Saturday, 29 January 2022 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የማዘጋጃ ቤቱ ጉዳይ....
                                      መላኩ ብርሃኑ

            የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በእውነቱ ዋይት ሃውስ መስሏል...
በበኩሌ የመስሪያ ቤቶች ቢሮ ‘ሪኢኖቬሽን’ እቅድና ትግበራን ጉዳይ የምቃወመው ሃሳብ አይደለም። ሰራተኛም ምቹ ስፍራ ተገልጋይም የሚያምር ከባቢ አይጠላበትም። በአሮጌ ቢሮና፣ በሚሸት ኮሪደር፣ በሚንቋቋ ወንበር፣ በአቧራ በተሸፈነ ጠረጴዛ ላይ ከተቀመጠ ሰራተኛ ስታንዳርድ አገልግሎት መጠበቅ አይቻልም።
በተለይም ከቀደመው እጅግ የተዝረከረከና ለእይታ ሳቢ ያልሆነ የመንግስት ቢሮ አወቃቀር አንጻር ሲታይ፣ የተጀመረው ስራ መልካም ነው ባይ ነኝ። እዚህ ላይ በ ‘ሪኢኖቬሽን’ ሰበብ ለግዢ ሂደት መጭበርበርና ለግለሰቦች ኪስ መዳበር የሚረዱ የሙስና በሮች እየሰፉ ስላለመሆኑ ማረጋገጫ የለኝም።
በተረፈ ዋናው ችግር ያለው ‘ፕራዮሪቲ’ በምንለው ነገር ላይ ነው። ቅድሚያ...የቅድሚያ ቅድሚያ በሚባለው ነገር ላይ።
እነዚህ የመንግስት ህንጻዎች የሚወጣባቸው ከፍተኛ ገንዘብ አሁን ካለብን የኢኮኖሚ ማነቆና ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት፣ እንዲሁም ግዙፍ መዋዕለንዋይ ከሚጠይቁ የድህረ ጦርነት ውድመት ጥገናዎች አንጻር ሲታይ የመስሪያ ቤቶችን ቢሮ የማስዋብ ስራዎች ‘አንገብጋቢ ናቸው ወይ?’ የሚለው ጥያቄ የሁሉም ነው።
ጠቅላዩ ከዚህ ቀደም ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ የቢሮዎች ‘ሪኢኖቬሽን’ ወጪ ከመንግስት ባጀት የሚመደብ ሳይሆን መስሪያ ቤቶች ባለሃብቶችንና ተቋማትን በማስተባበር (በቀላል አማርኛ በመለመን) በሚገኝ ገንዘብ የሚሰራ መሆን አለበት።
በርግጥ ይህ ሁሉ ገንዘብ በድጋፍ የተገኘ ስለመሆኑ ግን እርግጠኛ አይደለሁም። ከሆነም ነገ በውለታ ሰበብ የ‘እከክልኝ ልከክልህን’ አጓጉል አሰራር ይዞ መምጣቱ አይቀርም።
የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የተገነባባቸው ማቴሪያሎችና የቢሮ እቃዎች በቅርብ እንዳየኋቸው በቀጥታ ከውጭ ሃገር ‘ኢምፖርት’ የተደረጉ ናቸው። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ የወጣበት መሆኑ ማሳያ ነው። አሁን የዶላር ካዝናችን (እድሜ ለዳያስፖራው ርብርብ እንጂ) ኦልሞስት የተሟጠጠ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር ሲነገርም ሰምተናል። እና በዚህ ዶላር ወደ ሃገር ውስጥ መግባት የሚገባቸው አንገብጋቢ የህክምና ቁሳቁሶች፣ መድሃኒቶች፣ የምግብ ምርቶች፣ ነዳጅ ወዘተ እያሉ ይህ የቢሮ እቃ ‘ኢምፖርት’ የማድረግ ስራ ቀዳሚ መሆን ነበረበት ወይ? እላለሁ።
በተረፈ ከተማ ቢያምር የሚጠላ የለም... አይናችን ውብ ነገር ቢያይ፣ ያው ሃብቱ የራሳችን ነውና ደስ ይለናል እንጂ አንቃወምም...በተለይ እኔ በግሌ ባየሁት ሁሉ ደስተኛ ነኝ። ይህንን ላሰቡም ለሰሩም ምስጋና አለኝ።
ከዜናው በኋላ ግን ግንባታውን ሳይሆን ወጪውን ይዘው ያጉረመረሙ ዜጎች ላይ “ለምን ልማት ተሰራ እያላችሁ ታላዝናላችሁ?” የሚሉ የአንዳንድ አጓጉል ካድሬ ድምጾችን እየሰማሁ ነው። “ቅድሚያ ለሚያስፈልገው ጉዳይ ቅድሚያ ይሰጠው” ማለት ልማትን መቃወም አይደለም። ስራው አይጠቅምም ብክነት ነው ያለ የለም። መጠየቅን ያልለመዱ ሰዎች፣ ሰው ሲጠይቅ ባይበሳጩ ለጤንነታቸው ይጠቅማቸዋል።
ማዘጋጆች ሆይ!
ልክ እንደ ቢሮና ግንቡ አገልግሎቱም በዚሁ መጠን ህዝብን የሚያረካና የህዝብ እንባን የሚያስቀር ሲሆን ደግሞ ‘ማች’ ያደርጋልና ይህንንም አስቡበት።
(በመጨረሻም ...እዚህች አዲስ አበባ ካርታ ውስጥ ሌላው ሁሉ ሲጻፍ ሰፈሬ ‘ኦሎምፒያ’ ያልተጻፈበት ምክንያት ግን ምንድነው ብዬ ጓ ልበል እንዴ? አዲስ አበቦች አይደላችሁም ካላችሁን ...የራሳችንን ዕድል በራሳችን እንወስን እንዴ?....ቂቂቂቂቂቂ)

_________________________________________

                              ይህን ታውቃላችሁን?
                                     አበበ ሃረገወይን

               የመጀመሪያው የአማርኛ የሕክምና መጽሐፍ!
በእምዬ ምኒልክ ዘመነ መንግስት፣ የሩሲያ መንግስት በእርዳታ መልክ የጤና ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜዎች አበርክታለች። በተለይም ከአድዋ ድል ስድስት ወር በኋላ በርከት ያሉ ሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች በሐረር በኩል ገብተው መጀመሪያ የሩሲያ ሆስፒታል በኋላ ደሞ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የተባለውን መስርተዋል።
ሩሲያኖች በሐይማኖት ምስስልነት እርዳታ ለማድረግ እንጂ እንደ ሌሎች አውሮፓውያኖች የቅኝ ወይም የተለየ ጥቅም ለማግኘት ፍላጎት እንደሌላቸው ተመስክሮላቸዋል። ሩሲያኖቹ የጤና ባለሙያዎች ኢትዮጵያውያንን የሕክምና ስራ ለማስተማር በዚያን ዘመን የመጀመሪያውን የአማርኛ የሕክምና መጽሐፍ አሳትመው ነበር። ነገር ግን ደራሲውና ያጻጻፉ ሁኔታ እንዴት እንደነበር ፍንጭ አልተገኘም። በተጨማሪም የመጽሐፉ ኮፒ ይኑር አይኑር አይታወቅም።
አንባቢያን አዲስ አበባ ወመዘክር ወይም ሌላ ምንጭ ካለ፣ ስለዚህ መጽሐፍ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን እንማጠናለን።

___________________________________________

                           ፊት አልቦነት እና ባዶነት

                  (መልክ አልቦነት ወይም ምሳሌ አልቦነት)
                           ፉዣዥ

             ከታች ያለውን ልብወለድ ወይም የቢሆንስ ብለህ ልታነበው ትችላለህ።
እግዚአብሄር እንደ ሁሉም ነው። አንተ ደግሞ እስካሁን እንደ አንዱ ነህ። እንደ አንዱ ሆነህ እግዜር ጋር አትቀርብም። መንፈሳዊ መቀራረብ የባህሪ መቀራረብን ይጠይቃልና። መንገዱ አንድ ብቻ ነው። እንደ አንዱ መሆንህን መተው። ባዶ መሆን። የዛኔ ትቀርባለህ። ስትመለስ እስካሁን የነበረውን አንድነትህን በምስጋና አስረክበህ፣ የምትፈቅደውን ደስ የሚያሰኝህን አዲስ አንድነት ተቀብለህ ትመለሳለህ።
የፈለከውን ለመሆን እስካሁን ከሆንከው ነፃ መውጣት አለብህ። ጫማህን ማውለቅ አለብህ፣ ወደ እግዚአብሄር ለመቅረብ። ፊት አልባ መሆን አለብህ። #ጌም ኦፍ ትሮንስ;ን አስታወስከው።
ከዚህ ቀደም የኢንፊኒቲንና የዜሮን ዝምድና አንስቼ ፅፌ ነበር። ስለሚደንቀኝ።
ማንኛውም ቁጥር ላይ በፈለግኸው ፍጥነት እየደመርክና እያባዛህ ብትሄድ ኢንፊኒቲ ላይ ለመድረስ የሚቀርህ (በማንኛውም ጊዜ) ኢንፊኒቲ ጊዜ ነው። ራሱ ኢንፊኒቲ መጥቶ ካልተባዛብህ ወይም ካልተደረብህ። ምንም ቁጥር ኢንፊኒቲ ላይ ተደምሮ ኢንፊኒቲን ሊለውጥ አይቻለውም። ራሱ ግን ኢንፊኒቲ ይሆናል። ኢንፊኒቲ ላይ ተደምሮ እንደነበረው ሆኖ የሚቀጥል የለም። ኢንፊኒቲ ላይ ምንም ያህል ቁጥር ቢቀነስ፣ ኢንፊኒቲ ቢቀነስ እንኳን፣ ኢንፊኒቲ ለኢንፊኒቲ ቢካፈል እንኳን፣ ኢንፊኒቲ አይጎድልበትም።
ኢንፊኒቲ ሙሉነት ነው። ወሰን የለሽ ሙሉነት። ዜሮ ደግሞ አለ። ባዶነት። ባዶነቱ ራሱ ወሰን የለሽ ነው። ከኢንፊኒቲ ጋር ያለው ዝምድና ወሰን የለሽ መሆናቸው ነው። ለዚህ ነው ሙሉነትና ባዶነት ዝምድና አላቸው የምልህ። በባዶነት፣ በመልክ አልቦነት ወደ ኢንፊኒቲ ቀርበን፣ የፈቀድነውን ያህል ተሞልተን መመለስ እንችላለን የምልህ።
የሙጥኝ በማለት፣ በመደመር ሳይሆን በመቀነስና በማካፈል ወደ ኢንፊኒቲ መጠጋት ይቻላል።
መልካም ሳምንት!

________________________________________

                         ስለ “አብርሆት ቤተ መጻሕፍት”

             “አብርሆት” የሚለው ስያሜ የተሰጠውን ቤተ መጻሕፍት በተጣበበ ጊዜም ቢሆን ጎበኘሁ። ኪነ ሕንፃን በአካል ቀርቦ ማየትና በፎቶ ወይም በተንቀሳቃሽ ፊልም መመልከት ልዩነቱ አራምባና ቆቦ ነው። በተለይም የ”አብርሆት” ትክክለኛው Scale...especially human & outer scale...የሚታወቀው በአካል ስንጎበኘው ብቻ ነው። That is the fascinating phenomenon in experiencing architecture...በአጠቃላይ በቤተ መጻሕፍቱ የዲዛይን መነሻ ሐሳብና የውስጥ ዲዛይን ደስተኛ ነኝ። የዕውቁ የቅርፅ ባለሙያው በቀለ መኮንን(ረ/ፕሮፈሰር) ሥራም ምርጥ የሚባልና ለትንታኔ የራሱን ጊዜ፣ አቅምና ንባብ የሚጠይቅ ነው። ያም ሆኖ ለዛሬው ስለ ቤተ መጻሕፍቱ ያጤንኩትን አራት ነጥቦች ላንሳ፦
1. የውጪ የኮንክሪት ሥራ አጨራረስ እክል
በቤተ መጻሕፍቱ መፀነስና በአጠቃላይ ኪነ ሕንፃዊ ገፅታ ደስተኛ ብሆንም በውጪ በኩል በተለይም በኮንክሪት ሥራ አጨራረስ መከፋቴን ግን አልደብቅም። ፈፅሞ ይህን ድንቅ ቤተ መጻሕፍት የሚመጥን አይደለም። የኮንክሪት አጨራረሱ ያው በፓኔል ቅርፁ ላይ እንዲቆም የተፈለገ ይመስላል፤ የተፈጥሮ ገፅታ እንዲኖረው ተፈልጎ እንደሆነም አልጠፋኝም። “Concrete finish” በግንባታ አጨራረስ የተለመደ እንደሆነም አልዘነጋሁም። The point is that concrete finish has its own level of refinement. በብረት ፓኔሉ ቅርፅና መገጣጠሚያው ላይ ንፁሕ መስመሮች ካልታዩ ለሕንፃው የአለማለቅን ስሜት (A sense of unintentional unfinished look) ይፈጥራል..That is the schema behind unrefined concrete finish... ()
ከፊት ለፊት፣ በግራና በስተቀኝ ያለው የኮንክሪት ሥራው ለምን በዚህ ሁኔታ ሊያልቅ እንደቻለ የራሴ ግምቶች ነበሩኝ፣ የመጀመሪያው ሕንፃው ለምርቃት እንዲደርስ (ምናልባት ለዲያስፖራው ሲባል) ትንሽ የመቻኮል ሁኔታ ይኖር ይሆንን? የሚል ግምት ነበር። ሁለተኛው ግምቴ ምናልባትም ሆን ተብሎ ባለበት ሁኔታ እንዲያልቅ ተወስኖ ይሆን? የሚል ነው። ከሥራው ጋር ግንኙነት ያላቸውን ባለሙያዎች ጠይቄ ያገኘሁት ምላሽ ወደ ሁለቱም ግምቶቼ ያዘነበለ ነው። በጉብኝቴ ወቅት ያገኘዃቸው የኮንትራክተሩ ድርጅት ባለሙያ “ሕንፃው በዚሁ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ተፈልጎ ነው” ብለውኛል። በተቃራኒው ደግሞ የሕንፃው የኮንክሪት ሥራ እንዳላለቀ እና የፊኒሽንግ ሥራ እንደሚቀረውም መረጃው አለ። ምክንያቱ ይህ ከሆነ ቀሪው ሥራ በአፋጣኝ መሰራት አለበት፤ በኮንስትራክሽን ሥራ እንደዚህ በይደር የሚቆዩ ሥራዎች ጊዜው እየገፋ በሄደ ቁጥር ከነአካቴው ሳይጠናቀቁ እንደሚቀሩ የታወቀ ነው። የዚህ ፅሁፍ መልዕክትም የኮንክሪት የ”refinement” ሥራ ሕንፃውን በሚመጥን ደረጃ ያለ መጠናቀቁ ከጎብኚዎች ዓይን እንዳልተሰወረ የሚጠቁም ነው።
2. “አብርሆት ቤተ መጻሕፍት”ን የኳርትዝ ቀለም ይመጥነዋል?....ለዚያውም ወጥነት ጎድሎት የተዥጎረጎረ ቀለም!
ሌላው የተከፋሁት በአንዳንድ የሕንፃው አካል በተመረጠው በቴክስቸር ቀለም ነው፤ በአጭሩ ፋይን ኳርትዝ ነው የተቀባው። ይህ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በኮንዶሚኒየሞች ጭምር በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ቀለም ነው። አሰራሩም ቢሆን ጥንቅቅ ብሎ ያለቀ አይደለም። በዚህ ምትክ አሁን ገበያ ላይ ያሉ ለሕንፃው ተፈጥሮአዊ ገፅታን የበለጠ የሚያላብሱ አያሌ የቴክስቸር ቀለም ዓይነቶች አሉ። “አብርሆት”ን ኳርትዝ አልብሰውት እንዴት አልናደድ? ደግሞ ሌላም ጉድ አለ። የኳርትዙ ቀለም በአንድ ግድግዳ ላይ አንዳንዴ ሶስት ዓይነት ነው። ወጥ ከለር አይደለም። ይህ ለምን እንደሆነ ይገባኛል። የኳርትዝ የቀለሙ ዓይነት በአንድ ኮድ ሆኖ ሦስትና አራት ዓይነት ሊሆን ይችላል። በኳርትዝ ቀለም ምርት ወቅት ከአንድ ባች ምርት በኋላ ከለሩን ደግሞ ማመሳሰል ከባድ ነው። ስለዚህም አንድ ደንበኛ ኳርትዙ አንሶት የምርት ትዕዛዝ ለፋብሪካው ሲሰጥ በመጀመሪያው ኮድ የሚሰጠው ሌላ ዓይነት ከለር ነው። ለዚህም የኳርትዙ ጠጠር በየጊዜው ወጥ ያለመሆን በምክንያትነት ይጠቀሳል። በዚህ ምክንያት ለሚፈጠር ስህተት ብቸኛው መፍትሔ ቢያንስ ሁለት ቅብ የውሃ ቀለም ኳርትዙ ላይ ደርቦ ወጥ ከለር መቀባት ነው። መቼስ ከቡራቡሬነት ይሻላል።
3. “አብርሆት” ከሚለው ስያሜ ጋር በተገናኘ፦
አንዳንድ ፀሐፍት “አብርሆት” የሚለውን የቤተ መጻሕፍቱን  ስያሜ ከ17ኛውና 18ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓው የ“Enlightenment” ንቅናቄ ዘመን ጋር እያገናኙ ሲፅፉ ታዝቤአለሁ። እርግጥ ነው ያ ንቅናቄ በወቅቱ በርካታ አዎንታዊ እሴቶችን ለዓለም ማህበረሰብ አበርክቷል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ወቅቱ ቢያልፍም ከ”Age of Reason” ጋር በፍቅር የተሳሰሩ አያሌ ፀሐፍት ዛሬም ድረስ መኖራቸው እንግዳ ክስተት አይደለም። በእርግጥ የወቅቱ ንቅናቄ እንደወረደ ተቀባይነት እንዳለው የሚሞግቱ ጥቂት አሳቢያን ዛሬም ድረስ ቢኖሩም፣ በምክንያታዊነት(Reason) ላይ ብቻ የተመሠረተው የዚያ ዘመን የ “Enlightenment” ዕሳቤ በአብዛኞቹ ተመራማሪዎች ቅቡልነትን ካጣ ቢያንስ ወደ 60 ዓመታት አልፈዋል። ለምሣሌ የ17ኛውና 18ኛው ክ/ዘመን የ”Enlightenment” ዕሳቤ ስሜትን ከምክንያታዊነት አፋትቶ ነው የሚገነዘበው። ይህን በተመለከተም የ”Cognitive Science” ተመራማሪው አሜሪካዊዉ ጂዮርጅ ላኮፍ “The Poiltical Mind” መፅሐፉ ላይ የሚከተለውን ብሏል፦
“Take the old dichotomy between reason and emotion. The old view saw reason and emotion as opposites, with emotion getting in the way of reason. But Antonio Damasio showed in Descartes’ Error that this Enlightenment view is utterly mistaken. Instead, reason requires emotion. People with brain damage that makes them incapable of experiencing emotion or detecting it in others simply cannot function rationally. They cannot feel what decisions will make them—or anyone else—happy or unhappy, satisfied or anxious.”
ጂዮርጅ ላኮፍ “The Old View” እያለ የጠራው የአብርሆት (Enlightenment) ዘመንን ዕሳቤ መሆኑን አስምሩልኝ።
አሁን በኒውሮሎጂና በኮግኒቲቪ ሳይንስ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩን ከሆነ ስሜት ለምክንያታዊነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። እንደ J. G. A. Pocock ያሉ የታሪክ ምሁራን፣ ዘመነ አብርሆት በግልፅ የሚነገርለት የታሪክ መነሻ እንደሌለው ቢገልፁም፣ አብዛኞቹ የታሪክ ምሁራን የዘመነ አብርሆት ጭላንጭል ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው እ.ኤ.አ በ1685 ዓ.ም. እንደሆነ ያሰምራሉ...የዛሬ 336 ዓመት መሆኑ ነው። ስለዚህም የቤተ መፅሐፍቱን ስያሜ ከዚያ ወቅት ንቅናቄ ጋር ማገናኘት ከዚያ ወዲህ በ”Enlightenment” ዕሳቤ ላይ ለተሰነዘሩ ጠንካራ ሂሶችና ማስተካከያዎች ትኩረት እንደመንፈግ ይቆጠራል።
ስለዚህም ከቤተ መጻሐፍት ስያሜ ጋር በተገናኘ “አብርሆት” የሚለው ስያሜ መያያዝ ያለበት በቀጥታ ከመዝገበ ቃላት የቃሉ ትርጓሜ ጋር ነው፦ በእንግሊዝኛው “The state of having knowledge or understanding” ከሚለው። በእርግጥ “አብርሆት” የሚለውን ቃል አንጎላችን ወዲያው ከ”Age of Reason” ጋር ስለሚያቆራኘው ምናባችን ውስጥ የትርጓሜ ውዝግብ ቢፈጠርብን ሊፈረድብን ዘንድ አይገባም። በእኔ አተያይ ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች ስያሜዎች በሚመረጡበት ወቅት አሻሚ፣ አጨቃጫቂና ለአያሌ ትርጓሜዎች የሚጋለጡ ስሞች ምርጫ ውስጥ ባይገቡ እመርጣለሁ።
4. “አብርሆት”ንና ጥቁር “ቀለም”ን ምን አገናኛቸው?
በመንገዱ በኩል በአማርኛና በእንግሊዝኛ “አብርሆት ቤተ መጻሐፍት” የሚለው የሕንፃው ስያሜ፣ ለምን በጥቁር ቀለም እንደተፃፈ ሊገባኝ ስላልቻለ ተወዛግቤ ተመልሼአለሁ። “አብርሆት” እና ጥቁር ቀለም ግንኙነታቸው ምን ይሆን? ...”መሃይምነት የጨለማ ጉዞ ነው” ይባል የለ? እናም ከትምህርት ነክ አውድ ጋር በተገናኘ ጥቁር ቀለም ተቃራኒውን መልዕክት የሚያስተላልፍ መሰለኝ። በእኔ ምርጫ “አብርሆት ቤተ መጻሐፍት” የሚለው ስያሜው መፃፍ የነበረበት እዚያው በሕንፃው ላይ ጥቅም ላይ በዋለው በብርቱካናማ-ቢጫ ቀለም ነው። ችግሩ ያለው ከአጥሩ ኮንትራስት ጋር ከሆነም የብርቱካናማውን ቢጫ ባክግራውንድ ማስተካከል ያን ያህል አይከብድም ነበር። ለምሣሌ የብርቱካናማ-ቢጫ ፅሁፍ መደብ ጥቁር ማድረግ... ትርጉምም ይኖረዋል...ብርሃን ጨለማን አሸንፎ እንደሚወጣ ለመጠቆም! ደግሞም ከኮመንቶቹ ውስጥ በተሰጠኝ ማስተካከያ መሠረት፣ አጥሩ ላይ “ቤተ መፅሐፍት” ተብሎ የተፃፈው ትክክል እንዳልሆነ ተነግሮኛል። መባል ያለበት “ቤተ መጻሕፍት” ነው።
ለዛሬው ይብቃን።

Read 1488 times