Sunday, 06 February 2022 00:00

ሳምሰንግ በአመት 272 ሚ. ሞባይሎችን በመሸጥ 1ኛ ደረጃን መያዙ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የደቡብ ኮርያው የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ ሳምሰንግ በ2021 ብቻ 272 ሚሊዮን ያህል ስማርት ሞባይሎችን በአለማቀፍ ገበያ በመሸጥ፣ የአለማችን ግዙፍ የሞባይል አምራች ኩባንያነቱን ክብር ከአፕል ኩባንያ መረከቡ ተነግሯል፡፡
ሳምሰንግ በአለማቀፉ የስማርት ሞባይል ስልኮች ገበያ ያለው ድርሻ ባለፈው አመት ከነበረበት በ6 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የዘገበው ቴክራዳር ድረገጽ፤ ባለፈው አመት ለሽያጭ ያበቃው 256.6 ሚሊዮን ስልኮችን እንደነበረም አስታውሷል፡፡
ባለፈው አመት ግዙፉ የአለማችን የሞባይል አምራች ኩባንያ የነበረው የአይፎን ስልኮች አምራቹ አፕል በ2021 የፈረንጆች አመት ግን 235.7 ሚሊዮን ስማርት ሞባይሎችን በመሸጥ ወደ ሁለተኛነት ደረጃ ዝቅ ማለቱን አመልክቷል፡፡
አፕል ባለፈው አመት ከነበረው የአለማቀፍ የገበያ ድርሻ በ15.9 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ የቻይናው ኩባንያ ዢያኦሚ ዘንድሮ በ191 ሚሊዮን ሽያጭ የሶስተኛ ደረጃን መያዙንም ገልጧል፡፡
በ2021 በአለማቀፉ የስማርት ሞባይሎች ገበያ በድምሩ 1.3 ቢሊዮን ያህል ስልኮች መሸጣቸውን የዘገበው ሲኤንቢሲ በበኩሉ፤ ሽያጩ ካለፈው አመት የ4 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንና ባለፉት 4 አመታት የታየ የመጀመሪያው ዕድገት መሆኑንም አስረድቷል፡፡

Read 4692 times