Thursday, 03 February 2022 00:00

አፕል ለ15ኛ ተከታታይ አመት የአለማችን ዝነኛ ኩባንያ ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ቶዮታ ዘንድሮም ግዙፉ የአለማችን የመኪና አምራች ተብሏል

            የአለማችንን ዝነኛ ኩባንያዎች ዝርዝር በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ፎርቹን መጽሄት፣ ከሰሞኑም የ2021 መረጃውን ይፋ ያደረገ ሲሆን ላለፉት 14 ተከታታይ አመታት የአለማችን ቁጥር 1 ዝነኛ ኩባንያ ሆኖ የዘለቀው ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል ዘንድሮም በአንደኝነቱ ቀጥሏል፡፡
አምና 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘው የነበሩት አማዞንና ማይክሮሶፍት ኩባንያዎች፣ ዘንድሮም የደረጃ ለውጥ ሳያሳዩ በዚያው መቀጠላቸውን የፎርቹን መረጃ ያመለክታል።
የኮሮና ክትባት አምራቹ ኩባንያ ፋይዘር የ4ኛ ደረጃን መያዙ የተነገረ ሲሆን፣ በመዝናኛው ኢንዱስትሪ የተሰማራው ዋልት ዲዝኒ አምስተኛው የአመቱ ዝነኛ የአለማችን ኩባንያ ለመባል ችሏል፡፡
ቤክሻየር ሃታዌይ፣ አልፋቤት፣ ስታርባክስ፣ ኔትፍሊክስና ጄፒሞርጋን ቼዝ እንደቅደም ተከተላቸው በዝነኝነት ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን ተወዳጅ ኩባንያዎችን መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
በፎርቹን መጽሄት የአመቱ ዝነኛ የአለማችን ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ ከአንደኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ሁሉም የአሜሪካ ኩባንያዎች መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ የንግድ ዘርፍ ዜና ደግሞ፣ ታዋቂው የጃፓን መኪና አምራች ኩባንያ ቶዮታ ዘንድሮም የአለማችን ግዙፉ ኩባንያ መባሉን የዘገበው አውቶ ኒውስ፤ ኩባንያው በ2021 አመት ከ10.5 ሚሊዮን በላይ መኪኖችን መሸጡን አመልክቷል፡፡
ቶዮታ አብዛኞቹን መኪኖቹን ከ180 በላይ በሚሆኑ የአለማችን አገራት መሸጡን የጠቆመው ዘገባው፤ ቮልስዋገን ኩባንያ በበኩሉ 8.9 ሚሊዮን መኪኖችን በመሸጥ የ2ኛነት ደረጃን መያዙን ገልጧል፡፡

Read 1221 times