Saturday, 05 February 2022 12:10

የምክክር ኮሚሽን ወይስ የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

የአገራዊ ምክክር አላማ፣ “አንድ ሁለት ሕጎችን ለማሻሻል ብቻ” ሊሆን ይችላል፡፡ የምርጫ ህግ ማሻሻል፣ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ ቁጥብ ነው፡፡
ሕግ መንግስትን እስከ መቀየር የሚንደረደር የምክከር ዓይነትም አለ፡፡ “ ስር ነቀል አብዮት” ለመሆን ይዳዳዋል- ሁሉንም ነገር በአንዴና በቀላሉ ቀይሮ ለመገላገል፡፡
በለዘብታ ጀምሮ፣ ቀስ በቀስ በስሜት እየጋለ  የሚሄድ ደግሞ፣ሌላ የምክከር አይነት ነው፡፡ ከቁጥብነት ወደ ችኩልነት ይንሸራተታል፡፡ ጥቂት የህገ መንግስት አንቀጾችን የማሻሻል ጉዳይ ውስጥ ይገባል፡፡ ከዚያም ተሻግሮ፤ ነባሩን የማስወገድና አዲስ የማዘጋጀት ስሜት ይሟሟቃል፡፡
የምክክሩ ሙቀት፣ በሰከነ ስምምነት የተገኘ  እድገት ሊሆን ይችላል። ግን ፍሬን የለቀቀ የቁልቁለት ፍጥነትም ሊሆን ይችላል፡፡ ውጤቱ ከመነሻው ከቁጥብ ምኞት ጋር ሲነፃፀር፣እጅግ የተሻለና የላቀ፣…. አለበለዚያ ደግሞ፣ ነባሩን ሁሉ የሚያደፈርስና የሚያተራምስ ይሆናል ባዶ የሚያስቀር፡፡
             ዮሃንስ ሰ


                  ሶስቱም “ሀገራዊ ምክክሮች”፤ ከእየራሳቸው ፋይዳና ተስፋ ጋር፣ የየራሳቸው ፈተናና አደጋ አላቸው፡፡
ቆጠብ ለዘብ ያለ ምክክር፣ ብዙዎችን አይማርክም፡፡ አቅልለው ያዩታል፡፡ ችላ ይሉታል፤ “ለግብር ይውጣ”  ብቻ  የሚዘጋጅ ይመስላቸዋል፡፡ የሚያጣትሉትም ይኖራሉ፡፡
“በጥቂት ዋና ዋና የማሻሻያ ሀሳቦች አማካኝነት፣ ወደ መልካም ፍሬ ይደረሳል” ብለው አያስቡም፡፡
በዚህ በዚህ ምክንያት፣ “ለዘብተኛና ቁጥብ ምክክር” ብዙ ትኩረት ላያገኝ” ይችላል፡፡ ፈተና ነው፡፡
ግን ደግሞ፤ ለዘብ ያለ ምክክርና ቁጥብ የማሻሻል ሀሳብ፣ ብዙ አያጣላም፡፡
“ቁጥብ ምክከር”፣ ለውዝግብ አይመችም። አላስፈላጊ ንትርክ የሚፈጥሩ ሰዎችን አያበራክትም፡፡ ይሄ ጥሩ የቁጥብ ምክክር ገፅታ ነው፡፡
 ጥሩነቱም፤ በቅርቡ የጸደቀው “የምክከር አዋጅ”፣ ወደ ቁጥብንት ያዘነበሉ በርካታ አንቀፆችን ይዟል፡፡
ወደ አብዮታዊነት ያዘነበሉ አንቀጾችንም ጎን ለጎን  አሰልፏል፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 6 ውስጥ፣ከበርካታ ቁጥብ ሀሳቦች ጎን ለጎን የገባ፣ “አዲስ የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር” የሚል አባባል አለ፡፡ ቁጥብ ወይም ለዘብተኛ አባባል አይደለም። “አብዮታዊ አባባል ነው”  ሊባል ይችላል፡፡ ይህንን ስሜት የሚያገዝፉ ሌሎች አገላለፆች መኖራቸውም አይካድም፡፡
ቢሆንም ግን፣ የአዋጁ ጠቅላላ ይዘትና መልዕክት፣ ነባሩን ስርዓት የማስወገድና አዲስ ስርዓት የመፍጠር ሀሳብ ላይ የሚያጠነጥን አይደለም፡፡
ሙሉ ለሙሉ ህገ መንግስትን የመቀየር አላማ ላይ  ብቻ ያነጣጠረም አይደለም አዋጁ፡፡ ለዘብተኛም አብዮተኛም አዝማሚያዎች አሉት፡፡ ስር ነቃይ ዝንባሌንም፤ የጥንቃቄ የቁጥብነት ዝንባሌንም ይዟል አዋጁ፡፡
የምክክር ኮሚሽን የአላማ ዝርዝር ውስጥ የምናገኛቸውን ነጥቦች ተመልከቱ።
“ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ችግሮች፣ወሳኝ ምክንያቶችን በመለየት” …..ኮሚሽኑ የውይይትና የምክክር  ርዕሰ ጉዳዮችን ያዘጋጃል- ፡፡ (አንቀጽ 6.1)፡፡
ምክክሮቹ፣… “የአለመግባባት መንስዔዎችን  በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ” ላይ የሚያተኩሩ”  እንዲሆኑ ያደርጋል- ኮሚሽኑ (አንቀፅ 6.2)፡፡
“….አዲስ የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ ውይይቶች” እንዲካሄዱ ያደርጋል(አንቀጽ 6.3)፡፡
በአዋጁ አንቀጾች ውስጥ የሰፈሩ  እነዚህ አገላለፆች እንዲህ በቁንጽል ቀንጨብ ቀንጨብ ተደርገው ሲታዩ፣ የአብዮት ዝንባሌን አግዝፈው ያጋንናሉ፡፡
“የምክከር ኮሚሽን”፣ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ፤ ወደ “ህግ መንግስት አርቃቂ ኮሚሸን”  የተጠጋ መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ይሄኛውን ኮሚሽን ተከትሎ፤ ሌላኛው የሚመጣ ቢመስል አይገርምም፡፡
አብዮታዊ ስሜት ያዘሉትን አገላለፆች፣ ከጠቅላለው የአዋጅ ይዘት ጋር አገናዝበንና አነጻጽረን ስንመለከታቸው ግን፣ የአዋጁ ቁጥብነትና ጠንቃቃነት ያመዝናል ማለት ይቻላል።
ከሁሉም በፊት፣ የአዋጁን ጠቅላላ ይዘትና አላማ ለማስረዳት፣ በቀዳሚነት የተጻፉት የመግቢያ ነጥቦች፣ ለዘብ ቆጠብ ያሉ ናቸው።
“አገራዊ ጉዳች ላይ፣ የሃሳብ ልዩነትና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ፤ ይህን ልዩነትና አለመግባባት ለማርገብና ለመፍታት”… አገራዊ ምክክሮችን ማካሄድና አገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፣ አዋጁ እንደተዘጋጀ ይገልጻል- የአዋጁ መግቢያ፡፡
የሃሳብ ልዩነቶችን ማርገብና መግባባትን መፍጠር፣…የሚለው አባባል “አብዮታዊ አባባል ነው” አይባልም።
“የተሻለ አገራዊ መግባባትን ለመገንባት”
“በሂደትም የመተማመንና፣… ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት” በሚል ሃሳብ የመጣ አዋጅ እንደሆነም መግቢያው ይዘረዝራል።
“የተሻለ”፣ “በሂደት”፣ “ባህል” የሚሉት ቃላት፣ “ስር-ነቃይ አብዮትን” ሳይሆን፣ የመሻሻል ጉዞን፣ ጥንቃቄንና ስክነትን የሚጠቁሙ ቃላት ናቸው።
እነዚህ ሃሳቦችና ቃላት ጎልተው የተገለጹበት የአዋጅ መግቢያ፣ የቁጥብነት እንጂ የዘመቻ ዝንባሌን አያመለክትም። ይህም ብቻ አይደለም።
በአንቀጽ 3 ስር የተዘረዘሩ “የአገራዊ ምክክሩ መርሆዎች”፤ አነሱም በዙም፣ ነገርየው መንገድ እንዳይስት፣ ከልኩ እንዳያልፍ፣ ርቆ እንዳይነጉድ፣ ፍሬን እንዳበጥስ ይጠቅማሉ። መርሆች፣ መንገድን ለመምራትና ልክን ለማስያዝ፣ በሌላ ጎንም ድንበር ለማበጀት ያገለግላሉ። አዋጁ፤ በርካታ መርሆችን መዘርዘሩም ተገቢ ነው፡፡
 ምክክሮች፣ ምክንያታዊነትን የተከተሉ፣ ይሆናሉ ይላል አዋጁ፡፡
የአገር ሁኔታንና ርዕሰ ጉዳይን ያገናዘቡ መሆን እንደሚገባቸውም ተገልጿል፡፡
የሃሳቦች ተግባራዊነትንና እቅድን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸውም አንቀጹ ይዘረዝራል።
ምክክሮች፣ ለዲሞክራሲና ለሕግ የበላይት መርሆዎች ተገዢ መሆን እንደሚገባቸውም እዚያው ተጠቅሷል።
በእርግጥም፣ ትክክለኛ መንገድ ያልተበጀለት፣ የድንበሩ ልክ ያልተሰመረለት አዋጅ፣ ወይም የመንግስት ተቋምና ተግባር፣ ጨርሶ መኖር የለበትም።
“የሕግ የበላይነት” መርህ ደግሞ ዋና ነው፡፡  ይሄ መርህ ከሌለ፣ “ህግ” ተብሎ የጸደቀው አዋጅ ራሱ ከንቱ ይሆናል።
በአቋራጭና በጥድፊያ፣ ህጋዊ መንገድን ጥሶ፣ ህግ አይገዛኝም ብሎ፤ በዘፈቀደ አዲስ ህገ-መንግስት አውጥቶ እንካችሁ ቢል አስቡት።… እና ደግሞ ህገ-መንግስቱ እንዲከበር፣ ማለትም የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ሲጠብቅ ይታያችሁ።
ህግ አይገዛኝም ብሎ ሌላ ህግ ቢያመጣ የትም አያደርስም። ህግ የማይከበር ከሆነ፣ ህግ ቢሻሻል ቢለወጥ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ለዚህም ነው፤ የሕግ የበላይነት ከዋነኛ የፖለቲካ መርሆች መካከል አንዱ ሚሆነው።
የምክክር አዋጁ ይህን መርህ በግልጽ ማስፈሩ መልካም ነው። የመሻሻል እድልን የሚከፍት መርህ ነው፡፡ ግን ደግሞ የትርምስና የግርግር አደጋን የሚቀንስም ነው- መርሁ።
ይህም ብቻ አይደለም።
በአንቀጽ 6 የተዘረዘሩ አላማዎችም  ቢሆኑ፤ ከጥንቃቄ የራቁ ናቸው ማለት አይደለም።
“የሀሳብ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶች”፣ “የአለመግባባት መንስኤዎች” ላይ ያተኮሩ አንቀጾች፤ መቋጫ ለሌለው ንትርክ በር የሚከፍቱ፤ ወይም ደግሞ ለስር-ነቃይ አብዮት የሚጋለጡ መምሰላቸው አይካሄድም።
ነገር ግን፣ የምክክሮቹ ትኩረት፣ የሃሳብ ልዩነትና መንስኤ ላይ ይሆናል አይልም- አዋጁ።
ይልቅስ፣ የሃሳብ ልዩነቶችንና መንስኤዎችን በማገናዘብ፣ ኮሚሽኑ የምክክር ርዕሰ ጉዳዩን እንደሚመርጥ ነው አዋጁ የሚገልጸው።
ኮሚሽኑ፣ በጥበብ፤ ርዕሰ ጉዳይን መምረጥ፣ የሃሳብ አለመግባባትና ስረ መሰረት   ላይ ሰዎችን ከማነታረክ ይልቅ፣ የሚያግባቡ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ የሚያተኩሩ ምክክሮችን ማዘጋጀት ይችላል።

Read 11508 times