Saturday, 05 February 2022 11:55

የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በኮቪድ-19 ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ላይ ይወያያል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  ሁሉም ሚኒስትሮች በአፍሪካ አገራት የመሪዎች አቀባበል ላይ ተሳትፈዋል
                           
             ከ50 በላይ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎችና ተወካዮች ዛሬ ለሚጀመረው የአፍሪካ ህብረት 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ ከሃሙስ ምሽት ጀምሮ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን በመንግስት ካቢኔ የተካተቱ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር  ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከሞላ ጎደል ሁሉም ሚኒስትሮች በእንግዶች አቀባበል ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ጉባኤው በዋናነት የኮቪድ ወረርሽኝ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖን ይገመግማል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም ከተለመደው የአቀባበል ፕሮቶኮል በተለየ መልኩ ዘንድሮ  ሁሉም ሚኒስትሮች  ለጉባኤው አዲስ አበባ በገቡ በእንግዶች አቀባበል ስነ-ስርዓት ላይ እንደተሳተፉ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም መሰረት፣ የኢዜማ መሪ የሆኑት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የኮትዲቫሩን ፕሬዚዳንት አለማን ኦታራን የተቀበሉ ሲሆን፣ የታንዛኒያ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፊሊፕ ፓንጎ ደግሞ በአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበሩና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አቶ በለጠ ሞላ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ሌሎች ሚኒስትሮችም በዚህ የአቀባበል ስነ-ስርዓት ላይ የተሳተፉ ሲሆን የጋምቢያ ም/ፕሬዚዳንት ኢሳቶ ቶሬ በማእድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢ/ር ታከለ ኡማ፣ የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ በሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም፣ የሞሪታኒያ ፕሬዚዳንት መሃመድ አሎድ ጋዘኒ በመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ፣ የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማሳል በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ አቀባበል እንደተደረገላቸው የውጭ ጉዳይ  መረጃ ያመለክታል።
ዛሬ እና ነገ የሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት የጉባኤውን የመወያያ አጀንዳ የሚያስቀምጠው የአፍሪካ ሃገራት የሚኒስትሮች ጉባኤ ባለፈው  ረቡዕና ሐሙስ ባካሄደው ውይይት፣ የመሪዎቹ ጉባኤ በዋናነት በኮቪድ 19 ወረርሽኝና ባስከተለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ላይ እንዲወያይ  አጀንዳ ማስቀመጡን ያመለከተው የውጭ ጉዳይ  መረጃ፤  በዚህ አጀንዳ ስርም የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠርና መከላከል (CDC) ተቋምን አጠናክሮ ወደ ተግባራዊ ስራ በማስገባት ጉዳይ ላይ ሚኒስትሮች መወያየታቸውን ጠቁሟል።

Read 11100 times