Saturday, 29 January 2022 00:00

የጋዜጠኝነትና የደራሲነት ሕይወቱ

Written by  አጥናፍ ሰገድ ይልማ
Rate this item
(1 Vote)

ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያና አስተዳዳሪ አጥናፍሰገድ ይልማ ተሰማ፤ እናቱን አለወጥ ታምራትን የሚያስታውሳቸው ለእናትነት ካላቸው ፍቅርና አክብሮት በላይ እንደ ኾነ በአድናቆት ይናገራል፡፡ አጥናፍ ሰገድ ተወልዶ እስከ ሰባት ዓመት ዕድሜ ያደገው፣ በቀድሞ አጠራር፣ አሩሲ ጠቅላይ ግዛት፣ ጢቾ አውራጃ፣ ጠና ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ገርጌዳ በተባለ ቀበሌ ነው፡፡ ስለ እናቱ ያነሣውን አድናቆት ሲያስረዳ  «አባቱ ይልማ፣ ገና የስድስት ዓመት ሕፃን እያለሁ ነበር በሞት የተለየኝ፡፡ እናቴ፣ አንደ እናትም እንደ አባትም ኾና  እኔንና ኹለት ታናናሽ እኅቶቼን ኮትኩታ የማሳደግ ኀላፊነት የወደቀባት ገና የ22 ዓመት ወጣት እንደነበረች ነው፡፡ የሙት ልጆችን ለማሳደግ የወደቀባት ሸክም  ሳያንሣት እናቴ  እኛ ልጆቿ ከአባታችን የወረስነውን በርካታ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ሀብትና ንብረት በሞግዚትነት የማስተዳደር ኀላፊነትም  ነበረባት፡፡»
አባቱ ይልማ፣ የወላጆቹ አንጋፋ ወንድ ልጅ በመኾኑ፣ አባቱ ግራዝማች ተሰማ አባ ገንባው፣ በኑዛዜ፣ የቤተሰባቸው አለቃ በማድረግ ሰይመውት ነበር፡፡ አጥናፍ ሰገድም የወላጆቹ የበኩር ልጅ እንደ መኾኑ፣ እልቅናውን ጭምር ወረሰ፡፡ የሕፃን አጥናፍ ሰገድ እናት፣ አለወጥ የልጇ ሞግዚት በመኾኗ፣ በዚያ ለጋ ዕድሜዋ፣ የባለቤቷ ቤተ ሰቦች/የአማቾቿ አለቃ) በመኾን የሥራ ድርሻዋንና ኃላፊነትዋን  በሚያስደንቅ ብቃት መወጣቷን አጥናፍ ሰገድ በአድናቆት ያስታውሳል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ የእናቱ ቤተ ሰቦች፣ በልጃቸው ላይ የወደቀውን የቤተሰብ  የእልቅና ሸክም፣ (የቤተሰብ እልቅና በቀድሞው ዘመን በዕድሜና በሀብት የበለጸጉ አዛውንት አባቶች፣ በቁም ኑዛዜ፣ ከኅልፈታቸው በኋላ፣ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያፈሩትን ሀብት ንብረታቸውን፣ ለምንዝሮቹ እንዲያከፋፍል፣ የበኩር ልጃቸውን ይሾማሉ፡፡ ተሿሚው፣ ከማከፋፈሉ በፊት፣ ድርሻውን፣ ለቤተ መንግሥት ደጅ መጥኛ የሚኾነውን ጭምር፣ በብልጫ ይወስዳል፡፡ ሟች አባቱ ለማዕረግና ለሹመት የበቁ ከነበሩ፣ ተሿሚው ልጃቸው፣ አባቱን በመተካት ማዕረግና ሹመታቸው እንዲሰጠው ቤተ መንግሥትን ደጅ መጥናት ይኖርበት ነበር፡፡
የግራዝማች ተሰማ አባ ገንባው ቤተ ሰብ አባል በኾነ ሌላ ሰው በሞግዚትነት እንዲያዝ ባቀረቡት ዐሳብ ላይ ተመክሮና ተዘክሮ ስምምነት ላይ ስለተደረሰ፣ አለወጥና ሦስት ልጆቿ ከጢቾ ወደ እናታቸው አገር፣ /በቀድሞ አጠራርሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት/ ጉጉማ መልጌ ወንዶ ተዛወሩ፡፡ ጉጉማ መልጌ ወንዶ የአለወጥ አያት፣ የሲዳማ ምድብ ባሩድ ቤት ዋና አዛዥ ቱርክ ባሻ *ፊታውራሪ ወርቅነኽ ለማ  ግዛት ነበር፡፡  
አጥናፍ ሰገድ፣ በእናቱ ወላጆች ዘንድ፣ ሰባት ዓመት ያህል የነበረውን የፊደል ቆጠራና የልዩ ልዩ ባሕላዊ ልማድ/ሥልጠና/ ሰብእናው የተቀረጸባቸው ሥነ ምግባራዊ ዕሴቶች እንደ ኾኑ በአንክሮ ይናገራል፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ  አጥናፍ ሰገድ እንደሚለው፤  በወጣትነቱ በአያት ቅድመ አያቶቹ ግቢ፣ ከጎንደር፣ ደንቢያና ፎገራ ተመርጠው በመጡ፣ ሥሉጣን  ሞግዚቶች ተኮትኩቶ ማደጉን፣ እንደዚህ በማለት ያስረዳል። «--ከፍ ሲል ከፋሲል፣ ዝቅ ሲል ከቴዎድሮስ የደም ጥልቀት የሥጋ ልደት እንዳለን የዘር ሐረግ እየተመዘዘ ይነገረናል፡፡
 እርሱ እንደሚለው፤ ከቱርክ ባሻ ወርቅነኽ ጋር በሥጋ ልደት የሚዛመዱ ከጎንደር ተሰድደው በመምጣት፣ በጭፍርነት ያደሩ ያገር ልጆች /ጎንደሬዎች/ ሰባት ሲኾኑ፣ ዓመት ሲሞላቸው፣ ለሥልጠና ወደ ግቢ የሚላኩትን የፊታውራሪ ወርቅነህ የልጅ ልጅ ልጆች በኹለት ምድብ ከፍለው እንደ የዝንባሌያቸው ያሠለጥኗቸዋል። ከኹለቱም ምድብ ሠልጣኞች መካከል አቋርጠው ወደ የወላጆቻቸው ቤት የሚመለሱም ነበሩ፡፡ የግቢው ሥልጠና ኹለት ምድብ /ዘርፍ/ ነበረው፡፡ አጥናፍ ሰገድ የተሰለፈው በነፍጠኝነቱ ዘርፍ ነበር፡፡ በዚህ ዘርፍ የነበረው ሥልጠና ውኃ ዋና፣ ፈረስ ግልቢያ፣ አንካሴና ጦር ውርወራ፣ በጋሻ መከታ፣ ዱላ ስንዘራ፣ ምክቶሽ፣ አባርሮ የመያዝና ሮጦ የማምለጥ፣  በመጨረሻ የዒላማ ተኩስ የሚያካትት ሲሆን፣ ሥልጠናው ዕድሜን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ ሌላው የሥልጠና ዘርፍ፣ በዳር አገር የተተከሉ አብያተ ክርስቲያናትን በዲቁና፣ በቅስናና በድብትርና የሚያገለግሉና የካህናት ማፍለቂያ የኾኑ የአብነት ትምህርት ቤቶች የሚጠናከሩበት መንገድ ነበር፡፡
ከሰባት ዓመት የግቢ ቆይታ በኋላ፣ አጥናፍ ሰገድ በአካል ብቃት ጠንክሮ፣ በባሕላዊ የጦር መሣሪያ አጠቃቀም፣ «ቁጢት በጣሽ» ለመባል ምንም ያህል ባልቀረው የጠመንጃ ዒላማ ተኩስ ሠልጥኖ፣ ፊደል ቆጥሮ፣ በጎንደርኛ ዘይቤ፣ ባህላዊ የአስተዳደግ ሥርዓት ተለብሞ፣ በመጨረሻም፣ ስለ ግልገል ነፍጠኝነቱ እውቅና፣ ከአባቱ በውርስ የደረሰውን ነጭ ቃታ ቤልጂግ ጠመንጃ ከአንድ ዙር ዝናር ጥይት ጋር በይፋዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ተረክቦ፣ የዳማ ጌታ የሚል የፈረስ ስም ወጥቶለት፣ በአያቶቹ፣ በአጎቶቹ፣ በአክስቶቹና በሌሎቹም የግቢው አዛውንቶች ጨምር ተመክሮና ተመርቆ፣ በእናቱና በኹለት እኅቶቹ ታጅቦ ከሲዳማ ወደ አባቱ አገር አርሲ ጢቾ ተሸኘ፡፡
ቤተ ሰቡ ወደ አርሲ ጢቾ በመመለስ፣ በዐደራ የቆየውን ሀብትና ንብረት ከነዐላባው፣ እንደዚሁም የቤተ ሰብ እልቅናውን ከሞግዚታቸው በመረከብ ዐዲስ ሕይወት ጀመረ፡፡ ግልገል ነፍጠኛ አጥናፍ ሰገድ፣ በእናቱ እየታገዘ፣ በአባቱ ወንድምና እኅቶች ምንዝሮቹ ላይ የእልቅና ሥራውን ቀጠለ፡፡ ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን፣ በአጭር ተቀጭቶ የቀረውን የቄስ ትምህርት ቤት (ፊደል ቆጠራ) በተሻለ ለመቀጠል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አንደኛ ክፍል ገብቶ፣ የዘመናዊ ትምህርት ተቋዳሽ ተማሪ ኾነ፡፡
የመደበኛ ፖሊስ ሠራዊትና የወኅኒ ፖሊስ ተቋማት ከ1940 ዓ.ም ጀምሮ እየተስፋፉና እየተጠናከሩ ስለ ሄዱ፣ “የመትከያ- መንቀያ” መሬት ባለቤት የሆኑትን መኻል ሠፋሪዎችን ወኅኒ ቤቶችን፣ የመንግሥት ግምጃ ቤቶችን ወዘተ…፣ በወር ተራ የማስጠበቁ ሥርዐት እየከሰመ ሄደ፡፡ ይህ መልካም አጋጣሚ፣ አጥናፍ ሰገድ፣ በቤተ ሰብ እልቅና ሥራው ላይ ይጠፋ የነበረውን ጊዜ በትምህርት ላይ ለማዋል አስቻለው፡፡
እንዳለ መታደል ኾነና፣ ነሐሴ 16 ቀን 1945 ዓ.ም እናቱ አለወጥ ታምራት፣ በስምንት ቀን የተስቦ በሽታ በሞት ተለዩት፡፡ አጥፍ ሰገድ፣ የእናቱ ሞት ምን ያህል በመራር ኀዘን እንደ መታው ትውስታውን የሚናገረው በዕንባ እያጀበ ነው፡፡ «እናቴ፣ ለ’ኔ እናት ብቻ አልነበረችም። አባትም፣ ሞግዚትም፣ አስተማሪም ነበረች» በማለት እራሮቱን እና ሰቀቀኑን ይገልጻል።፡ እኅቶቹንና  በውርስ የደረሳቸውን ሀብትና ንብረት የማስተዳደር ከባድ ኀላፊነት ሙሉ በሙሉ በአጥናፍሰገድ  ጫንቃ ላይ ወደቀ፡፡ ውጣ ውረዱን ከትምህርቱ ጋር ደርቦ መቋቋም አቃተውና ትምርቱን ከዐምስተኛ ክፍል አቋርጦ  መልከኛ(  መልከኛ ርስቱን በሑዳድ፣ በእኩል፣ በሢሶ፣ በሞፈር ዘመት በጪሰኞች እያሳረሰ፣ እንደዚሁም፣ አጎራባች ወይም ጎዳንቱ  አርብቶ አደሮች ለግጦሽና ለድርቆሽ ከሚጠቀሙበት የመሬቱ ሥረጌ ዓመታዊ ግብር በመቀበል የሚተዳደር የመሬት ከበርቴ ነው፡ ) ኾነ፡፡ አጥናፍሰገድ፣ በኹለት ዓመት ውስጥ፣ ከአንደኛ ክፍል ተነሥቶ ዐምስተኛ ክፍል የደረሰው፣በሁለት ጊዜ የማለፍ እድል  /Double Promotion / እንደ ነበር በማስታወስ «ደግ ጊዜ ነበር» ብሏል፡፡
አጥናፍሰገድ፣ ትምህርቱን ትቶ ገና በጋሜነት የጀመረው የመልከኝነት ሕይወት እንደ ዐዋቂ ለብሶ ተኮፍሶ አደባባይ መዋሉና«አንቱ - እርስዎ » መባል በቀረው አክብሮት የማኀበራዊና ቤተ ሰባዊ ግንኙነቱ መቀጠሉ የልብ ልብ እየሰጠው ሄደ፡፡ ለጋውና ጥዑም የመልከኝነት ሕይወት ተቋርጦ ወደ ትምህርት ቤት የተመለሰበትን አስገዳጅ ኹኔታ አጥናፍሰገድ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል:-
«…አንድ ቅዳሜ፣ የጢቾ ገበያ ቀን፣ እኽል ሽጬ የመሬት ግብር ለመክፈል ደፋ ቀና በማለት ላይ እንዳለኹ፣ የትምህርት ቤታችን ፖሊስ አለቃ ጋሼ ከበደ ሰላሌ፣ ከኹለት አጃቢዎቹ ጋር አስቁመው ትምህርት ቤት ትፈልጋለኽ´ አሉኝ፡፡ ስለምን ጉዳይ´ አልኋቸው፡፡ የተፈለግኽበትን ምክንያት እዚያ ሄደኽ ትረዳለኽ - ቅደም!´ ተባልኹ፡፡ ነገሩ የምር እንደ ኾነ ተረድቼ ያለማንገራገር ተከተልኋቸው፡፡ ትምህርት ቤት እንደ ደረስንም ምክትል ዳይሬክተሩ ቢሮ አስገብተውኝ፣ ሰላምታ ሰጥተው ወጡ። ምክትል ዳይሬክተሩ አጥናፍሰገድ እንኳን ደኅና መጣኽ´ በማለት ስመው እንድቀመጥ ከጋበዙኝ በኋላ `ትምህርት እንዳቋረጥኽ ሰምተናል፡፡ ችግርኽንም ተረድተናል፡፡ በዚህ ለጋ ዕድሜ የወደቀብኽን የቤተ ሰብ አስተዳደር ኀላፊነት እኔ ከጎንኽ ቆሜ አግዝኻለኹና እባክኽ ወደ ትምህርትህ ተመለስ´ በማለት አዝነውና ተክዘው ጠየቁኝ፡፡
«…እምቢ ብዬ የትም እንደ ማልደርስ ተረድቼ፣ ጥያቄያቸውን ተቀብዬ፣ ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታኅሣሥ 1946 ዓ.ም ሥራየን ስሠራ ከቆየኹ በኋላ፣ ወደ ትምህርት ቤት ተመለስኹ፡፡” አጥናፍ ሰገድ፣ የ1948 ዓ.ም የአንደኛ  ደረጃ መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና አልፎ፣ በ1949 ዓ.ም ዐዲስ አበባ ንግድ ሥራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት /ኮሜርስ/ ተመደበ፡፡ ከትምህርት ቤቶች ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ጋር ተያይዞ፣ በተግባረ እድና በኮሜርስ ትምህርት ቤት ስፖርተኞች መካከል በ1951 ዓ.ም በተፈጠረ ዐምባጓሮ ምክንያት፣ በትምህርት ቤቱ ወንድ ተማሪዎች ላይ በጅምላ ከተጣለው ቅጣት በኋላ፣ በተለይ ለግንባር ቀደም የዐምባጓሮው ተሰላፊዎች የተሰጠውን ከባድ ተግሣጽና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ባለመቀበል፣ ወደ አባቱ አገር ተመልሶ የተቋረጠውን የመልከኝነት ሕይወት ለመቀጠል ወስኖ ነበር፡፡ ሆኖም የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የሚስተር ዊልያም ናጊብ ልዩ ረዳት፣ አቶ አስፋው ከበደ ውሳኔውን በወንድማዊ ምክር ስላስቀየረው፣ ወደ ሥራ ዓለም ገባ፡፡ ሥራውንም አፈላልጎ ያስያዘው አቶ አስፋው መኾኑን በማድነቅ፣ ዘመን ያልሻረው ወዳጅነታቸውን አስታውሷል፡፡
አጥናፍ ሰገድ ሥራ የጀመረው ግንቦት 1951 ዓ.ም በመከላከያ ሚኒስቴር፣ የምድር ጦር መምሪያ ሥር በተቋቋመ የጽሕፈትና የትራንስፖርት ማሠልጠኛ ማዕከል፣ በመምህርነት በ175 ብር ደመወዝ ነበር፡፡ ሥራ እንደ ያዘ፣ የመጀመሪያ የቤት ሥራ ያደረገው፣ እሱ እንደ ወንድምነቱ ሳይጠየቅ ለባል ተድረው የነበሩትን እኅቶቹን የሺንና ላቀችን ከየባሎቻቸው አሰርቆ ወደ ዐዲስ አበባ ማስመጣት ነበርና ከብዙ ስውር ውጣ ውረድ ሙከራ በኋላ፣ ተሳክቶለት፣ እንደ ገና የቤተ ሰብ አስተዳዳሪ ኾነ፡፡ እነ የሺም ዐዲስ አበባ መጥተው፣እየተማሩ፣የቤት ውስጥ ሥራውን ቀጥ አድርገው በመያዝ ተጋገዙ። የመምህርነቱን ሥራ የያዘው በዝንባሌ ሳይኾን፣ በአማራጭ እጦት ስለ ነበር፣ በሚፈቅደው ሥራና ደመወዝ ለመቀጠር ያደረገው ጥረት ተሳክቶለት፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ፍቅር ማኀበር ሥር ተቋቁሞ የነበረው የመነን መጽሔትና የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ አሳታሚ መሥሪያ ቤት የትርጉም፣ የትየባና የዜና ዘጋቢነት ሥራ በ250 ብር ተቀጠረና ጋዜጠኛ ኾነ፡፡
ደረጃ በደረጃም በማደግ የጋዜጣ ሙያ ቁንጮ እስከ ኾነው ዋና አዘጋጅነት በሙያው  አደገበት። በዚኽ ረገድ   የኢትዮጵያ ድምፅ የእንግሊዝኛ ዕለታዊ /THE VOICE OF ETHIOPIA/ ጋዜጣ የምሽት አዘጋጅ፣  የኢትዮጵያ ድምፅ የዐማርኛ ዕለታዊ ጋዜጣ ም/ዋና አዘጋጅ፣  የዐዲስ ዘመን ዐማርኛ ዕለታዊ ጋዜጣ ተቀዳሚ ምክትል ዋና አዘጋጅ / CITY DESK EDITOR/  የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሳምንታዊ የዐማርኛ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣  በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የክፍላተ ሀገር ዜና ፣ቀጥሎ የዐዲስ አበባ ዜና ዝግጅት ዋና አዘጋጅ በመኾን አገልግሏል፡፡
አጥናፍሰገድ በቀድሞው የዘውድ ሥርዓትና በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራስያዊ ሪፑብሊክ መንግሥት፣ እንደዚሁም ባኹኑ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አንድነት ዲሞክራስያዊ ግንባር መንግሥት፣ በነፃው የግል ፕሬስ  በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኃን ውስጥ በመሳተፍ ያበረከተውን ሙያዊ አገልግሎት፣ ትሁት በኾነ ኩራት ያስታውሳል፡፡ በተለይም የነፃ ግል ፕሬስ ወርቃማ ዘመን በነበረው፣ ቅድመ 1997 ታሪካዊው ብሔራዊ ምርጫ ወቅት፣ በጦቢያና በልሳነ ሕዝብ ጋዜጦችና መሔቶች አማካይነት፣ ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመኾን፣ ሕዝብ እውነተኛ የሥልጣን ምንጭና ባለቤት መኾኑን፣ (ነፃው ፕሬስ የሕዝብ አንደበት፣ ዐይንና ዦሮ መኾኑን) በማሳወቅ፣ ያስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል፣ የሙያዊ ተጋድሎአቸው ሕያው ምስክር እንደ ነበር አፍን ሞልቶ መናገር እንደሚቻል ይገልጻል፡፡
አጥናፍሰገድ በጋዜጠኛነቱ ምክንያት አብዛኛውን የሥራ ሕይወቱን በሥነ ጽሑፍ ዙሪያ አሳልፏል፡፡ በአስተዳደር ሥራውና በማኅበራዊ ጉዳዮች አገልግሎቱ ከፍተኛ ልምድ አካብቷል፡፡ በጡረታ ዘመኑ ደግሞ ይህን ልምዱን ለተተኪው ትውልድ ለማካፈልና ለማውረስ ወደ ድርሰት መስመር ገብቷል፡፡ በዚህ መሠረት በ1997 ዓ.ም. “የበደል ካሳ” የተሰኘ የመጀመሪያ ረጅም ልብ ወለድ መጽሐፉን አሳትሟል፡፡ የአጥናፍ ሰገድ ሁለተኛ ድርሰቱ በ2008 ዓ.ም. የታተመው “የእንስሳት ዐመፅና ድርድር ከሰው ልጅ ጋር” የተሰኘ፣ በግጥም የተሰናዳ የፖለቲካ አሽሙር (Political Satire) ነው፡፡ ሦስተኛ ሥራው  በ2006 ዓ.ም.  አዘጋጅቶ ለንባብ የአበቃው “የአቤቶ ኢያሱ አነሣሥና አወዳደቅ” የተሰኘው የታሪክ መጽሐፉ ነው፡፡ አራተኛው መጽሐፍ #የሕይወቴ ምሥጢር፣ የተፈተነ ጋብቻ ኢዮቤልዩ; የተሰኘው ግለ ታሪክ ነው፡፡ የአጥናፍሰገድ አምስተኛ መጽሐፍ “አገር የፈታ ሽፍታ” (ታሪካዊ ልብ ወለድ ) በ2009 ዓ.ም. ታትሟል፡፡
ነፍሳቸውን ይማር!   

Read 1125 times