Print this page
Saturday, 29 January 2022 00:00

በጳውሎስ ሆስፒታል የተቋረጠው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና እንዲጀመር ተጠየቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

የኩላሊት በጎ አድራጎቱ የፊታችን ሐሙስ በጊዮን ሆቴል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር አዘጋጅቷል
                            
             የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት፣ በጳውሎስ ሆስፒታል ይሰራ የነበረውና በኮቪድ ምክንያት የተቋረጠው የኩላሊት ንቅለ ተክለ ህክምና እንዲጀምር ተማፀነ፡፡ በጎ አድራጎት ድርጅት የፊታችን ሐሙስ ጥር 26 በጊዮን ሆቴል ከጠዋቱ 3፡00-12፡00 ድረስ ከሁለት ብር ጀምሮ ማህበረሰቡ ገንዘብ እንዲለግስ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ይህን የገለፀው ከትላንት በስቲያ በጊዮን ሆቴል ብሉ ሳሎን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲሆን ተማሪዎችን ጨምሮ የትኛውም የማህበረሰብ ክፍል ከሁለት ብር ጀምሮ ያለውን በመለገስ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋና በበጎ አድራጎት ድርጅቱ በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰሩ የፊልም ባለሙያና የ“ላምባ” ፊልም ደራሲ አንተነህ ሀይሌ፣አርቲስት ይገረም ደጀኔና ጋዜጠኛ የትናየት አበራ በጋራ በሰጡት መግለጫ በበርካታ ግርግሮች መሃል የኩላሊት ህመምተኞች  ጉዳይ ችላ መባሉን ጠቁመው በዚህም የተነሳ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ታማሚዎቹን ለመርዳ በመቸገሩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
በጳውሎስ ሆስፒታል ይደረግ የነበረው የኩላሊት ንቅለ ተክለ ህክምና መቋረጥ በታማሚዎች ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የገለፁት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ አሁን ላይ በኮቪድ ምክንያት የተቋረጡ የተለያዩ አገልግሎቶች በመጀመራቸው የኩላሊት ንቅለ ተከላውም በአስቸኳይ እንዲጀምር ጠይቀዋል፡፡
እንደ አይን ባንክ ሁሉ የኩላሊት ባንክ እንዲከፈት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ሰለሞን፤ ይህም ተግባራዊ ቢደረግ ኩላሊት የሚለግሳቸው ወዳጅ ዘመድ የሌላቸው ታማሚዎችን ሁሌ በዲያሊስስ ከመሰቃየት መታደግ ያስችላል ብለዋል፡፡ ይህንና መሰል ከኩላሊት ጋር በተያያዘ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን የያዘ ሰነድ ከጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን የገለፁት አቶ ሰለሞን ይህም ሰነድ የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት በምከር ቤቱ እንዲጸድቅና ተግባር ላይ እንዲውል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሀሙስ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ተማሪዎች፣ ዲያስፖራዎች፣የንግዱ ማህበረሰብ፣የመንግስት ሰራተኛውና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍና ከሁለት ብር ጀምሮ የሚችለውን ያህል  ድጋፍ እንድያደርግ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ሰለሞን፤  ይህም በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከገባበት አጣብቂኝ ለጊዜውም ቢሆን እፎይታ  እንዲያገኝ ያግዘዋል ብለዋል፡፡


Read 960 times