Saturday, 29 January 2022 00:00

አድማስ ትውስታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የድሮ ጋዜጣ ማስታወቂያዎች
ዘመናዊ የልብስ ስፌት ት/ቤት
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጎዳና፣ ሲኒማ አምፒር አጠገብ፣ ከመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ጎን፣ በዘመናዊ ዕቅድ የልብስ አቆራረጥና አሰፋፍ የማስተምር መሆኑን እገልጣለሁ።
ካሎራማ ተርቦያቪች
(አዲስ ዘመን፤ 24ኛ ዓመት፤ ህዳር 25/ 1957፤ ቁጥር 288፤ ገፅ 1)
***
ማስታወቂያ
የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ማተሚያ ቤት “ብርሃንና ሰላም”፣ ባለመስመር ሉክ መሸጡን ለገዥዎች ያስታውቃል።
(አዲስ ዘመን፤ 24ኛ ዓመት፤ ህዳር 25/ 1957፤ ቁጥር 288፤ ገፅ 1)
***
ፈረሳችሁ አምርሮ ቢጠፋ ጋጣውን መመልከት ጥቅም የለውም። “ኢንሹራንስ ግቡ።” ለሚጠፋባችሁ ሃብት ሁሉ ዋስትና ከአንበሳ ኢንሹራንስ ግዙ።
 አድራሻ፡- የስልክ ቁጥር- 11073፤ የፖ.ሳ.ቁ - 1167፤ ሃቬል መንገድ፣ አዲስ አበባ፤ አስታውሱ ለማንኛውም ዓይነት ኢንሹራንስ ነው።
(አዲስ ዘመን 24ኛ ዓመት፤ ህዳር 25/ 1957፤ ቁ. 288፤ ገፅ 1)
***
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማተሚያ ቤት፤ ብርሃንና ሰላም ማስታወቂያ
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለትምህርት የሚያገለግሉ ፅሁፎችና የታሪክ መፃህፍቶች፣ ደንቦችና ልዩ ልዩ ከክሊሼ የሚታተሙ ፎቶግራፎች በመጻሕፍት ቤቱ መሸጡን ለመጻህፍት ወዳጆች እናስታውቃለን።
የሚገኘውም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንገድ፣ ከማተሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ አጠገብ ነው።
የስልክ ቁጥር፡- 1528፤ የፖስታ ሳጥን ቁጥር፡- 1843
(አዲስ ዘመን 6ኛ ዓመት ፤ ግንቦት 10/ 1938፤ ቅፅ 3፤ገፅ 1)
***
እንዲህም ተዘግቧል!
የአቶ ሞቢል አደጋ
የጦር ሚኒስትር ፊታውራሪ ሙሉጌታ በታህሳስ 9 ቀን በአቶ ሞቢል ሆነው በአራዳ መካከል ባለው በዋናው መንገድ ሲሄዱ ኃይለማርያም የሚባለው አቶ ሞቢል ነጂአቸው ከመጠንቀቅ ቀርቶት አቶሞቢሉን ከግንብና ለኤሌክትሪክ ማብሪያ በተሰራው ሲሚንቶ መካከል አግብቶ አጋጭቶት አቶ ሞቢሉ ተጎዳ። ፊታውራሪን ግን መስተዋት ተሰብሮ ጥቂት እጃቸውን አደማቸው እንጂ ምንም ጉዳት አላገኛቸውም።
ምክንያቱም ከልባቸው ድፍረት የተነሳ ባይደነግጡ ነው እንጂ ፈርተው ቢሆን ሰውነታቸው ሲላላ ወደ ላይ አዘልሎ ራሳቸውን አቶ ሞቢሉ ይመታቸውና ይጎዱ ነበር። ከዚህ ቀደም ካደረጉት ድፍረት (ጉብዝና) አያንስም። ነገር ግን ለኃያላን ሃይልን፣ ለጠቢባን ጥበብን የሰጣቸው ዓምላክ፣ ከክፉ አደጋ ስለአዳናቸው እጅግ ልናመሰግነው ይገባናል።
(ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ፤ ታህሳስ 16/1923)
***
ሴቶች ተረከዘ ረዥም ጫማ እንዳያደርጉ ተከለከለ
በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት  ውስጥ ተቀጥረው የሚያገለግሉ ሴቶች በሥራ ጊዜ ተረከዝ ያለው ባለታኮ ጫማ እንዳያደርጉ ተከለከሉ። ከብረት የተሰራው ሹል የሴቶች ጫማ ሰራተኞቹን እንደፍላጎታቸው ሊያራምዳቸውና ሊያሰራቸው ስለማይችል፣ በሥራ ሰዓት ልጥፍ ጫማ ብቻ እንዲያደርጉ የተፈቀደ መሆኑን የማተሚያ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ትናንት በሰጡት ወሬ ለመረዳት ተችሏል።
ጫማው ለሥራ ፍጥነት አዋኪ ከመሆኑም በላይ፣ ከፕላስቲክ የተሰራውን የማተሚያ ቤት ወለል እየሰረጎደ አበላሽቶታል ሲሉ አቶ ለማ የተጠቆመውንና የተበሳሳውን ወለል አሳይተውናል።
ሴቶቹ ታኮ ጫማ የማድረግ ፍላጎት ካላቸው፣ ልጥፉን ጫማ ይዘው በመምጣት ከማተሚያ ቤቱ ሲደርሱ፣ ቀይረው ወደ ሥራቸው ለመሰማራት እንደሚችሉ ተነግሯል።
ተቀያሪውን ታኮ ጫማ የሥራ ሰዓት እስኪያልቅ በተወሰነላቸው ቁምሳጥን ውስጥ ሊያስቀምጡት እንደሚችሉ ተገልጿል። የተከለከለውን ጫማ አድርጋ የተገኘች የማተሚያ ቤቱ ባልደረባ፣ ቅጣት ሊደርስባት እንደሚችል በትናንትናው ቀን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷታል በማለት ሥራ አስኪያጁ በተጨማሪ አስረድተዋል።
(አዲስ ዘመን፤ ጥቅምት 29/1938)
(ምንጭ፡- ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ100ኛ ዓመት መጽሔት፤ 1914 - 2014)


Read 992 times