Wednesday, 09 February 2022 00:00

የመፈንቅለ መንግስት ልምምድ በአፍሪካ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በአፍሪካ በ45 ዓመታት ውስጥ 80 የተሳኩ የመንግስት ግልበጣዎችና 247 ያልተሳኩ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች ተደርገዋል።
አፍሪካ ባለፉት 11 ዓመታት (ከ2010 ወዲህ ብቻ) 12 የተሳኩ የመንግስት ግልበጣዎችና 30 ያልተሳኩ የመንግስት ግልበጣ ሙከራዎች፤ በድምሩ 42 መፈንቅለ መንግስትና የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አስተናግዳለች፡፡
ለምሳሌ፡- ቡርኪና ፋሶ በ11 ዓመት ውስጥ የዛሬ ሳምንት የተሳካ የመንግስት ግልበጣ እና 2 ሙከራ፤ ማሊ በ11 ዓመት ውስጥ 3 የተሳካ የመንግስት ግልበጣ እና አንድ ሙከራ (2012፤ 2020፤ 2021 (በዓመት ሁለት ጊዜ)፤ ሱዳን በ11 ዓመት ውስጥ 2 የተሳካ የመንግስት ግልበጣ እና 2 ሙከራ (በ2021 በአንድ ወር ውስጥ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራም የመንግስት ግልበጣም አድርጋለች)፤  የተሳካ መፈንቅለ መንግስት  ካደረጉ ሌሎች አጋራት መካከል ኒጀር፤ ሊቢያ (ሂደቱ የቀጠለ ግልበጣ)፤ ዚምባብዌ፤ ግብጽና ጊኒ ይገኙበታል፡፡
ለንጽጽር ባለፉት 11 ዓመታት በእስያ 4 የተሳኩ የመንግስት ግልበጣ ተደርገዋል! ማለትም የመን 2 ጊዜ፤ ታይላንድ እና ማይናማር አንድ አንዴ እንዲሁም 2 የግልበጣ ሙከራ ቱርክ እና ባንግላዲሽ ሲሆን በአውሮፓ ባለፉት 11 ዓመታት ሞንተኔግሮ አንድ ሙከራ፤ በላቲን_አሜሪካዋ ኢኳዶር አንድ ሙከራ ብቻ ነው የተከናወነው፡፡
ለምሳሌ፡- ከአትዮጵያ በስተቀር አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከአውሮፓ ቅኝ ገዢዎቻቸው በአንጻራዊነት ነጻ ከወጡበት ከ1960ዎቹ ጀምሮ በርካታ የመፈንቅለ መንግስትና የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በትጋት አድርገዋል!
መንግስታትን በሃይል መለወጥ ወይም መፈንቅለ መንግስት በብዙ የዓለማችን ሀገራት ከሺ ዓመታት በፊት የነበረ ልማድ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ጃፓን የመጀመሪያዋን የመንግስት ግልበጣ ያደረገችው የዛሬ 1566 ዓመት ነበር በታሪኳ ለ16 ጊዜ ያህል የተሳኩም ያልተሳኩም መፈንቅለ መንግስቶች አድርጋለች፤ ነገር ግን  ጃፓኖች የመጨረሻውን ሙከራም ሆነ ግልበጣ ያከናወኑት የዛሬ 52 ዓመት ነው፡፡
አሜሪካ በታሪኳ 10 ጊዜ ሙከራም የተሳካም መፈንቅለ መንግስት ስታደርግ፣ የመጨረሻዋ የዛሬ 88 ዓመት ነበር፤ ስፔን በታሪኳ 36 ጊዜ ሙከራም የተሳካም መፈንቅለ መንግስት ስታደርግ፣ የመጨረሻዋ የዛሬ 37 ዓመት ነበር፤ ኢራን በታሪኳ 25 ጊዜ ሙከራም የተሳካም መፈንቅለ መንግስት ስታደርግ፣ የመጨረሻዋ የዛሬ 42 ዓመት ነበር፤ ፈረንሳይ በታሪኳ 17 ጊዜ ሙከራም የተሳካም መፈንቅለ መንግስት ስታደርግ ያደረገች ሲሆን የመጨረሻዋ የዛሬ 60 ዓመት ነበር!
ኢትዮጵያ ባለፉት 121 ዓመታት ውስጥ 6 ጊዜ  ያህል ሙከራም የተሳካም መፈንቅለ መንግስት ስታደርግ፤ ቡርኪና ፋሶ በ60 ዓመት ውስጥ 11 ጊዜ ሙከራም የተሳካም መፈንቅለ መንግስት አድርጋለች፡፡ የመጨረሻዋ የዛሬ ሳምንት ነው፤ ሱዳን በ60 ዓመታት ውስጥ 10 ጊዜ ሙከራም የተሳካም መፈንቅለ መንግስት ስታደርግ፣ የመጨረሻዋ የዛሬ 2 ወር ነው፤ ያካሄደችው፡፡
አልጀዚራ ከዚህ ቀደም ዋቢ ባደረገው ጥናት፤ በአፍሪካ አህጉር ወስጥ ከ1960 እስከ 2000 ብቻ በየዓመቱ በአማካይ 4 መፈንቅለ መንግስት ይደረግባታልም ይሞከርባታልም ብሏል፡፡ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ  ባይሳካም  እንኳን በአገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ውድመት የሚያስከትል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
“Why Nations Fail” የተሰኘ መጽሐፍ ሀገራት ድሃ የሚሆኑበትን ምክንያት ሲያስረዳ፤ “ዋናው ምክንያት በሰዎች በሚፈጠር የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት ሁኔታ ነው! ድህነት የሚመጣውም የሚባባሰውም” ብሏል፡፡ ስለዚህ አፍሪካ በመንግስት ግልበጣ ተጠምዳ ሃብቷን ለመጠቀምም ሆነ ተቋማትን ለማጠናከር የሚሆን አቅም መፍጠር ተቸግራለች፡፡
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሲጀመር ጊኒ፤ ማሊ፤ ሱዳንና ቡርኪና ፋሶ መፈንቅለ መንግስት ካደረጉ የወራት እድሜ ይዘው ነው! 14 አባል ሀገራት ለህብረቱ የሚገባቸውን መዋጮ ባለመክፈል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል (60 ከመቶ የህብረቱ በጀት ድጎማው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ነው! ዋነኞቹ አሜሪካ፤ ካናዳ፤ ቻይና፤ የአውሮፓ ህብረት፤ ወዘተ)፡፡
አፍሪካ በብዙ መልኩ እራሷን ጠንካራ በማድረግ በዓለም ላይ ተፎካካሪ አህጉር ለመሆን የመሪዎችን_ቁርጠኝነትና የዜጎችን_ትብብር መፈለጓ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በአባል ሀገራት መካከል ጠንካራ ትብብር ያስፈልጋል (የአፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጠና መመሥረቱ አንዱ መልካም እርምጃ ነው)፡፡ ይህ ጉዳይ አፍሪካ ላደጉ ሀገራት ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና መልኩን እየቀየረ ከመጣው የቀጠናዊ ፉክክር አንጻር ቀላል ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡
መጪው ጊዜ ለአባል ሀገራት እጥፍ ስራ የሚጠይቅ ነው። የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ የተሳካ እንዲሆን ምኞቴ ነው!
ረዥም ዘመን በስልጣን ላይ የቆዩ መሪዎች
1. የኢኳቶሪያል ጊኒ መሪ ቲዶር ኦቢያንግ ስልጣን ከያዙ 43 አመታቸው ነው
2. የካሜሮን ፕሬዝዳንት  ፖል ቢያ ስልጣን ከያዙ 40 አመታቸው ነው
3. የኡጋንዳ መሪ ዩዌሪ ሙሴቬኒ   ስልጣን ከያዙ 36 አመታቸው ነው
4.የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ስልጣን ከያዙ 29 አመታቸው ነው
5.የኮንጎው መሪ ዲኒስ ሳሶ ስልጣን ከያዙ 25 አመታቸው ነው
6. የጅቡቲው መሪ  ኢስማኤል  ኡመር ጉሌ ስልጣን ከያዙ 23 አመታቸው ነው

Read 6844 times