Saturday, 05 February 2022 12:16

“እኔ ልፈትናቸው ብዬ ነው እንጂ...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 "ምን መሰላችሁ...እዚህ ሀገር ቦተሊከኛውም፣ ባለ ኳሱም፣ ባለ መፍትሄ ሀሳቡም ባለ ምናምኑ ውድድሩም...አለ አይደል...ሽንፈትን መቀበል፣ ከእኛ የተሻለ መኖሩን ማመን በራሳችን ላይ ‘ፒስቶሏን’ ማዞር ነው የሚመስለን፡፡ ምናልባት ከእኛ እጅግ በጣም የተሻሉ ሀሳቦች ያሉት፣ ከእኛ በጣም የተሻለ የሥራ ብቃት ያለው፣ ከእኛ በጣም የተሻለ የመግባባትና አብሮ የመኖር ባህሪይ ያለው መኖሩን መቀበል ራሳችንን ካስቀመጥንበት የህልም ዙፋን ላይ ማውረድ ነው የሚመስለን፡፡--"
            
          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... “ላቭ ኢዝ ብላይንድ” ምናምን መባባል በጀመሩ በአምስተኛ ወሩ እሷዬዋ ፀሀይ ብልጭ እንኳን ባላለችበት አውላላ ሜዳ ላይ አስጥታው ትሄዳለች፡፡ ቢጫ ካርድ የለ፣ ‘ፍሬንዶች’ን ምከሩት ምናምን የለ...በቃ ከሊስቱ ይሰረዛል፡፡ እናላችሁ...... አንዳንዴ እንደ ምቁነት ነገር ይሞካክረን የለ... ጓደኞቹ “እሰይ እንኳን ፈነገለችው፡፡ እኛም ትንሽ ተንፈስ እንበል እንጂ!” ምናምን ይላሉ፡፡ አሀ...በተገናኙ ቁጥር ብቻ ሳይሆን ይህንን መከረኛ የእጅ ስልክ እየደወለ መከራቸውን ያበላቸው ነበራ!
“እየውላችሁ...ብታዩዋት እኮ እኔ ራሴ እንደ እኛ ሰው መሆኗንም እጠራጠራለሁ። ምን አለፋችሁ... መልአክ ነው የምትመስለኝ!” የምር ግን...በተረትነቱ ብቻ ሳይሆን የእውነት ‘ላቭ’ ልቡን ‘ብላይንድ’ ያደረገው እንትና እኮ አሪፍ ‘ሮማንስ ኖቭል’ ምናምን ጸሀፊ ባይወጣው ነው! አሀ...ልክ ነዋ! ለስንት ዓመት የቅርብ ወዳጃችሁ ሆኖ የኖረ ሰው በድንገት በአንድ ጊዜ ተለውጦ  አይደለም እሱ ምስኪን፣ ሮሚዮ እንኳን ብሏቸው የማያውቃቸውን የፍቅር መግለጫ ቃላት  ሲያዥጎደጉድላችሁ ሌላ ምን ማሰብ ይቻላል!
“ገና ጩጬ ሳለሁ እቤታችን ይመጡ የነበሩ አባ እከሌ ለማዘር ሲነግሯት፣ ይህ ልጅ ሲያድግ የምትገጥመው ሴት ፈጣሪ ለእሱ በተለይ ቀብቶ ያስቀመጣት ናት ሲሉ እሰማቸው ነበር፡፡” ጎሽ! እሰየው ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡
እናላችሁ... ‘ደምፕ አድርጋው’ ስትሄድ (ቂ...ቂ...ቂ...) የምር ግን አንዳንዴ እኮ በፈረንጅኛ ሲሉት በቃ ወሽመጥ ቁርጥ የሚያደርግ ነው የሚመስለው፡፡ ልክ ነዋ...አውላላ ሜዳ ላይ የተሰጣ እኮ ቢያንስ፣ ቢያንስ ተነስቶ አቧራውን አራግፎ እያፏጨ ጉዞ መቀጠል ይችላል፡፡ ‘ደምፕ’ ተደረገ ግን...በቃ መጨረሻው ያው ‘ደምፕ’ የሚደረጉ ነገሮች የሚከማቹበት ነው፡፡ ስሙ ያልተጠራው...አለ አይደል...እንደ አቅሚቲ ‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ ለመሆን ነው፡፡ እናማ “ደምፕ አደረገችህ!” “ደምፕ አደረገሽ!” ስትባሉ ፈረንጅ አፍ ስለሆነ ለስለስ ያለ እንዳይመስላችሁ ለማለት ነው፡፡
ታዲያላችሁ አጅሬው ያው ያለማስጠንቀቂያ ጥላው ስትሄድ እንደዛ መንግሥት ሰማያት በራፍ ሲያደርሳት የነበረችውን እንትንዬን በአንድ ጊዜ የመልአክነቱን ክንፍ ነቅሎ በቦታው ጭራና ቀንድ ያበቅላላታል፡፡
“እንደዚህ ውጭ እንደምታዩዋት መሰለቻችሁ!”
“ምን ማለት ነው?”
“ጠባይ የሚባል ነገር አጠገቧ ያልደረሰባት፣ የሆነች ሰይጣን ነገር እኮ ነች፡፡ እናንተ እንዲህ ውጭ እንደምታዩዋት እየመሰለቻችሁ ነው፡፡” ልብ አድርጉልኝማ...የውዳሴ ቃላቱን ሲከምርባቸው ለነበሩ ለእነዛው ጓደኞቹ ነው እኮ ይህንን የሚለው።
“እንደዛ ከሆነ ለምን መጀመሪያውንስ ገርልፍሬንድ አደረግሀት?”
“ግፊት በዛብኛ!”
“ግፊት በዛብኝ ምን ማለት ነው?”
“አትሰሙኝም እንዴ! እኔ እኮ መጀመሪያም ገርልፍሬንድ ትሆነኛለች ብዬ አይደለም፤ ቤተሰብና ዘመድ ግፊት ሲያበዛብኝ ብጠጋት ምን ይጎድልብኛል ብዬ ነው፡፡”
“እና አሁን ጥላህ በመሄዷ ምንም አልተሰማህም?”
“ለምን ለእኔ ስትል በእግሯ ሞንጎሊያ አትገባም!”
ተው፣ ተው ተው! ይቺን እንኳን እሷ ጥላህ ከሄደች በኋላ በነበሩት ሦስትና አራት ሳምንታት ስታስባት የነበረች ነች!
ምን መሰላችሁ... እዚህ ሀገር ቦተሊከኛውም፣ ባለ ኳሱም፣ ባለ መፍትሄ ሀሳቡም ባለ ምናምኑ ውድድሩም...አለ አይደል...ሽንፈትን መቀበል፣ ከእኛ የተሻለ መኖሩን ማመን በራሳችን ላይ ‘ፒስቶሏን’ ማዞር ነው የሚመስለን፡፡ ምናልባት ከእኛ እጅግ በጣም የተሻሉ ሀሳቦች ያሉት፣ ከእኛ በጣም የተሻለ የሥራ ብቃት ያለው፣ ከእኛ በጣም የተሻለ የመግባባትና አብሮ የመኖር ባህሪይ ያለው መኖሩን መቀበል ራሳችንን ካስቀመጥንበት የህልም ዙፋን ላይ መውረድ ነው የሚመስለን፡፡ እናላችሁ ንትርኩም፣ ጭቅጭቁም፣ ምናምኑም የበዛው ስንትና ስንቶቹ ከእኛ ቀድመው እያየናቸው እያለም... “በቃ አንደኛ ነኝ ብያለሁ፣ አንደኛ ነኝ!” በሚል አይነት በሁሉም ነገር ወርቅ ሜዳሊያው ካልተጠለቀልን በቀር የምንለው ነገር፣ መአት ነገር እያበላሸብን ነው፡፡
ለምሳሌ እሷዬዋ ለሆነ ከፍት የሥራ ቦታ ትወዳደራለች፡፡ (ስሙኝማ... ይሄ ቦታው ላይ አስቀድሞ ሰው ከተቀመጠበት በኋላ እንደ አውሎ ነፋስ መከላከያ አይነት “ክፍት የሥራ ቦታ” እያሉ ማስታወቂያ ማውጣት አሁንም አለ እንዴ! አለ አይደል... በሽውታም፣ በሹክሹክታም የምንሰማቸው ደስ የማይሉ አሉባልታ ሊሆኑም ላይሆኑም የሚችሉ ነገሮች ስላሉ ነው፡፡)
እናላችሁ...እሷዬዋ ለቃለመጠይቅ እንኳን ሳትደርስ ዘጭ ትላለች፡፡ እንዲህ ለውድድር ተቀምጣ ዘጭ ስትል አምስተኛዋም፣ ሰባተኛዋም ሙከራዋ ሊሆን ይችላል፡፡
“አንቺ...የሥራ ውድድር ያልሽው እንዴት ሆነልሽ?”
“እባክሽ አልተሳካም!”
“ምን ላይ አበላሽቼ እንደሆን እንጃ ገና የጽሁፉ ፈተና ላይ ነው የጣሉኝ...” ብሎ ነገር  የለም፡፡ ሞታለቻ!
“እኔ እኮ እንደማይሆን ገና ስመዘገብ ነው ያወቅሁት፡፡ እንደው ለምን አልሞክርም ብዬ እንጂ ውጤቱ ምን እንደሚሆን ቀድሜ አውቀው ነበር፡፡”
“ምነው፣ ምን ተፈጠረ! ወደቅሽ እንዴ?”
“አውቄው ነበር እኮ ነው የምልሽ፣ እነሱ አስቀድመው ቦታውን ለውሽሞቻቸው አመቻችተው እኛን የፈተኑን አወዳደሩ ለመባል ነው፡፡”
እናላችሁ...ችግሩ ምን መሰላችሁ... አስቀድሞ “የወርቅ ሜዳሊያው ለእኔ አንገት ተብሎ የተሠራ ነው፣” ብለን ስለደመደምን ሌላ አንገት ላይ ሲጠልቅ ስናየው እንዴት ብለን እንቀበለው! በሆነ ጉዳይ “ከእኔ አያልፍም፣” ብለን በእርግጠኝነት የጠበቅነውን፣ ያለቀ የደቀቀ ጉዳይ ያልነውን “የለም፣ ከአንተ የተሻሉ ሌሎች በርካቶች አሉ...” ስንባል በየትኛው አንጀታችን እንሸከመው! ምክንያት መፍጠር አለብን፡፡
“እኔ ልፈትናቸው ብዬ ነው እንጂ ቦታውን ይህን ያህል ፈልጌው አይደለም። ከእኔ የተሻለ እንደሌለ ባውቅም ለሌላ መስጠታቸው የጠበቅሁት ነው፡፡”
እናላችሁ... በሁሉም ነገሮች ከእኛ የተሻሉ መኖራቸውን መቀበልና ስንሸነፍ ደግሞ “አዎ፣ ከእኔ በተሻሉት ተበልጫለሁ...” ማለት እያቃተን ቀላሉ ነገር ሁሉ እየከበደን ነው ለማለት ያህል ነው፡፡
ስሙኝማ...የሽንፈት ወሬ ካነሳን አይቀር የሆነች ታሪክ ትዝ አለችኝማ! በፊት፣ በፊት ጊዜ አንድ ቦክሰኛ ነበር... የሆነ ለምንም ለማንም የማይመለስ እናቶች “ከይሲ...” የሚሉት አይነት፡፡ ፍርሀት የሚባል ነገር ስሙን አያውቀውም የሚባልለት ነበር። እናላችሁ.... አንድ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ የቦክስ ውድድር እዚህ ከዑጋንዳ ቦክሰኛ ጋር ይደርሰዋል፡፡ ከጨዋታው በፊት ፉከራው ተዉትማ፣ ያውም ተወዳዳሪው ምን አይነት ይሁን ምን ሳያውቅ እኮ ነው!
“አንደኛውን ዙር ሳታጋምስ ምንጣፍ ነው የማደርጋት!”
“በአምቡላንስ ነው ሀገሩ የሚመለሳት!”
ታዲያላችሁ...ቀኑ ደረሰና ሁለቱም መድረኩ ላይ ይወጣሉ፡፡ እናማ...ይኸው የእኛው ሰው የኡጋንዳውን ቦክሰኛ ከእነጋዋኑ ሲያየው “ይቺን ወፍማ በአንድ አፐርከት ከአዲስ አበባ ኤንቴቤ ነው የማደርሳት፣” አይነት ዕብሪት ይሰፍርበታል፡፡ ጋሼ ኡጋንዳ ሆዬ፤ ጋዋኑን ወለቅ ሲያደርግ ምን ቢሆን ጥሩ ነው...የጡንቻ መአት ተገምዶ! ተጠቅልሎ! ተጠቅልሎ! “እንደዚህ ውጭ እንደምታዩዋት መሰለቻችሁ!”
እናላችሁ ግጥሚያው እንደተጀመረ ኡጋንዳ ሆዬ ተንድርድሮ ይቀርበውና ቡጢውን መሰንዘር ይቀጥላል፡፡ ግን ሰዋችንን ፊቱን ሙሉ ለሙሉ ሊያገኘው ቀርቶ አይጨርፈውም፡፡ ታዲያላችሁ... ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቀኙን ሲሰነዝር የእኛን ሰው አገጭ በጣም በስሱ ጨረፍ አድርጎት ያልፋል፡፡ የእኛው ‘ጀግና’ አይፈነገልላችሁም! ወዲያው ይነሳል ተብሎ ሲጠበቅ ለሽ ይልላችሁና ዳኛው መቁጠር ይጀምራል፡፡ አጅሬው ሊንቀሳቀስ ነው! ዳኛው ቆጥረው ይጨርሱና ጋሼ ኡጋንዳ በቡጢ ሳይሆን በአንድ ጭረት አሸናፊ ሆኖላችሁ ቁጭ! ቦክሰኛችን ምን ቢል ጥሩ ነው... “መቶኝ ሳይሆን ጓንቱ ላይ የቀባውን የሆነ ነገር ሲያስነካኝ ነው የወደቅሁት!;
አንድ ቀን ግን ጠጅ አስለፍልፋው ጉድ አደረገችው፡፡ ለካስ ጡንቻውን ሲያየው “በዚህ ካገኘኝ አያስተርፈኝም፡፡ ምን እዳ አለብኝ!” ብሎ ነው ‘በራስ ተነሳሽነት’ ለሽ ብሎ የተቆጠረበት፡፡  ዳኛው መቁጠራቸውን ቢቀጥሉ ኖሮ ማንኮራፋት ባይጀምር ነው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...
እናማ... መበለጥን ማመን ክፋት የለውም። “እኔ ልፈትናቸው ብዬ ነው እንጂ...” ማለቱ ብዙም ወንዝ አያሻግርም ለማለት ያህል ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1705 times