Saturday, 29 January 2022 00:00

‘ያበጠ ከንፈር’ ፖለቲካ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ወዳጅነታቸው ጥብቅ ከመሆኑ የተነሳ እሱዬው ቤተሰብ አይነት ሆኗል፡፡ እዛ በመጣ ጊዜም እንደ እንግዳ ሳሎን ጭብጥብጥ ብሎ ተቀምጦ...አለ አይደል... “በጠራራ ፀሀይ እዚህ ድረስ መጥቼ እነኚህ ሰዎች ሻይ እንኳን አይሰጡኝም እንዴ! ምን አይነት ችጋራሞች ናቸው!” ምናምን እያሉ በሆድ መራገም የለም፡፡ ሰትት ብሎ...መኝታ ቤቱም፣ ኩሽናውም ብቻ ቤቱ ምኑም ሳይቀረው ዘው ማለት ነው፡፡  ፍሪጁን እንኳን የግሉ መጋዘን አይነት ነው የሚያደርገው፡፡ ብቻ ቤቱን ከባለቤቶቹ እኩል ይንሸራሸርበታል። እናላችሁ አንድ ቀን እንደለመደው ሲመጣ መጀመሪያ የተቀበለው የቤቱ አባወራ ጥያቄ ይሆናል፡፡
“ስማኝ መቼም አንተ ሁሉም ነገርህ ገና ፕሪሚቲቭ ነው...ግን ዛሬ ከነጋ ዩቲዩብ ገብተሀል?”
“አዎ፣ ምነው ጠየቅኸኝ?”
“ኢንተርቪውን አይተኸዋላ!”
“የምን ኢንተርቪው?”
“እነኛ ባለስልጣናቱ የሠጡትን ነዋ! እንደው የሚናገሩት ሁሉ ግርም አላለህም?”
እሱዬው የተባለውን ነገር የተወሰነውን አይቶት ስለነበር ለመናገር ይልና ድንገት ጸጥ ይላል፡፡ ታዲያላችሁ... ምን ሀሳብ ቢመጣበት ጥሩ ነው... “ሰውየው ሰልለው ተብሎ ተላከብኝ እንዴ! ይሄኔ ግርም ይለኛል ብለው ሄዶ አሳብቆ ድርግም ሊያስደርገኝ ነው!” (ኸረ እባክህ እኛ አቅም ኖሮን ባንሰማ የሚሰማ አንድዬ አለ! “ለአንተ ነፍሴን እሰጣለሁ!” ስትባባሉ የኖራችሁትን የክፉ ቀን ወዳጅህን በአንድ ጊዜ የዲያብሎስ ቀንድና ጭራ ትሰጠዋለህ እንዴ!)
እናላችሁ... ያለንበት ጊዜ የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ አሀ...ልክ ነዋ! ይሄ የጠቀስነው ሰው ቀደም ሲል አይደለም ስልጣን ላይ ያሉ ፖለቲከኞችን፣ ገና ሊሾሙ ይችላሉ ብሎ ያሰባቸውን ሳይቀር በቀብድ መልክ ልክ ልካቸውን መንገር የማይደክመው ነበር እኮ! (እኔ የምለው...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... በቀደም ጆ ባይደን አንዱን የፎክስ ጋዜጠኛ ጥያቄ ከጠየቃቸው በኋላ “ሰን ኦፍ ኤ ቢ...!” ያሉበትን ቪዲዮ አያችሁልኝማ! “የዓለም የሞራል ከፍታ ላይ ያለነው እኛ ነን...” የምትል ሀገር መሪ! ለነገሩ የእኛ ቦተሊከኞች አንዳንዴ አይበሽቁም ማለት አይደለም፡፡ እንክት አድርገው ይበሽቃሉ። ግን ደግሞ በሆድ ነዋ! በቃ...“ከየትም ተለቃቅመው እየመጡ...ምናምን ብለው ያጠጡናል እንጂ ካሜራ ተደቅኖ “ሰን ኦፍ ምናምን!” አትሞከርም፡፡ እንደ ዘንድሮ ነገረ ሥራችን ግን ይቺ ‘የስሌት ጨዋነት’ ምን ያህል እንደምትዘልቅ እሱ ይወቀው አንጂ፡፡
እናላችሁ...ስለ ቦተሊካ (በተለይ ስለ አንዳንድ ቦተሊከኞችና የቦተሊካ ቡድኖች)፣ ወይንም ‘የእንትን ሀገር ሰው ስለሆነ ሙዚቀኛ ምናምን የሚጠይቀን እንደ ቀድሞ “ዝም ብሎ ለጨዋታ ያህል ነው፣” የምንለው ነገር እየቀረ ነው፡፡
እናላችሁ...ምን ለማለት ነው፣ ጊዜው እኮ የፍሬንዶች ቁጥር በሆነ፣ ባልሆነው እየቀነሰ ያለበት ስለሆነ፣ እንዲሁ ለጨዋታ ያህል ብለን የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች፣ ለ‘ስፓዪንግ’ እንዳይመስሉብን ጠንቀቅ ይሻላል ለማለት ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ “ስትሄድ ውላ የተመለሰችውን...” እንትናዬ፣ “አንቺ! ከንፈርሽ ይህን ያህል ያበጠው ከሰው ተጣልተሽ ነከሱሽ ወይስ ንብ ነድፋሽ ነው!” ማለት እንዲሁ ለጨዋታ ያህል ነው ሊባል ይችላል፡፡ ግን “ነከሱሽ...” ማለትን ምን አመጣው!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ዘንድሮ ምን አይነት ነገር አለ መሰላችሁ...የፈለገውን ጉዳይ አንስታችሁ በፈለጋችሁት መንገድ መተርጎም ይቻላል፡፡ ዝም ብሎ ከንፈርሽ ያበጠው ምን ሆኖ ነው እንደማለት መንከስና ንብ ምን ቤት ናቸው፡፡ እሷዬዋም በሆዷ “በእሱ ቤት እኮ ብልጥ ሆኖ ከማን ጋር እንደዋልኩ ሊሰልልኝ ነው!” ብትል አይፈረድባትም፡፡ እመኑኝ...ለ‘ስለላ’ እንኳን ባይሆን ያበጠው ከንፈር ነገር ለቀናት ትኩስ የሴራ ትርክቶች መፈልፈያ ሆኖ ሊሰነብት ይችላል...እድሜ ለማህበራዊ ሚዲያ!
“ካበጠው ከንፈር ጀርባ ያለው ድብቅ ምስጢር ነው?”
“ስላበጠው ከንፈር ያልተነገሩ አሁን የደረሱን እውነቶች!"
“ካበጠው ከንፈር ጀርባ ስላለው ሴራ ከውስጥ አዋቂ ያገኘነው አስደንጋጭ መረጃ!”
“ያበጠው ከንፈር ፖለቲካዊ ጥልፍልፎሽ እስከ ዋሽንግተንና ብረስልስ ሊደርስ ይችላል ተባለ!”
እናላችሁ በራሱ ጊዜና በራሱ ምክንያት ያበጠ ከንፈር እንኳን ፖለቲካዊ አጀንዳ ሊሆን የሚችልበት ዘመን ላይ ነን ለማለት ያህል ነው፡፡
ታዲያላችሁ... ያበጠ ከንፈር ፖለቲካ...እንዳንተማመመን፣ ከአንድ ማዕድ እንዳንቆርስ እያደረገን ነው፡፡
የሆነ የምታውቁት ሰው በርቀት ታያላችሁ፡፡ አብራው ማንነቷ የማይለይ ነጠላ የተከናነበች ልጅ አለች፡፡ እናላችሁ...አብሯችሁ ያለው ሰው... “አንተ! አንተ! ያ እንትና አይደለም እንዴ?” ይላችኋል፡፡
“አዎ ነው፡፡”
“አብራው ያለችው ማነች?”
“በደንብ ስላላየኋት አላወቅኋትም፡፡”
“አጅሬው ጭራሽ እያከናነበ መውሰድ ጀመረ እንዴ!”
“አንተ ደግሞ ዝም ብለህ አትዘባርቅ! ዘመዱ ልትሆን ትችላለች፡፡”
“እኔ ዘመዶቹን ሁሉ አውቃቸዋለሁ፡፡”
“እና!...”
“ነጠላ የምትከናነብ ዘመድ የለችውማ!” (ቂ...ቂ...ቂ...)
እኔ የምለው ግን...ያቺ አምስት ለአንድ ነው እንደሱ አይነት የሚባለው ነገር አሁንም አለ እንዴ! አይ ነገርዬው ይወራበት ስለነበር ነው፡፡ ልክ ነዋ...የ"ሥራ ጉዳይ" ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተጨማሪ ዝርዝሮች አሉት ይባል ነበራ! “እከሊት የት ዋለች፣ የት አደረች?” “እከሌ ከእነማን ጋር ነው የሚያመሸው? የት፣ የት ቦታ ነው የሚዞሩት?” ምናምን ሁሉ ይባል ነበር ሲባል እንሰማ ነበራ!
እናላችሁ...ከብዙ ዓመታት ልምድ በኋላ፣ ይሆናሉ ብለን ያልገመትናቸው ነገሮች ስለበዙብን ትንሹንም፣ ትልቁንም ነገር እንጠረጥራለን፡፡ እናንተ  የጤፉ ማዳበሪያ (ዘንድሮ በጆንያ የቪ.አይ.ፒ ስለሆነ ነው!) ተራግፎ “ይቺን ሳምንትስ እሺ እንደምንም ብለን እናልፋታለን፡፡ የሚቀጥለው ሳምንትስ ቤተሰቤ ምን ሊቀምስ ነው?” እያላችሁ እንቅልፍ እያጣችሁ፣ ሌላ ጊዜ ታይቶ የማያውቅ የእኔ ቢጤ በቀን ሦስት ጊዜ እየተመላላሰ ሲለምን...አለ አይደል... “ይሄ ሊለምን የመጣ ሳይሆን ሰልላቸው ተብሎ ተልኮብን ነው፣” ብላችሁ ብትጠረጥሩ በቃ ‘ናቹራል’ ነው፡፡ ልክ ነዋ... በፊት ‘አንናቹራል’ የነበሩት ነገሮች ሁሉ የእለት በዕለት ነገሮች የሆኑበት ዘመን ላይ ደርሰናላ!
‘ያበጠ ከንፈር’ ፖለቲካ!
ለምሳሌ፣ እንበልና ከተገናኛችሁ ረዘም ያለ ጊዜ ካለፈ ወዳጅ ጋር ድንገት ትገጣጠማላችሁ፡፡  ያው በቃ፣ የተለመደውን እንዴት ነህ? ደህና ነህ ወይ?...“ያቺ የዘጠነኛ ክፍሏ ልጅ አገባች ወይስ ሲንግል ነች?” ምናምን ከተባባላችሁ በኋላ እሱዬው ጎንበስ ብሎ ምን ቢያይ ጥሩ ነው... ‘ሹዛችሁን።’ ማለት የሸመታችሁት ሳይሆን የፕሮሚስ ቀለበት ለመግዛት ብድር እያፈላለጋችሁ ሳለ ሜዳ ላይ አስጥታችሁ እንትን ሀገር የሄደችው እሷዬዋ የላከችላችሁ፡፡ እና የድሮ ወዳጅ ምን ቢል ጥሩ ነው...“በጣም አሪፍ ጫማ ነው ያደረግኸው...; ምናምን ይላል። (“ጫማ የሚያዩት እንትናዬዎች ናቸው፣” የሚባል ማን አጥንቶ እንደደረሰበት ያልተረጋገጠ ነገርን ላለመድገም ያህል ነው።) እናማ...አሪፍ ጫማ ነው፣ ደስ ሲል፣ ወይም “አሸወይና ነው፣” ምናምን ቢባል ምን ክፋት ይኖረዋል! ከዛ ቀጥሎ ምን ቢል ጥሩ ነው...
“መሥሪያ ቤት ደህና ይከፍሉሀል?” እየው እንግዲህ...ደህና ለስለስ ብሎ የጀመረ ቀናችሁን ሊያቆረፍደው ነው፡፡ ደግሞ እኮ ኮሚክ ነው...‘ደህና መክፈል’ ማለት ምን ማለት ነው? (ድሮ “እሱ እኮ በወር አንድ ሺህ ብር ይዝቃል!” ሲባል “ጉድ! ጉድ! እንዲያው ይህን ሁሉ ብር ምን ያደርገዋል!” ይባልበት የነበረው ጊዜ ጭራሽ ከ‘ሜሞሪ’ እንኳን ጠፋና አረፈው!)
“አዎ ለእኔ የሚበቃውን ያህል ይከፍሉኛል፡፡” ከዛ የሚቀጥለው ጥያቄ...
“ለመሆኑ ስንት ነው የሚከፍሉህ?” (ምን አገባህ! ተናግሮ ከሚያናግር ይሰውራችሁ፡፡) እናላችሁ...ይቺ የወር ክፍያን ቁጥር መጠየቅ በዘንድሮ ‘ዲክሺነሪያችን’ ወሬ ማነፍነፍ ሳይሆን ‘ስለላ’ ልትሆን ትችላለች፡፡ በቃ፣ ሲመስለንስ! ልክ ነዋ...እሱ የቁጥር ጥያቄ ያነሳው ወይ እማወራዋ “ሰልልኝ” ብላው ሊሆን ይችላላ! ወይ የሆነ ኮሚቴ ነገር መዋጮ ምናምን ሊል ፈልጎ “እስቲ እንደ ቀልድ አስመስለህ ሰልለው፣” ተብሎ ሊሆን ይችላል፡፡
‘ያበጠ ከንፈር’ ፖለቲካ!
እኔ እኮ ..በቃ የእንትን ሰፈርን ’ፌመስ’ አፕሬቲቭ አምስት ደብል ገልብጦ የትውልድ ቀኑን ሲጠይቁት ቀኑን ብቻ ሳይሆን ማዘር ላይ ምጡ ምን ያህል ጊዜ እንደቆየባቸው ማናዘዝ ይቻላል፡፡ አለ አይደል...እሱ ብቻ ሳይሆን ጣጥ ብሎ የመጣው ‘ዳድ’፣ ያውም ከርቀት አየት ካደረገ በኋላ... “እንዲህ አይነት ልጅማ ከእኔ አብራክ የወጣ አይደለም!” ብሎ ሆስፒታሉን እንደቀወጠው ሁሉ ሊናገር ይችላል፡፡ እናማ...‘ኢንፎርሜሽን’ ለማግኘት ሳይሆን ‘ስፓዪንግ’ ነገር የሚፈልግ ሰው ‘ታርጌቱን’ እንትን ሰፈር ወስዶ ‘ፌመሷን አፕሬቲቭ’ ደብል፣ ደብሏን መጋት ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1660 times