Saturday, 29 January 2022 00:00

የኢትዮጵያ ፖለቲካና የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት

Written by  ፕ/ር አድማሱ ገበየሁ
Rate this item
(1 Vote)

 "ምዕራባውያን በህዝብ የሚወደድ መሪ አይፈልጉም"
                  
                 አለም ሁሌም የፉክክር፣ የውድድር መድረክ ነች። መንግስታት የሚያደርጉት ፉክክር ደግሞ የፉክክሮቹ ቁንጮ ነው። አንዱ የሌላው የበላይ ለመሆን በሚያደርጉት ፉክክር፣ ደካማ የሚሏቸውን ወይም በእርዳታ የሚደጉሟቸውን ሃገራት በስራቸው ለማሰለፍና ጎራቸውን ለማጠናከር ሁሌም ይታትራሉ፡፡
በተለይ ምዕራባውያን የሚባሉት በዋናነት በአሜሪካና እንግሊዝ የሚወከሉት ሃገራት፣ በተቋማት ደረጃም እንደ ዓለም የገንዘብ ድርጅት ያሉት፣ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ታዳጊ ሃገራት ላይ ያላቸው ጫና ከፍተኛ ነው፡፡ እነዚህ መንግስታት በስራቸው እንዲሰለፉ ለሚፈልጓቸው ሃገራት ዲሞክራሲን ለማጠናከር በሚል ሰበብ እርዳታ ይሰጣሉ።
ዲሞክራሲን ለማጠናከር ይበሉ እንጂ በአንጻሩ እነዚህ ሃያላን አገራት እርዳታ ሲያቀርቡ በዋናነት በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ለእነሱ ተገዥ ሎሌ መሆኑን በሚገባ አረጋግጠው ነው። ያ መንግስት ለእነሱ ሎሌ ሆኖ  እስከቀጠለ ድረስ በምርጫም ይሁን በሌላ  መንገድ ስልጣኑን እንዲያጣ አይፈልጉም።
ብዙ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች በስልጣን ላይ ለመቆየት ከህዝባቸው ይልቅ አስተማማኝ ደጀናቸው አድርገው የሚያስቡት ምእራባውያን መንግስታትን የሆነውም ለዚህ ነው። ለእነሱ ተገዥ እስከሆኑ ድረስ ከስልጣናቸው እንደማይነሱ ስለሚያውቁ፣ ሁሌም ከህዝባቸው ጥቅም ይልቅ ለምዕራባውያኑ ጥቅም ሲሰሩ ነው የሚታዩት። ይሄ በአፍሪካ ሃገራት አሁንም ድረስ በሰፊው የሚታይ እውነታ ነው።
ለምሳሌ በኢትዮጵያ ወያኔ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ጨቋኝና በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት የሌለው እንደነበር አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን የእነሱን ጥቅም በሚገባ ያስጠብቅ ነበር፤ በተለይ በቀጠናው ሃገራት ላይ ፍላጎታቸውን ይፈጽምላቸው ነበር። ስለዚህ ለዲሞክራሲ እንቆማለን የሚለውን ዲስኩራቸውን ወደ ጎን ትተው፣ በተግባር ከዲሞክራሲ ጋር የተፋታውን ወያኔን በስልጣን ላይ ለማቆየት ጥረት ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ “ለምን ወያኔን ትደግፋላችሁ?” ሲባሉ፤ “እሱ ከስልጣን ከተነሳ በብሄር የተከፋፈለችው ሃገር ልትፈርስ ትችላለች የሚል ስጋት አለን” ይላሉ። እውነታው ግን ሃገር ትፈርሳለች የሚለው ሳይሆን እንደ ወያኔ ታዛዥ መንግስት ላናገኝ እንችላለን የሚል ስጋታቸው ነው፡፡
ምዕራባውያን በህዝብ የሚወደድ ወይም የተወደደ መሪ ሲመጣ በጣም ነው የሚደነግጡት። ምክንያቱም በህዝብ ተወዳጅ የሆነ መሪ ለምዕራባውያኑ ተገዥ አይሆንም፡፡ ለእነሱ እንደማይታዘዝላቸውም አሳምረው ያውቁታል። እንዲህ አይነት መሪዎች በአፍሪካ ምድር ብቅ ብለው ብዙም ሳይቆዩ ሲጠፉም ታዝበናል። ምዕራባውያኑ አሁንም በአፍሪካ ውስጥ በህዝብ የሚወደድ መሪ እንዲኖር አይፈልጉም። በኢትዮጵያም ጉዳይ ያለ ቅጥ ጫና የማብዛታቸው ሚስጥር ይኸው ነው።
እኔ የታሪክ ባለሙያ ባልሆንም የታሪክ አንባቢ ነኝ። ከዚህ አንጻር በየዘመናቱ ኢትዮጵያ  ከውጭ ሃይሎች የተረጋረጡባትን ፈተናዎች ለመመርመር እሞክራለሁ። በዚህ ሙከራዬም፣ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ታሪክ፣ ትልቁን የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት ፈተና የተጋፈጠችው በአፄ ምኒልክ የሥልጣን ዘመን እንደነበር ለማወቅ ችያለሁ። ይህም የውጭ ሃይሎች ፍላጎትና ጣልቃ ገብነት  የአድዋ ጦርነትን ፈጥሯል። ከዚህ ጉልህ ጦርነት ባሻገር ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን፣ ኢትዮጵያን የመቀራመቻ ስምምነት ፓሪስ ላይ ተፈራርመዋል።
በወቅቱ ይሄን ኢትዮጵያን የመቀራመቻ ስምምነት ሰነድ፣ አፄ ምኒልክ እንዲፈርሙ በድፍረት ቀርቦላቸው ነበር። እሳቸው ግን ማናቸውም የስምምነቱ ፈራሚ ሃገራት በማይደርሱበት ጥበብ ነበር፣ ይሄን ስምምነት ከመፈረም ያመለጡት። አፄ ምኒልክ፤ “ለኛ እንደዚህ ካዘናችሁልን ጥሩ ነው፣ እኛም ከስጋታችን ተላቀናል። ነገር ግን እኛን ከበላይ ሆናችሁ ለመቆጣጠር አታስቡ፤ እንደውም የኛ ስጋት እናንተ ነበራችሁ፤ አሁን እናንተ ለኛ እንደዚህ የምታስቡ ከሆነ ስጋታችን ተቃሏል፤ ከእንግዲህ የሚያስቸግረን የለም። እናንተም ባላችሁበት እኛም ባለንበት ተማምነን መቀጠል ነው ያለብን” በማለት መለሱላቸው። ይሄ እንግዲህ የሃገራቱ ስምምነት በወቅቱ ለኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ ፈተና እንደነበር አመላካች ነው።
በሌላ በኩል፣ ጣሊያን በአድዋ መሸነፏ በመላው አፍሪካና ጥቁሮች ዘንድ መነቃቃትና መነሳሳት መፍጠሩ በኢትዮጵያ ላይ ጫናዎች እንዲበራከቱም አድርጓል። ልክ አሁን ኢትዮጵያ ስትነካ “በቃ” (No more) በሚል እንደተቀጣጠለው እንቅስቃሴ ነበር የሆነው።
ለኔ ከዚህ ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት በኋላ ተመሳሳይ ፈተናና ችግር የገጠመን በአሁኑ ዘመን ነው፡፡ አሁን ያለው ችግር የውስጥ ጦርነት ቢመስልም እውነታው ግን ሌላ ነው። በህዝብ የሚወደድ መሪ የማይፈልጉት ምዕራባውያኑ፤ በህዝብ የሚጠላውን (ስለዚህም ለኛ ከመታዘዝ ውጪ ምንም አማራጭ አይኖረውም የሚሉትን) ወያኔን ወደ ስልጣን የመመለስ ተልዕኮ ላይ ናቸው፡፡ ወያኔ በራሱ ሃይልና አቅም ዳግም ወደ ስልጣን መመለስ እንደማይችል ያውቃሉ። ስለዚህም ለወያኔ ማንኛውንም ድጋፍ እያደረጉለት በሱ በኩል በሥልጣን ላይ ያለውን የኢትዮጵያን መንግስት መዋጋትን ነው እንደ ስልት የያዙት። በሃሰተኛ ወሬና ፕሮፓጋንዳ ጦርነቱን ለማሸነፍም ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ ይሄ የጦርነቱ ትልቁ ሃይል እንደሆነ ያውቁታል። ለዚህ ነው ፕሮፓጋንዳው በስፋት በዓለም እንዲናኝ የተደረገው። በዚህ ስልት እነ ዶ/ር ዐቢይን ለማንበርከክ ነበር የታለመው፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ ደግሞ ሴራቸውን ቀድመው ነቁባቸው፡፡ ሴራቸውን ለማክሸፍም ህዝባቸውን ነው ደጀን ያደረጉት። የህዝብ ድጋፍን አበራከቱ። በዚህ መንገድም የምዕራቡን ሴራ ማክሸፍ ተቻለ ማለት ነው። አሁን ላይ መንግስት የህዝብ ድጋፍ ያለው መሆኑ የምዕራባውያን ስጋትን በእጥፍ ነው የጨመረው። ይባስ ብሎ ሌሎች “በተዘዋዋሪ ቅኝ” ተገዝተናል የሚሉ የዓለም ህዝቦች “በቃን” የሚለውን እንቅስቃሴ መቀላቀላቸው፣ ነገሩን አቀዝቅዘው መያዝ እንዳለባቸው ሳያስገነዝባቸው አልቀረም፡፡
ከዚህ በኋላ ምን ይሆናል ከተባለ፣ ምናልባት የ”በቃ” እንቅስቃሴ በምዕራባውያኑ ላይ የሚጠናከርባቸው ከሆነ መቼም ቢሆን ወታደር አዝምተው ጦርነት ለመግጠም አያስቡም፡፡  
በሌላ አንጻር፣ ኢትዮጵያን ከዚህ በኋላ ለመጉዳት የሚያደርጉት ነገር አይኖርም። እኛም ይሄን የሚቀለብስና የሚቋቋም ስነልቦና ልናዳብር ይገባል። ህዝብና መንግስት አሁን የተጋፈጥነውን ተግዳሮት በፅናት ከተቋቋሙ እነዚህ ምእራባውያን በመጨረሻ መለሳለሳቸውና ሃሳባቸው የማይጠቅም መሆኑን መረዳታቸው አይቀርም።
አሁን ላይ ሁኔታውን ስንገመግመው፣ ምዕራባውያኑ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። በኢትዮጵያ ላይ  ያቀዱት ሴራ  ሌላ ራስ ምታት ነው የፈጠረባቸው። ሌሎች ሰጥ ለጥ ብለው የሚገዙላቸው መንግስታት ዜጎች ሌላ ነገር እንዲያስቡ ወይም እንዲነቁ አድርጎባቸዋል። ይሄ ንቃት እየጎለበተ ከሄደ ደግሞ የሚፈጥረውን ጠንቅቀው ይረዳሉ። አሁን አፍሪካውያን #ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ የተደረገው ነገ በኛ ላይ መደረጉ አይቀርም” የሚል እሳቤን እየያዙ መምጣታቸው፣ ለምዕራባውያን አስደንጋጭ ነው የሚሆንባቸው።
ከዚህ አንጻር ምዕራባውያኑ ከዚህ ቀደም የነበረውን አካሄዳቸውን ቆም ብለው መመርመራቸው አይቀርም። አሜሪካንም ሆነ ሌላው ሃያል መንግስት ለዚህ “የንቃት” እንቅስቃሴ ጦር ማዝመት እንደማይችሉ ስለሚያውቁ፣ ከእንግዲህ ከአሁን ቀደም እንዳደረጉት ሰው አገር በጉልበት ጣልቃ ለመግባት ይሞክራሉ የሚል ግምትም የለኝም። በተለይ ኢትዮጵያን በወታደራዊ ሃይል ለማንበርከክ ይሞክራሉ ብዬ አላምንም።
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው  ጽሁፍ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከፕ/ር አድማሱ ገበየሁ ጋር ካደረገው ቃለ-ምልልስ የተሰናደ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን።


Read 379 times