Saturday, 29 January 2022 00:00

ረዳት ፕሮፌሰር ትንግርቱ ገ/ፃዲቅ በተለይ ለአዲስ አድማስ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

• “ወራሪው ሃይል የራሱን ህዝብ አንቆ ለመግደል እየታገለ ያለበትወቅትነው”
 • "ህገ መንግስቱ ለጋራ ውርደታችን መንስኤ መሆኑ አያጠራጥርም"

          በክብረ መንግስት አዶላ ተወልዶ ሀዋሳ ከተማ ነው ያደገው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ተናግሮ ሰውን የማሳመን ብቃት እንደነበረው አብሮ አደጎቹ ይመሰክራሉ:: በአሁኑ ወቅት በጅጅጋ ዩኒቨርስቲ የሶስዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆን ባለፉት 10 ዓመታት በዩኒቨርስቲው ውስጥ በተለያዩ ሀላፊነቶች አገልግሏል፡፡ ከሃላፊነቶቹ መካከል የዩኒቨርስቲው ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳሬክተር፣  የማህበራዊ  ሳይንስ ኮሌጅ ዲን፣ የስደተኞች ጥናት ተቋም ዳይሬክተርና የትምህርት ክፍል ሀላፊ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በዲያስፖራ ኢንጌጅመንትና በትምህርት ላይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ያሉት ሲሆን፣ በስደትና ፍልሰት እንዲሁም በአገር ውስጥ መፈናቀል ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን ያደርጋል፡፡ ለጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ሶስት ትልልቅ የስትራቴጂክ ፕላኖች ከሰሩት ምሁራን አንዱ ነው፡፡
የዛሬ እንግዳችን በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የሶስዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር የሆነው ትንግርቱ ገ/ፃዲቅ፤ በአሁኑ ወቅት በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) “ነጋሪት” በተሰኘ ዕለታዊ ፕሮግራም ላይ ከህግ ምሁሩ ውብሸት ሙላትና አስግደው ሽመልስ ጋር በመሆን የሚያቀርበው  ወቅታዊ የፖለቲካ ትንታኔ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በባህርዳር ተገኝታ ከረ/ፕ ትንግርቱ ገ/ፃድቅ ጋር  በወቅታዊ ጉዳዮች፣ በአገሪቱ ስጋቶችና ተስፋዎች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርጋለች። እነሆ፡-




                በመጀመሪያ አሁን ያለው ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ በአንተ እይታ ምን እንደሚመስል ብትገልፅልኝ?
የሀገሪቱ ሁኔታ ሲባል ብዙ ሰው የሚያየው በጠቅላይ ሚኒስትሩና በህዝቦች መካከል ያለውን ነው፡፡ ወይም ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያው ለእለት ጉርሳችን የሚሆን ወሬ ይዞልን ሲመጣ እሱን ነው የምናየው፡፡ ነገር ግን የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ የፖለቲካ ጎኑ ብቻ አይደለም የሚታየው፡፡ ማህበራዊም ፖለቲካዊም የኢኮኖሚና ዲፕሎማሲ ሁኔታዎችም መታየት አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳይ ነው የምናየው ማለቴ ነው፡፡ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ታየዋለህ ስትይ ፖለቲካዊ ሁኔታውን ከሆነ ፖለቲካዊ ሁኔታው በብዙ ለወጦችና የለውጥ ሂደቶች ውስጥ ያለና አገሪቱ በብዙ አጣብቂኝ ውስጥ የተከበበችበት፣ በአንድ በኩል ከሰሜን የተነሳው ወራሪ ሀይል በራሱ የሀገር መከላከያ  ሰራዊት ላይ ጦርነት የከፈተበት፣የብዙ ሀገራትን አጀንዳ ተሸክሞ ሀገርን ለማፍረስ እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን አሸማቅቆና ሀገራቸውን  ነጥቆ ራሱ ሀገርን ለመምራት የሚፍጨረጨርበትና በዚህም የህልውና ጦርነት የምናደርግበት ወቅት ነው፡፡
ሁለተኛ ህዝቦች በማንነታቸው ተፈርጀው፣ በተለይ የአማራና የአፋር ህዝብ የፌደሬሽኑን ጦርነት በጫንቃቸው ላይ ተሸክመው፤ በአማራና በአፋር የህይወት መስዋዕትነትና በመከላከያ ሰራዊት ተጋድሎ ፌደሬሽኑን ለማዳን የተቻለበት ወቅት ላይ ነን፡፡ በሚቀጥሉት ሁለትና ሶሰት ወራት ምን አይነት ነገር እንደሚኖር ደግሞ አብረን የምናየው ነው፤ ምክንያቱም ወያኔ እስካለ ጦርነት አለና፡፡ እንደዚያም ቢሆን ግን ብዙ ዋጋ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ሁኔታ አልፏል፡፡ በተለይ እነዚህ ሁለት ክልሎች ደግሞ (አማራና አፋር) ባለፉት 13 እና 14 ወራት ከፍተኛ ጫና የተሸከሙበት ነው አማራ ት/ቤት አልሰራም ባንጻሩ ደግሞ ሁለትና ሶስት ሺህ ት/ቤቶች ወድመውበታል፡፡ ብዙ ዩኒቨርስቲዎች አልተሰሩለትም፤ ያሉትም ወድመውበታል፡፡ መንገድ አልተሰራለት፤ም ብዙ መንገዶችን አጥቷል!! ብዙ ቁጥር ያላቸው የጤና ተቋማትም ወድመውበታል።
በአፋር እንደዚሁ በጣም ከፍተኛ የሰብአዊ ኪሳራና በርካታ የመሰረተ ልማት ውድመት ተከስቷል፡፡ ይህ ከመሆኑ አንጻር እነዚህ ህዝቦች ላይ በጣም ከፍተኛ ግፍ የተፈፀመበት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የትግራይ ህዝብ በወረሪው የሽብር ቡድን ወደማይፈልገው የወራሪው ቡድን ጭሰኝነት  ውስጥ ገብቷል፡፡ በዚህም ትግራይ በታሪኩ ካደረጋቸው ጦርነቶች ሁሉ በከፍተኛ ሁኔታ ልጆቹን ያጣበትና እጅግ የከፋ እልቂት የተስተዋለበት፣ ህዝቡ በኢኮኖሚ የደቀቀበት፣ማህበራዊ ግንኙነቱ በከፍተኛ ደረጃ የተስተጓጎለበትና ምናልባትም የወራሪው ሀይል የራሱን ህዝብ አንቆ ለመግደል እየታገለ ያለበት ወቅት ነው፡፡
በመሀል ሀገር ደግሞ እንደምትመለከችው ብዙ አይነት ፍላጎቶች አሉ፡፡ ይሄ መንግስት ምርጫ ቢያሸንፍም ገና ስልጣኑን ለማደላደልና ለማጠናከር እየታገለ ያለ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ስልጣኑን ለማደላደልና ለማጠናከር 10 ዓመት ፈጅቶበታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣንን በቀላሉ ማደላደል አይቻልም፡፡ አሁንም ይሄኛው መንግስት በጥረት  ላይ ነው ያለው፡፡ ሙሉ ለሙሉ በደህንነትም ሆነ በዲፕሎማሲው የበላይነትን ለመያዝ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የእነ በረከት የትህነግ መዋቅር ሙሉ በሙሉ በብዙ ክልሎችና የመንግስት መስሪያ ቤት አሰራሮች ላይ እንዳለ ተቀምጦ ያለበት እንደመሆኑ እነዛን  ለመቀየር ብዙ ጥረት እየተደረገ  ነው። በነዚህ ሂደቶች መንግስት ራሱ ሊታነቅ የሚችልበት እድል አለ፡፡ ምን ማለቴ ነው? ከውስጥ የተለያየ አጀንዳ እየተሸከሙ በሀገርና በህዝቦች መካከል በመቆመር፣ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት መንግስት እንዲፍረከረክ የማድረግ፣ በውጭም ላለውም ደካማ እንደሆነ ለማሳየትና ለማጋለጥ፣ ከዚህም ጎን ለጎን የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅም ሆነ ከዚህ በፊት ያሳደጋቸውን ወላጅ አባታቸውን ትህነግንም ለመጦር በዚህ ደረጃ ዋጋ እየከፈሉ ያሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ ከውጪም ከውስጥም ብዙ አይነት ጫናዎች ያሉበት ነው፡፡ እንደምታውቂው ዓለም አቀፍ ጫናውም ቀላል አይደለም፡፡ እንደገና ያለንበት ቀጠና የሱዳን አለመረጋጋት በራሱ የተለየ ተፅዕኖ ይፈጥራል፣ በሌሎች ሀገራትም በሶማሊያ ከእነፎርማጆ ጋር የተፈጠረው ችግር አለ። እነዚህ ሁሉ ቀጠናዊ ችግሮች የየራሳቸው ተፅዕኖ ስላላቸው፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በአንድ ዳይሜንሽን ብቻ እንዲህ ነው ብለሽ በአጭሩ የምታስቀምጪው ሳይሆን በጣም ሰፊና አንድ መፅሀፍ ሊወጣው የሚችል ጉዳይ፡፡
ቀደም ሲል ትህነግ የሌሎች ሀገራትን አጀንዳ ተሸክሞ አገር ለማፍረስ የተነሳ ሀይል መሆኑን ጠቅሰሃል፡፡ ነገር  ግን ትክክለኛ የጦርነቱ አላማ ሀገር ማፍረስ ብቻ ነው ወይስ ተመልሶ ወደ ስልጣን የመምጣት ፍላጎት አለው? እንደምንሰማው ህወኃት በ1983 ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር መንግስት ሆኖ ሀገር የመምራት ዓላማ ስለነበረው አንዲትም መሰረተ ልማት አላወደመም። በአሁኑ ጦርነት የትምህርትና የጤና ተቋማትን፣ ፋብሪካና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን አውድሟል፡፡ ትህነግ የከፈተው ጦርነት ትክክለኛ ዓላማ ምን  ይመስልሃል?
ጦርነቱን የጀመረው አካል ብቻ ነው የጦርነቱን ዓላማም ሆነ  የጀመረበትን ምክንያት የሚያውቀው፡፡ ጦርነት የተከፈተበት ህዝብ ግን ራሱን የመከላከል ግዴታ ነው የሚኖርበት፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ ህገ-ወጥ ቡድኖችን አደብ ማስገዛትና ሀገርን መጠበቅ፣ ትውልድን ከጥፋት መታደግና የሀገርን ሀብቶች ከጥፋት ማዳን የመንግስታዊ መዋቅሩ ግዴታና የህዝብ ሀላፊነትም ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን ህወኃት በዋናነት ጦርነቱን የጀመረበት ምክንያትና ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ትግራይን ለቆ ከወጣ በኋላ አማራና አፋርን የወጋበት ምክንያት የተለየ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰሜን ዕዝን ያጠቃበት ዋነኛው ምክንያት ትግራይ ተከባለች በሚል ምርጫ አካሂዶ “ቅቡልነት ያለኝ መንግስት እኔ ነኝ፤ ሌላው ህገ ወጥ ነው” በሚል ጦርነት ከፍቶ ሰሜን ዕዙን  ሙሉ ለሙሉ አቅም እንዳይኖረውና ዋጋ እንዳይሰጥ በማድረግ፣ ከዚያም  ያንን የተተኳሽ ብልጫና  ያሰለጠኑትን 250 ሺህ ሰራዊት ይዘው ገስግሰው አዲስ አበባ ላይ የራሳቸውን መንግስት ለመመስረት ነበር፡፡ ያ በዋናነት ጦርነቱ የተጀመረበትና ሰሜን ዕዙ የተጠቃበት ምክንያት ነው፡፡ የስልጣን ናፍቆትና ጥማት እንደዚህ ዓይነት ካልኩሌሽን (ስሌት) ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡
ይሄ ህልማቸው ተቀለበሰ፡፡ በዚህ መልኩ ይቀለበሳል ብለው አላሰቡም። የመሳሪያ የበላይነታቸው በአየር ሀይል የበላይነት ተወስዶ፣ የዘረፉትና ያከማቹት መሳሪያ ሙሉ ለሙሉ ወደመባቸው፤ ብዙ ጥቃትም ደረሰባቸው፡፡ አዲስ አበባን እቆጣጠራለሁ ያለው ሀይል ፈርጥጦ ተንቤን በረሃ ገባ። እናም ያ  ለእነሱ ትልቅ የስነ ልቦና ስብራት የፈጠረ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ መከላከያ ላይ ያደረሱትን ጫና በተለያየ መንገድ ሰምተነዋል፡፡ በጀነራሎቹም በጠቅላይ ሚኒስትሩም በተደጋጋሚ ሲገለፅ ነበር። ወደ አማራና ወደ አፋር ሲመጡ ግን መርሳት የሌለብሽ፣ ወያኔ ጦርነቱን የጀመረው ብቻውን አቅዶ  ብቻውን አስቦ አለመሆኑን ነው፡፡ እኔ ብቻውን ነው የሚል ፍፁም እምነት የለኝም፡፡ አንደኛ ሰሜን ዕዝ የተወጋበት እና አማራና አፋር የተጠቁበት ምክንያት አንድ አይነት አይደለም። የአማራን ህዝብ ማዋረድ፣ ማሸማቀቅ አንገት ማስደፋት፤ የአፋርን ህዝብ የመናቅ የማዋረድ  ተግባር ፈፅመዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ህዝቦች የኢትዮጵያና የፌደራል መንግስቱ ዘብ አድርጎ የማየትና እነዚህን ህዝቦች ካላዋረድን፣ ካለሸማቀቅንና አንገት ካላስደፋን አገሪቱን እንደፈለግነው  መዘወር አንችልም የሚል እምነት ስላላቸው ነው፡፡
ትህነግ ለምንድን ነው በአማራው ላይ ጥላቻ አለው የሚባለው፡፡ እስቲ ወደ ኋላ ወደ ታሪኩም እንምጣ?
በጣም በብዙ ምክንያት!! በጣም በበርካታ ምክንያት ነው የሚጠሉት፡፡ ይሄ የመቶ ዓመት ፕሮጀክት አይደለም፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ትውልዶች ማርክሲስት ትውልዱ ከተነሳ በኋላ በተለይ ከአድዋ ድል በኋላ ሙሉ በሙሉ አማራን የሚያዩት እንደ ቅኝ ገዥና ነጭ አባቶቻቸውን እንዳሸነፈባቸው ህዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያን አብዝቶ በመውደዱ የነሱ ክብር እንደተነካ አድርገው ነው የሚወስዱት። በራሳቸው ማኒፌስቶም ላይ ትግራይ ለደረሰበት ማህበራዊ ውርደት ተጠያቂው አማራ ነው ብለው ፅፈዋል፡፡ “የትግራይ ህዝብ መገለጫ ልመና ሽርሙጥናና መሰል ነገሮች ናቸው፤ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው አማራ ነው” ብለው ፅፈዋል፡፡ ስለዚህ አማራን እንደ ህዝብ ካላዋረድንና ካላጠፋን በዚያ ልክ መቆም አንችልም የሚል ድምዳሜ ይዘዋል፡፡ እናም ያ የአስተምህሯቸው መሰረት ሆነ፡፡ ወያኔ በጣም ከሚያስገርመኝ ባህሪው አንዱን ልንገርሽ፡፡ ውሸትን ለራሱ ይናገርና ለዚያ ውሸት መኖር ይጀምራል። ያንን ለራሱ የነገረውን ውሸት በፍጹም እውነትነት ይቀበለዋል፡፡ እናም በጊዜ ሂደት “በትክክልም አማራ ጠላታችን ነው ማለት ነው” የሚለውን ራሱ ፈጥሮ ትርክቱን ከፃፈው በኋላ እውነት ነው ብሎ አመነ። ከዚያም በኋላ እንዴት ይቀይረው። የመቀየር ድፍረቱንስ ከየት ያምጣው? ለዛ ነው መንግስት ሆኖ ነገር ግን ተገንጣይ ሆኖ የኖረው፡፡ ትህነግም ህወኃትም ሆኖ አገር የመራ በምድር ላይ ብቸኛው ድርጅት ነው። “ከዚህ አገር ነፃ እወጣለሁ” እያለ ያንን አገር የሚያስተዳድር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ  ራሱ የፃፈውን ፅሁፍና ውሸት ለመቀየር ያመነበትን ሀሰትና የሀሰት ትርክት ለመታገል በዚያ ልክ  በራስ መተማመን ያለው ቡድን አይደለም፡፡ ለፃፈው ሀሰት ታማኝ ሎሌ ነው-ትህነግ፡፡
አንደኛ በቡድን ነው የሚያስቡት፡፡ አንዱ ከመሃከላቸው ተነስቶ “የለም ይሄ ትክክል አይደለም” ቢል እንደ እባብ ይረባረቡበትና እናጠፋሃለን ይሉታል እንጂ፤ “ሀሳባችን ስህተት ነው፤ የአማራ ህዝብ ጠላታችን አይደለም” የሚል ነገር  አይሞከርም፡፡
የተለየ ሀሳብ የመቀበል ባህል የላቸውም ማለት ነው?
በትክክል! በዚህ ምክንያት የተለየ ሀሳብ የማስተናገድ፣ ሰላማዊ የሆኑ የፖለቲካ ውይይቶችን የማካሄድ ባህል የላቸውም ፍፁም እብሪተኞች ስለሆኑ በአሸናፊነት ስነልቦና ሁሉን ነገር እንቋጫለን ብለው ስለሚያምኑ ያንን አድርገዋል፡፡ እናም በአማራና አፋር ህዝብ ላይ የፈጸሙት ጦርነት ስልጣን ከመፈለግ ብቻ አይደለም፤ በዋናነት ህዝቦቹንም ስለሚጠሉ ነው፡፡ የዚህ መገለጫ ደግሞ መነኮሳትን መድፈር፣ በጋራ ሆኖ መጸዳዳት፣ ለምሳሌ የወሎ ዩኒቨርስቲ ኮሪደሮችን ብታይ ሆን ብለው በጋራ ነው የተጸዳዱበት፡፡ አስከሬን ቤት ውስጥ መቅበር፣ ካህናትንና ሼሆችን መድፈር…በዚያ ልክ ህዝብን እንደዚያ ለማድረግ መምጣት በየትኛውም አይነት የፖለቲካ ፍላጎት የሚገለጽ አይደለም፡፡
ሌላው፣ አንቺ ያነሳሽው፣ “ከዚህ በፊት ሲመጡ እንደዚህ ጥፋት አልፈፀሙም ነበር፣ አሁን ምን አዲስ ነገር መጣ” ብለሻል። አንደኛ አሁንም ከስልጣን ለመባረራቸው ተወቃሽ የሚያደርጉት የአማራን ህዝብ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በኢህአዴግ ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ዶ/ር ደብረፅዮን ወደ ትግራይ ተመልሰው ስብሰባ ባደረጉ ጊዜ፣ የትግራይ  ህዝብ ዶ/ር ደብረ ፅዮንን “አማራ ከድቶናል የሚባለው  እውነት ነው ወይ? ብሎ  ነበር የጠየቃቸው፡፡ አማራ ስለከዳን ነው የተሸነፍነው የሚል ድምዳሜ ነው የወሰዱት፡፡ “ትግሉንም ሁሉንም የጀመረው አማራ ነው ለሽንፈታችን መንስኤ አማራ ነው ድጋሚ ወደ ስልጣን ብንመጣም ተግዳሮታችን አማራ” ነው የሚል ፅኑ እምነት ስላላቸው ነው የአማራን ህዝብ የሚጠሉትና ኢላማ የሚያደርጉት፡፡ ይሄ እንግዲህ በቅርብ ያለውን የፖለቲካ አረዳድና የወያኔን የስልጣን አተያይና ናሬቲቭ ነው የምነግርሽ፤ ነገር ግን በርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ምክንያቶች አሉ፡፡ ቅራኔው በጣም ዘመን ተሻጋሪና ምናልባትም እስከ 11ኛው ክፍለ ዘመን ይሄዳል፡፡ ቅራኔው ደግሞ የበለጠ ማህበራዊ መሰረት እየያዘ መጣ፡፡ እናም መጨረሻ ላይ ታሪክና በታሪክ  እውቀት ሊያስደግፉት ሞክረዋል፡፡ የአማራ ህዝብ  የትግራይን ህዝብ እንደጎረቤት ህዝብ መስተናገድ አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ወያኔዎች ደግሞ የአማራን ህዝብ መዋረድ እንዳለበት አንድ ስብስብ ይቆጥሩታል፡፡ ያ ስህተታቸው ደግሞ አሁን ላሉበት ማህበራዊ ውርደት ዳርጓቸዋል፡፡ ይህንን ኑሮ እንዲኖሩ፣ይህንን ግፍ እንዲያዩ፣አሁን ላሉበት እጅግ አስከፊ ህይወት የዳረጋቸው የአማራና አፋርን ህዝብ በጠላትነት መፈረጃቸው ነው፡፡ ሌላው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ቅራኔ ነው። ኢትዮጵያ አስፈላጊ ሲሆን የምትዘረፍ ናት፤ ከዚያም ውጪ ደግሞ ህዝቦቿን አዋርዶ ባሪያ አድርጎ መግዛት ነው- ህልማቸው፡፡ በቅርቡ አንድ  የነሱ ሰው አህጉር እንሆናለን” ሲል ነበር፡፡ ብዙዎች የመሰላቸው “አህጉር እንሆናለን” ብሎ ድንገት የተናገረው ነው፡፡ አይደለም! አገሩን እንኳ ሊፈልጉት ይችላሉ። አህጉር ግን እንዴት ብለሽ በስህተት የተናገረው ሊመስልሽ ይችላል፡፡ እንዴት  ያስባሉ መሰለሽ? “እኛ አፍሪካዊ አይደለንም” የሚል እምነት አላቸው፡፡ “የተለየን ነን፤ በጥቁር ዘር ውስጥ በጣም የተለየ ቦታ ስላለን ከፈለግን አውሮፓ መሆን እንችላለን” ይላሉ።
ልክ የአዶልፍ ሂትለር  የጀርመን ህዝብ የተለየ ነው በሚል አስተሳሰብ አይሁዶችን የፈጀበት ዓይነት ማለት ነው?
ትክክል ነው!! እንግዲህ የትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘት፣ አፍሪካ ውስጥ መካተት መቸም መልክአ ምድራዊ እውነት ነው አይደለም? ይህን ክደው እንደ አውሮፓዊ ራሳቸውን ለመቀበል ይህንን ያህል እርቀት ይሄዳሉ፡፡ የትግራይ ህዝብ ባህልና እምነት ያንን ባይፈቅድም የሚመራው የሹምባሽና የባንዳ ስብስብ፣ የቅኝ ገዢዎች ሌጋሲ አስቀጣይ ስለሆነ፣ “እኛ አውሮፓ” ነን ቢሉም ሆነ ራሳችውን እንደ አህጉር ቢቆጥሩ ምንም የሚደንቅ ነገር አይደለም ማለቴ ነው፡፡ ወደ ዋናው ነጥብ ስንመለስ፣ የአማራ ህዝብ የሚጠላበትንና የሚወጋበትን እንዲሁም የሰሜን ዕዝ የተወጋበትን ምክንያት ለይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ጦርነቱ በዐቢይ አህመድና በትግራይ መካከል የተነሳ፣ ለስልጣን ተብሎ የሚደረግ ጦርነት አድርጎ የሚያስብ ብዙ አማራ አለ አማራ ብቻም ሳይሆን ሌላው ኢትዮጵያዊም እንደዚህ ያስባል፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ በአማራ ህዝብ  ላይ ይህን ያህል ጥፋት ባልደረሰ ነበር፡፡ 11 ሚ. ህዝብ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተፈናቅሏል፡፡ እስከ 4 ሚ. የሚጠጋ ተማሪ ት/ቤት እየሄደ  አይደለም፡፡ በወሎና በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ማለቴ ነው፡፡ ት/ቤቶችን የሃይማኖትና የጤና ተቋማትን በአጠቃላይ የአማራ ህዝብን የኑሮ መሰረት፣ የምግብ ዋስትናውን፣ የአኗኗር ዘይቤውን፣ አደጋ ውስጥ ለማስገባትና ምናልባትም ህዝቡን ወደ ድንጋይ ዘመን ለመመለስ ብዙ ርቀት ሄደዋል፡፡ ከዚህ ቀደም መንግስት ሆነው በተቋም ደረጃ በተደራጀ መልኩ በአማራ ህዝብ ላይ ከፈፀሙት በደል ይልቅ አሁን በገሃድ አለም እያየ በቪዲዮ እየተቀረጸ፣ እነሱም የሚፈጽሙትን በደል በእብሪት እየተናገሩ፣ ያንንም በኩራት እያሳዩ በግልጽ በድለውታል፡፡ ይህ  ፈጽሞ ሊረሳ የሚችል አይደለም፡፡ ይህን ጉዳይ አሁን ያለውም ወደፊት የሚመጣውም የአማራ ትውልድ “በዚህ ልክ ለምንድን ነው የምንጠላው” የሚለው ላይ ጥልቅ ጥናትና ምርምር ቢያደርግ ጥሩ ነው። ለወደፊትም እንደ ህብረተሰብ  ዳግማዊ ውርደት ውስጥ ላለመግባት ምክንያቱን ማወቅ አለበት።
ለአማራው ህዝብ መገፋት አንዱና ዋነኛው ምክንያት ህገ-መንግስቱ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።  በህገ መንግስቱ  ላይ “ይህን ህገ-መንግስት ማጽደቅ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት በብሄር ብሄረሰቦች መካከል የተፈጠረውን የተዛባ ግንኙነት ለማስተካከል ነው” የሚለውን ሀረግ ምሁራን  በመጥቀስ፣ በውስጡ መርዝ ያዘለ ነው “የተዛባ” የሚለው አማራን ጨቋኝ፣ ሌላውን ተጨቋኝ ብሎ የሚፈርጅ ትርጓሜ ተሰጥቶት፣ በዚህም አማራ ዋጋ እየከፈለ ነው ሲሉ ይደመጣል። አንተ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ? ታምንበታለህ?
ጥሩ፡፡ ከዚህ በፊት አምንበት ነበር። የህገ-መንግስቱ ጥያቄ በዋናነት የአማራ ህዝብ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል። ህገ-መንግስቱ በህዝቦች መካከል የተዛባ ትርክት አለ ይላል፣ የኢትዮጵን ህዝቦች ማህበራዊ ድርና ማግ አዋርዷል፣ ህገ-መንግስቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚነሱ ችግሮችና ቅራኔዎች በብዙ መልኩ መንስኤ ሆኖ ቆይቷል። በዚህ ላይ ምንም ጥርጥር የለም። አሁን ግን ህገ-መንግስቱ ይቀየር ማለት ያለበት የአማራ ህዝብ አይደለም። ምክንያቱም የአማራ ህዝብ ብቻ የህገ-መንግስቱ ዘብ ሊሆን አይችልም። የአማራ ህዝብ ብቻ የዚህ አገር ዘብ ነኝ ሊል አይችልም። ህገ-መንግስቱ ለጋራ ውርደት ዳርጎናል ካለ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ እንደ ህዝብ ነው መጠየቅ ያለበት። የጻፈውን ወረቀት እያመለከ እስከ መቼ ነው የሚኖረው? እና ይሄ አምላኩ አይደለም። በጣም የደንቆሮ ስብስቦች ናቸው የጻፉት፡፡ ምናልባትም የአንድ ሰው ቅዠት ግፋ ቢል የሶስት ሰው ቅዠት ነው የሚሆነው። ይህንን እብደት ማረቅ ያስልጋል። ህገ-መንግስት እኮ የሰው ልጆች የሚተዳደሩበት ህግ ነው፣ የዛሬ 20ና 30 ዓመት የተጻፈ። የሰው ልጆች የጻፉትን  ህገ-መንግስት በእውቀት እየዳበሩና እየሠለጠኑ ሲሄዱ፣ እያረቁና እያስተካከሉ ምቹ ያደረጉታል። ህገ-መንግስትን አላርቅም አላስተካክል ማለት በትክክል የሚያሳይሽ የዚህን ህገ-መንግስት አዘጋጆች ድንቁርና ነው። የሰው ልጆች በየትኛውም ዘመን ላይ ፍጹም አይደሉም። እያሻሻሉ ከስህተቶቻቸው እየተማሩ ነው የሚሄዱት። ስለዚህ ህጎቻቸው ገደቦች ስላሏቸው እያስተካከሉ እያዳበሩ ነው የሚሄዱት እና ይሄ የተለመደ የህገ-መንግስት ባህሪ ነው።
ለሰው ልጆች ህይወትና አኗኗር ምቹ እንዲሆኑ እያዳበሩ መሄዱ ተገቢም አስፈላጊም ነው። አሁን በዋናነት  ህገ-መንግስቱ ይቀየርልን ማለት ያለበት ደግሞ ትግራይ ነው። ህገ-መንግስቱ ይቀየርልኝ ማለት ያለበት ወያኔ ነው። በፌደራል አደረጃጀቱም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የስልጣን አተያይ ለውጥ መምጣት አለበት ብሎ የሚጠይቀውም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የአማራ ህዝብ አይሆንም። የትግራይ ህዝብ ነው የሚሆነው። የአማራ ህዝብ ከዚህ በፊት “ህገ-መንግስቱ ከሰውነት ተራ ያወረደናል፤ እኛ እንደ አማራ ዛሬ ዋጋ እየከፈልን ነው። ነገ ግን ህዝቡ ሁሉ ዋጋ ይከፍልበታል” እያለ ሲጮህ ኖሯል። በዘርና  በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ አትመስርቱ፣ ህዝቦችን በድንበር እያጠራችሁ ሀገር ከምትሰጣቸው የዜግነት ክብር ዝቅ አታድርጉ” እያልን እኛኮ ሺህ ጊዜ ብዙ ዓመት ጮህን፤ ይህ ህገ-መንግስት እንዲቀየር። “እኩል እንሁን፤ በሰውነት ደረጃ እንቀመጥ” አልንኮ! የአማራና የትግራይ ህዝብ ሁሉም በተለያየ ቋንቋ የሚናገር ግን አንድ ቤተሰብ ነው ብለናል፤ ደጋግመን!! አይ አይገባችሁም ተባልን። ስንት ዓመት ተፎከረብን። አሁን ግን ራሳቸው የህገ-መንግስቱን ትሩፋት እያዩት ነው። አሁን ይሄ የትግራይ ጉዳይ ነው። ሌላው እውነታ፤ አሁን ባለው ህገ-መንግስት እንኳን አማራ ክብሩን አስጠብቆ መቀጠል የሚችልበት አቅም  ላይ ነው ያለው።
አሁን ላይ የህዝቦቹን ሰላም፣ የህዝቦቹን ክብር፣ የፖለቲካ መብቱን፣ የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነቱን በሀገሪቷ ውስጥ አስጠብቆ መሄድ የሚችልበት ዕድል አለ። አሁን ላይ ህገ-መንግስቱ የሚጎዳው ከአማራ ይልቅ የኢትዮጵያን ህዝቦች ነው። እውነታው፤ የሕገ-መንግስቱን የመቀየር ጥያቄ  ማንሳት ያለባቸው “ሰው እንሁን እኩል ሆነን፤ እንዝለቅ በሀገራን ሳንሸማቀቅ እንኑር” የሚሉ፣ ለሰውነት ክብር የበቁ፣ ከመንጋነትና ከትንንሽ ስብስብ ወጥተው፣ ሰው ሆነን መኖር ይገባናል የሚሉ ኢትዮጵያዊያን መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ ህገ-መንግስት አንድ ሰው ከዘሩና ከጎጡ ወጥቶ ሲሄድ ዋጋ የለውም፤ ከሰፈሩ ሲወጣ የሚደረስበትን እናውቃለን። በየትኛው ማዕቀፍ ነው እንደ ሰው ተከባብረን የምንኖረው ስንል፣ ህገ-መንግስታችን ተሸሽሎ በእኩልነት አይን ሲያየንና ሲያስተናግደን ነው። አሁን ያለው ህገ-መንግስት የጎሳዎች ቃል ኪዳን እንጂ የዜጎች ቃል ኪዳን አይደለም። እናም ህገ-መንግስቱ የዜጎች ቃልኪዳን ተብሎ ሲተረጎም ይገርመኛል። የትኞቹ ዜጎች ተሰባስበው ነው ቃልኪዳን የፈጸሙት? ህዝበ ውሳኔ አላደረግንም፣ ዜጎች የወከሏቸው ቡድኖች አይደሉም በህገ-መንግስት ማርቀቅ ሂደት ውስጥ የተሳተፉት። ጎሳ ወክለናል የሚሉ፣ የጎሳ ቡድኖች ስብስብ ነው የነበረው። ኢትዮጵያንም የሚያያት የዜጎች ሀገር  አድርጎ ሳይሆን የጎሳ ስብስብና ጥርቅም አድርጎ ነው። ከዚህ አንጻር አሁን  ያለው ህገ-መንግስት የጋራ ውርደታችን ምንጭ ነው፤ በዚህ ጥርጥር የለኝም። ይሄኛው ትውልድ አላስተካክለውም ቢል፣ የተሻለና የነቃ ትውልድ ሲመጣ ያስተካክለዋል።
ትህነግ ከተናጠል ተኩስ አቁሙ በኋላ ባገኘው ፋታ የአማራና የአፋርን አካባቢ በመውረር፣ እስከ ሰሜን ሸዋ ዘልቆ በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ አድርሷል። ከዚያም በጥምር ጦር ሀይሉ ተጋድሎ ወደመጣበት ቢመለስም፣ ሰራዊቱ ትግራይ ክልል እንዳይገባ ተገድቧል፡፡ የዚህ ውሳኔ ትርፍና ኪሳራው ምንድን ነው? አንተስ ይህን ውሳኔ ጠብቀህ ነበር? አሁንስ ይሄ ውሳኔ ትህነግ አቅም እንዲያዳብርና ለሌላ ጥቃት እንዲዘጋጅ እድል አይሰጠውም ትላለህ?
መልካም! እንግዲህ ሁላችንም በምናውቀው ሙያና ዘርፍ ነው አስተያየት የምንሰጠው። የሚሊታሪ ሰዎች ምክንያት ይኖራቸዋል። እኔ በበኩሌ፤ በዋናነት ግፍና በደል እንደደረሰበት የአማራና የአፋር ህዝብም ሆነ በሌላውም የኢትዮጵያ ህዝብ ላደረሱት ጥቃት ዋጋ መክፈል አለባቸው ብዬ ነው የማምነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብም መከላከያው ወደ ትግራይ  በፍጥነት ገብቶ ይሄን ጥፋት ያስተባበሩ፣ በዚህ ወንጀል የተሳተፉ፣ ሀገርንና የሀገርን ክብር ያዋረዱ ሰዎችን ለፍትህ ማቅረብ አለበት ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ይሄ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ነው። ነገር ግን ይሄ የህዝብ ፍላጎት ደግሞ ከወታደራዊ ሳይንስ አንጻር አዋጪ ነው አይደለም የሚለው ተገምግሞ መወሰን ያለበት ነው የሚሆነው፡፡ እኛ የሚሊታሪ ተንታኝ አይደለንም። እንደ ህዝብ ግን ይሄ ቡድን ትጥቅ እንዲፈታ ካልተደረገ፣ አጥፊዎች ለፍትህ ካልቀረቡ ወያኔ የሚረጨው መርዝ ካልጠፋ፣ የወያኔ አመራሮች ለፍርድ ቀርበው ተጠያቂ ካልሆኑ በሀገር ላይ የሚደርሰው ጥፋትና በደል ይቀጥላል የሚል እምነት አለን። መንግስትም ቢሆን ከዚህ የተለየ አቋም ያለው አይመስለኝም። ወያኔ እስካለ ድረስ  ኢትዮጵያ ውስጥ እርቅ ወይም ውይይት ይመጣል የሚል እምነት የለም። ወያኔ ኢትዮጵያንም ሆነ ኤርትራን እንዲሁም ሌሎች ሀገራትን የሚያተራምስ ወንበዴ ነው፡፡ ወያኔን እንደ አንድ ወንበዴ እንጂ እንደ አንድ  የፖለቲካ ኢንቲቲ አይደለም የማየው። ለጥፋት የተፈጠረ ቡድን ነው። ብዙ ሰው ጥፋቱን ምክንያታዊ ሊያደርግለት ይጥራል። ነገር ግን ትክክል አይደለም። ወያኔ እንደዛ አይነት ፍጡር አይደለም፤ ፖለቲካን አያውቀውም፤ የፖለቲካ እውቀት የሌለው ደንቆሮ ባይሆን ኖሮ ከሥልጣን ከተባረረ በኋላ አሁንም እንኳን የማሸነፍ እድል ነበረው፡፡ እብሪትና ድንቁርና እየተመራ ከፈጸመው ጥፋትና ውድመት አንጻር ነገ ሰላም ይሰጠናል የምንለው ቡድን አይደለም። በዚህ ምክንያት መከላከያ ወደ ትግራይ ዘልቆ እንዳይገባ ሲደረግ ለብዙ ኢትዮጲያዊያን እኔን ጨምሮ ግርምት ፈጠሮብናል። ግን አለመግባቱ የራሱ የሆነ ጥቅምም ጉዳቶትም ሊኖሩት ይችላሉ። ለምሳሌ ይህ ቡድን በመቶ ሺህ የሚቆጠር ጦር እያንቀሳቀሰ እንደሆነ ጀነራል አበባው ነግረውናል። በተመሳሳይ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስትም ራሱን እያዘጋጀ ነው። ጀነራል አበባው ከሰሞኑ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ ትግራይ የኢትዮጵያ ግዛት በመሆኑ እንደሚገቡና ህግና ስርዓትን እንደሚያስከብሩ ገልፀዋል። መንግስትም በዋናነት ለድርድር ካቀረባቸው ሶስት ዋና ዋና ነገሮች አንዱ ቡድኑ ትጥቅ እንዲፈታ ነው። ከዚያ ባሻገር እጅ እንዲሰጥ ነው። መንግስት የመግባቱ ጉዳይ አያጠራጥርም፤ የጊዜ ጉዳይ ነው። እንዲያው ዝም ብሎ በስሜታዊነት ገብቶ ሰራዊትን ለጉዳት መዳረግ የታክቲክ ብልጠት አይደለም። አሁንም በራያና በጎንደርም በአደርቃይ በኩል  ብዙ ነጻ ያልወጡ የአማራ አካባቢዎች አሉ። እነዚህን አካባቢዎችም ሆነ የትግራይን ህዝብ ከዚህ አጥፊ ቡድን ነጻ ማውጣት አስፈላጊ ነው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ መገባቱ አይቀርም።
የህዝቡ ስጋት ደግሞ አለ። በተናጠል ተኩስ አቁሙ ወቅት ወያኔ ትንፋሽ ሰብስቦ ይህን ሁሉ ጥፋት እንዳደረሰው ሁሉ የሰራዊቱ ትግራይ አለመግባት ያን እድል አሁን ላይ አያገኝም ወይ የሚል ነው። በዚህ ላይ ያለህ አስተያየት ምን ይመስላል?
ተገቢ ስጋት ነው። ወያኔ ሰው ሊያስጥለን ይችላል። በታላቅ ትጋት ላይ ነው ያለው። ነገር ግን መሳሪያ ጨርሷል። ሎጂስቲክ እንኳን ከአማራ የዘረፈው ቀለብ ሊኖረው ይችላል። ያም ቢሆን ህዝቡን የሚመግበው ነው። ግን በዋናነት ጦርነት ለመክፈት የሚያስችል  የትጥቅ ክምችት የለውም አሁን ባለበት ሁኔታ። እነዚህን ነገሮች መንግስት በቅርበት እየተከታተለ ያለ ይመስለኛል። እኛ እንደ ህዝብ ግን ማወቅ ያለብን ወያኔ ጥፋት ከመፈጸምና ከመተናኮስ እንደማያርፍ ነው። አሁን እኔና አንቺ በምንነጋገርበት  በዚህ ጊዜ እንኳን በአፋር በኩል እያደረገ ያለው ግልጽ ነው። ስለዚህ በማንኛውም ጊዜ በአማራ ክልልም ጥፋቱን  ሊቀጥል ይችላል። የአማራ ክልልም በዛ ቁመና ላይ መገኘት አለበት። ጦርነቱ ገና አላላቀም። ገታ (ፖዝ) ነው ያደረግነው። ጦርነቱን ለማስቀጠል ፖዝ የተደረገውን ቦታ ክሊክ ማድረግ ብቻ ነው የሚያስፈልገው። ወያኔ ጦርነቱን አላቆመም፤ እኛ ነን ፖዝ ያደረግነው። የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ ጦር በዓለም የተመሰከረለት ጦር ነው። በማንኛውም ሰዓት ወያኔን ዲቫስቴት ማድረግ ይችላል። ነገር ግን ድጋሚ እንደቀደመው አይነት እልቂት እንዳይፈጸምና 100 ሺህ የትግራይ ወጣት እንዳይረግፍ ጥንቃቄ እየተደረገም ሊሆን ይችላል። ሌሎች  የሰላም አማራጮች ካሉ እየተፈተሸ ሊሆንም ይችላል፡፡ በእርግጠኝነት የምነግርሽ ነገር ግን ወያኔ ድጋሚ መጥቶ ጥፋት ቢፈጽም የሚታገሰው አይነት መንግስት አይደለም ያለው።

Read 3277 times