Saturday, 05 February 2022 11:47

(ይህ ዓምድ ከአገር ውስጥና ዓለማቀፍ የህትመት ውጤቶች የተመረጡ መረጃዎችና ዘገባዎች በአጭሩ የሚቀርብበት ነው፡፡)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በአብዬ ግዛት የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ በናይጄሪያዊው ጄኔራል ተተኩ


           ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ትገባኛለች በሚሏት የአብዬ ግዛት የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ጦር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሜጄር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ተሰማ፣ በናይጄሪያዊ ጄኔራል እንደተተኩ የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የናይጄሪያ ጦር አዛዥ የሆኑትን ሜጀር ጄኔራል ቤንጃሚን ኦሉፌሚ ሳውየርን በአብዬ ለድርጅቱ ሰላም አስከባሪ አዛዥ አድርገው መሾማቸውን ድርጅቱ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡባት አብዬ ግዛት በተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቲቷ እንዲወጣ ሱዳን መጠየቋን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስማማቱን ባለፈው ዓመት ማስታወቁ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ሱዳን ባወጣችው መግለጫ የኢትዮጵያ ጦር በሌሎች የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲተካ መስማማታቸውን ብትገልጽም፣ ከየትኛው አገራት እንደሆነ አልተጠቀሰም።
በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ከአብዬ ግዛት እንዲወጡና በሌላ አገር ጦር እንዲተኩ ሱዳን ተመድን በተደጋጋሚ መጠየቋ ይታወሳል። በወቅቱ የሱዳን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ ሠራዊት በምሥራቃዊ የሱዳን ድንበር አካባቢ እየተጠናከረ ባለበት ጊዜ ስትራቴጂክ በሆነው የሱዳን ማዕከላዊ ስፍራ ላይ የኢትዮጵያ ኃይሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ምክንያታዊ አይሆንም” ብሎ ነበር።
በተፈጥሮ ሀብት በታደለችው የአቢዬ ግዛት የመንግሥታቱ ድርጅት ካሰማራቸው ሰላም አስከባሪዎች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው። በዚህ ኃይል ውስጥ በአጠቃላይ 4,190 ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ሰላም አስከባሪዎች የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 3 ሺህ 158 ወታደሮችና ሰባት የፖሊስ መኮንኖች ከኢትዮጵያ መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ተሰናባቹ ሜጀር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ተሰማ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ በአብዬ ቆይታቸው ወቅት ላሳዩት ትጋት፣ ከፍተኛ አገልግሎትና ውጤታማ አመራር አንቶኒዮ ጉቴሬዝ  ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
 (ቢቢሲ)



Read 751 times