Saturday, 05 February 2022 12:27

ታጥቆ እንዳይጠብቅ፤ ወይኔ ወይኔ እያለ ይኖራል” “ተዓጢቑ ከይሕሉ፣ ወይለይ ወይለይ ይብል ይህሉ” - የትግርኛ ተረት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የሩሲያ መሪ የነበሩት ጆሴፍ ስታሊን አንድ ጊዜ  አደረጉት የተባለው ነገር ዛሬ እንደ ተረት ተጠቃሽ ነው፡፡ እነሆ፡-
ጆሴፍ ስታሊን ሰውን ስብሰባ ጠርተዋል። ተሰብሳቢው ፀጥ ብሎ ንግግራቸውን ያዳምጣል፡፡  አስፈሪ አምባገነን የተባሉ፣ ሰው ጤፉ የሆኑ፣ የሰው ነፍስም ከትንኝ የሚያንስ የሚመስላቸው መሪ ናቸው፡፡ ተሰብሳቢው ሁሉ የሳቸውን ክፉነት አሳምሮ ስለሚያውቅ፣ ፀጥ ረጭ ብሎ ከማዳመጥ በስተቀር ጥያቄ አይጠይቅም፤ አስተያየትም አይሰጥም፡፡
ታዲያ የዚያን ቀን ስታሊን ንግግር እያደረጉ ቆመው ሳለ፣ አንድ ሰው ከታዳሚዎቹ መካከል አስነጠሰ!
ስታሊን፣ “ማነው አሁን ያስነጠሰው?” ሲሉ ጠየቁ
ማንም መልስ አልሰጠም፡፡
ሁሉም ጭጭ አለ፡፡
ሁሉም አቀርቅሮ መሬት መሬት ያያል፡፡
ሁሉም በየሆዱ፤
“ማንን ፈልገው ይሆን? ማን ይሆን የፈረደበት? ወንድ ይሆን ሴት ዛሬ የስታሊን በትር የሚያርፍበት?” ይላል።
 ያ ያስነጠሰውም ሰው ቢሆን፣ “እኔ ነኝ ልበላቸው፤ይሄ የተፈጥሮ ጉዳይ እኮ ነው እላቸዋለሁ” አላለም፡፡ የሚከተለው ምን እንደሚሆን ያውቃልና ፀጥ አለ፡፡
 ስታሊን ሆዬ አንጋቾቻቸውን ጠሩና፤
“ከአዳራሹ ወንበሮች የመጨረሻ ሁለት መስመሮች ላይ  ያለውን ህዝብ፣አስወጥታችሁ ግደሉልኝ !” አሉ
አንጋቾቹም፤ “በጓድ ስታሊን ትዕዛዝ መሰረት፣ የሁለቱንም ረድፍ ሰዎች በሙሉ ወስደን፣ረሽነን መጥተናል!” አሉ፡፡
አሁንም አዳራሹ ፀጥ ብሏል፡፡ መናገር ቀርቶ ቀና ብሎ የሚያይ ሰው ጠፋ።
 ስታሊን፤ “አሁንም አትናገሩም? ያስነጠሰው ማን ነው?” አሉ በቁጣ፡፡
ከዚያ ወደ አንጋቾቻቸው ዞር ብለው፤
“አሁንም የኋለኞቹ ሁለት መስመሮች ላይ ያለውን ሰው አስወጡና ረሽኑ!”አሉ፡፡
አንጋቾቹም ሁለት መስመር ላይ ያሉትን ሰዎች በሙሉ  አስወጥተው ረሽነው ተመለሱና፤
“ጓድ፤በታዘዝነው መሰረት አጠናቀን ተመልሰናል! ግዳጃችንን ተወጥናል!” አሉ፡፡
ስታሊንም ወደ ሕዝቡ ዞረው፤
“አሁንስ አትናገሩም? ማን ነው እኔ ከምስባኩ- ከመናገሪያው ጀርባ ቆሜ ንግግር ሳደርግ ያስነጠሰው? ብትናገሩ ይሻላችኋል!?” አሉ፡፡
 አሁን የቀረው ሰው፣ ሁለት ተርታ ብቻ ነው። ይሄኔ አንድ መነጽር ያደረጉ አዛውንት ፈራ ተባ እያሉ ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው፣ በኮሰሰ ድምጽ፤
“እኔ ነኝ ጓድ!” አሉ
“ጓድ ይማርዎት!” አላቸው፤ ስታሊን።
አዛውንቱም፣
“ያኑርዎት!” አሉና መለሱ
*   *   *
ከስታሊን በትር ይሰውረን!! አሜን!!
 መሪና ተመሪመ አለቃና ምንዝር፣ዋና ስራ አስኪያጅና የስራ ሂደት ሃላፊ ወዘተ የሚፈራሩበት ስርዓት ምንጊዜም ዲሞክራሲያዊ አይሆንም፡፡ የበላይን ከልኩ በላይ የመፍራት ልማድ አደገኛ ነው፡፡ አለቅየው የበታቹን በማርበትበትና በማርበድበድ የሚያምን ከሆነ፣ የበታቹ ቅጥና አቅል የሌለው ሰው ይሆናል። አልፎ ተርፎ ዳተኛና ዋልጌ ይሆናል፡፡ የባሰበትም የሚኖርበትንም አገር ትቶ ይሰደዳል-ይኮበልላል፡፡ ኢ-ፍትሀዊ የሆነ የስራ ግንኙነት መፈጠሩ አይቀሬ ነው!   የጌታ የሎሌ ግንኙነት ነውና ለህዝብም ለሀገርም አይበጅም፡፡
ከበታቹ ሰራተኛ ፍርሃት በመነሳት አለቅየው የባሰ በመኩራራትና በማስፈራራት ለረጅም ዘመን ተፈርቶ እንደሚኖር ዓይነት ስሜት ይሰማዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ለዘለዓለም እሱ ብቻ የሚመራ፤እሱ ብቻ የሚገዛ ይመስለዋል፡፡ He mistakes longevity for eternity እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ። በቀጥታ ስናጤነው፣ ረጅም እድሜን ከዘለዓለማዊነት ያምታታዋል እንደማለት ነው፡፡ በሀገራችን ብዙ መሪዎች ይሄን ሲፈጽሙ አስተውለናል፡፡
ከዚህም ይሰውረን!
ኢ-ወገናዊ፣ ኢ- ፍትሃዊ፣ ኢ- አምባገነናዊ አሰራርን የመቀበል መንገድ ብቻ ነው- አዋጪው፡፡ ስነ ምግባራዊነትና ሙያዊነት (ethics and Professionalism) ዋና መሳሪያችን ሊሆኑ ይገባል፡፡ በመሳሪያችን በአግባቡ መገልገልና ሀላፊነትን አለመሸሽ እንዲሁም ተጠያቂነትን በወጉ ማመን ቁልፍ ጉዳያችን መሆን አለበት፡፡
በተደጋጋሚ የተከሰቱ ችግሮችን፣በተደጋጋሚ አንስተን፣በተደጋጋሚ እንፈታቸዋለን ብለን፣ ቃል ገብተን ስናበቃ፤ እዚያው ትናንት የተነሳንበት ቦታ እንገኛለን- back to square one እንደማለት ነው! ያንን ለማሻሻል የትናንት እንከኖቻችንን በሚገባ በመመርመር፣ ማረሚያዎቻችንን አንድ በአንድ በመለየት ወሳኝ መፍትሔዎችን በአግባቡ መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ በየቦታው የሚያጋጥሙ የሙስና ቅርንጫፎችን ያለመታከት ቆራርጠን መጣል አለብን፡፡
እንደ ታሪክ  ስላቅ ሆኖ የሚነገር አንድ ወግ አለ፡- “የአሜሪካ የሀገር ደህንነት አማካሪ ለእስራኤል የፍትህ ሚኒስትር /የአሜሪካና የእስራኤል የህዝብ  ጉዳይ ኮሚቴ (AIPAC)”  እንዲህ ሲሉ ጠየቁ አሉ:- (AIPAC) ውስጥ ያለ፣ የሚፈራኝ ሰው ታውቃለህ ወይ?”  
ዋናዋ እንጀራ ጋገሪ ራሷ አሜሪካ ሆና ሳለ፣ የውስጥ ሰው ከእስራኤል ፈለገች ማለት ነው። የሙስና ጥልቀቱና ርቀቱ ይለያይ እንጂ ሀያላን ሀገሮች ውስጥም አለ። ስር ከሰደደ መመለሻም የለው! “አባይን፣ በአንድ ጊዜ ከመነሻውም ከመድረሻውም  መጨለፍ አይቻልም” ይለናል፤ “ራስ ኤላስ መስፍንና ኢትዮጵያ” የተባለው መፅሐፍ። ሁሉንም በአንድ ቅፅበት ፈትተን አንችለውም፤ ቅደም ተከተል አበጅተን ተራ በተራ ማስወገድ መልመድ ይኖርብናል፡፡ “ፈጣን ልማድ ያሻል” ብለን፣ ፈጣን ውድቀት እንዳይመጣ እንጠንቀቅ!
ዞሮ ዞሮ ለሁሉም እጅግ ወሳኙ ዝግጁነት መሆኑን አንርሳ! ሆይ ሆይ ብለን ተዋክበን ኋላ ማጣፊያው እንዳያጥረን መንገዳችንን አስቀድመን መጥረግ ይኖርብናል፡፡ አለበለዚያ “ታጥቆ እንዳይጠብቅ፤ ወይኔ ወይኔ እያለ ይኖራል” እንደሚባለው የትግሪኛ አባባል እንሆናለን፡፡


Read 12103 times