Saturday, 05 February 2022 11:56

ጡት ማጥባት …..በስራ ላይ ላሉ እናቶች

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 በ2021 ለንባብ የበቃው አለምአቀፍ የጡት ማጥባት Journal ወይንም ጋዜጣ ላይ ሙሉ ከበደ እና ቢንያም ሰይፉ ያወጡትን መረጃ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰራተኞች ህግ ስለወሊድ ፈቃድ የወጣውን ደንብ አክለን ወደአማርኛ በመመለስ ለንባብ ብለናል፡፡ በቅድሚያ ግን አን ዲት ወላድ ሴት ያጋራችንን እውነታ እናስነብባችሁ፡፡
‹‹…የትምህርት እድል አግኝቼ ወደ ስዊድን አገር ተጉዤ ነበር፡፡ በዚያም ትምህርቴን ጨርሼ እስከምመለስ ድረስ የተወሰኑ አመታት ቆይቻለሁ። አብራኝ የነበረች ጉዋደኛዬ እህትዋ በዚያው ትኖር ስለነበር ብዙ ነገር የመመልከት እድል አግኝቼአለሁ። ከሁሉ በላይ የሚያስ ደስተኛና የሚያስቀናኝ እህትየው ልጅ ወልዳ ያረፈችው ወይንም በህግ የተሰጣት የወሊድ ፈቃድ ነው፡፡ በአገሩ የሚሰጠው የወሊድ ፈቃድ ለሴትዋ ብቻ ሳይሆን ለወንዱም ጭምር ነው፡፡ የተወለደውን ልጅ በአግባቡ ለማሳደግ ሲባል የሚሰጣቸው የወሊድ ፈቃድም ለልጁ ሲባል እንጂ ለወላጆች አይደለም የሚል እምነት አለ፡፡
በስዊድን አገር አንዲት እናት ልጅ ስትወልድ ለእናትየውም ሆነ ለአባትየው ለእያንዳንዳቸው የ240 ቀን በድምሩ 480 ቀናት (አራት መቶ ሰማንያ ቀናት) ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ እናትየው ብዙ እንድታርፍ ከተስማሙ ከአባ ትየው 150 ቀናትን መበደር ትችላለች፡፡ አባትየው ዘጠናውን ቀን ለሚስቱ ሳይሰጥ እርሱ እራሱ ልጁን መንከባከብ እንደሚገባው ህጉ ያስገድዳል፡፡ በተጨማሪም ልጁ ልክ ሲወለድ አባትየው አስር የስራ ቀናትን በፈቃድ ወስዶ ህጸኑን እና እናትየውን የመንከባከብ መብት አለው፡፡ የደመወዝ ጉዳይ እንደ ስራ ጊዜውና እንደ ክፍያው መጠን የተለያየ ይሁን እንጂ ሁሉም ወላጅ ልጅ ሲወልድ በፈቃድ ወቅት ገንዘብ ይከፈለዋል። ስራ የሌላቸውም ሴቶችም ቢሆኑ መጠ ነኛ ክፍያ ይሰጣቸዋል፡፡ ለሁሉም የወሊድ ፈቃድ ክፍያውን የሚሰ ጠው መንግስት እንጂ የሚሰሩበት ድርጅት አይደለም፡፡ ምናልባት የሚያ ገኙት ክፍያ ከፍተኛ ከሆነ እና የማዘጋጃ ቤቱ የክፍያ ጣሪያ የማይሸፍነው ከሆነ አንዳንድ ድርጅቶች ክፍያውን የሚያሟሉበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ይህም የተወለዱት ልጆች በተገ ቢው ሁኔታ እንዲያ ድጉ የሚረዳ አሰራር ነው፡፡ አባትየው የእረፍት ጊዜውን በጊዜው ባይጠቀ ምበት እንኩዋን ዘጠና ቀን እስኪቀረው ድረስ የቀረውን ጊዜ እስከ አራት አመት ድረስ ሳቃጠል ይጠቀምበታል፡፡ ሳይቃጠል ሊቆይ የሚችለው ፈቃድ የዘጠናው ቀን ብቻ ሲሆን ይህ ደግሞ ልጁ አስራ ሁለት አመት እስኪሆነው ድረስ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ ህጻኑ በእናትየው ፈቃድ ጊዜ ከስድስት ወር በላይ ጡት ጠብቶ ወደ ስራ ገበታዋ ትመለሳለች፡፡ በአባትየው ፈቃድ ጊዜ ደግሞ ህጻኑ እድሜው አንድ አመት እና ከዚያ በላይ ሆኖት ወደ ህጻናት መዋያ ከገባ በሁዋላ አባትየውም ወደ ስራው ይገባል፡፡
በእርግጥ ሀገሩ ሀብታም ስለሆነ ከዚያ ጋር መፎካከር ሊያስቸግር እና በብዙ ሀገራትም ላይተገበር ይችላል፡፡ ነገር ግን የአስተሳሰብና የአካል ብቃቱ የተሙዋላ ልጅ ለማሳደግ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጡ ያሳያል፡፡ በእኛ አገር ያለው የወሊድ ፈቃድ ምናልባት ከአንዳንድ አገሮች የተሻለ ነው ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ህጻኑ ለስድስት ወር ጡት ጠብቶ እስኪያድግ ድረስ እንኩዋን ቢሆን ምን አለበት? የአባትየውን የወሊድ ፈቃድ ግን ማንሳት አልፈልግም፡፡
ከአዲስ አበባ ልደታ
የዚህች እናት ትዝብት የብዙ እናቶች እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ እንደየሀገራቱ የኢኮኖሚ አቅም የእናቶች የወሊድ ፈቃድ ጊዜ መለያየቱ በእርግጥ የታወቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በየደረጃው ሲሻሻል ቆይቶ አሁን በተሸሻለው የሰራተኛ ህግ በስራ ላይ ያሉ ሴቶች ልጅ ሲወልዱ 120 ቀን የወሊድ ፈቃድ ከክፍያ ጋር እንዲሆን ተወስኖአል። ይህንን የአራት ወር ጊዜ በመከፋ ፈል ሰላሳው ቀን ከወሊድ በፊት እና ዘጠናው ቀን ደግሞ ከወሊድ በሁዋላ እንዲሆን ህጉ ይደነ ግጋል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ እናቶች ከወሊድ በፊት የሚወሰደውን ፈቃድ ሳይወስዱ ይወልዱና አራቱንም ወር ከወሊድ በሁዋላ ይጠቀሙበታል፡፡ ነገር ግን በብዙዎች ዘንድ የማይመከር አካ ሄድ ነው፡፡ ምክንያቱም ከወሊድ በፊት የሚሰጠው ሰላሳ ቀን ለመውለድ ሲቃረቡ እዳይደክሙና እረፍት እንዲያደርጉ ሲሆን በሌላም በኩል የመውለጃ ጊዜያቸው ከደረሰ በሁዋላ እንደሚፈለገው ሊንቀሳቀሱ ወይንም ሊሰሩ አይችሉም ከሚል እሳቤ ነው፡፡ የወንዶች የአባትነት ፈቃድ ግን በመንግስት መስሪያ ቤት የሚሰሩ ከሆነ አስር የስራ ቀናት በግል ድርጅት የሚሰሩ ከሆነ ደግሞ ሶስት የስራ ቀናት ይሰጣቸዋል፡፡
ሙሉ ከበደ እና ቢንያም ሰይፉ በአለም አቀፍ የጡት አጠባብ Journal በ2021 በኢትዮጵያ በስራ ላይ ያሉ ሴቶች ጡት ማጥባት ምን ያህል የህግ ጥበቃ እና ድጋፍ የተደረገለት ነው ከሚል ያሰፈሩት የጥናት ውጤት የሚከተለው ነው፡፡
የእናት ጡት ማጥባት በአለም አቀፍ ደረጃ የህጻናቱን ሞት በመቀነስ ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው ነው፡፡ የሴቶች አቅም መጎልበት ለህጻናቱ የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ እና ህጻናቱ ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ በማድረጉ ረገድ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ባለፉት አስርት አመታት በኢትዮጵያ ያለው የሴቶች ስራ መቀጠርና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግ ቀስ በቀስ ከፍ እያለ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይሁን እንጂ የሴቶች ስራ ላይ መሰማራት ከልጅ መውለድና ጡት ማጥባት ጋር በማያያዝ በተሳሳተ መንገድ በስራው ላይ ችግር ይፈጥራል በሚል የሚ ተረጉሙ መኖራቸው የሚስተዋል ነው፡፡ በእርግጥ በስራ ላይ ያሉ ሴቶችን ጡት የማጥባት ጊዜ እንዲወስን ተደርጎ የወጣው ህግ እና እቅድ በመስሪያ ቤታቸው ሊደረግላቸው የሚገ ባውን ድጋፍ ስለሚደነግግ ሰራተኛ የሆኑ እናቶች ከወሊድ ፈቃድ ሲመለሱ በስራ ገበታቸው ላይ የሚኖራቸውን መብትና የስራ ይዞታቸውን እንደሚያ ስከብር እሙን ነው፡፡ ይህንን ጥናት ያቀረቡት ባለሙያዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ የተደነ ገገው ህግ፤ ፖሊሲ፤ እና አሰራር በትክክል የህጻናቱን መብት አክብሮአል ለማለት ያስቸግራል፡፡ እናቶች በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠላቸው የጡት ማጥባት መብት በኢትዮጵያ ሲከበር የማይታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌም በብዙ ሀገራት ተግባራዊ የተደረገው ስራ ላይ ያሉ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት የሚያጠቡበት ስፍራ በአቅራቢያቸው ወይም በሚሰሩበት ተቋም ውስጥ መኖሩ በኢትዮጵያ ብዙም የሚታይ አይደለም። በስራ ቦታዎች አካባቢ ጡት የማጥባት መብት አለመከበሩ ይበልጡኑ የሚጎዳው ህጻናቱን መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ ተሻሽሎ የወጣው የሰራተኛ ህግ ቁ.1156/2019 የእናቶችን ደህንነት በመጠበቁ ረገድ አብዛኛውን የአለም አቀፍ የሰራተኛ ህግ የያዘውን ቢያካትትም ነገር ግን ስራ ላይ ያሉ እናቶችን ጡት የማጥባት መብትና አቅማቸውን እንዳይጠቀሙ የሚያደርጋቸውን አሰራር በመከላከሉ ረገድ ደካማ የሆነ አሰራርን የሚከተል ነው፡፡ የተሻሻለው ህግ ቁጥር 1064/2017 በየመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚጠቡ ህጻናት የሚውሉባቸው ቦታዎች ወይንም እናቶች ጡት የሚያ ጠቡበት እና የሚንከባከቡበት ክፍል እንዲኖር ይደነግጋል፡፡ ይህ ግን አንዳንድ ቦታ ቁጥራቸው አነስተኛ ለሆኑ እናቶች ተግባራዊ ቢደረግም በአብዛኛው ብዙ እናቶች በሚሰሩበት እንደ ግብርናና የኢኮኖሚ ተቋማት ውስጥ ተግባራዊ ያልተደረገ በመ ሆኑ ጡት የሚጠቡ ህጻናትንም ሆነ የሚያጠቡ ሰራተኛ እናቶችን መብት የሚነካ ነው ፡፡ አለም አቀፉ የሰራተኞች ህግ ILO ባወጣው ህግ መሰረት የአገራቸውን አሰራር የነደፉ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሀገራት ልምድ እና አሰራር በመቅሰም የሚያጠቡ እናቶች በስራቸው አካባቢ ለህጻናቶቻቸው የሚያገኙትን መቆያና ጡት ማጥቢያ ማቋቋም ቸል ሊባል አይገባውም እንደ ጥናት አቅራቢዎቹ እማኝነት፡፡  
በኢትዮጵያ አንዲት እናት ልጅ በምትወልድበት ጊዜ የሚሰጣት የወሊድ ፈቃድ ህጻኑ ጡት ብቻ መመገብ አለበት ተብሎ ከተቀመጠው የስድስት ወር ጊዜ ያነሰ በመሆኑ በአስተሳሰቡና በአካል ብቃቱ የተሟላ ልጅን ከማሳደግ ጋራ በእጅጉ ይቃረናል። በእርግጥ ይህ የወሊድ ፈቃድ ከምንም ተነስቶ በየደረጃው እያደገ የመጣ መሆኑ ባይካድም አሁንም የነገዎቹን ተተኪዎች መብት በሚየሟላ መልኩ መቀረጽ ይገባዋል፡፡
ጥናት አቅራቢዎቹ ያጠቃለሉት የጡት ማጥባትን የሚመለከተው ህግ በመስሪያ ቤቶች የጡት ማጥቢያ ቦታዎች ካልተዘጋጀ እና ድጋፍ ካልተደረገ እንዲሁም አሰራሩ በእቅድ ካልተደገፈ ጡት የሚያጠቡ ሰራተኛ እናቶችን በትክክል ልጆቻቸውን የጡት ወተት እንዳ ይመግቡ ስለሚያደርግ መብታቸውን ይጋፋል። ከምንም በላይ ደግሞ የጡት መጥባት መብት ያላቸውን ህጻናት ደህንነት የሚቃወም አሰራር ይሆናል፡፡ ፖሊሲ አውጪዎች፤ መንግስት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲ ሰጡና ህጉ ተሻሽሎ የወሊድ ፈቃድ ስድስት ወሩን ለማጥባት እንዲያስችል እንዲሁም እናቶች በስራ ቦታቸው ልጆቻቸውን የሚያጠቡበት ስፍራ እንዲያገኙ እንዲሁም አጥብተው ወደ ስራ የሚመለሱበት ስፍራ ቢዘጋጅላቸው እና ልጆቻቸውን በተመቻቸ ሁኔታ እንዲ ያሳድጉ ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል ምንጭ ያደረግናቸው ሙሉ ከበደ እና ቢንያም ሰይፉ ከአለም አቀፍ የጡት ማጥባት Journal ፡፡
በኢትዮጵያ በተገቢው መጠን ጡት አለመጥባት ለህጻናት ሞት ፤ህመም እና ባልተመጣጠነ ምግብ ለመሰቃየት ምክንያት ነው፡፡

Read 11478 times