Saturday, 05 February 2022 11:53

የነዳጅ ጥራትና ስርጭት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ነው

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

  •  ለነዳጅ እጥረቱ አንዱ ምክንያት ነዳጅ  በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገር እየወጣ በመሆኑ ነው ተብሏል
          •  መንግስት ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት በሚፈጥሩ ወገኖች ላይ የማያዳግም እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል
          •  በነዳጅ ግብይት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የተቋቋመው መ/ቤት ሥራውን ሳይጀምር ዳግም ሊደራጅ ነው
              
            በነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦት፣ ጥራትና ስርጭት ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ። ሰሞኑን በከተማችን አዲስ አበባና በአማራ ክልል  የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት በሚያባብሱ ወገኖች ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል።
አንዳንድ ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎችና የነዳጅ ማደያዎች ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት ለመፍጠር ከሚያደርጉት ህገ-ወጥ አሰራር እንዲታቀቡ ያሳሰበው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፤ እነዚህ ወገኖች ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ ግን የሚያዳግም እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል። የመጪው የካቲት ወር የችርቻሮ ነዳጅ መሸጫ ዋጋ ባለበት እንደሚቀጥልም  ሚኒስቴር መ/ቤቱ አስታውቋል።
ሰሞኑን በተለይም በአዲስ አበባና በአማራ ክልል የተፈጠረውን  ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ለመፍታት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በባህርዳር ከተማ የመከረ ሲሆን በክልሉ የነዳጅ እጥረቱ የተፈጠረው ነዳጅ በኮንትሮባንድ  ወደ ጎረቤት አገር እየወጣና እየተሸጠ በመሆኑና ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ለክልሉ ማድረስ ያለባቸውን ነዳጅ ለማደያዎች በትክክል እያደረሱ መሆን አለመሆናቸውን የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ ነው ተብሏል።
በዚሁ ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃ/ማርያም እንደተናገሩት፤ እነዚህን ለነዳጅ እጥረቱ መነሻ ምክንያት የሆኑትን ህገ-ወጥ አሰራሮች በማስወገድ በክልሉ የታየውን የነዳጅ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።
የአማራ ክልል ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ፣ በክልሉ ለተፈጠረው የነዳጅ እጥረት መነሻ ምክንያት አንዳንድ ባለሃብቶች በህገ-ወጥ መንገድ ለመበልጸግ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መሆኑን አመልክተው፤ ይህንን ችግር ለማስወገድና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭቱ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ሊደረግበት የሚገባ ዘርፍ ቢሆንም አሰራሩ ለህገ-ወጥ እንቅስቃሴ የተመቸ በመሆኑ ከፍተኛ ድጎማ እየተደረገበት ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የነዳጅ ምርት የህገ-ወጥ ነጋዴዎች ሲሳይ ሲሆን ቆይቷል። ይህንን ህገ-ወጥ አሰራር ለማስቀረት ያስችላል የተባለውና በነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦት፣ ጥራትና ስርጭት ላይ ጥበቅ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል አሰራር  ተግባራዊ ሊደረግ ነው።
ይኸው በዘርፉ ተሰማርተው ይሰሩ የነበሩ የተለያዩ ተቋማትን በማዋሃድ በነዳጅ ጉዳዮችና ግብይት ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥርና ክትትል በሚያደርግ ተቋም ስር ይጠቃለላሉ ተብሏል።
በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር  መ/ቤት ስር ይደራጃሉ የተባሉት  የነዳጅና ነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን፣ በማዕድን ሚኒስቴር ስር የነበረው የፔትሮሊየም ምርቶች ጥራት ተቆጣጣሪ ዳይሬክቶሬትና ኢነርጂ ባለስልጣን ናቸው። እነዚህ ተቋማት ከተዋሃዱ በኋላ የነዳጅ አቅርቦትና  ስርጭት የሚመለከቱ ጉዳዮች በሙሉ በአንድ ተቋም ስር እንዲተገበር ይደረጋልም ተብሏል።
ከተቋቋመ የሁለት ዓመት ዕድሜን ያስቆጠረው የነዳጅና ነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትን ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን፣ በነዳጅ ጉዳዮች ጥራትና ግብይት ላይ ቁጥጥር ያደርጋል ተብሎ ሃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ ባለስልጣን መ/ቤቱ ገና ራሱን በማደራጀት ላይ ሳለ ስራውን ሳይጀምር ዳግም እንዲዋሃድ መደረጉም ታውቋል።
በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከቀን ወደ ቀን እየናረ ቢሆንም፣ በአገራችን ያለው የችርቻሮ ዋጋ በጥር ወር በነበረው እንዲቀጥል ተወስኗል- በሊትር 31 ብር ከ74 ሳንቲም። ይህ የቤንዚን የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋ ባለፈው ህዳር ወር 2014 ዓ.ም በሊትር 25 ብር ከ85 ሳንቲም የነበረ ሲሆን ከታህሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ 31 ብር ከ74 ሳንቲም እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።

Read 9194 times