Saturday, 29 January 2022 00:00

ደቡብ ሱዳን እጅግ የከፋ ሙስና ያለባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ተባለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዴንማርክ፣ ፊንላንድና ኒውዚላንድ እጅግ አነስተኛ ሙስና ያለባቸው አገራት ተብለዋል

          ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 ሙስና በአብዛኞቹ የአለማችን አገራት ተባብሶ መቀጠሉንና ከአለማችን አገራት መካከል እጅግ የከፋ ሙስና የታየባት ደቡብ ሱዳን መሆኗን አለማቀፉ ተቋም ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በ180 የአለማችን አገራትና ግዛቶች ያደረገውን የሙስና ሁኔታ ጥናት መሰረት አድርጎ ከሰሞኑ ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ እንዳለው፣ ደቡብ ሱዳን ከ100 ነጥብ 11 ብቻ በማግኘት ከአለማችን አገራት መካከል በሙስና መስፋፋት የ1ኛ ደረጃን ለመያዝ ችላለች፡፡
ሶማሊያና ሶርያ በተመሳሳይ 13 ነጥብ በማግኘት በሙስና ሁለተኛውን ደረጃ መያዛቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ቬንዙዌላ በ14 ነጥብ በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም አመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ 88 ነጥብ ያገኙት ዴንማርክ፣ ፊንላንድና ኒውዚላንድ በአንጻሩ እጅግ አነስተኛ ሙስና ያለባቸው ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡
ጥናቱ ከተሰራባቸው 180 አገራት መካከል 70 በመቶ ያህሉ የከፋ የሙስና ችግር እንዳለባቸው ለማወቅ መቻሉ የተገለጸ  ሲሆን ባለፉት 10 አመታት 154 የአለማችን አገራት ሙስና እየተባባሰባቸው ወይም መሻሻል ሳይታይባቸው መቅረታቸውን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ ሙስና የቀነሰባቸው በአንጻሩ 25 አገራት ብቻ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡


Read 1160 times