Saturday, 29 January 2022 00:00

የባንዲራዎቻችን ወግ

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

"--አመራሮቹ አንዳንዴም ቢሆን ትንፋሻቸውን ሰብስበው ሲቀመጡ እንደ ቀልድ የጀመሩት ነገር ከምር ሲሆን የታዘቡ ይመስላል። በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም ክልሎች ባንዲራዎቹን በሕገ መንግሥታቸው እውቅና አልሰጡም። ግራ የገባቸው ሕግ አውጪዎች በሚጠቀሙባት “ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ዓረፍተ ነገር አልፈውታል። --"
           
              የባንዲራ ነገር ብዙ አከራክሮናል፥ አወዛግቦናል፤ ለሕይወት መጥፋት ምክንያት ሲሆንም አይተናል። ሀሳቡ በትክክል ምን እንደሆነ ግልፅ ባይሆንም የባንዲራ ቀንንም እናከብራለን። እንደ ክልሎቻችን ቁጥር ከሆነ እስካሁን ደርዘን የሚሞሉ ባንዲራዎች አሉን። የክልልነት ጥያቄ ያቀረቡትም ወደፊት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡ የባንዲራ ጉዳይ በተለይም በአሁኑ ወቅት ከፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር በፅኑ እየተቆራኘ መጥቷል። "በፌደራል መንግሥት ደረጃ በሀገሪቱ ባንዲራ ላይ እንዲያርፍ የተቀመጠው ዓርማ የፖለቲካ ሥልጣንን በያዙና ሕጉን እንዳሻቸው በሚፅፉ ቡድኖች የተቀረፀ ነው፤ እኛን አይገልፀንም" ከሚለው ጀምሮ "የሰይጣኖች ሲያልፍም የ“ኢሉሚናቲ”፥ “ፍሪሜሶን” እና ገለመሌ የሚባሉ ድርጅቶች ምልክት ነው; ሲባል አድምጠናል። የባንዲራ ጉዳይ ከስሜት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ በአዋጅና በመመሪያ ዕልባት መሥጠት አስቸጋሪ ነው። መደማመጥና ለውይይት በር መክፈት በጊዜ ሂደትም ቢሆን መሃል መንገድ ላይ ያገናኝ ይሆናል።
በሀገራችን በርካታ ባንዲራዎች ብቅ ያሉት ከ1983ቱ የመንግሥት ለውጥ ጋር ነው። በወቅቱ 14 ክልሎች ተመስርተው የነበረ ሲሆን ያኔ ሁሉም መለያው ይኑራቸው አይታወቅም። ነገር ግን በ1987ቱ ሕገ መንግሥት መሠረት፤ ዘጠኝ ክልሎችና ሁለት የከተማ መስተዳድሮች ሲቋቋሙ ሁሉም ባንዲራ አግኝተዋል።
በዚህ ፅሁፍ የምንዳስሳቸው ሁለት ባንዲራዎች ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ፈጠራ ናቸው። ከድርጅቶቹ ህልውና በፊት ምንም ታሪክ የላቸውም።
ሕወሓት ዓርማና ባንዲራውን የት እንደቀረፀው፣ ምንስ ማንፀባረቅ ፈልጎ እንዳወጣው ማጣቀሻ ማግኘት አልተቻለም። ዓርማውን ቢያንስ ሁለት ጊዜ መቀየሩ ግን እርግጥ ነው። ኮከቧም ብትሆን መጀመሪያ ላይ ቀይ ነበረች። እንዴት ወደ ቢጫነት እንደተቀየረች አይታወቅም። የሆኖ ሆኖ ግን ክልሉን ሲቆጣጠር የድርጅቱን ባንዲራ የክልሉ አድርጎታል። የፖለቲካ ድርጅትና መንግሥት በተደበላለቁባት ሀገር ማንም እንደዚህ አይነቱን እርምጃ አይገዳደርም።
ኢህዴን የተባለው የሕወሓት አማርኛ አፍ በሕዳር 1973 ዓ.ም ሲመሰረት ተመሳሳይ ዓርማና ባንዲራ ተውሷል። ልዩነቱ የመደቦቹና የቅርፆቹ ቦታ መቀያየር ነው። ኢህዴን በኋላ ላይ ብአዴን ተብሎ ሲያስተዳድር እንደ ፈጣሪው ሁሉ የራሱን ባንዲራ የክልሉ አድርጎታል።
ሁለቱ ባንዲራዎች በአካባቢው ካሉት እጅጉን ይለያሉ። የመለያው ምክንያት ከማንነታቸው፣ ከባህላቸውና ታሪካቸው ጋር የሚያያዙበት ክር አለመታየቱ ነው። ድርጅቶቹ በተቋቋሙባቸው ዓመታት ጎረምሳ ማርክሲስቶች እንደ ዓርዓያ ይወስዷቸው የነበሩ ሀገሮች ኮከብ፥ ማጭድና መዶሻ መለያቸው ነበር። ከዓርማዎቹ፥ ድርጅቶቹ ከተቋቋሙበትና ይዘውሯቸው ከነበሩ ግለሰቦች ሰብዕና በመነሳት ስለ ባንዲራዎቹ መላምት መስጠት እንችላለን።
ከተለያዩ ሀገሮች ባንዲራዎች ጋር ሲተያዩ፣ የኛዎቹ ድርጅቶች ከቻይና በተለይም ከቬትናም ጋር ግልባጭ እስኪመስሉ ድረስ ተመሳሳይነት አላቸው። የሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል ምናልባት አህጉሮች ሁሉ ተጣብቀው አንድ ነበሩ በሚባልበት በጎንድዋና ዘመን ካልሆነ በስተቀር በምንም አይነት ከሩቅ ምሥራቅ ሀገሮች  ጋር ሊገናኝ አይችልም። በወቅቱ በገነነው ፖለቲካ ምክንያት ሶቪየት ሕብረት ከደርግ ጋር በማበሯ #ከኔ በላይ ኮሚኒስት ላሳር; የሚሉት ነፃ አውጪዎች፣ ሶቪየትን “ሶሻል ኢምፔሪያሊስት” እያሉ ሲተቹ እንደነበር ስለ ፓርቲዎቹ የተፃፉ ታሪኮች ያትታሉ፡፡ ስለዚህ ማጭድና መዶሻ በባንዲራዎቹ ላይ ያለመገኘቱ ምክንያት ይኸው ሊሆን ይችላል። በአንፃሩ ደግሞ ደርግ ልዩነታቸው ግልፅ ያልሆኑ ኢማሌድህ፥ ኢሰፓአኮ፥ ኢሰፓ የሚባሉ ድርጅቶችን በሚያመርትበት ወቅት የሚያወጣቸው ዓርማዎች በማጭድና መዶሻ ያበዱ ነበሩ።
ስለዚህ "እኛ የገበሬ አብዮት ነውና የምናካሂደው ለቻይናና ለቬትናም እንቀርባለን" በሚል ይመስላል የቢጫው ኮከብ ተመራጭነት። የቻይና ባንዲራ በቀይ መደብ ላይ ሆኖ አንድ ትልቅና እሱን ያጀቡ አራት ቢጫ ኮከቦች አሉት።  በዊከፒዲያ ላይ ስለባንዲራዎቹ እንደተፃፈው፤ ቀዩ መደብ በሀገሪቱ የተካሄደውን የኮሚኒስት አብዮት የሚያሳይ ሲሆን ትልቁ ኮከብ ፓርቲውን ይወክላል። እሱን ያጀቡት አራቱ ኮከቦች የቻይና ሕዝቦች በኮሚኒስት ፓርቲው ዙሪያ መሰባሰባቸውን ያሳያል።
በአንፃሩ ደግሞ የቬትናም ባንዲራ በቀይ መደብ ላይ ሆኖ አንድ ቢጫ ኮከብ መሀሉ ላይ አለው። ቬትናም ቢጫ ቀለምን የመጠቀም የረጅም ዘመን ታሪክ እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለማንኛውም ግን የኛዎቹ ክልሎች ባንዲራዎቹን እንደ ቀልድ ጀምረዋቸው ሳያውቁት ብዙ እንደተጓዙ የገባቸው ይመስላል። በአማራው ክልል ከካድሬዎቹ በስተቀር ድሮም ከምር የቆጠረው ያለ አይመስልም። ባንዲራው እንደሚቀየር በተነገረ ጊዜ እንኳ ብዙ ሰው “የትኛው?” ያለ ነው የሚመስለው። በአንፃሩ ግን ትግራይ ውስጥ ከምር ተወስዷል። በአልባሳትና በተለያዩ ቁሳቁሶች አንዳንዴም የጋማ ከብቶችም ላይ ተቀብቶ ይታያል። እንደዛም ሆኖ አልፎ አልፎ የባንዲራውን ጉዳይ የሚያነሱ ቢኖሩም ድምፃቸው በጫጫታው ተውጦ ይቀራል።
አመራሮቹ አንዳንዴም ቢሆን ትንፋሻቸውን ሰብስበው ሲቀመጡ እንደ ቀልድ የጀመሩት ነገር ከምር ሲሆን የታዘቡ ይመስላል። በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም ክልሎች ባንዲራዎቹን በሕገ መንግሥታቸው እውቅና አልሰጡም። ግራ የገባቸው ሕግ አውጪዎች በሚጠቀሙባት “ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ዓረፍተ ነገር አልፈውታል።
የኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት ግን ክልሎቹ በሕጋቸው እንኳ ለማስገባት ድፍረት ያጡባቸውን ባንዲራዎች ዘክሯቸዋል። መታሰቢያም አውጥቶላቸዋል። በዚህ በመሴንጀርና ቴሌግራም ዘመን ሰዎች ቴምብር ትዝ ሊላቸው ቀርቶ ደብዳቤ እንኳን አይልኩም የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል። መቼ ነው ለመጨረሻ ጊዜ ፖስታ ቤት የሄድነው? ግን ቴምብሮች ከዛ የራቀ ትርጉም አላቸው። ሃገሮች ለኑሮ ዘይቤአቸው፥ ለባህላዊ እሴቶቻቸው፤ ለዕደ ጥበቦች፥ ለመልክዓ ምድራቸው፥ ለሰው ሀብቶቻቸውና ለመሳሰሉት ዕውቅና የሚሰጡባቸው መንገዶች ናቸው። ቴምብር ላይ መውጣት ትርጉም አለው።
የአማራ ክልል ባንዲራ ምንም ይሁን ምን ምክር ቤቱ ጉዳዩን ማየት መቻሉ በራሱ ጥሩ ጅምር ነው። ሌሎችንም “ተስማምተን ነው እንዴ ያወጣነው?” የሚል ጥያቄ እንዲጠይቁ ያደርጋቸው ይሆናል። እያወዛገቡን ያሉትም ዓርማዎች ምንም በበቁ ሙያተኞች ቢቀረፁ ለሕዝቡ ረቂቅ ከሆኑ “እኮ ምን ለማለት ነው?” ከሚለው ሴራ ፍለጋ ማምለጥ አይችሉም።

Read 427 times