Saturday, 29 January 2022 00:00

“መቼ ይሆን አሜሪካ የምንደርሰው?” አለ፤ አሜሪካ የኖረ ሰው

Written by  ( ከኢሳይያስ ልሳኑ ቤተሳይዳ ሜሪላንድ - አሜሪካ)
Rate this item
(1 Vote)

 ሴት አያቴ የተኙበትን አፈር ገለባ ያድርግላቸውና ቤሳ (ደብዳቤ) ጻፍልኝ እያሉኝ ስላደግሁኝ ነው መሰል ደብዳቤ ማንበብና መጻፍን አብዝቼ እወዳለሁ። እንደ ዛሬ ልጆች በምህጻረ ቃል - ‘ቴክስት’ የሚሉት እጅግም አይማርከኝም፡፡ ያጠረ የኢሜይል አጻጻፍም፣ ጥበብን እያሸሸው ስለሚመስለኝ እፈራለሁ። ድሮ - ድሮማ ሲነገረን ፍቅረኞች እንኳን በደብዳቤ ነበር ልብ ለልብ የሚገናኙት፡፡ ታዲያ ይህን ሰሞን አሜሪካና እኛ - እኛና አሜሪካ በሀሳብ ሲወዘውዙኝ ቆዩና በመሀሉ አንድ የቆየ ጦማር (ደብዳቤ) አግኝቼ በደስታ በንባብ ወጣሁት። አንዱ ከሀገር ቤት ለወንድሙ እዚህ ሀገር አሜሪካ ላለ ያደረሰው ደብዳቤ ነው።
“ለውድ ወንድሜ  - ለጤናህ እንዴት ይዞሃል?” ብሎ ይጀምራል፣ “እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። ወንድሜ አሜሪካስ እንዴት ናት? ከዚያ የመጡ ሰዎች አሜሪካ ያሉ ታቦቶች ምስጋና እንጂ ልመና አይሰሙም እያሉ ይነግሩናል። ኢትዮጵያ ያለውን ታቦት ለምነህ ስታበቃ ሲሳካልህ፣ አሜሪካ ሄደህ ለተመሳሳዩ ታቦት ታመሰግናለህ ማለታቸው ነው። ወንድሜ፤ በአቶ እከሌ የላክልኝ ገንዘብ እንደነበር ስሰማ ደስ አለኝ። ገና ስለብሩ ሰምቼ ሳላበቃ ያመጣው ሰውዬ በልብ ድካም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ስሰማ ግን የደነገጥኩት ይሄ ነው አይባልም። ድንጋጤዬ ለእኔ ይሁን ለሰውየው በውል አላወቅሁትም። ብቻ ስደነግጥ “የሰው ገንዘብ ይዞ ሞት ይፈቀዳል እንዴ?’ ብዬ ነበረ አሉ፡፡ ብሩም ባይደርሰኝ እኔ አሜሪካ አንተ ዘንድ ብደርስ እናፍቃለሁ” ይላል፡፡
ስለ አሜሪካ መምጣት ያለ ግምትና ህልም ራሱን የቻለ ትልቅ ጉዳይ ነውና ይቆየን። እና በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ወዲህ እንምጣ፡፡ እዚህ አሜሪካ ከመጣን በሁዋላ ያለንና የኖርንበት ሁኔታ የሚኮረኩረን ነገር ብዙ ነው። እንዲህ ሆነ - አንድ አሮጌ የብዕር ጓደኛዬ፣ እዚህ አሜሪካ ሌላ ስቴት የሚኖር፣ ደጋግሜ ስልክ ብመታለት አልመልስልህ ይለኛል። ድሮ ሀገር ቤት ለሰፈሩ ‘አቶ እከሌ ቤት ባለው ስልክ አስደውሎ ጥሩልኝ’ እንደሚባለው፣ እኔም በዘመድ አዝማዶቹ አፈላልጌ አገኘዋለሁ።
“ምነው ወንድሜ ጠፋህብኝ?” ብዬ እጀምራለሁ፤ “አሜሪካ ሀገር ገብቶ ደግሞ መገናኘት እንዲህ ይቸግራል እንዴ?” እለዋለሁ። “እባክህ ተወኝ ጃል እኔ ገና አሜሪካ ለመድረስ እየሞከርኩ ነው፣” ብሎ አሳቀኝ። አሜሪካ መኖርና ከአሜሪካ መድረስ አንድ አይደለም በሉልኝ።
አንድ ወዳጄ ታሞ ልጠይቅ ሄጄ ነው። ለሰውነቱ ‘ደም’ አስፈልጎት ከዚያው ከሆስፒታሉ ከነበረው ተሰጥቶት - አገግሞና ሻል ብሎት ከቤቱ መጥቶ እያወጋን ነው።
“ይገርማችኋል፤ እኔ እንደናንተ የአሜሪካ ዜግነት ጠይቄና ምዬ አይደለም ያገኘሁት በደም ነው - የክሪስና የስሚዝ ደም ተሰጥቶኝ በደም አሜሪካዊ ሆኛለሁ፣” ብሎ አሳቀን። አንዷ ታዲያ ቀበል አድርጋ፤ “ኦ ለዚህ ነዋ እንግሊዘኛ መቀላቀል የጀመርከው” ብላ ሌላ ሳቅ ጨመረችበት። ሳቅ ከተጀመረ አይቀር አይደል - ‘የወንዱ የስሚዝ ብቻ ሳይሆን የሜሪም ደም ተቀላቅሎ ይሆናልና ተጠንቀቅ” ብሎ ጨመረበት ሌላው። የቋንቋ መቀላቀልና ማዥጎርጎር ነገር ከተነሳ ከእዛች ሀገሬ የምሰማው የ’ምሁራን’ ይባል የባለስልጣን ንግግርና ትንተና፣ ግማሽ በግማሽ የተለጣጠፈ ‘እንግልጣር’ እየሆነብኝ ተቸግሬያለሁ፡፡ ቋንቋችን ምሉዕ መሆኑን ስለምረዳ ይህ እንደ ቡትቶ የመለጣጠፍ ነገር ቢቀር ብዬ እመኛለሁ፡፡ ምኞት አይከለከልም በሉኝ፡፡
ከዚሁ ሳልወጣ (የዘንድሮ ቃለ ምልልስ አድራጊዎች አባባል ትመስላለች) አንድ ወግ ላጫውታችሁ፡፡ ቧልት ቢመስልም ብትስቁም ታሳስባለች፡፡ አንዱ ከፍርድ ቤት ቆሞ ቋንቋ እየቀላቀለ አስቸገረ አሉ። ዳኛው መለስ አድርገው፤ “ስማ ከዚህ በሁዋላ በአማርኛ ብቻ ተናገር! እንግሊዘኛ እንዳትቀላቅል” ብለው አስጠነቀቁት። ያ የመቀላቀል አባዜ የተጠናወተው ሰው እንደገና ሲናገር መቀላቀሉን ቀጠለ፡፡ ጠረጴዛውን መቱና “በል ከዚህ በሁዋላ በእንግሊዘኛ ብቻ ተናገር!” ይሉታል፡፡ ያኔማ ዓይን ፍጥጥ - ጥርስ ግጥጥ፡፡ እና ወገኖቼ፤ ቋንቋ እውቀት አይደለምና አለመቸገር ነው። - በነገሬ ላይ እዚህ ዲያስጶራም ያለ ችግር ነው ይሄ፡፡   
ርዕሰ ነገሬ እኛ አሜሪካ ስንኖር ነው። በደምም ይሁን በውን ዙሪያ ገባውን ሳየው፣ አሜሪካ የደረስንም ያልደረስንም ብንኖርም፤ ሳንደርስ የደረስን የሚመስለን መኖራችንን እያስተዋልኩ ደግሞ ፈገግ እላለሁ።
ወገኖቼ፤ ሰሞኑን ዲያስጶራ ባለፍ አገደም እያያችሁ ነውና ይሄ ሁሉ ሳትሉ የቀራችሁ አይመስለኝም፡፡ ለነገሩ እዚህ አሜሪካ ምድር ሆነን ልባችን እዛ ሲገፋፋ የምንውለውን ብትቆጥሩን ደግሞ ጉድ ይባላል፡፡ ታዲያ ምን አለ መሰላችሁ? እዛ ሀገር ቤት ሂልተን ሆቴል ተቀምጠው፣ ለሳምንት ኢትዮጵያን እናውቃለን፣ ብለው የሚጽፉ ፈረንጆች አይነት ነገር አለ። እዚህ ሀገርም አሜሪካን ከእግር እስከ ራሱ አወቅነው ብለን የምንዘፍን አይነቶች። ገበሩና ውስጡ እንዴት ውስብስብ እንደሆነ እንዘነጋለን። ግን ሀገሩ ውስጥ ሲኖር በተለይ ስደተኛ ሲሆኑና ከነገ ዛሬ ሀገሬ እገባለሁ ብለው ሲያስቡ የሚገጥም ነገር አለ። እሱን ትታችሁት አንዳንዱ ቤት ከሀገር ቤት የመጡ አረጋውያን ሳይቀሩ ይህን የ‘ሶፕ ኦፔራ’ ሲኒማ፣ የ‘ቶክ ሾው’ ሲኮመኩሙ ውለው ከርመው ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በሁዋላ በስልክ ስታወጓቸው፤  እኔ የምልህ “ያች ኦፕራ ደህና ናት?” “ሪኪ እንደከሳች ነው?” - “ዶክተር ፊል ምን አለ?” የሚሉ ብትሰሙ አትገረሙ።
ችግር አለ ወገኖቼ። አሜሪካ ቴሌቪዥኑ ይሁን አኗኗሩ - ኪስ ባዶ ቢሆን እንኳን ያለዎ የማስመሰል ኩራት ይሰጣል። የቤቨርሊ ነዋሪዎችን ኑሮ በቴሌቪዠን ያዩና እርስዎ ሽቦው ከሚዋጋ ፎቴ ላይ ተቀምጠው ያሉበትን ይረሱታል። እርግጥ ነው የፈካ ማሽላ (ፖፕ ኮርን) በትልቅ ሳህንና ቆንጆ ቲቪ ያለንበት ኑሮ አይነፍግም፡፡  ያ ሲተኛ የወርቅ ጆንያ ተሸክሞ ሲንገዳገድ ከህልሙ ሲነቃ “ምነው ነቃሁ፣” ያለውን የሀገሬን ሰው ያስታውሰኛል። ደግሞ ሠርተንና ለፍተን ቢከፈለንና ገንዘብ አገኘን ቢባል በኑሮው ልክና ደረጃ ነው፡፡ ታዲያ ሀገር ቤት በዶላር ጥማትና ፍለጋ ስንመሳቀልና ስንሯሯጥ ስለኖርን ነው መሰል በዶላሩ ወረቀት ላይ እንደተሳለችው ንስር ዘርፈፍ የምንል አለን። ይመስለኛል አሜሪካ ያገኘነውን ዶላር በሀገር ቤት የብር ምንዛሪ አስልተን በአንድ ጀንበር ደረት የምንነፋም አንታጣም።
እዚህ ሀገር ከልምድህ ተናገር ብባል ‘አለኝ’ ሲሉ፣ ‘የለኝም’ አብሮ ወዳጅ ሆኖ ከቤትዎ የሚገባበት ሀገር ነው። እና ‘እንደምንዋልክ ሀብት’ ብለው ከመቀመጫዎ ከፍ ሲሉ፣ ‘ድህነትና ችግር’ ተቀምጦ ያገኙታል ብል ትንቢት አይደለም። ግን ጥቂት ሶልዲ ቋጥሮ ደረት ነፋ  የሚያደርግና የዕዳ መኪናውን ሲሾፍር እጁን ሳይሆን እግሩን ብቅ አድርጎ ሊያሳየን የሚናፍቅ ሰው ትታዘቡ ይሆናል። በነገሬ ላይ አንተ ወንድሜ እግርህን ለማውጣት የሚቃጣህ ከቁርጭምጭሚትህ ላይ አልቦ ብታደርግበት ደስ ይላል ይልቅ።
እና ወግ ከጀመርኩ አይቀር በባዶ ኩራትና በቴሌቪዥን በተቀፈቀፈ ቅዠት ከማን አንሼ የሚል ትዕቢት ስልችት ይላል ስታዩት። ልታይ ልታይ የማለት በሽታ ደግሞ አለ።  የማህበራዊ መሰላላችን ፈርሶ - የመደበላለቅ ስሜት ተጠናውቶን የለ? የጤናው ዶክተር ተቀምጦ - የበሽታ አይነትና መድሃኒት የሚያዝ ሰው ቢገጥም መከራከር አያስፈልግም። ፖለቲካ የሆነ እንደሆነማ - ሁሉም ያውቃልና ዝም የሚል ላይገኝ ይችላል። እንደውም ሁሉም እኩል ስለሚናገር አድማጭም የለም፡፡ እምፈራው አሁን ሀገር ቤት ለደግ ከገባው የእኛ ዲያስጶራ ጋር - ‘ተንታኝና’ ‘ምድርን የተሸከመ’ የሚመስል አንዳንድ ካጋጠማችሁና ከአሜሪካ ነኝ ካላችሁ - “የለም አንተ እንደውም አሜሪካ አልደረስክም” በሉልኝ። ችግሩ ምን መሰላችሁ? - ይሄ ማህበራዊው መገናኛ እንደልብ ሆኖ ‘ዩቲዩብ’ ላይ ‘እንዲህ መሆን አለበት የሚለውን መራቀቅ’ የያዘ ሰው ሳያስበው ‘ተወደድኩ’ (like ያደረጉኝን ተመልከት ይላል) ብሎ በራሱ ፍቅር ያብዳል። ይህን ዕብደት ደግሞ የቱም ጠበል አያነጻም። ብቻ ከአሜሪካ ነኝ ካለ - ገና አሜሪካ አልደረስክም በሉልኝ፡፡  
እና ስለ ሁሉም ነገር ከሰማይ በታች ከምድር በላይ ላለና ለሆነ ሁሉ እውቀት ያለን የሚያስመስል መንፈስ አሜሪካ በስደት ስትኖሩ ይጫናል ልበል? ትንሽ እውቀት የሚሏት አይነት፡፡ ትንሽ ጉግል አድርጎ ወይም ተባራሪ ‘የፊት ገጽ’ (facebook) አንብቦ - ‘ምሁራዊ’ ትንተና የመስጠት ነገር አለ - የሚያስደነግጥ። ደግሞ ይኼ ሀገር አጓጉል ኩራት ይሰጣል ብያለሁ። ቴሌቪዥኑ - ዶላሩ - እና መኪናውና የሚያብረቀርቀው ላላወቀው ‘ንጉሥ ነኝ’ ብሎ ለብቻ ይኮፍሳል። እና የአውቃለሁ ትዕቢት እንደ ክት ልብስ ለብሶ መሄድ ይመጣል።
በዚያ ላይ የሌለንን አለን የማለት ነገርም ይከተላል። በዚያ ላይ የአንዳንዱ ከመሀል የቀረውን ሰው ውሸት ስሰማ፣ ሰማይ ቤት ሆነ የተባለን ቀልድ ያስታውሰኛል።
ምድር ላይ ላለው ሰው ለእያንዳንዱ አንዳንድ የግድግዳ ሰዓት በስሙ ይሰቀላል አሉ። እና ሰውየው ሲዋሽ የሰዓት ማመልከቻዋ እጀታ መዞር ትጀምራለች። ውሸቱ በበዛ ቁጥር ስትሽከረከር ይታያችሁ። ታዲያ የአንዳንዱ ውሸት ስለሚበዛ ሰማይ ቤት መላዕክቱ አየሩ ሲወብቃቸው የግድግዳውን ሰዓት እንደ ማራገቢያ (ፋን) ይገለገሉበት ይመስለኛል።
እውነቱን መነጋገር ይሻል መሰለኝ። እዚህ ጠበል ይዞ የሚሄድ ወዳጅና ዘመድ በገደደበት ቦታ መስመር ሲለቁ ካልተመካከርን - ደግሞም እውነቱን ካልተነጋገርን ችግሩ ይወርሰናል። ደግሞ የሆነውን የሚነግረን ሰው ሲገኝ “ምክሩን አንቺ እህቴ ነሽ” ማለት ነው። በዛሬ ጊዜ እውነቱን የሚነግረን ማግኘትም ይገዳል። ቆመው ሲናገሩ የሚያጨበጭበው ሁሉ ‘ወዶኝ ነው’ ብለህ የምታስብ ከሆነ ወንድሜ ተሳስተሃል፡፡
ሳታውቀው ገበያ የወጣ የወግ ዕቃ እየሆንክ ነው ስልህ በትህትና ነው። አንዱ የጀመረውን ሁሉም ተከትሎ ማጨብጨብ ወግ በሆነበት ወቅት መታለል እንዳይገጥምህ አስባለሁ፡፡ ጠጋ ብሎ እውነቱን የሚነግር ሰው ለማግኘት መጸለይ ያስፈልጋል።
ሴትየዋ የሆነችውን ልንገራችሁ። ዶክተሯ ዘንድ ሄዳ ነው።  “ዶክተር እስቲ ተመልከተኝ። ዛሬ ከእንቅልፌ እንደነቃሁ በመስታወት ፊቴን ሳየው ዓይኔ ከረጢት ከስሩ አንጠልጥሏል። ጸጉሬ ተንጨባሮ ከርድዷል። ቆዳዬ ተጨረማምቷል። ልክ አጽም መስያለሁ። ምንድን ነው የሆንኩት?” ትለዋለች። ለአፍታ ተመልክቷት፤ “በዚህ ጊዜ የምነግርሽ ዓይንሽ ደህና እንደሆነ ብቻ ነው” አላት ይባላል።
መቼ ይሆን አሜሪካ የምንደርሰው አለ - አሜሪካ የኖረ ሰው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1046 times