Monday, 07 February 2022 00:00

ሥነ - ህይወት እና ሣይንስ (ከደስታ ሌላ ምን?)

Written by  አብዲ መሃመድ
Rate this item
(0 votes)

   (ክፍል ሁለት)
የሀገራችንና በጠቅላላ የአለማችን የተፈጥሮ ሀብት ችግር ላይ እንዳለ እናውቃለን። በየሚዲያውም ይነገራል። ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ምን ያህል እንስሳት እናውቃለን ብለን እንጠይቅ። ስለ ተፈጥሮና  ይህችን  ምድር  ከኛው ጋር ተጋርተው ስለሚኖሩት ህያው-ፍጥረታት ብዙ ግንዛቤ የለንም ፡፡ ለዚህም ነው የ“ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ” ሲባል ብዙ ጊዜ ግር የሚለን። የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት አንጻር ሲመዘን ለአለም ምን ያህል ኢምንት ፍጥረት መሆኑ በይበልጥ የምትፈክርና-የምታጎላ ግሩም ገለፃ በቅርቡ ለንባብ በበቃው የዶ/ር ኤልያስ ገብሩ “ጥሞና” መጽሐፉ ውስጥ አስፍሮት አንብቤያለሁ። በርሱ ልንደርደር!… “ከተፈጥሮና ፍጥረት እውነታ ጋር ስንዛመድ የኛ አካል ምድር ላይ ልክ “ዳይኖሰር” ላይ እንደቆመ ቫይረስ ይመሰላል፡፡ እሱንም ሳንረሳ በዚሁ ላይ  የህዋ አካላትን ግዝፈት ደግሞ እናስብ፡፡ ለምድር ቅርቧ ኮከብ ፀሃይ፣ ከመሬት 1.3 ሚሊዮን እጥፍ ትበልጣለች፡፡ እናም ከፀሃይ በሚሊዮንና ቢሊዮን እጥፍ የሚበልጡ ክዋክብት እንዳሉ እናክልበት። እናም ከዚህ አንጻር የኛ አካልና ቁሳቁስ ኢምንት ሳይሆን ምንም ነው፡፡ ለብዙሃኑ ግን ይሄ እውነታ አይገለጥም፡፡ ምክንያቱም ለቅማል ከምንዱባን አንዱ የራስ-ቅል አለሟ ነው፣ ቀጫጭን ጸጉሮቹም ዋርካዎች ሊመስሏት ይችላሉ፡፡ ማን ያውቃል? አንድ ጢኖ ባክቴሪያ ደግሞ በተራው እዚሁ ቅማል ላይ አህጉሬ ነው ብሎ ከትሞ ይሆናል፡፡ ሀቁ ግን ለህያው ማንኛችንም እንዲያው ከቁጥር የማንገባ እፉኝት ነንና አንኩራ፤ አንስገብገብ፣ አንመጻደቅ፣ አንታበይ።  ድርጊታችን ፍጥረትን በሙሉ ያገናዘበ ይሁን፡፡(ገጽ 188)
የስነ-ህይወትና ሳይንሳዊ ስልትን እንዲሁም አስተሳሰብን ያነገበ መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ የማዘጋጀት ልምድ የሃይማኖት ተጽእኖ ስለሚጫነው እንደልብ ስር መስደድ አልቻለም፡፡ በባህልም የተገረገረ በመሆኑ ለብዙ ተደራሲያን በስፋት ማዳረስ አልተቻለም። በወጉ ስር እንዲሰድ ለማስቻል እንደ ማንይንገረው ሸንቁጥ ያሉ ስራዎችንና ሙከራዎችን ማበረታታትም እውቅና መስጠትም ይኖርብናል፡፡ ይህ ሲሆን ረቂቅ የሆኑ የህያው ተግባራትን፣ ብዙ ሰዎች ሊረዱት በሚችሉት መጠን፣ በሀገር በቀል ቋንቋ በመጽሐፍ መልክ ማበርከትም- ማበራከትም ይቻላል ብዬ በጽኑ አምናለሁ።  ሽብሩ ተድላም ይህንኑ ያጠናክራሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ በደራሲው ሁለቱም ሥራዎች መግቢያ ላይ ባሰፈሩት ቀዳሚ-ቃላቸው …. ማንይንገረው ሸንቁጥ ወጣት እና መምህር እንደሆነ ጠቅሰው፣ በተለይ በአስተማሪነት ያገኘው አንድን ጉዳይ ግልጥ አድርጎ የማቅረብ ልምድ የረዳው ይመስላል፤ ስለዚህ ሳይንሳዊ እውቀትን በግልጽና በቀላሉ ለመረዳት በሚያስችል መንገድ በመጽሐፉ ውስጥ ለማስፈር ተሳክቶለታል… ሲሉ ምስክርነታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ የፍጥረት ተግባራትን ብዙ ተደራስያን ሊረዱት በሚችሉት አቀራረብና ቋንቋ ማዳረስም  እንደሚቻል ቀደም ሲል  “ባለ አከርካሪዎች” በሚል መጽሐፉ በሚገባ አሳይቶናል። ይህም ሳይንሳዊ እውቀትን በአማርኛ ቋንቋ ለመተንተን መቻሉን ያረጋግጣል።  እኔም ባሳለፍነው ሳምንት በክፍል አንድ ጽሁፌ ይህንን ሥራ ለመዳሰስ ሞክሬ ነበር፡፡ ሆኖም ፕሮፌሰሩ  ስለ ደራሲው የሰጡትን ምስክርነት በይበልጥ እውነትነቱን የምናረጋግጠው ለዛሬ ቀጠሮ የያዝኩለትን “ከደስታ ባለፈ” ገልጠን ስናነብ  ብቻ ነው። ወደዚያው እናምራ፡፡
በስነ - ህይወት ሣይንስ  ጥናት ውስጥ የሰው ምድብ ከእንስሳት ጎራ ነው፡፡ ሰው ያልሆኑ ሌሎች ብዙ ዝርያዎች ከእንስሳት ወገን አሉ፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኘው “ፍሬ ሃሳብ” እንስሳትን ከኛው ተጨባጭና ነባራዊ እውነታ ጋር አቆራኝቶ የሚተርክ ነው፡፡ የመጽሐፉ ጭብጥ የሚያጠነጥነው በሰዎችና ሌሎች እንስሳት ወሲባዊ ጠባይና ግንኙነት ዙሪያ ላይ ነው፡፡ ደራሲው ርዕሱን “ከደስታ ባለፈ” ሲል የሰየመው፣ ወሲብ ከሚያስገኘው የደስታ ስሜት ባለፈ፣ በሳይንሳዊ ጥናት ተደግፎ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦችን የሚተነትን በመሆኑ ነው። ወሲባዊ ፍላጎትን የማስተናገድ ግፊት፣ ዘርን የማስቀጠል  ሁነኛ ግብረ- አካላዊ እንቅስቃሴ በመሆኑ፣ ሩካቤን ከደስታ ባለፈና በላቀ ማሰብ እንድንመረምረው ግድ ይለናል። በርግጥ ይህንን ስል ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም ብዙ ሰዎች ከባህል፣ ከሃይማኖት፣ ከግብረ-ገብ ጋር አያይዘው በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ያላቸው ድፍረት ውስን እንደሆነ ይታወቃል። መሠረታዊውን እውቀት ለመረዳት መጣር-መጣጣርን ሣይቀር የነውርነት ካባ አልብሰነዋል። በነውርነት መፈረጁ በፋንታው ብዙ ማህበራዊ ምስቅልቅል ችግሮችን ይዞብን ሲመጣ ይታያል፡፡ ነውር ነው ብለን ያወገዝነውን በአደባባይ ለመነጋገር ባንደፍርም፣ የተፈጥሮን ውስጣዊ ግፊት ማቆም ግን አይቻለንም፡፡ ስለዚህ ወሲብን በአግባቡ መረዳት እንጂ እንደሌለ ክደን መጀመር የለብንም፡፡ መሠረታዊ በፍጥረት ላይ የተደረገ ሣይንሣዊ  ዕውቀትና ግንዛቤ ካለ ግን ለመነጋገርና መፍትሄ ለማበጀት ጥርጊያ መንገድ ያበጃል፡፡ ወሲብን በተሳሳተ መንገድ እንድንረዳ ለሚያደርጉን ዕውቀት-አጠር አስተሳሰብ ሰዎች ሰለባ ሆነን ከመደናገርም ያድነናል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት ቁም ነገሮች፣ በግኝቶችና አስተሳሰቦች ላይ የተመረኮዙ ናቸው፡፡ ከእውቀት ይልቅ ወሲብ ላይ ተንተርሰው ለስሜት ያደሉ ጉዳዮችን የማንይንገረው መጽሐፍ አያካትትም ፤ ይህም የመጽሐፉ ሌላኛው ጠንካራ ጎኑ ነውና ሊደነቅ ይገባዋል፡፡
የወሲብ ጠባይ ተፈጥሮአዊና የሠው ልጆችም ሆኑ  ሌሎች እንስሳት፣ መሰላቸውን እየተኩ ትውልዳቸው እንዲቀጥል የሚያስችላቸው ወሳኝ የሕይወት እንቅስቃሴ አንዱ አካል ነው፡፡ እንስሳቱ  ለስነ-ቃሎቻችን፣ ለተረቶቻችን  ገፀ-ባህሪያት  ከመሆን ባለፈ የሚጋሩን አያሌ ጉዳዮች እንዳላቸው ሲገባን እንደነቃለን ፡፡ መሠረታዊ ልዩነቶቻችን ያን ያህል የተራራቁ አይደሉም፡፡ ለአብነት.. ወሲባዊ ጠባይ በሰዎችም ሆነ በእንስሳ በጎላ ሁኔታ መታየት የሚጀምሩት የአካል እድገት ደረጃ በሚደረስበት ጊዜ መሆኑ… ሆርሞን በማመንጨት “ለሰው ለአቅመ አዳም የደረሱ” እንደምንለው፣ ለእንስሳቱ ደግሞ ለርቢ ደረሱ እንላለን፡፡ ሌላው ከተቃራኒ ፆታ ጋር ለመሳሳብ የሚደረግ ሂደትን ሲያመለክት፤ በሰዎች ዘንድ ማሽኮርመም፣ ማማለል ተብሎ የሚጠቀሰው… ለሌሎች እንስሳት ደግሞ ድርያ ሲባል ትርጓሜውም ወደ ተራክቦ የሚወስዱበት ማማለያ ስልታቸው ነው፡፡ ከሌሎች እንስሳት በላቀ ከሰው ጋር እጅጉን ተመሳሳይነት ያላቸው ኤፖች ወሲባዊ ጠባይ ይዘረዝራል፡፡ በተለይ በዘረ-መል ደረጃ የሚደረገው ምርምር፣ ቀደም ብሎ ታስቦ በማይታወቅ መልኩ፣ ቺምፓንዚዎች ከሰው ጋር ያላቸው ልዩነት የ1 ፐርሰንት ብቻ መሆኑን ጭምር አሳውቋል፡፡
በዚህ ረገድ… የእንስሳ ወሲባዊ ጠባዮች ላይ  ትኩረት ተሰጥቶ መጠናት የጀመረው፣ “የእንስሳት ጠባይ ጥናት” እንደ-አንድ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ብቅ ካለበት ከ50 አመታት በፊት ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ፣ ወሲባዊ ጠባዮችን በተመለከተ ብዙ ጥናቶች በመካሄዳቸው፣ አሁን ባለንበት ሁኔታ የተሻለ ጥራት ያለው እውቀት ተሰናድቶ ይገኛል፡፡
ማንይንገረው ከጥልቅ ጥናቱ ከተሰናዱት ውስጥ ያነጠራቸውን አንድ ሁለቱን እንምዘዝ … “በስነ-እንሰሳት አጥኚዎች ዘንድ ወሲባዊ ጥምረት በሦስት መንገዶች ሊገለጽ ይችላል። አንደኛው ጥምረት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ከአንድ ተጣማሪ ጋር ሊኖር የሚችለውን ተራክቦ ያመለክታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ “የወለዱዋቸውን ልጆች” በጋራ ለማሳደግ ሲሉ በየቡድናቸው ውስጥ የሚኖራቸው ጥምረት ሆኖ ጎን ለጎን ግን በቡድናቸው ውስጥ ወዳሉ ሌሎች ተቃራኒ ጾታዎች በመሄድ የሚወሰልቱትን ያካትታል። አብዛኛዎቹ አጥቢዎች ከአንድ ለአንድ ዘላቂ ጥምረት ያፈነገጡ፤ ወንዶች ከብዙ ሴቶች፣ሴቶች ከብዙ ወንዶች ጋር ሩካቤ በመፈፀም የሚታወቁ ሆነው እናገኛቸዋለን። የዘረ-መል ምርመራ የአእዋፍ መንደርን  ድብቅ ገመናና የዘመናት ታላቅ ሚስጥርን አደባባይ አውጥቶታል፡፡ የቆረቡ ጥንዶች ዋነኛ ምሳሌ ናቸው የሚባሉት እንደ “ስዋን” ያሉት ወፎች ሳይቀር፣ ፍሬያቸው የጋራ እንዳልሆነ መስክሯል፡፡ ባተሌው ወንድ የጎረቤት ልጅ እንደሚያሳድግ አያውቅም፡፡ በሌላኛው ጥናት ደግሞ መካን ከሆኑ አእዋፍ ወንዶች ጋር የተጣመሩ ሴቶች ጫጩት ፈልፍለው ተገኝተዋል፡፡ የመሃን ባተሌ ዘሬን ተካሁ ብሎ ጭራሮ ይለቅማል፣ ጎጆ ይገነባል፣ ምግብ ያቀርባል፡፡
10 ሺህ ከሚሆኑት የአዕዋፋት ዝርያዎች ውስጥ፣ አብዛኞቹ ወፎች አስመሳዮች እንጂ ከአንድ የቆረቡ እንዳልሆኑ  ቢታወቅም፣ ከአጥቢዎች በተሻለ ቁጥር እንደ እርግብ፣ አልባትሮስ፣ ጥቁር ጥንብ አንሳን የመሣሳሉ የአዕዋፍ ዝርያዎች በታማኝነት የአንድ ለአንድ ዘለቄታዊ ጥምረት ማሳያ ምሳሌዎች ሆነው ይወሰዳሉ፡፡
በተለየ መልኩ ደግሞ፣ እንቁላሎቻቸውን ሌሎች ያዘጋጁት ጎጆ ውስጥ በመጣል፣ አንዳችም ሣይለፉ በሌሎች ላብ ዘራቸውን የሚያስቀጥሉ አታላዮችም ይገኙበታል፡፡
እንደ ጎሪላና ነጭ ዝንጀሮ ባሉት ዝርያዎች፣ አንድ ወንድ በበላይነት ብዙ ዕቁባቶችን በዙሪያው በኮለኮለበት፣ ብቻውን ከሁሉም ጋር ሩካቤ በመፈፀም፣ ዘሩን ያባዛል። ሴቶቹ ወደ ሌላ ውልፊት እንዳይሉ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። ወንድ ልጅ ለአቅመ ርባታ ሲደርስ ይባረራል። በተመሳሳይ ቡድን ውስጥ በምናያቸው ጭላዳ ዝንጀሮዎች ውስጥ ያሉ ዕቁባቶች ደግሞ ድንበር የማስከበር ተሣትፎአቸው የላቀ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከሌሎች በተለየም ወንዱ ጫና የሚያሳድርባቸው ሆነው አይገኙም፡፡ ተለሳልሶ ለቀረበ የጎረቤት ወንድ፣ በጊዜያዊነትም ቢሆን ልባቸውን እንደሚሰጡ በሳይንሳዊ ጥናት ታውቋል፡፡
በባዮ-ሎጂ ረገድ በሰው ልጅ መካከል ያለው ፆታዊ መሣሣብ በሌላ የእንስሳት ዝርያዎች ዘንድ ከሚገኘው ጋር ተመሣሣይና አንድ አይነት ይዘት ያለው ነው፡፡ እያንዳንዱ የዝርያው አባል በደመ-ነፍስ ወደ ተቃራኒ ፆታ የማዘንበል ስሜት አለው፡፡ ተፈጥሮ በውስጣቸው ያኖረችው እጅግ ብርቱ የመዋለድና የመባዛት ፍላጎት… የመዋለድ ብቃት ያላቸውን የተቃራኒ ፆታ አባላት እርስ-በርስ እንዲሣሣቡና እንዲፈላለጉ ያስገድዳቸዋል፡፡
ሌላው በጸሀፊው ከተደነቅሁባቸው ጥረቶች፣ ሳይንሳዊ ዕውቀትን ከባህላችን ጋር ለማጣጣም መሞከሩ ነው፡፡ በማህበረሰባችን ከእውነት የራቁ እምነቶችንም ለመሸርሸርና ለማስወገድ እንደ አስረጂ ተጠቅሞበታል። መጽሐፉ ውስጥ ከተጠቀሱት እንስሳት ጋር ያለውን እምነት እየጠቀሰ፣ የአንዳንድ እምነቶችን ፋይዳ ቢስነት አበክሮ አሳይቷል።
ሳጠቃልል፣ የስነ-ህይወት ሣይንስ እውቀት የሚናቅ አይደለም፡፡ ለደሃ አገር ሣይንሣዊ ባህል ለማዳበር እንደሚያገለግል አያጠራጥርም፡፡ እንደኛ ያሉ ብዙ ታዳጊ ሀገሮች፣ በአጭር ጊዜ ሣይንሣዊ አስተሳሰብን ለማዳበር ብሎም ቴክኖሎጂን ለመገንዘብ የበቁት በአገር በቀል ቋንቋ ሣይንስ-ነክ ርዕዮቶችን ተደራሽ አድርገው በመጠቀም ነው፡፡ የሩቅ ምስራቅ አገሮች ለዚህ ሂደት ተጨባጭ ማስረጃዎችም- ማረጋገጫዎችም ናቸው፡፡ ስለዚህ በጉዳዩ ላይ የምሁራን ፍርሀትን ያገለለ ተሳትፎ የሚጠበቅ ነው። በዋነኝነት የሳይንስ እውቀት ራሱን ችሎ ግቡን እንዲመታ አጓጉል ይሉኝታ መቀረፍ  ይኖርበታል፡፡ ሽብሩ ተድላም የምሁራኑ ንፉግነት ተገቢ አለመሆኑን እንዲህ በማለት ይተቻሉ ፡፡ "…በባህላችን ሰው ምን ይለኝ የሚል ስጋት ስለአለ ብዙ ምሁራን በጽሁፍ የመሳተፍ ፍላጎት የላቸውም፤ በተለይ ከተለመደው ባህል አጉራ ዘለል ሲመስላቸው እንዲሁም ሃይማኖታዊ ትችት ሙግት የሚጋብዝ ሲመስላቸው፡፡ ይህ ተገቢ አይመስለኝም፡፡
ጠቃሚ የሆኑ የእውቀት ማዳበርያ መረጃዎችን ያሰባሰበ፣ “ሰው ምን ይለኝ ይሆን? የሚለውን ያላነገበ” ጽሁፍ ማዘጋጀትና ለአንባብያን ማቅረብ ጥቅም አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ በአስተያየት፣ በአስተሳሰብ፣ በክርክር፣ በውይይት የዳበረ አስተሳሰብ ነው እየነጠረ፣ እየጠራ ሊሄድ የሚችል፣ ብሎም ተዓማኒነቱ የሚጎላና ተቀባይነት የሚኖረው ብዬ እገምታለሁ፡፡"  (ቀዳሚ - ቃል)  
በርግጥ ዛሬ-ዛሬ ሣይንሣዊ ይዘት ያሏቸው ጽሁፎችም - መጽሐፎችም ተሰራጭተዋል።  በቂውን ያህል ባይሆንም  እየተሰራጩም ናቸው ለማለት ያስደፍራል። የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ ሣይንሳዊ አስተሳሰብ ለማዳበር አንቱ የሚባል ጥረት እያደረገ ይገኛል። ለዚህም ግብአት የሚሆኑ መጽሐፍቶች (ባደረኩት ሀሰሳ) እዚህም እዚያም ለመታዘብ ችዬአለሁ። ቀደም ሲል የፕሮፌሰር ሽብሩ  “ዝግመት ለውጥ” እና “ህያው ፈለግ” የተሰኙትን ሲሆን በማስከተል ደግሞ እነሆ ሣይንስን ህዝባዊ ለማድረግ ተከታትለው የማንይንገረው ሽንቁጥን አበርክቶልናል፡፡ ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኛም ለዛሬ (ጥረቱ ይቀጥል እያልን)  ደራሲውንም - አካዳሚ ፕሬሱንም ልናመሰግን እንወዳለን፡፡


Read 2769 times