Saturday, 29 January 2022 00:00

የኡራኤል አካባቢ የጤና ስፖርት ማህበር በ10ኛ ዓመቱ ላይ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የኡራኤል አካባቢ የጤና ስፖርት ማህበር ባለፈው ሳምንት በሪቫን ላውንጅ 10ኛ ዓመቱን በድምቀት አክብሯል። የጤና ስፖርት ማህበሩ የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር ባዘጋጀውና 11 ቡድኖችን ባሳተፈው ውድድር አሸናፊ ሆኗል።
የኡራኤል አካባቢ ጤና ስፖርት ማህበር በዙርና ጥሎ ማለፍ ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች 14 በማሸነፍና፤ በ2 አቻ መውጣት ችሏል። በፍጻሜ ጨዋታ ከቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ የጤና ስፖርት ማህበር ጋር ተገናኝቶ 3ለ0 በማሸነፍም የዋንጫው ተሸላሚ ሆኗል።
በ10ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ላይ የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አሸኔ ባሰሙት ንግግር ጤና ስፖርት ማህበሩ ከ10 ዓመታት በፊት በሲሳይ ፈለቀ አስተባባሪነት በፅጌ ሆቴል መመስረቱን አስታውሰው፤ የማህበሩ አባላትን ያልተገደበ አስተዋጽኦም አመስግነዋል።
በክብረ በዓሉ ላይም ማህበሩ ያገኘውን ዋንጫ ለቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን እንደሚያስረክብ ያስታወቀ ሲሆን በእለቱ፤ ለቡድኑ አባላት የተዘጋጁ 25 ሜዳልያዎችን ከመስጠቱም በላይ ልዩ አስተዋጽኦ ለነበራቸው አባላትና ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች የተለያዩ ሽልማቶችና ስጦታዎችን አበርክቷል።
ቦንቱ ትሬዲንግ፣ ፋልኮኔት ትሬዲንግ፣ ሮሚና ትሬዲንግ፣ ሰከላ ትሬዲንግ እና ዓለም ሰፋ ትሬዲንግ ባልተቆጠበ ድጋፋቸው አብረውን ሠርተዋል ቆይተዋል ያሉት ሊቀመንበሩ አባላቱ በማህበሩ ስፖርታዊ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዙሪያ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ ለሚያደርጉት ጥረት ልዩ ምስጋና አቅርበዋል።
በ10ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ የክብር እንግዳ ነበሩት የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ከበደ ናቸው። የኡራኤል አካባቢ ጤና ስፖርት ማህበር በሚያደርገው የተጠናከረ እንቅስቃሴ በአርአያነት እንደሚታይ የጠቀሱት አቶ እሸቱ፤ የስፖርት ማህበሩ በከተማው በሚዘጋጁ የጤና ስፖርት ውድድሮች በሁሉም የዕድሜ ምድቦች ንቁ ተሳትፎ ነበረው ብለዋል። የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ባሻገር ለስፖርት ማህበራቱ ምክርና ሃሳብ በመስጠት በቅርበት እንደሚሰራ፣ በየዓመቱ ተጨዋቾችን በመገምገምና የየቡድኖቹን ሁኔታ በመከታተል እንደሚንቀሳቀስ ለማወቅ ተችሏል።
የኡራኤል አካባቢ የጤና የስፖርት ማህበር ቋሚና የክብር አባላት ብዛት እስከ 50 ይደርሳል።
የአባላት ስብስቡም በተለያዩ የግል ንግድ፣ ኮንስትራክሽንና ሌሎች ስራዎች የሚንቀሳቀሱትን ያካትታል።
በአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር የተመዘገቡ ከ42 በላይ የጤና ስፖርት ማህበራት የነበሩ ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብዛታቸው ወደ 22 ወርዷል። የስፖርት ማህበራቱ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ከመንግስት የሚፈለገውን ትኩረት ማጣታቸው፤ የተሻለ አደረጃጀት አለመያዛቸውና በስፖርት መሰረተ ልቶች አለማሟላት ለብዛታቸው መቀነስ ምክንያት አድርጎ ለመጥቀስ ይቻላል።
የኡራኤል አካባቢ የጤና ስፖርት ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አሸኔ ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስያየት በእነሱ ማህበር ትልቁ ችግር ከመጫወቻ ሜዳ ጋር የተገናኘ ነው።
ለሜዳ ክራይ በሰዓት ከ1000-1500 ብር በመክፈል ለከፍተኛ ወጭ እየተዳረግን ነው የሚሉት ሊቀመንበሩ መንግስት ማህበረሰቡ ለሚያደርገው የስፖርት እንቅስቃሴ የተሻለ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል። የስፖርት ማዘውተሪያዎችን መጠቀም የምንችልበትን ዕድል ቢያመቻች የሚል ሃሳብም አቅርበዋል።
የኡራኤል አካባቢ ጤና ስፖርት ማህበር ከህክምና ወደ ሜዳ መሄድ በሚል መርህ መንቀሳቀስ ይቀጥላል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በማህበሩ  ዙሪያ የተሰባሰቡ አቅም ያላቸውን ግለሰቦችና ድርጅቶች በማስተባበር በስፖርቱ ላይ ኢንቨስት በሚያደርጉበት ሽርክና እንዲሰሩ አቅደናል። በታዳጊዎችና  በወጣቶች እግር ኳስ ስልጠና ላይ ለመስራት እንደሚያስቡ፤ በረጅም ጊዜ እቅድም የራሳችንን ክለብ የምንመሰርትበት የስራ እቅድ እያዘጋጀንም ነው ብለዋል።
የጤና ስፖርት ማህበር በአባላት መካከል ጠንካራ ትስስር በመፍጠር፣ አንድነትና  ወዳጅነት በማምጣት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል። ማህበራት በስፖርቱ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያደርጉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል። የገቢ ማስገኛ ውድድሮች በማዘጋጀት፣ በስፖንሰርሽፕን እና በተለያዩ ንግድ  እንቅስቃሴዎች  በመስራት፣ በሌሎች ስፖርቶች የሚኖራቸውን ተሳትፎ በማሳደግ፣ ከሌሎች ማህበራት ጋር በተቀናጀ መንገድ በመስራት ማህበረሰቡን ሊያነቃንቁበት ይቻላል።
ከተመሰረተ ከ28 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የአዲስ አበባ የጤና ስፖርት ማህበር የስፖርት ፍቅርና ዝንባሌ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ምድቦች ከፍሎ በማወዳደር ሃላፊነቱን ለመወጣት ያለውን ፍላጎት የኡራኤል፤ አካባቢ የጤና ስፖርት ማህበር ባዘጋጀው ልዩ ስነ-ስርዓት ላይ አስታውቋል።  
የአዲስ አበባ የጤና ስፖርት ማህበር እድሜያቸው ከ35 ዓመት ላይ የሆናቸውን ግለሰቦች በማካተት ዜጎች አገርን መጥቀም እንዳዲችሉ ከአልባሌ ሱስና አላስፈላጊ ስብዕናዎች እንዲጠበቁ፣ ከተለያዩ በሽታዎችና ጭንቀቶች በመታደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል። የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር በድረገጹ ከሰራቸው ካሰፈረው መረጃ መገንዘብ እደሚቻለው በዓለም ከ35 እና ከዚያም በላይ የሆኑ አገራት የጤና ስፖርት ብሔራዊ ቡድኖች አሏቸው።

Read 2498 times