Sunday, 06 February 2022 00:00

በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ትኩረት የሚሹ ስምንቱ የአፍሪካ ወቅታዊ ቀውሶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   ዛሬና ነገ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ጨምሮ በአህጉሪቱ ለተከሰቱ ስምንት አሳሳቢ ቀውሶች፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ሊያስቀምጥ እንደሚገባ ዓለማቀፉ  የግጭቶች ጥናት ተቋም (ክራይስስ ግሩፕ) ባወጣው ሪፖርት አሳስቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ2022  አፍሪካ በጽኑ ትፈተንባቸዋለች የተባሉ ስምንት የቀውስ ሁኔታዎችን በዝርዝር ያቀረበው ተቋሙ፤ ጉባዔው በዋናነት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እየቀጠፉ ያሉት ግጭቶችን ማስቆም በሚቻልበትና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በአህጉሪቱ በሚፈጠርበት ሁኔታ ላይ ሊመክር ይገባል ብሏል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ፣ ምዕራብ  አፍሪካና መካከለኛ አፍሪካ የተከሰቱ ጦርነትና ግጭቶች እንዲሁም ህዝባዊ አመፆች የ2021 ፈታኝ ሁኔታዎች  እንደነበሩ ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ እነዚህ ሁኔታዎች በ2022 የሚቀንሱበት መንገድ ካልተበጀ፣ አህጉሪቱ የከፋ ሰብአዊ ቀውስ  ውስጥ  እንድትገባ ያደርጋታል ብሏል፡፡
ከጦርነትና ግጭት ባሻገር በተለይ በምስራቅ አፍሪካ የተፈጥሮ አየር መዛባት  የፈጠረው የድርቅ ሁኔታም በጉባኤው ትኩረት ሊደረግባቸው ከሚገቡ ጉልህ ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
ባለፈው 2021 ዓ.ም በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሱዳንና ኢትዮጵያ ጦርነትና ህዝባዊ አመፅ መከሰቱንና እስካሁንም ሃገራቱ ሁነኛ መረጋጋት ውስጥ እንዳልገቡ፤ በተመሳሳይ  በቻድ፣ ጊኒ፣ ማሊና ኮትዲቯር የመፈንቅለ መንግስታት ማጋጠማቸውን፣ በቱኒዚያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሱማሊያና ሊቢያ ደካማ መንግስታት በመፈጠራቸው ቀውሶች መከሰታቸውን  ተቋሙ አመልክቷል።
እነዚህን የአህጉሪቱን የራስ ምታት የሆኑ ጉዳዮች ዋና አጀንዳ አድርጎ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤው ሊወያይና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሚመጣበትን ሁኔታ ሊያበጅ ይገባዋል ያለው ክራይስስ ግሩፕ፤ ስምንቱ እጅግ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ብሎ የዘረዘራቸው የሚከተሉት ናቸው፡፡
የቻድ ጉዳይ  
ለረጅም ዓመታት ቻድን ያስተዳደሯት ፕሬዚዳንት እድሪስ ዴፒ በሚያዚያ 2021 መሞታቸውን ተከትሎ፣ የ37 ዓመቱ ልጃቸው መሀማስ ዴፒ በሀገሪቱ መከላከያ ሀይል ታጅቦ ስልጣን መቆናጠጡን ያልተቀበሉ የፖለቲካ ሀይሎች ተቃውሞ እያሰሙ ሲሆን ይህም ሀገሪቱን ወደለየት ቀውስ እንዳይወስዳት ስጋት አጭሯል፡፡
በወቅቱ ጉዳዩን እንደ ህገ-ወጥ የተመለከተው የአፍሪካ ህብረትም፣ በአባታቸው እግር ለተተኩት መሃማት ዕውቅና ነፍጎ የነበረ ቢሆንም፣ ያን ያህል ተፅኖ መፍጠር ሳይችል ቀርቶ የሃገሪቱን ችግር ሊፈታ አለመቻሉን ያስታወሰው ክራይስስ ግሩፕ፤ በዚህ የመሪዎች ጉባኤ በተለይ አሁን ያለውን ፕሬዚዳንት ተቀብሎ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ ግፊትና ማበረታቻ ማድረግ ይገባዋል ብሏል፡፡
በቻድ ያለውን ቀውስ ለመፍታት አፍሪካ ህብረት ዋናውን የማሸማገልና የማደራደር ሚና በመውሰድ በሃገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች መካከል ሠላማዊ ውይይቶች የሚካሄዱበትን አውድም መፍጠር እንደሚገባው ተቋሙ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት
ላለፉት 14 ወራት በዘለቀው ጦርነት በ10 ሺዎች መገደላቸውንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ይህ ጦርነት ረሃብን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለይ በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት፣ በመንግስትና በአማጺው ህወኃት መካከል ንግግሮች የሚካሄዱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ መሆኑን፣ ነገር ግን የአፍሪካ ህብረት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ጥረቱ ፈጣን ውጤት እያመጣ አለመሆኑን ይገልፃል፡፡
ህብረቱ በጉባኤው ላይ ጉዳዩን ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ አድርጎ ሁነኛ ግጭት ፈቺ መፍትሔ እንዲያፈልቅ፣ ጠንካራ አሸማጋይ ቡድን እንዲያደራጅና በሃገሪቱ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት የሚካሄድበት ሁኔታ እንዲፈጠር ግፊት እንዲያደርግ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
በዚህ ጦርነት ስለተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም ትኩረት ሰጥቶ በጉባኤው  እንዲወያይ ጠይቋል - ክራይስስ ግሩፕ፡፡
የሊቢያ ጉዳይ
እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ በቀውስ እየተናጠች የምትገኘው ሊቢያን ከበለጠ ጥፋት ለመታደግ፣ በተለይ የውጭ ሃይሎች ከሃገሪቱ ላይ እጃቸውን የሚያነሱበትን ሁኔታ አስመልክቶ ህብረቱ አጀንዳው አድርጎ እንዲመክር እንዲሁም በሊቢያ ካሉ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ህብረቱ ጠንካራ ልኡክ አደራጅቶ ተቀራርቦ የሚሰራበትን ሁኔታ እንዲፈጥር  ተቋሙ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
የሞዛምቢክ ቀውስ
በሞዛምቢክ ካቦ ዴልጋዶ ግዛት ውስጥ በአማጺያንና በመንግስት ሃይሎች መካከል በተከሰተው ግጭት ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውንና ከ750 ሺህ በላይ መፈናቀላቸውን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ የሞዛምቢክ መንግስት ጉዳዩን በውይይትና የአካባቢውን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አዳዲስ ውሳኔዎችን በመወሰን ወደ መፍትሄው እንዲቀርብ ግፊት ሊደረግበት ይገባል ብሏል፡፡
ጉዳዩ ከጋዝ ማዕድን ጋር የተያያዘ በመሆኑም የተፈጥሮ ሃብቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ መፍትሄውን ያፋጥነዋል ያለው ሪፖርቱ፤ በዚህ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ሁሉን አቀፍ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ተግባራዊ የሚደረጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ አመልክቷል፡፡
አለማቀፍ የግጭቶች ጥናት ተቋም (ክራይስስ ግሩፕ)፤ በዚህ ሰፊ ሪፖርቱ ከዘረዘራቸውና መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል፣ ህብረቱም ዋነኛ አጀንዳ አድርጎ ሊወያይባቸው ይገባል ካላቸው ቀውሶች መካከል በ5ኛ ደረጃ የቡርኪናፋሶ  መፈንቅለ መንግስት ጉዳይ፣ የሳህል መንግስትና አማጺያኑ ግጭት፣ በ6ኛ ደረጃ የሶማሊያ ጉዳይ፣ በ7ኛ ደረጃ የሱዳን የሽግግር መንግስት ቀውስ እንዲሁም፣ በ8ኛ ደረጃ በአህጉሪቱ በአየር ፀባይ መዛባት ምክንያት የተፈጠሩ የድርቅና ሌሎች ተፈጥሯዊ ቀውሶችን መፍታት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት የሚሉት ናቸው፡፡
ከሦስት ዓመታት መቋረጥ በኋላ ዘንድሮ የሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ጥር 28 እና ነገ ጥር 29 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 2916 times Last modified on Saturday, 05 February 2022 12:31