Saturday, 05 February 2022 11:50

የከረዩ አባ ገዳና የገዳ አባላትን የገደሉ የጸጥታ ሃይሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ኢሰመኮ ጠየቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኦሮሚያ ፖሊስ ድርጊቱን የፈጸሙትን ለህግ አቀርባለሁ ብሏል
                      
              የከረዩ የሚቺሌ ገዳ የጅላ አባላት የተገደሉት በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መሆኑን በምርመራ ማረጋገጡን የጠቆመው  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ ድርጊቱን የፈጸመና  ያስፈጸሙ የጸጥታ አካላት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡና ለተጎጂዎች ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው የጠየቀ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ በበኩሉ የኮሚሽኑን ሪፖርት ተቀብሎ የራሱን ማጣራት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ህዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም የከረዩ አባገዳን ጨምሮ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላትን የገደለው በአሸባሪነት የተፈረጀው የሸኔ ቡድን ነው ሲል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባደረገው ማጣራት ግን ግድያውን የፈጸመው የክልሉ የጸጥታ ሃይል መሆኑን ማረጋገጡን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው፣ በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ላይ ያደረገውን ምርመራ የያዘ ሪፖርት ባለፈው ረቡዕ ጥር 25 ይፋ ባደረገ ወቅት ባወጣው መግለጫ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ህዳር 22 ቀን 2014 የከረዩ የሚቺሌ  ገዳ አባላት ተሰባስበው የገዳ ስነስርዓት ከሚፈጽሙበት አረዳ ጂላ 39 ያህሉ በክልሉ የጸጥታ ሃይሎች ታፍሰው መወሰዳቸውን ኮሚሽኑ አመልክቷል።
በወቅቱ ለግለሰቦቹ መታሰር ምክንያት የሆነውም ህዳር 21 ቀን 2014 ለስራ ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ሄደው ወደ መተሃራ ከተማ በመመለስ ላይ በነበሩ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ሃይሎች የተፈጸመው ጥቃት ሲሆን በዚህም ጥቃት 11 የፖሊስ አባላት መገደላቸውንና 17 ያህሉ መቁሰላቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል።
ይህን ተከትሎ በነጋታው ህዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6 ሰዓት ጥቃቱን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ የከረዩ ሚችሌ አባገዳዎችና የጂላ አባላት መኖሪያ ወደሚገኝበት ጡጢቲ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ዴዲቲ ካራ ወደተባለ ሥፍራ የደረሱት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች፣ 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው በኮሚሽኑ ሪፖርት ተጠቁሟል።
ከእነዚህ በጸጥታ ሃይሎች ከተያዙ የከረዩ ሚችሌ ገዳ አባላት መካከል 16 ሰዎች ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ተወስደው፣ 14ቱ መሬት ላይ እንዲተኙ ተደርገው በጥይት ተደብድበው መገደላቸውንና ሁለቱ ወደ ጫካ ሮጠው ማምለጣቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።
ግድያው ከተፈጸመ በኋላም የሟቾች ቤተሰቦች አስክሬን እንዳያነሱ በፖሊስ መከልከላቸውን፣ በዚህም በከፊል የሟቾች አስክሬን በአውሬ መበላቱን የጠቆመው ሪፖርት፤ ቀሪዎቹ 23 ግለሰቦች ወዴት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ ቆይቶ ከሁለት ሳምንት በኋላ አንደኛው አስክሬን ለቤተሰቦቼ መሰጠቱን፣ በዚህ አስክሬን ላይ በተደረገ ምርመራም፣ ግለሰቡ ክፉኛ መደብደቡን የሚያመላክት ውጤት መገኘቱን አስታውቋል።
ቀሪዎቹ 22 የሚችሌ ገዳ አባላት ከሳምንት በኋላ መለቀቃቸው በሪፖርቱ የተመለከተ ሲሆን 15ቱ ግለሰቦች ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ ከህግ አግባብ ውጪ መገደላቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ ይህን የግድያ ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ የፀጥታ አካላት እንዲሁም በፖሊስ አባላት ላይ የግድያና የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች በህግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ ሊደረግ እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳስቧል። ለሟቾች ቤተሰቦችና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸውም ተገቢ የሆነ ካሳ እንዲሰጣቸውም ጠይቋል- ኮሚሽኑ።
ይህን የኮሚሽኑን የምርመራ ሪፖርት በአዎንታ የተቀበለው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፤ ድርጊቱ ከህግ አግባብ ውጪ የተፈጸመ መሆኑን አምኖ፣ ድርጊቱን የፈፀሙ የፀጥታ አባላትን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።
“በድርጊቱ እጁ ያለበትን የትኛውም አካል ለህግ ያቀርባል” ያሉት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን እስካሁን ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ሁለት ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ቀሪ  የወንጀል ምርመራው በዝርዝር ተከናውኖ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

Read 6762 times