Saturday, 29 January 2022 00:00

ከጡረተኛ የለቀማ ባለሙያው ጋር

Written by  ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
Rate this item
(0 votes)

 • ኮምፒውተር ሲመጣ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ቤት ማደር የጀመርነው
   • “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን “ኢትዮጵያ ትውደም” ብለን አውጥተናል
                     
               የዓለም የኅትመት ታሪክ ብዙ የቴክኖሎጂ ዕድገቶችና ማህበራት ለውጦችን አልፏል። በድንጋይና በእንጨት ላይ እየቀረጹ ከመጻፍ የጀመረው የህትመት ታሪክ፣ ዲጂታል የሚባለው ዘመን አመጣሹ ቴክኖሎጂ ላይ አርፏል። በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች ውሰጥ የነበሩ ልፋቶች፣ ተግዳሮቶችና መስተጋብሮች ከአሮጌው የአሰራር ሂደትና መሳሪያ ጋር አብረው ይረሳሉ። ስለዚህ ያለፈው ዘመን ስልተ-ምርትም ሆነ በዚያ ዘመን ስልተ- ምርት ውስጥ ዋነኛ ተዋንያን የነበሩት ሰራተኞች የስራ ታሪክ ይዘነጋል። ከነአባባሉ “ወደፊት ለመሄድ ወደ ኋላ መንደርደር” ነውና ዘመናዊው የዲጂታል ማሽን ከመምጣታቸው በፊት የኅትመት አካል የነበረውንና በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለረጅም ዓመታት ሥራ ላይ የዋለውን የ”ለቀማ”ን ሂደት ለመቃኘት አሰብን።
በብዙ ዓለማት ላይ ታሪክ ከሆነ የቀየው ይህ የ”ለቀማ” ህትመት፣ በሀገራችንም ታሪክ ለመሆን በማኮብኮብ ላይ ነው። መጪው ትውልድም ሆነ ዘመናዊውን የህትመት ሂደት ብቻ የሚያውቁ ሰዎች ለጉዳዩ ባዕድ ናቸው፤ በመሆኑም የህትመት ኢንዱስትሪው ዛሬ ላይ ከመድረሱ በፊት ምን ያህል የሰራተኞችን መስዋዕትነት ይጠይቅ እንደነበር ላይረዱ ይችላሉ። ይህንን ብዥታ ለማጥራትና ሰራተኞቹን ለመዘከር በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ውስጥ ለረጅም አመታት በ”ለቀማ” ሥራ ላይ የነበሩትና አሁን ጡረታ የወጡትን አቶ ሸዋንግዛው አምደመስቀልን ደራሲና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ስለቀደመው ስራቸውና ተያያዥ ጉዳዮች አነጋግሯቸዋል።
ጠያቂ፡-እስቲ ከስምዎ እንነሳ?
መላሽ፡- ሸዋንግዛው አምደመስቀል እባላለሁ።
ጠያቂ፡- ብርሃንና ሰላም መቼ ተቀጠሩ?
ሸዋንግዛው፡- የገባሁት በ1966 ዓ.ም ነው፤ ጃንሆይ ሳይወርዱ ነው በቀን ሰራተኝነት የገባሁት። በቀን 90 ሳንቲም ነበር የማገኘው፤ 90 ሳንቲሟ ተጠራቅማ በሳምንት ነበር የምትከፈለን። 90 ሳንቲሟ ግን አንዳሁኑ አትምሰልህ፤ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት በሷ በልተን እናድራለን፤ የቤት ኪራይ ከፍለን የምናድረውም በሷ ነው። ስራችን ጥቅል ወረቀት ከመኪና አውርዶ መጋዘን ማስገባትና የታተመ መጽሐፍ መኪና ላይ መጫን ነው። ጥቅል ወረቀቱን ከመጋዘን እየገፋን ወደ ጋዜጣ ክልል ማድረስም የእኛ ስራ ነው። እዚያው እየሰራሁ በ1967 ዓ.ም “መሬት ለአራሹ” ታወጀ፤ ወዲያው “90 ቀን የሞላው ሰራተኛ ቋሚ፣ መሆን ይችላል፤ ድርጅቱም ሰራተኛውን ማባረር አይችልም!” የሚል አዋጅ ወጣ። ማታ አዋጁ ተነግሮ ጠዋን እኛን መዘገቡ። የመጀመሪያው ተመዝጋቢ እኔ ሆንኩ። ደመወዛችንም አድጎ በወር 55.00 ብር ሆነ።
በወቅቱ የሚታተሙት መጻህፍት የጸሎት መጻህፍት፣ ውዳሴ ማርያም፣ ጾመ ድጓ አይነት መጻህፍት ናቸው። በኋላ ላይ ደርግ መጻህፍቱን ሰብስቦ አቃጠላቸው።
ጠያቂ፡- እንዴት ወደ ለቀማ ሥራ መጡ?
አቶ ሸዋንግዛው፡- መጀመሪያ ለቀማ (Proof) አንሺ ነበር፤ ከዚያ ተወዳድሬ ነው “1ኛ ለቃሚ” ተብዬ ወደ ለቀማ ክፍል የተዘዋወርኩት።
ጠያቂ፡- “ለቀማ” ሲባል ግን ምን ማለት ነው? (በኮምፒውተር ዘመን የመጡት ልጆች አያውቁትም ብዬ ነው የጠየቅሁዎት)
አቶ ሸዋንግዛው፡- “ለቀማ” ሲባል ጽሑፍ ከጋዜጠኞች ይመጣል አይደል፣ ጋዜጣም ይሁን መጽሐፍ እያንዳንዱ ፊደል በእጅ ተለቅሞና ተገጣጥሞ ነው ጽሁፍ የሚሆነው። እያንዳንዱ ፊደል በብረት ተቀርጿል። ያን ጊዜ ኮምፒውተር  የለም። እንዳሁኑ በአንዴ ተረረም ተደርጎ አይጻፍም። ለምሳሌ የአንተ ስም ማን ነው?
ጠያቂ፡- ቴዎድሮስ፤
አቶ ሸዋንግዛው፡- “አ” ”ቶ” ”ቴ” ”ዎ” ”ድ” ”ሮ” ”ስ” እየተባለ እያንዳንዱ ፊደል በብረት መያዣ እየተለቀመ ተገጣጥሞ ነው “አቶ ቴዎድሮስ” የሚባለው። በእያንዳንዱ ፊደል መሀል ደግሙ ቃላቱ እንዳይገጣጠሙ ፊደሎቹን የሚያራርቅ ሌላ ብረት የተቀረጸ  አለ። ፊደሎቹን  የሚቀርጽ ብረት አለ። ማሽኑ የቀረጸውን እየወሰድን እንዘረዝራለን። ከ”ሀ” እስከ “ፐ” ድረስ ያለው ፊደል ይቀረጻል። ከዚያ በመልቀሚያ ፒንሳ እያዳንዷን ፊደል ልክ ይሁን ስህተት ለማወቅ ይታተምና ለአራሚዎች ይሰጣል። አራሚዎቹ ደግሞ የተሳሳተውን ቃል እያረሙ ይጽፋሉ። እሱን አይተን እኛ ደግሞ የተሳሳተውን እናርማለን፣ የጎደለውን እንሞላና እንደገና እንዲታረም እንሰጣለን። ለምሳሌ “ቴ” የሚለው “ቱ” ተብሎ ቢሆን “ቴ”ን ከተቀረጸው ፊደል መሀል ሰፍተን አውጥተን በማስገባት “ቱ”ን ደግሞ ከመሰሎቿ ጋር እንቀላቅላታለን። አራሚዎቹ ሲፈርሙበት ነው ወደ ህትመት የሚሄደው። ስራው በጣም አድካሚ ነው። አሁን እኮ ቀልድ ነው፣ ስራ አይደለም። የእኛ ግን የጉልበት ስራውስ፣ ማታ 4፡00 ሰዓት ገብተን ጠዋት 2፡00 ሰዓት ነው ጨርሰን ወደ ቤት የምንሄደው።
ጠያቂ፡- እያንዳንዱ ጋዜጣ በእንዲህ አይነት ነው የሚታተመው?
አቶ ሸዋንግዛው፡- ጋዜጣም ሆነ መጽሐፍ እንዲህ ነው። “አዲስ ዘመን” “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ”፣ “በሬሳ”፣ “አልዓለም”  አለ። ወደ 12 ጋዜጦች አሉ-ብርሃንና ሰላም የሚታተሙ። በአንድ ሌሊት ሁለት ሶስት ጋዜጦች ሊኖሩ ይችላሉ። ሁሉም በዚህ መልኩ ተለቅመው ታርመው ነው የሚሰሩት። በተለይ “አዲስ ዘመን” ሲታተም ከመንግስት የሚመጣ አስቸኳይ ዜና ሊኖር ይችላል። እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት እና ሰባት ሰዓት ልንጠብቅ እንችላለን። ይህ ሁሉም ሆኖ ጋዜጣው ለጠዋት መድረስ አለበት። ጋዜጣው ጠዋት 12፡00 ሰዓት መከፋፈል አለበት።
ጠያቂ፡- ሁሉም ጽሑፍ ጥንቃቄ ቢፈልግም አንዳንድ ጊዜ የመንግስት አዋጅና መመሪያዎች ሲሆኑ ምን አይነት የተለየ ጥንቃቄ ታደርጋላችሁ? ስህተት ቢፈጠር በቀላሉ ማረሚያ  ወጥቶ ብቻ የሚበቃ ላይሆን ይችላልና፤
አቶ ሸዋንግዛው፡- ሁሌም ጥንቃቄ አለ። የመንግስት አዋጅ ሲሆን ደግሞ የበለጠ ጥንቃቄ ይኖራል። ምን ሆኖ ስህተት ሊፈጠር ይችላል። አንድ ጊዜ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለው “ኢትዮጵያ ትውደም” ተብሎ ወጥቷል። “ቅ” መሆን የነበረበት ፊደል “ው” ሆኖ ወጣ። የትርጉሙ ልዩነት ግን የትየለሌ ሆነ። እንደዚህ ሆኖ ወጣ እንግዲህ። ሶስት ቦታ እኮ ነው የሚታየው፤ ግን አለፈ። ሌሊት እንቅልፍ አለ፣ ድካም አለ።
ጠያቂ፡- “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለው “ትውደም” ሆኖ ሲወጣ እናንተ ላይ ምን ደረሰባችሁ?
አቶ ሸዋንግዛው፡- ያን ጊዜ ሆን ብሎ የሚተናኮል የለም። ስህተቱ በድካም የተነሳ እንደተፈጠረ ስለተረዱ እግዜር ይስጣቸው ምንም አላሉኝም።
ጠያቂ፡- ማኛውም አዋጅ ከህዝብ ቀድሞ እናንተ ጋር ይደርሳል። ይህ መሆኑ እናንተ ላይ ምን ጫና ይፈጥራል?
አቶ ሸዋንግዛው፡ በደርግ “እነ ሻምበል ሸዋፈራሁ ከነግብረ አበሮቻቸው ተደመሰሱ!” የሚል ዜና ማታ ላይ መጣ። ገና ሰው አልሰማውም ዜናውን። ዜናውን እያየን እንሰራለን እንጂ ስለ ዜናው ማውራት አንችልም። ማንም ማንንም ቀና ብሎ አያይም። ውስጣችን ደህንነቶችና ኢሰፓዎች አሉ፤ ይከታተሉናል። እርስ በእርስም ማውራት አንችልም፤ ያስቀጣል፤ አንዳንድ ጊዜ እዚያው ማተሚያ ስራ ላይ ያደረ ሰው ትልቅ ዜና ታትሞ ሳያውቀው ጠዋት ከሰው እኩል ሊያየው ይችላል። እርስ በእርስ “እንዲህ ሆነ´ኮ” እያልክ አታወራም።
ጠያቂ፡- በወቅቱ እናንተ ጋር ከሚታተሙ ጋዜጦች ይበልጥ ትኩረትና ጥንቃቄ የሚደረግበት ጋዜጣ የቱ ነው?
አቶ ሸዋንግዛው፡- “ሰርቶአደር” ጋዜጣ ነው። ሰርቶአደርን የሚያነቡት ትልልቅ የመንግስት ባለስልጣናትና የኢሰፓ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ አይናችንን ከጋዜጣው ላይ ሳንነቅል ነው የምንሰራው። ሶስት አራቴ ይታረማል። በእርግጥ እንደዚያም ሆኖ ስህተት አይወጣም ማለት አይደለም።
ጠያቂ፡- አሁን የለቀማ ስራ ሙሉ በሙሉ ከስራ ውጭ ሆኗል?
አቶ ሸዋንግዛው፡- እንደዚያ ነው እንግዲህ። ማህተም ቀረጻ ላይ ብቻ ነው። ሌላ የለም። “ኧረ እንኳንም ጠፋ!”
ጠያቂ፡- የለቀማ ስራን እንዲጠሉት ያደረገዎት ምንድን ነው?
አቶ ሸዋንግዛው፡- ሁሉም ነገሩ! ጉልበትህን ይጨርሰዋል፤ ሰውነትህን ይበላዋል፤ የአይን ጸር ነው። ደግሞ በዚህ ላይ አይንህን ሙጥጥ ያደርገዋል። እኔማ ጥላቻዬ ለጉድ ነው። እንግዲህ ጡረታ አንድ ሶስት አመት ሆነኝ። እዚህ የምኖርበት አካባቢ አንድ የግል ማተሚያ ቤት “እንቅጠርህ” ሲሉኝ “እምቢኝ" ነው ያልኳቸው። ማተሚያ ቤት ውስጥ ስገባ እንኳን ትዝታዬ ጥሩ አይደለም። እኔ እንግዲህ መ/ቤቴን በጣም እወደዋለሁ። ሕይወቴን የኖርኩበት ነው። ልጆች ወልጄ፣ አስተምሬ ለቁምነገር ያበቃሁበት ቤት ነው። ለቀማን ሳስታውስ ግን እንደመታመም ነው የሚያደርገኝ። የቀን ስራ ሳይጨመር 41 ዓመት ተኩል በዚህ ኖርኩኮ። አይበቃኝም!?
ጠያቂ፡- ኮምፒውተር እንደመጣና ለቀማ ስራ እንደቀረ የእናንተ ክፍል አባላት ተደሰቱ ወይስ ቅር አላቸው?
አቶ ሸዋንግዛው፡-  ለቀማ ክፍል ለጊዜው ደስ ያለው የለም። እንደውም ተከፍተናል። የኮምፒውተር መምጣት እኛን ከስራ ውጭ ሊያደርገን ሆነ። ሁሉም ስጋት ውስጥ ገባ። በኋላ ሽግሽግ መጣ። ለቀማ ክፍል በድርጅቱ ውስጥ በጣም ይፈራል። “6ኛው ክፍለ ጦር” ነበር የሚባለው። የጋዜጣ፣ የመጽሐፍና መጽሔት ስራን በዋነኝነት የሚሰራው ያ ክፍል ስለሆነ “ቶሎ ፈጽሙላቸው” ነው የሚባለው። 4ኛ ፎቅ ይፈራል፤ ይሰማል። “ከስራ እንቀነሳለን” የሚል ስጋት ፈጠረብን። ዘመናዊ ትምህርት የተማሩት ለኮምፒውተር ስልጠና ገቡ።
ጠያቂ፡- ሰልጥነው ሲወጡስ ያ ሁሉ የጉልበት ስራ፣ ሸክሙ፣ ድካሙ ቀርቶ ጉዳዩ ሁሉ አንድ ኮምፒውተር ላይ የሚያልቅ ሲሆን ሰልጥነው የመጡት ምን ተሰማቸው? (ከበፊቱ ጋር ሲያነጻጽሩት)
አቶ ሸዋንግዛው፡- አሄሄሄ… እሱንማ… ማን ነበረ ስምህን ያልከኝ?
ጠያቂ፡- ቴዎድሮስ
አቶ ሸዋንግዛው፡- ይኸውልህ አቶ ቴዎድሮስ…. እነሱማ እንደታምር ቆጠሩት። አንድ ሰው ጉልበትህን ሲበዘብዝ ቆይቶ ነጻ ስትወጣ እንዴት ነው? ጭራሽ ለቀማ ክፍልን ማየት እስከመጥላት ደረሱ። እውነት አላቸው ደግሞ፤ ከባርነት ነው ነጻ የወጡት። 8 ወር ነው የሰለጠኑት። ወይ 10 እና 12 ይሆናሉ የሰለጠኑት።
ጠያቂ፡- እርስዎ እንግዲህ የኖሩት ለቀማ ላይ፣ ቃላት ማረም ላይ ነው። አሁን ጡረታ ወጥተውም ቢሆን፤ የሆነ ቦታ ሲሄዱ የተጻፈ ሲያዩ፤ ከሌላው በተለየ ቃላት ላይ አያተኩሩም?
አቶ ሸዋን ግዛው፡- አተኩራለሁ እንጂ። ጋዜጣ ላይም ቶሎ ቶሎ የቃላቶች ስህተት ይታየኛል። ሌላው ዝም ብሎ አንብቦ ያለፈውን እኔ “አይ እንዲህ መባል ነበረበት እንጂ” እላለሁ። ዘመኔን የገፋሁበት ስለሆነ ስህተቱ ይታየኛል። እድሜዬን ሙሉ ቃላት ሳስተካክልና ስህተት ስሰራ ነው የኖርኩት። ይኸውልህ የለቀማ ስራ ያንገሸግሸኛል አይደል? እሱ ግን ለጥራት ይሆናል። ከለቀማው ኮምፒውተሩ ለብዙ ስህተት የተጋለጠ ነው። እንደውም በኋላ ላይ ለምደውት ነው እንጂ ፊትማ ስህተት በስህተት ነበር። ኮምፒውተር ሲመጣ ለቃሚውን ከድካም ቢያድነውም፣ አራሚውን ግን የባሰ አድካሚ ነው የሆነበት። ብዙ ስህተት ይኖረዋላ።
ጠያቂ፡- በለቀማና በኮምፒውተር መካከል ያለው መስረታዊ ልዩነት ምንድን ነው? (ከእናንተ ከሰራኞቹ አንጻር)
አቶ ሸዋንግዛው፡- ስማ እንጂ አቶ ቴዎድሮስ፤ ምንም አንድ የሚያደርገው ነገር የለም። ኮምፒውተሩ ከተበላሸ ምን ይሆናል? ከተበላሸ ደግሞ ይሰራል። ይሄ እኮ በየቀኑ የብረቱ ፊደል ይቀረጻል። እስከ 3፡00 ሰዓት ሰርቼ እሱን መዘርዘር ነው። ለአንዱ ጋዜጣ ወይም መጽሐፍ የሆነው ፊደል ለሚቀጥለው ብዙም አያገለግልም። እያንዳንዱ ሆሄ በየቀኑ እንደ አዲስ ተቀርጾ ነው። እሱን መዘርዘርና በየሳጥኑ ማስቀመጥ አድካሚ ነው። በየቀኑ ፊደል መቅረጽ፣ መዘርዘርና ማስተካከሉ ብዙ ጉልበት ይጠይቃል። የመጀመሪያው ስራችን ካዙ (ሳጥኑ) ውስጥ ፊደሎቹን መሙላት ነው። እራሱን የቻለ የተሰራባቸውን ፊደል እየጠለቀ ፊደል የሚቀርጽ ክፍል አለ።
ጠያቂ፡-የአሁን ከጊዜ ልጆች ላይ ቃላትን በተገቢው ቦታ  አለመጠቀም፣ የአማርኛ ቃላትን አለማወቅ ይታያል። “ሁ” የሚለው ፊደል በ”ው” ተተክቶ ሲገለጽ ይታያል። “አደርጋለሁ” በማለት ፋንታ “አደርጋለው” ሲባል በተደጋጋሚ ይታያል። በ”ው” እና በ”ዉ” መሀከል ልዩነት ሲደረግ አይታይም። እርስዎ ይህንን ሲያዩ ምን ይላሉ?
አቶ ሸዋንግዛው፡- ያው ምን እላለሁ፤ አንዳንዱ ጋር ሄደህ አታርምም። ብርሃንና ሰላም የሚመጡትን ለማረምና ለማስካከል እንሞክራለን። የሚባውንና የማይባውን እናሳያለን። ሌላውን ግን እያየህ ማለፍ ነው። መቼም መሳሳት ሳይሆን ስህተት መሆኑን እያወቁ ዝም ማለት አስቸጋሪ ነው። ግን ምንም ማድረግ አትችልም።
ጠየቂ፡- እንደው አቶ ሸዋንግዛው ቅድም ስለ ፊደል ቀረጻ ሲያነሱ ከ400 ገጽ በላይ የሆነ መጽሐፍ አለ። ለምሳሌ በዚያ መጽሐፍ ውስጥ አንድ ሆሄ (“ላ”፣ “ካ” ወይም ሌላ) አንዱ ገጽ ላይ ከ50 በላይ ሊኖር ይችላል። ስለዚህ 400ው ገጽ ላይ ይህች ሆሄ ከ50 በላይ ትገባለች። በዚህ ስሌት አንዷ ቃል ከ2000 በላይ ማለት ናት። ይህ ሁሉ ይቀረጻል ማለት ነው?
አቶ ሸዋንገዛው፡- አዎ! ሌላ ምንም ምርጫ የለም። በየጊዜው በጎደለው  እየተሞላ ይሄዳል። ፊደል የሚቀርጸው ማሽን ስራ አይፈታም። ፊደል ሲቀርጽ ነው የሚውለው።
ጠያቂ፡- በየቀኑ?
አቶ ሸዋንግዛው፡- አዎ በየቀኑ! እሱን እኮ ነው የምልህ። አድካነቱም እሱ ላይ ነው። አሁን ለሚመጡ ልጆች ሊገባቸው አይችልም። አንዱ ኮምፒውተር ይሄን ሁሉ ይሸፍነዋል። የዛ መጽሐፍ ህትመት ተጠናቆ ሌላ መጽሐፍ ሲመጣ፣ ያ ሁሉ ፈርሶ እንደገና ነው የሚሰራው። የብረት ፊደሎቹን ደርድረህ ከቦታ ቦታ መሸከም ቀላል ስራ መሰለህ? አድካሚ ነው። ጉልበታችንን እንክት አድርጎ ነው የበላው። ድካሙን መለስ ብዬ ሳስበው ያንገፈግፈኛል። ድካሙ እንዲህ አይምሰልህ። እዚያው ማሽኑን እየተደገፍን እንቅልፍ ይዞን ይሄዳል። ኮምፒውተር ሲመጣ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ቤት ማደር የጀመርነው። የእኔ ቤት እንግዲህ መሳለሚያ ነው። ማታ 4፡00 ሰዓት ሰርቪስ መጥቶ ነው የሚወስደኝ። አንዳንድ ጊዜ ሰርቪሱ ይቀርና ከመሳለሚያ 4 ኪሎ በእግሬ የምሄድበት ጊዜ አለ። በአንድ ሌሊት 3 ቦታ በአብዮት ጥበቃዎች ተይዤ አውቃለሁ። ጠብመንጃም ተደግኖብኛል። በደርግ ጊዜ ሰዓት እላፊ አለ፤  በየመንገዱ ያስቆሙሃል። እኛ በስራው ጸባይ “ከሰዓት እላፊ ነጻ” የሚል ወረቀት ተሰጥቶን የያዝን ቢሆንም አንዳንዱ አብዮት ጥበቃ አይሰማህም። ወረቀቱን እያየም ስልጣኑን ለማሳየት ያንገላታሃል። በእውነት መከራ አሳልፈን ነው እዚህ የደረስነው። እኔ በበኩሌ ያንን ሁሉ አልፌ አሁን በህይወት ኖሬ ይህንን ታሪክ መናገሬ ራሱ እንደ ትልቅ በረከት ነው የምቆጥረው። አምላኬን አመሰግነዋለሁ።
ጠያቂ፡- እኔም ለፈቃደኝነትዎ እርስዎን አመሰግናለሁ።
ምንጭ፡- (የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት 100ኛ ዓመት መፅሔት)


Read 986 times