Saturday, 05 February 2022 12:37

የመገረምን ጥግ ማለፍ…

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(2 votes)

 የፓትሪክ ሰስኪንድ ‹‹ግሬኖል›› እንደ አልበርት ካሙ ንጉሥ ቄሳር ካሊጉላ መሉ ስልጣን ያለው ንጉስ አይደለም፡፡ እንዲያውም ግሬኖል በንባብ ብቻ ጉንፋን በሚያስይዝ የግማትና ጥንባት ትርኪምርኪ የዓሳ ጭንቅላቶች መሀል ወድቆ የተገኘ አንድ ጉስቁል ፍጡር ነው፡፡ ሆኖም ሁለቱም ገፀባህሪያት በአንድ የንባብ ትውውቅ ብቻ በነፍሳችን ጥልቅ ስርቻ የሚፈጥሩት የሕይወት ንዝረት፣ ከለመድነው የዘልማድ ኑረት አናጥቦ ዘለግ ላለ ጊዜ የሚያስቆዝም ልዩ ኃይል አለው፡፡
ያገሬ ሰው ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ይላል፡፡ በፓትሪክ ሰስኪንድ ‹das perfume› (ጉድ ሲናጥ-- ተሾመ ዳምጠው) አመፀኛ ልብ ወለድ ውስጥ እንዲህ ሆነላችሁ። ጊዜው በ1770ዎቹ በፈረንሳይ ሀገር…  የዚህ ልብ ወለድ ዋና ገፀባህሪ ‹ግሬኖል› እናት በተወለደበት ቅፅበት እንደ ሌሎቹ አራት ወንድምና እህቶቹ የተከማቹ የበሰበሱ የዓሳ ጭንቅላቶች መሃል ጥላ ልትገድለው ስትሞክር እጅ ከፈንጅ ተያዘች። ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለዚህ ድርጊቷ በአደባባይ በስቅላት ተቀጣች፡፡
ሕፃኑ በቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች በጎነት ለቅጥር ሞግዚቶች ተሰጠ፡፡ በቀጠለው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ የውርደት፣ የሃፍረት፣ የውድቀት ሰንሰለት እየተመላለሰበት፣ ከሞግዚት ሞግዚት እየተንከራተተ አደገ፡፡ በሁሉም ነገር ችላ የተባለ ማንም ለቁምነገር የማይፈልገው ሰዋዊ መስተጋብሮችን ሁሉ በጭካኔ የተነጠቀ ምንዱብ ሰው ሆነ፡፡ ይሄም በቀጠለው ጊዜ ያረገዘውን ድብቅ ቂም እንዲጸንስ አደረገው፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ለሕይወት ስሜት አልባ፣ ገልጃጃ ይመስል የነበረው ለጋ ታዳጊ፣ አንድ የፀደይ ዕለት ድንገት ‹‹አፈር›› አለ፡፡ ቀጥሎ ዝም ያለው የምናብ ዓለም ሕሊና ሊገምተው እስከማይችለው ጥግ እስኪተረማመስ ድረስ የተፈጠረው ምስቅልቅል የተጀመረው በዚህች የማሽተት ልዩ ቅፅበት ነበር፡፡
ልዩ የማሽተት  መክሊት ባለቤት መሆኑን ያወቀው ግሬኖል፤ በዙሪያው የተሰበሰቡ በሺህና በብዙ ሚሊዮናት የሚቆጠሩ ግማት፣ ክርፋት፣ ጥንባት፣ ቁናሶችን ሁሉ በአዕምሮው እየተነተነ መመዝገብ ጀመረ። ግሬኖል ከቆዳ አለስላሽነት እስከ ሽቶ ቀማሚነት በተሸጋገረባቸው ዓመታት ይሄው የማሽተት ስል ደመነፍሱ ይበልጥ እያደገ እያደገ ሄደ፡፡ በዙሪያው ያለው ዓለም ሁሉ የከበበውን ሚሊዮናት ቁናስ፣ ግማት፣ ክርፋት፣ ብስናት ሁሉ በአዕምሮው የሚመዘግበው ግሬኖል፣ እሱ ግን ለራሱ አካላዊ ጠረን እንደለሌለው ተገነዘበ፡፡ በሽቶ ዝግጅት ልሂቃን ባለሙያዎች መናኸሪያነት ወደምትታወቀው ግራሰ ከተማ ሄዶ ለራሱ እጅግ ልዩ የሆነውን ሽቶ ከመስራቱ በፊት ለሰባት ዓመታት በዋሻ ውስጥ ለብቻው አሳለፈ፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት ግሬኖል የተነጠቃቸውን ክብር፣ ሞገስ፣ ፍቅር እንቶፈንቶዎች የሚያስመልስበት ከዚህ በፊት ማንም ያልሰራውን ልዩ ሽቶ የመስራት ውጥን ያዘ፡፡ ይህንን ልዩ ሽቶ ለመስራት የበርካታ ልጃገረዶች ጠረን የግድ ያስፈልጋል፡፡ በግራሰ ከተማ ውስጥ ያሉ ልጃገረዶች ሁሉ ያሉበትን በጠረናቸው አማካኝነት ጠንቅቆ የሚያውቀው ግሬኖል፤ አንድ በአንድ ሃያ አምስት ልጃገረዶችን በጭካኔ እየገደለ ባዘጋጀው ሰም ጠረናቸውን መዘበረ፡፡
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምናነበው ግሬኖል በዕውንና በቅዠት ዓለም መካከል የሚዋልል የማይጨበጥ (illusinist) የተረት ዓለም ይመስላል፡፡ የግሬኖል ታሪክ  ከአፈታሪክ እስከ እውናዊ ሕይወት እየዋለለ፣ የንባብ ህሊናችን ብዙ ቅጥሮችን እንዲጥስ ያስገድዳል፡፡ የእውነታ ዓለምና የምናብ ዓለም የሃሳብ ድንበሮች ተጥሰው ሕይወት በነውጡ መሃል እንኳን ዝርግ ገፅታን ይዛ ትታያለች፡፡ ግሬኖል እንደ ካሊጉላ ይህች ዓለም የተገነባችበትን ልክ ያልሆነ አወቃቀር የሚቃወም ይመስላል፡፡ ሆኖም ለግሬኖል የዚህ ተቃውሞውም ሆነ የመፍትሔ እርምጃው መነሻም መድረሻም ጠረንና ሽቶ ብቻ ነው፡፡
ግሬኖልን ጠጋ ብለን በየዋህነት ስንረዳው፣ እኛ ለምንኖርበት ዓለም በመጠኑ የቀረበ የሲሲፐስ መንታ ፍጥረትነት ይነበብበታል።   ግሬኖል ዘመኑን ሙሉ የኖረው ልክ ትናንት በጎልማሳነት ዕድሜ ወደ ሕይወት በእንግድነት እንደተጠራ ሁሉ ግር እየተሰኘ ነው፡፡ አኗኗሩ ከሺ ዓመታት በፊት የሆነውንና ከሺ ዓመታት በኋላ የሚሆነውን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ሰው ለምንም ያለመጓጓት የታከለበት ሆነ፡፡ እንዲያው መኖር ግዴታው ስለሆነ ብቻ የሚኖር ይመስላል፡፡
በመጨረሻ ግሬኖል ከተረሳ እንደ ትንኝ ከተናቀ ማንነት ተነስቶ ጠባቧን የግራሰ ዓለም በአንዲት ጠብታ ሽቶ ብቻ በቁጥጥሩ ስር ማድረግ ቻለ፡፡ ከዚህች የብልቂያጥ ሽቶ ጥቂት ብቻ አጥቅሶ ለሮማው ጳጳስ ደብዳቤ ቢጽፍ፣ መድኃኒትዓለም ክርስቶስ እንደገና ተከስቷል ብለው ሊያውጁ ይችላሉ፡፡ አዎ አንድ ሙሉ ስልብ ገልጃጃ ስንኩል ኑረት የገበረለትን ዓላማ አሳክቷል፡፡ ከዚህ በፊት ማንም ያልሰራውን ታላቁን የሽቶ ጠረን መስራት ችሏል፡፡
በዚያች የብልቂያጥ ሽቶ የሚመኛቸው፣ የሚፈልጋቸውን እንደ ሰው ያጣቸውን ምኞቶቹን በሙሉ በቀላሉ ማሳካት ይችላል፡፡ ጠረኑን ለራሱ አዘጋጅቷል፡፡ የተፈጥሮ ጠረን አልነበረውም ብሎ አባባል ተራ ትርክት አይደለም፡፡ ጠረን ማንነት ነው፡፡ ጠረን አልባነቱ እንደ መርገምት ተቆጥሮ ገና በለጋነቱ ከሞግዚት ሞግዚት አንከራቶታል፡፡ ይሄን ልሙጥ የሆነ መለኮታዊ ፌዝ የሚመስል ዕጣፈንታውን በሰራት የብልቂያጥ ሽቶ ተዓምር ገለበጠው። ያጣውን ታላቅ ሞገስ በምልዓት ማስመለስ ችሏል፡፡ ማንም ነገሬ የማይለው ግሬኖል፣ በቀማመት ጠረን ምክኒያት ሁሉንም ሰብዓዊ ፍጥረት ከአለቃ እስከ ምንዝር በአድናቆት እግሩ ሥር እንዲደፉ ማድረግ ቻለ፡፡ ሲያልቅ ምንም ያልነበረው ምንዱቡ ግሬኖል፣ ሁሉንም ሲያገኝ ግን ሞትን ተመኘ። ለምን?
ሁለት ምላምታዊ ምልሶች ብቻ ማስቀመጥ እንችላለን... ግሬኖል ታላቁን ልክ የለሽ ሞገስ ያጎናጸፈውንና ከመስቀያ ገመዱ ያስጣለውን ሽቶ ከሰራ በኋላ መንፈሳዊ ልዕልናን ተቀዳጅቷል፡፡ በሌላ አነጋገር መለኮቱን መስሏል፡፡ እንደ ምስራቃዊያኑ አስተሳሰብ፣ የሰው ልጅ  አምላክን የመሆን የማከል ስንኩል አቅም የተቸረው ጥጥረት ነው፡፡ (Man is a potential God) አሜሪዊው ጋዜጠኛና ፈላስፋ ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን በበኩሉ፤ ‹‹ሰው ድብቅ መለኮታዊነት ተሰጥቶታል፡፡ ሰው ጅል ጅልኛውን የሚጫወት አምላክ ነው›› ይላል፡፡ ሰው የሕይወት ዘመን ትግሉ ሁሉ ወደ ገነት የመመለስ ወደ አምላኩ የመጠጋት፣ ቢቻል አምላኩን የማከል፣ የመዋሃድ ሂደት ይመስላል፡፡ አምላክን የመሆን፣ የማከል፣ የመገናኘት ምኞቱ ፍጽምና የሚገኘው ደግሞ በሞት ብቻ ነው፡፡ ሰው የቱንም ያህል ቢበቃ፣ ቢራቀቅ፣ በሕልውና እያለ ማለቂያ በሌለው ሂደት ወደ መለኮቱ ይጠጋል እንጂ ሊነካው አይችልም፡፡ የግሬኖል ለመሞት የመጣደፍ የመቋመጥ መሻት መነሻው ይሄው ምኞት ሊሆን ይችላል፡፡  
በሌላ መልኩ ግሬኖል ዘመኑን የታተረለት ታላቁን ሽቶ የመስራት ምኞት ከተሳካ በኋላ ሌላ የሕይወትን ሸክም የሚቋቋምበት የመኖር ዓላማ አጥቷል፡፡ ይሄን ባዶነት ለማምለጥ ሞትን እንደ አቋራጭ ማምለጫ አስቦትም ይሆናል፡፡ ምናልባት...                       
‹ጉድ ሲናጥ› በሕይወት ስድ አወቃቀር በግፍ የተደፈጠጠ ሰብዕ ለግብስብሱና ብልጭልጩ ዓለም ግድ የለሽ መስሎ በማሽተት ልዩ መክሊቱ ሲያሸምቅ (ሲያደባ)፤ ነፍስ በጠረን ስም አፍንጫ ጫፍ ተንጠልጥላ ለሕልውና ስታቃስት፤ ውበት ቁብ ትኩረት አጥቶ ለጠረን ሲባል በጭካኔ ሲሰዋ፤ ዝብርቅርቁን ተከትሎ ጠባቧ ዓለም ስትናወጥ ...  እንደገና አንድ ሙሉ ስልብ፣ ገልጃጃ፣ ስንኩል ኑረት የገበሩለት የብልቃጥ ሽቶ ከመስቀያ ገመዱ ሲያስጥል፤ መልሶ ሰውን ያክል ፍጡር እንደ ብስኩት፣ እንደ አንዳች ትንግርት በሚያስብል ሁኔታ ቀረጣጥፎ ሲያስበላ…ግር እየተሰኘን የምናነብበት ልብወለድ ነው፡፡ … ህም…እውነትም ‹‹ጉድ ሲናጥ››…
ዓለማየሁ ገላጋይ በትርጉም መጽሐፉ ጀርባ ላይ ባሰፈራት ምጥን ሐተታ፤ ‹‹…‹ጉድ ሲናጥ› የሰው ልጅ ሕልውና አፍንጫ ጫፍ ተንጠልጥላ ሁለመና በጠረን ኃይል ስር የሚወድቅበትና እንኳን ሊሞከር ታስቦ የማያውቅ ድንቅ ስራ ነው፡፡›› ይላል፡፡ መጽሐፉ ለህትመት እንደበቃ በጀርመን ሀገር ለ9 ተከታታይ ዓመታት የሽያጭ ሰንጠረዡን ተቆጣጥሮት ነበር፡፡  

Read 1373 times