ፣ በችግሮች ዓይነትና በእንቅፋቶች ብዛት፣ አገር ምድሩ ባይሰክርና ግራ ባይጋባ ኖሮ፣ “የመግባቢያ ምክክር” ያስፈልግ ነበር?
ፈተናዎችን በመዘንጋት፣ የምኞትን ጫፍ ይዘን እየተሸከረከርን፤ “ምክክር ደረሰልን። መግባባት ያምጣልን” ብንልስ? በምኞት የተጋረደ ድፍን አስተሳሰብ፣… ራሱን የቻለ ትልቅ ፈተና ይሆንብናል።
ምክክር፣…. “በምን መንገድ? በምን ጉዳይ ላይ? ለምን ውጤት?” ብለን ከልብ ካላሰብንበትና በተግባር ካልተጋንበት፣ ጠቃሚ ውጤት አያመጣም።
በተቃራኒው፣ አለመግባባትን ለማግነን፣ ንትርክን ለመጋበዝ፣… ብሽሽቅንና ውንጀላን ከማርገብ ይልቅ፣ ለማራገብ የተመቻቸ ሊሆን ይችላል።
ምክክርን የሚያመክኑ በርካታ ችግሮችና ሰበቦች አሉ።
የጥርጣሬና የብልጣብልጥነት ቅኝት፣ አንዱ ችግር ነው። በተቀናቃኝ ጎራ የተቧደኑ ሰዎች፣ እርስበርስ በጥርጣሬ ሲተያዩ፤… ሁሉም ነገር፣ የማስመሰያ ተውኔት ወይም የይምሰል ወግ ይሆንባቸዋል። ለሴራና ለተንኮል የተደገሰ፣ ወይም ለሴራና ለተንኮል የሚጋብዝ ሆኖ ይታያቸዋል።
ማንኛውንም ነገር፣ የመናቆሪያ ምቹ አጋጣሚ ማድረግ፣… ልዩ የፖለቲካ ጥበብ፣ እጅግ የላቀ የብልጠት ከፍታ ይመስላቸዋል። ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ፣ ተቃናቃኛቸውን ለማጥላላትና ለመወንጀል ካልተጠቀሙበት፣… እንደ መሞኘት፣ እንደ የዋህነት ይቆጥሩታል። መበለጥ ይሆንባቸዋል።
በጥርጣሬና በብልጠት ላይ የሚተማመኑ ሰዎች፤ ሁሉንም አይነት ስብሳባ የአለመግባባት ምድጃ፣ ማንኛውንም ጉዳይ የሙግት ማገዶ፣ ማድረግ አይከብዳቸውም።
አገሩና ዘመኑ ደግሞ ለዚህ ይመቻል።


                 2. የኢትዮጵያ ነገር፣ እንደታሰበው አይሆንም። በጅምላ ፍረጃ ሳቢያ።

          የእርቅ እና የይቅርታ ሙከራ፣ ለጸበኛ ግለሰቦች ሁነኛ መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል። ቅራኔ ውስጥ ለተዘፈቁ ድርጅቶች፣ ተቋማት ወይም ማህበራትም፣ የይቅርታና የእርቅ መንገድ፣ ጥሩ የመፍትሄ አማራጭ ሊሆን ይችላል- ለዘለቄታው ሕግንና ስርአትን በሚያሻሽል መንገድ።
እርቅና ይቅርታን ለማብዛት፤ ሕዝብ አዳምን በሙሉ፣ የሄዋን ትውልድን ሁሉ፣ በጎራ ማቧደን ግን፣ እርቅን አያመጣም። በተቃራኒው፣ የጅምላ ጥላቻንና ውንጀላዎችን ያራባል።….
ከዚያም ባሻገር፣ ዛሬ በሕይወት የሌሉ፣ ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ ሰዎችን እየጠቀሱ፣ ዛሬ የመወነጃጀል ቅዠት ይለመዳል። የዛሬ ነዋሪዎችን በጅምላ ከሳሽና ተከሳሽ፣ ካሳ ጠያቂና ባለ እዳ ለማድረግ፣ የጥንት ታሪኮችን ወይም ተረቶችን እየዘበዘቡ እልፍ ንትርኮችን የመፈልፈል ጥፋት ይሆናል - መዘዙ።
እንደዚህ አይነት ስህተት ላይ ላለመውደቅ፣ ጥንቃቄ የተደረገ ይመስላል - በምክከር አዋጁ ላይ። እንዴት?
“እርቀ-ሰላም” ወይም “እርቅና ይቅርታ” ሲባል፤ ስያሜው በቀጥታ፣ ከፀብና ከበደል ጋር በግድ እየተዛመደ፣ የውዝግብ ሃሳቦችን ይጋብዛል - የመረረ ጥላቻንና ጭፍን ውንጀላዎችንም ጭምር እየጎተተ ሊያመጣ ይችላል።
“ምክክር” የሚለው ስያሜ፣ እንደዚያ አይነት ሸክም የለውም።
ምክክር፣ የግድ፣ ከጥላቻ ወይም ከፀብ ጋር መዛመድ አያስፈልገውም። ፀብ የሌላቸው ሰዎችም ይመካከራሉ። በሃሳብ የማይቃረኑ ሰዎችም መነጋገር ይችላሉ። “ምክክር” የሚለው ቃል፣ ከቅራኔ ትርጉም ጋር አለመጎዳኘቱ ጥሩ ነው።
ሰዎች በጅምላ እንዲቧደኑ የሚገፋፋ ቅኝትስ?
ለዘረኝነትና ለሌሎች የጥፋት ቅስቀሳዎች የሚያጋልጥ የአስተሳሰብ ቅኝት፤ ብዙ ነገሮችን በቀላሉ ያበላሻል። የምክክር አዋጁ፣ እንዲህ አይነት ቅኝት ክፉኛ የተጫጫነው አይደለም። ግን፣ ሙሉ ለሙሉ የፀዳ አይደለም።  “የህብረተሰብ ክፍሎች” የሚለውን የጅምላ አባባል መጥቀስ ይቻላል። ለጭፍን የፍረጃ ጣጣ ያጋልጣል።
“የህብረተሰብ ክፍል ተወካይ”  እና “የምክክር ተሳታፊ”፣ ማን ማን እንደሚሆን የመወሰን ውጥንቅጥ አይፈጠርም? “ሀቀኛ ተወካይ፣ የውሸት ተወካይ” የሚል ሽኩቻና መናቆር መምጣቱ ይቀራል?
ከዓመት በፊት በተካሄደው ሌላ የምክክር ሙከራ ላይ እንዳየነው፤  “ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ያሳተፈ አካታች ምክክር” ተብሎ ሲጀመር ችግር የሚያመጣ አይመስልም። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ፣ ሰዎች በጎራ ወደ ማቧደን ይንሸራተታል። ወደ ጅምላ ፍረጃ ይወርዳል፡፤ ሃሳቦች ለዘር ወይም ለጾታና ለእድሜ በኮታ የሚከፋፈሉ ይመስል።
“የምሁራን ወገን ምን ይላል? የሃይማኖት ወገንስ ምን ወሰነ? የወጣቶች ወገን አቋምስ ምንድነው? የሴቶች ወገን ሃሳብስ ምን ሆነ? ወደ ሚል ጭፍን ፍረጃና ወደ መጥፎ ስህተት መንሸራተት፤ በጣም ቀላል ነው።
ጭፍን የጅምላ ፍረጃ፣ ከመሰረታዊ ችግሮች መካከል አንዱ እንደሆነ መገንዘብና አስቀድሞ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
በጅምላ መፈረጅ፣ በጭፍን መቧደንን ያስከትላል። በሌላ አነጋገር፤ መግባባት ከመፍጠር ይልቅ፤ ቅራኔን ያባብሳል።  ከወዲሁ በጥንቃቄ ካልተስተካከለ፤ ማለቴ ነው።
ከዚህ አንጻር፤ የምክክር አዋጁ፤ የአደገኛ ስህተቶች ወጥመድ ውስጥ ላለመግባባት የጥንቃቄ አዝማሚያ የሚታይበት ቢሆንም፤ የተሟላ አይደለም። ይቀረዋል። ተጨማሪ ጥንቃቄዎች ያስፈልጉታል- ከተቻለ፤ ህጉን በማሻሻል፣ ካልሆነም፣ አዋጁን ተከትለው በሚመጡ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ።
የምክክር ተሳታፊዎች፤ በእድሜ እና በፆታ፣ በትውልድ ቦታና በመኖሪያ አድራሻ፣ በኑሮ ደረጃና በመተዳደሪያ ሙያ፣ በብሔረሰብ ተወላጅነትና በሃይማኖት ተከታይነት፣… ብዙ ገፅታ ይኖራቸዋል። ጥሩ ነው። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ የምክክር ተሳታፊ፣ እገሌን ብሔረሰብ ወይም እከሌን ሃይማኖት የሚወክል ሃሳብ ሊናገር አይችልም።
“የክርስትያን የፖለቲካ ሃሳብ”፣ “የሙስሊሞች የፖለቲካ ሃሳብ” የሚባል ሃሳብ የለም።” የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ሃሳብ ይሄውና” ብሎ የሚናገር ሰው ቢገጥማችሁ አስቡት። የትም አገር በየትኛውም ዘመን እንደዚህ አይነት፣ “የጋርዮሽ ጠቅላይ ገዢ ሃሳብ” ኖሮ አያውቅም፤ ሊኖርም አይችልም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮማ፣ “ምክክር” እና “መግባባት” የሚሉ ቃላት ትርጉም አይኖራቸውም።
“ሰዎች፤ በየግላቸው ማሰብ የማይችሉና ሃሳብ የማይጨብጡ፤ የአንድ ዛፍ ቅጠሎች ናቸው” ካልተባለ በቀር፤ “የወጣቶች ወገን ሃሳብ” ብሎ ነገር የለም።
“ከማዕከላዊ የጋርዮሽ ጣቢያ” የሚተላለፍላቸውን “የጋርዮሽ ሃሳብ” እየተቀበሉ የሚያስተጋቡ ድምፅ ማጉያ መሳሪያዎች አይደሉም-ሰዎች።
የሃሳብ መመሳሰልና መስማማት ይኖራል፤ የሃሳብ ልዩነትና አለመግባባትም ይኖራል- ሁሌም፣ በሁሉም ቦታና በሁሉም ጉዳይ።
አንዱ ወጣት የተናገረው ሃሳብ፣ ብዙ ወጣቶች የሚስማሙበት ሊሆን ይችላል። የሌላ ወጣት ሃሳብ ደግሞ፣ ጥቂት ወጣቶች ብቻ የሚስማሙበት ይሆናል። ከዓመት በኋላ ደግሞ፣ሀሳቡን ሊቀይር ይችላል። እሱ ወደተወው ሃሳብ የሚያዘነብሉ ወጣቶችም ይበዙ ይሆናል።
ሰዎች፣ የግል አእምሯቸውን መጠቀምና ማሳብ፣ ማገናዘብና ማመዛዘን፣ ሀሳብ መጨበጥና ሀሳብ መለወጥ ይችላሉ። በግል ማሰብ ካልቻሉስ?
ካልቻሉማ፣ ምክክር ምን ያደርጋል?
እያንዳንዱ ሰው “የጋርዮሽ ሃሳብ እስረኛ”፣ “የአከሊት ወገን ፎቶ ኮፒ”፣
“የእከሌ ወገን አሻራ”፣
 “የእገሊት ወገን ልሳን”፣
 “የእገሌ ወገን በቀቀን” ከሆነ ፣… የመመካከር አቅም አይኖረውም። በግል ማሰብ የማይችል ፍጡር መመካከር አይችልም።
 ሌላው ቀርቶ፣ ለአቅመ ሃሳብ ያልደረሰ ህጻን፣ ራሱን የሳተ ሰው፣ በስካር የዞረበት ጎልማሳ፣ እንቅልፍ የወሰደው አዋቂ እንኳ፣ ለጊዜው የመመካር አቅም አይኖራቸውም። ለምን? ለጊዜው፣ የአእምሮ አቅማቸውን በአግባቡ መጠቀም አይችሉም። የግል አእምሮ እንጂ ሌላ የማወቂያና የማሰቢያ መሳሪያ የላቸውም።
የምክክር ስረ መሰረት የግል አእምሮ ነው።
“የዚህ ወይም የዚያ ወገን” የመሆን ጉዳይ አይደለም። በግል የማሰብ አቅምን የመጠቀምና ያለመጠቀም ጉዳይ ነው።
በአጭሩ፤ ችግሮችን ለመፍታትና መፍትሄዎችን ለማፈላለግ የታሰበ ጥረት፣ ችግር ፈጣሪ እንዳይሆን እንጠንቀቅ ለማለት ነው።
“የመግባባት ምክክር”፣ መግባባትን የሚያመክን እንዳይሆን፣ “የእገሌ ወገን፣ የእገሊት ጎራ፣ የእከሌና የእከሊት ተወካይ” ከሚሉ የጅምላ ፍጃዎች፣ 40 ክንድ ሳይሆን 40 ምዕራፍ መራቅ ይኖርብናል።
ጠቃሚ መረጃዎችንና ሃሳቦችን ማበርከት የሚችል ማንኛውም  የሰው አይነት ሁሉ፣ በብቃቱ ልክ ይሳተፍ። መፍትሄ የመፍጠር ብቃት ያለው ሰው፤ ወጣት ይሁን ጎልማሳ፣ ወንድ ይሁን ሴት፣ የመሃል አገርም ሆነ የዳር አገር ኗሪ፣ የዚህም ሆነ የዚያ አካባቢ፣ የእገሌ ብሔረሰብም ሆነ የእገሊት ብሔር ተወላጅ፣ የእንትን ሃይማኖት አማኝም ሆነ ተከታይ፣… ቁምነገሩን በግል ይናገር። መረጃዎቿን በግል ታቅርብ። እሷም ሆነች እሱ፣ሃሳባቸውን ያስረዱ።
መረጃው እውነት ነው? መረጃዋ እውነት ነው? ቁምነገር ላይ ያተኮረ ነው? የተሟላ ነው?... በዚህ መንገድ ንግግራቸውን እንመዝነው።
ሃሳቧ ትክክል ነው? ሃሳቡ ፋይዳ አለው? የሚያዋጣና የሚያዛልቅ የመፍትሄ መርህ ይሆናል?... በዚህ መንገድ ሃሳባቸውን እንዳኘው። ተሳታፊዎች ሁሉ፣  በዚህ መንገድ ብቻ በግል እንድንመዝናቸው ይፍቀዱ።
“የብሔረሰብ ወይም የሃይማኖት ተወካይ ነኝ “በማለት፤ ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ጎራ በጅምላ ሊቧደኑን፣ ለጭፍን ድጋፍና ለጭፍን ተቃውሞ በመንጋ ሊያንጋጉን አይሞክሩ። አለበለዚያ፣ ምክክር፣ መፍትሄን ሳይሆን መከራ ያመጣብናል።
በጭፍን የመቧደን በሽታን ለመፈወስ ፍቱን መድሃት እንደማበጀት፣ በተቃራኒው በሽታውን የሚያባብሱና የሚያግለበልቡ ድግሶች መሆን የለባቸውም፤ የምክክር ስብሰባዎች።
በሃይማኖት ተከታይነት ወይም በዘር በተወላጅነት የመቧደን ጭፍንነትን ለመከላከል የሚመኙ ሰዎች፤ “ወጣቶች”፣ “ሴቶች”፣ “አካል ጉዳተኞች” የሚሉ የጅምላ ፍረጃዎችን ግን በይሁንታ ይቀበላሉ። አላዋቂነት ነው ወይም ጥንቃቄ የጎደለው አስተሳሰብ።
“የወጣቶች ሃሳብ”፣ “የሴቶች ወገን ሃሳብ”፣… “የዚህኛው ወይም የዚያኛው ማህበረሰብ ክፍል ሃሳብ” ብለን ስንፈርጅ፣ ጭፍን የጋርዮሽ አስተሰሳሰብን እያስተጋባን መሆናችንን መገንዘብ አለብን። ዘረኝነትም ከዚህ የተለየ አይደለም።
ሀሳብ፣ የጋርዮሽ ከሆነ፤ የኦሮሞ ሃሳብ፣ የአማራ ሃሳብ፣ የትግራይ ሃሳብ፣ የሶማሌ ሃሳብ፣… እያለ ዘረኝነትን ቢሰብከን፣… አማራጭ ሃሳብ የማቅረብ፣ ዘረኝነትንም የመከላከል አቅም አይኖረንም።
በጅምላ የሚፈረጅ የጋርዮሽ አስተሳሰብ (Collectrism) ይዘን፣ በጅምላ እየፈረጀ በመንጋ የሚያቧድን ዘረኝነት ጥፋትን መከላከል አንችልም። ይልቅስ  ለዘረንነት ጥፋት እንመቻቻለን።
የእንትን እምነት ተከታይ፣ እያለ ለሚያቧድን የሃይማኖት ፖለቲካም እንጋለጣለን።
“ሃብታምና ድሃ” እያሉ በመንጋ ለሚያቧድኑ፣ የዝርፊያ ሽሚያን ወይም የምቀኝነት ውድመትን ለሚደግሱ ክፉ ሰዎች እንንበረከካለን።
ሁሉንም አይነት የጅምላ ፍረጃ፣ በሁሉም ገጽታው ስንከላከል፣ ጭፍን የጋርዮሽ አስተሳሰብን እርም ብለን ስንተው፤ ያኔ ነው፣ የዘረኝነት ጥፋቶችን የመግታት አቅም የሚኖረን።
“የአካል ጉዳተኞች ሃሳብ”፣ “የከተሜዎች ሃሳብ”፣ የሴቶች፣ የገበሬዎች፣ የነጋዴዎች፣ የሸማቾች ሃሳብ… “የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳብ”… እያልን የጅምላ ፍረጃን የምናስፋፋ ከሆነ ግን፣… እስካሁን እንዳየነው አሳዛኝ ጥፋቶችን መከላከል ያቅተናል።
በተለይ ደግሞ፣… ኦሮሞና አማራ፣ ክርስቲያንና ሙስሊም፣ እንትን ሃይማኖትና እንቶኔ ብሔረሰብ፣ መጤና ነባር፣ ሃብታምና ደሃ፣ እያሉ በጭፍን ለሚያቧድኑ የጥፋት አዝማቾች እንመቻቸዋለን።
ለዚህም ነው፤ “የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳብ” እና “የሕብረተሰብ ክፍል ተወካይ” የሚሉ አገላለጾች ላይ በብርቱ መጠንቀቅ የሚገባን።


               3. መሰረታዊ አገራዊ ጉዳች ላይ መመካከር፣ ወይስ የልዩነቶች መንስኤ ላይ መወነጃጀል?


          በጥበብና በአስተዋይነት የሚያራምድ ጥንቁቅ አስተሳሰብ ባይርቀን ኖሮ፤ “የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽን”፣ “የምክክር ኮሚሽን” የሚሉ ጣጣዎች ባላስፈለጉን ነበር። ስህተቶችን በጊዜው ማረም፣ ችግሮችን ከስር ከስር ማስተካከል አያቅተንም ነበር።
የጥበብና የጥንቃቄ አስተሳሰብን አፅንተው የጨበጡ ሰዎች እስካልተመናመኑ ድረስ፣ መፍትሄ አይጠፋም፤ ችግሮች አይበዙም፤ አይከማቹም።
ችግሮች ቢከማቹም፤እንኳ ቀስ በቀስ ይቃለላሉ። ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮርና በማስተዋል፤ በማገናዘብና በማወቅ፣ የማስተካከያ ሃሳብ በመቅረጽና የተቃና መንገድ በመቀየስ፣… ይህንንም በመመካከርና በመተጋገዝ፣ ስር የሰደዱ ችግሮችን ማቃለልና ማስወገድ ይቻላል። ይቻል ነበር።
የጥበብና ጥንቃቄ አስተሳሰብ ካልጎደለን በቀር፣ “ምክክር” ተብሎ የተጀመረ ሃሳብ፣ የክርክርና የንትርክ፣ የውዝግብና የውግዘት፣ የውንጀላና የዛቻ ግርግር እንዳይሆን አያሰጋም ነበር።
አሁን ግን በጣም ያሰፈጋል።
ጥበበኛና ጥንቁቅ አስተሳሰብ ለምልክት ያህል እንኳ የጠፋበት ዘመን ላይ ነው የምንኖረው።
ተናጋሪዎች በቀላሉ ነው ነገረኞች የሚሆኑት። ጊዜ አይጅባቸውም። ሰበብ ካገኙማ፣ ማን ይመልሳቸዋል።ሰበብ ባይኖር እንኳ፣ እልፍ ሰበብ የሚፈጥሩ ሞልተዋል። ለዚህም ነው፤ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው።
በአስተማማኝ የስክነት ዘመን ላይ፣ ቶሎ ቶሎ መራመድ፣ ለአደጋ አያጋልጥም። ብዙ አያሰጋም። ትንሽ ጥንቃቄ በቂ ነው።
በቀውጢ የስካር እና የቅዠት ዘመን ላይ ግን፣ በጣም በጣም መጠንቀቅ ነው የሚያዋጣው። ጥቃቅን የሚመስሉ ሰበቦች ሁሉ፤ በምን ፍጥነት እየተግለበለቡ እንደሚዛመቱ፣ የቱን ያህል አገሬውን እንደሚያናውጡ ለመገመት ያስቸግራል- በተሳከረ ዘመን።
ሳይታሰብ፣ ነገሩ ሁሉ ከቁጥጥር ውጭ ይጦዛል።
“መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መመካከር”፤ “አገራዊ መግባባትን መፍጠር”፣ ተብሎ የተጀመረውን ሃሳብ ተመልከቱ።
በጎ ጎኖቹን ለማየት አያስቸግርም።
ትኩረትን ሰብሰብ ለማድረግ ይረዳል- “መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች” በማለት ማዕቀፉን ወይም ወሰኑን አበጅቷልና።
አላማውንም ይገልጻል- “አገራዊ መግባባትን መፍጠር” በማለት።
መንገዱን ወይም ዘዴውንም ጠቅሷል - “ምክክር” በማለት። በእርግጥም…
1ኛ፣ በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ፣
2ኛ፣ ትክክለኛ ሃሳቦችና የማስተካከያ መፍትሄዎች የሚቀርቡበት የምክክር መሰናዶ በማዘጋጀት፤
3ኛ፣ የመማማርና የመግባባት እድልን ማስፋት፣… ይቻላል።
ታዲያ፣ “ይቻላል” ማለት፣ ነገሩ አልጋ በአልጋ ይሆናል ማለት አይደለም። ትክክለኛ ሃሳቦችና ማስተካከያ መፍትሄዎች፤ እንደ ልብ አይገኙም።
“ሞልተዋል”፤ “የስብሰባ አዳራሽ ስለጠፋ እንጂ፣ የምክክር ኮሚሽን ስላተቋቋመ እንጂ፣ አካታች መድረክ ስላልተዘጋጀ እንጂ፣ ትክክለኛ ሃሳቦችና መፍትሄዎችማ ሞልተው ተርፈው”… የሚሉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።
ነገሩ እንደዚህ ቀላል መስሎ የሚታየን ከሆነ፤ የችግሩን ክብደት ገና፣ አልተረዳነውም ማለት ነው። ፅኑ የአስተሳሰብ ድህነት ተንሰራፍቷል። ከኑሮ ድህነትም ይብሳል ፈተናው።
የትክክለኛ ሃሳቦች እጦት፣ ከባድ ፈተና ነው።
የኑሮ ድህነትን በማስተባበያ ማስወገድ አይቻልም። የአስተሳሰብ እጥረትም እንደዚያው ነው። በአዳራሽ እጥረት የሚመካኝ አይደለም።
“የስንዴና የዘይት እጥረት የለም። የክምችትና የአቅርቦት እጥረት ሳይሆን የስርጭት ጉድለት ነው ችግሩ”… ይህን ማስተባበያ ከዓመት ዓመት መናገር፣ ቅንጣት መፍትሄ እንደማያመጣልን፣ በተግባር ያየነው አለምክንያት አይደለም።
ስር የሰደደ ድህነት፣ በሰፊው የተንሰራፋበት አገር ውስጥ ሆነን፣ “የምርት እጥረት የለም፤ ችግራችን የስርጭት ጉድለት ብቻ ነው” ብንል፣ እንዴት አሳማኝ ሊሆን ይችላል?
አሳማኝ ከመሰለን፣ መፍትሄ የማግኘት፣ ተስፋ የለንም። ምርትን የማሳደግና ኑሮን የማሻሻል እድል አይኖረንም።
የማጓጓዝ ብቻ ሳይሆን የማምረት እጦት ነውና- ዋናው የኑሮ ድህነት።
የሃሳብና የእውቀት ችግርም እንዲሁ፤ የመድረክና የአዳራሽ እጦት ብቻ ሳይሆን፤ የትክክለኛ ሃሳብ እጦትንና እጥረትንም ያጠቃልላል።
የእውቀትና የሃሳብ ድህነት፣ የአስተሳሰብና የመርህ እርዛት ነው ዋናው ችግር።
እናም፤ በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መመካከርና መግባባት፣ ቀላል ስራ አይሆንም፤ አልጋ ባልጋ አይደለም። ከፍተኛ ጽናትንና ጥረትን ይጠይቃል-በተለይ ትክክለኛ ሃሳቦችንና መፍትሄዎችን የመጨበጥ ብርቱ ጥረት።
ይህን ከባድ ስራ፤ አቅልለን ስናየውና ስናወሳስበው ደግሞ ተመልከቱ።
የሃሳቦች ልዩነት ላይ ሳይሆን፣ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ማተኮር፣ ያዋጣል።
“በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ የሃሳብ ልዩነቶችን ለማርገብና አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፤ ምክክር ይደረግ” ብንል እንጀምር። ከዚያስ ምን ይከተላል?
“የሃሳብ ልዩነቶችን ለማርገብ”፣ … ያው፤ በቅድሚያ፣ የተካረሩ የሃሳብ ልዩነቶችን ሰብስበንና አጉልተን ማሳየት ይኖርብናል።  የሃሳብ ልዩነቶችን መዘርዘር፣ መተንተን፣ የአንዱን ሃሳብ ድክመት እየቀነሱ መጥቀስ፣ የሌላኛውን ሃሳብ ጥንካሬ እየለዩ ማጉላት፣ አንዱን ከሌላው ጋር ማነጻጸር፣ ከተመሳሳይነታቸው ይልቅ ልዩነታቸውን፣ ከተቀራራቢነታቸው ይልቅ ርቀታቸውን ማሳየት የግድ ይሆናል።
መለያየታቸውንና መራራቃቸውን አጉልን፣ አለመግባባታቸውን አድምቀን ካላሳየን በስተቀር፣መቀራረብና መግባባት የማይኖር ይመስለናል። እዚህ ላይ ነው ጥያቄው።
“ልዩነት፣ መራራቅ፣ አለመግባባት ገንኖ የሚታይበትና የሚተነተንበት መድረክ” አይሆንም ወይ ምክክሩ?”
“የእገሌ የሃሳብ ልዩነት፣ አላግባብ የትችት ኢላማ ሆኗል።”
ምክክሩ “የእገሊትን ሃሳብ ለማቆንጀት የሚያገለግል መሳሪያ ነው።”
“የእከሊት ፓርቲ፣ የእንትን ድርጅት፣ የእንቶኔ ማህበር መጠቀሚያ ነው።”... የሚሉ ውዝግቦችስ አይበረቱም? የሚያግባቡ ትክክለኛ ሃሳቦች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ የሚያለያዩ ሃሳቦች ላይ መንዛዛት ከበዛ፣ መነዛነዝና መነጫነጭ፣ መጨቃጨቅና መናቆር መበራከቱ አይቀርም።
ለዚህም ነው፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው።
የሃሳብ ልዩነቶችን እየመዘዙ በዚያው ተተብትቦ ላለመቅረት፤ የመፍትሄ ሃሳችና መርሆች ላይ ማተኮር ይበጃል። “የሃሳብ ልዩነቶች እና መሰረታዊ መንስኤያቸው” ላይ ያተኮሩ አንቀጾች፣ የውዝግብ ማቀጣጠያ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
ከሃሳብ ልዩነትም ተሻግሮ፣ “እነ እገሌ ናቸው የልዩነት መንስዔ”፣ “እነ እከሊት ናቸው የልዩነት መነሻ”፤ “የድሮ ታሪክ ነው ሰበቡ”፤ “ቅራኔ የአዳም ተፈጥሮ መሆኑ ነው የልዩነት መንስኤ” እያልን እንዳንሳከር እንጠንቀቅ።

Read 2523 times