Monday, 07 February 2022 00:00

አዳም ረታ፤ በይነ - ዲሲፕሊናዊ ንባብ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(2 votes)

     (ክፍል አንድ)
፩. ፍልስፍና
እንደ መነሻ፡ ምዕራባውያን እጅግ የዳበረ የሥነ ጽሑፍ ባህል ስላላቸው በማኅበራዊ ንቃተ ኅሊና ግንባታ ሂደት ትልቁን ሚና ለሚጫወቱት ጸሐፍቶቻቸው የሚሰጡት እውቅና እና ቦታ ከፍ ያለ ነው፡፡ የእነዚህ አገራት የሥነ ጽሑፍ እድገት የአንዱ ትውልድ ጸሐፍት የሌላኛውን ትውልድ ጸሐፍት ሥራ ልዩ ሥፍራ ሰጥቶ የማጥናት ባህሉ እጅግ የዳበረ እንዲሆን ረድቶታል፡፡ ይኸ ባህላቸው የቁሳዊና ሰብአዊ ልህቀታቸው የጀርባ አጥንት ነው፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ከአራት ምዕተ ዓመት በፊት የራሳቸውን ፊደል ቀርፀው ሥነ ጽሑፍን ከጀመሩ ጥንታዊ አገራት ውስጥ አንዷ ብትሆንም፣ በተለያየ ሰበቦች ይህ ሥልጣኔዋ በማሽቆልቆሉ ባለንበት ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ፈፅሞ የማንበብና የመጻፍ ክህሎትን ያልጨበጠ አያሌ ትውልድን በጉያዋ የታቀፈች አገር እንድትሆን ተገድዳለች፡፡ ሥነ ጽሑፉ ያልዳበረ ማኅበረሰብ የአእምሮ ትሩፋቶች የሆኑትን ቅኔን፣ ፍልስፍናን፣ ሥነ ጥበብን፣ ሙዚቃን… ወዘተ ወደ ጎን የሚገፋ ነው፡፡ በተቃራኒው፣ የእንዲህ አይነቱ ማኅበረሰብ ብርቱ ግብ በቁስ መደርጀት ነው፡፡ ርዕዮተ ዓለሙን የሚጽፍበትን ቱባ ቋንቋውን ያዳበረ አገር ከሌሎች አገራት ቀንበር ነፃ ሆኖ በሁለት እግሩ መቆም የሚችል አገር ነው፡፡ ይኸ አይነቱ ማኅበረሰብ ቱባ ፍልስፍናውን፣ ባህሉንና ሃይማኖቱን ይዞ ስለሚኖር ሥነ ልቦናው ከፍ ያለ ነው፡፡ ሥነ ጽሑፉ ያደገ አገር የማንነቱ መገለጫዎች የሆኑትን ፍልስፍናውን፣ ቅኔውን፣ ሃይማኖቱን፣ ኪነ ጥበቡንና ዕደ ጥበቡን ለቀሪው ዓለም ማኅበረሰብ አበርካችም ይሆናል፡፡   
በምዕራቡ አገራት በታላላቅ ደራሲዎቻቸው በእነ ጆሴፍ ኮንራድ፣ ፊዮዶር ዶስቶየቭስኪ፣ ቻርልስ ቦድሌር፣ አልበርት ካሙ፣ ጀምስ ጆይስ፣ ዊሊያም ፎልክነር እና ማርሴል ፕሮስት ሥራ ላይ የተሠሩ ጥናቶች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ በተቃራኒው፣ በኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲዎች ሥራዎች ላይ የተጻፉ ጥናቶችና ሥነ ጽሑፋዊ ሂሶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህም ጥቂት ጥናቶች ለብዙኀኑ ኅብረተሰብ ተደራሽ ያልሆኑ፣ በውጭ አገር ቋንቋ ለኮሌጅ የመመረቂያ ማሟያ ጽሑፍ የተሠሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ታላላቅ ደራሲያን ሥራዎችን በጥልቀት የሚፈክሩ በአገራዊ ቋንቋ ተጽፈው ለህትመት የበቁ ሥራዎች ጥቂት ናቸው፡፡ እነዚህም ሥራዎች ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ናቸው፡- የመጀመሪያው ሥራ፣ በታዋቂው ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ሥራዎች ላይ አተኩሮ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ሕይወትና ክህሎት በሚል ርእስ ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ የሠራው ሥራ ነው፡፡ ሁለተኛው ሥራ፣ በበአሉ ግርማ ሥራዎች ላይ አተኩሮ በአሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ  በሚል ርእስ እንዳለጌታ ከበደ የሠራው ሥራ ነው፡፡ ሦስተኛው ሥራ፣ የታዋቂው ኢትዮጵዊ ባለቅኔ ጸጋዬ ገብረመድኅን ሥራዎች ላይ አተኩሮ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ ሥራዎችና ፍልስፍና በሚል ርእስ ደሳለኝ ሥዩም የሠራው ሥራ ነው፡፡ ሦስተኛው ሥራ፣ በባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ ሥራዎች ላይ አተኩሮ ኢትዮጵያዊነት እምነት፤ ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ በሚል ርእስ ፋሲካ ከበደ የሠራው ሥራ ነው፡፡ አራተኛው ሥራ፣ እንደ ዓለማየሁ ሥራ ሁሉ በደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ላይ አተኩሮ ማስታወሻ በሚል ርእስ ዘነበ ወላ የሠራው ሥራ ነው፡፡ በሚካኤል ሽፈራው የተሠራው ምስጢረኛው ባለቅኔ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን በጸጋዬ ገብረመድኅን የቴአትር ሥራዎች ላይ በማድረጉ (ዘውጉ ሌላ በመሆኑ) ከላይ ከጠቅስኳቸው ሠራዎች ተርታ አልመደብኩትም፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ላይ የተሠሩ ሌሎች ሥራዎች ቢኖሩም አካዳሚያዊ በሆነ መልኩ ስላልተሠሩና የደራሲያኑ ግለ ታሪክ ላይ ስለሚያተኩሩ ከላይ ከጠቅስኳቸው ሥራዎች ተርታ አልመደብኳቸውም፡፡
ሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጽሑፍ ሂስ፣ በይነ-ዲስፕሊናዊ የሆነ አካዳሚያዊ የጥናት ሥራ (interdisciplinary literary study) እና ሥነ ጽሑፋዊ ሀቲት (literary discourse) እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፣ እነዚህ ሦስቱ ተሰናስለው ሲጓዙ አይስተዋልም፡፡ ይኸ የታላቁን ኢትዮጵያዊ ደራሲ አዳም ረታ ሥራዎች የሚዳስሰው ጽሑፍ የእዚህ ቁጭት ውልደት ነው፡፡ ወደፊት (የሚያነበውና የሚጽፈው ህዝባችን አሁን ካለው ግማሽ በመቶ ፈቀቅ ሲል) ሥነ-ጽሑፋችንም አብሮ ይመነደጋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ የአሁኑ ትውልድም፣ ወደፊት በኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ሥራዎች ላይ ብዙ ጥናቶችን ሠርቶ ለንባብ እንደሚያቀርብ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ኀልዮአዊነት (existentialism)  
ኀልዮአዊነት የሥነ ክስተታዊ ሥነ ኑባሬ ንድፈ ሐሳብ፣ የግብረ ገብ አስተምህሮ፣ የሥነ መለኮት አስተምህሮ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብ፣ የፍካሬ ልቡና እና የሲኒማ ንድፈ ሐሳብ ነው፡፡ የእዚህ ፍልስፍና ዋናው ደቀ መዝሙር ፈረንሳዊው ፈላስፋ ዣን-ፖል ሳርተር ነው፡፡ ሳርተር የኀልዮአዊነት ፍልስፍና መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦችን ያቀረበበት ታላቅ የፍልስፍና ሥራው ቢንግ ኤንድ ነቲንግነስ (Being and Nethingness) ይሰኛል። የዚህ መጽሐፍ አንኳር ጭብጦች (core tenet) ንቃተ ኅሊና (consciousness) እና ነፃነት (freedom ) ነው፡፡
የሳርተር የሥነ ክስተታዊ ሥነ ኑባሬ ንድፈ ሐሳብ (phenomenological onology theory) እንደሚነግረን፤ ዓለሙ ውስጥ የሚገኙ ነገሮች (beings) ሁለት አይነት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው፣ ነፃነትን ተጎናፅፎ የተፈጠረው የሰው ልጅ (nethingness) ነው፡፡ ይኸ ፍጡር የተጎናፀፈው ልዩ መለያው ንቃተ ኅሊናው (consciousness) ነው፡፡ ሁለተኛው፣ ንቃተ ኅሊና የሌላቸውና ባሉበት ረግተው የሚዘልቁ ግዑዛን ነገሮች (being) ናቸው፡፡ እንደ ሳርተር እሳቤ፣ ፈጣሪ በህልውና ባለመኖሩ ምክንያት፣ የሰው ልጅ፣ እንደ ግዑዛን ፍጥረታት ቀድሞ የተሠራ ተፈጥሮ (essence) የለውም፤ ዓለሙ ውስጥ ከተከሰተ በኋላ ራሱ ተፈጥሮውን ይሠራል እንጂ (ሳርተር፣ 2007፡ ገጽ 22)፡፡
     አዳም ረታ ከሌሎች የአገራችን ጸሐፍት በተለየ መልኩ በርካታ የኀልዮአዊነት ፍልስፍና ጭብጦችን በጥልቀት የዳሰሰ ደራሲ ነው፡፡ አዳም፣ በድርሰት ሥራዎቹ ውስጥ በጥልቀት ከዳሰሳቸው የኀልዮአዊነት ፍልስፍና ጭብጦች (existential themes) መካከል አንዱ እኩይ እሳቤ (bad faith) ነው፡፡ ይኸን ጭብጥ የምናገኘው ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ በተሰኘው የደራሲው የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ውስጥ በሚገኘው ቀዳዳ በተሰኘው አጭር ልብወለድ ውስጥ ነው፡፡
እንደ ዋናው የኀልዮአዊነት አቀንቃኝ ሳርተር፣ ንቃተ-ኅሊና ያለው የሰው ልጅ (being-for-itself) ከግዑዛን ነገሮች (being-in-itself) በተቃራኒ ምንጊዜም ህልውናውን በፈለገው መልኩ መቀየስ የሚችል ነፃ ፍጡር ነው፡፡ ነፃነት፣ ሳርተር እንደሚነግረን፣ ብቸኛ መገለጫችን በመሆኑ ፈፅሞ ነፃ አለመሆን አንችልም፡፡ ሳርተር እንዲህ ጽፏል፣ “I am condemned to exist forever beyond my essence, beyond the causes and motives of my act. I am condemned to be free” (ሳርተር፣ 1956: ገጽ 439)፡፡ ከእዚህ በተቃራኒ፣ እንደ ሳርተር እሳቤ፣ እኛ እያንዳንዳችን የራሳችን ሕይወት ደራሲያን የመሆናችንን ነባራዊ ሐቅ የምንክድ ከሆነ በእርግጠኝነት በእኩይ እሳቤ ወድቀናል (ሳርተር፣ 2007: ገጽ 47-48)። በተመሳሳይ፣ ቀዳዳ በተሰኘው ልብወለድ ውስጥ የምናገኛት ማርታ የተባለችው ገጸባሕርይ፣ ንቃተ ኅሊናን የተጎናፀናፈች ነፃ ፍጡር መሆኗን በመካድ፣ በእኩይ እሳቤ ወድቃ ራሷን ንቃተ ኅሊና እንደ ጎደላቸውና ተፈጥሯቸው ወይም ባሕርያቸው (essence) በተፈጥሮ ወይም በሌላ አካል ተወስኖሻዊ (determination) እንደሆኑ ፍጡራን (being-in-itself) ቆጥራ ኃላፊነቷን ስትሸሽ እናገኘታለን (አዳም፣ 2003፡ ገጽ 73)፡፡ ይቺ ገጸባሕርይ፣ አስገዶም ከተባለው የሕግ ባሏ ተሸሽጋ ደበበ ከተባለ የልጅነት ወዳጇ (ይኸ ገጸባሕርይ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የሚማር የልብወለዱ ዋና ገጸባሕርይና ተራኪ ነው) ጋር የምትማግጥ ገጸባሕርይ ናት (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 68)፡፡ ማርታ፣ ከደበበ ጋር ወሲባዊ ወዳጅነት የጀመረችው ገና በኮረዳነት እድሜዋ ነበር፡፡ ታዲያ፣ በእዚህ እድሜዋ ነበር ቤተሰቦቿ ለአስገዶም የዳሯት። የማርታ ተድሮ መሄድ የእሷንም የደበበንም ልብ የሰበረ ሐዘን ፈጥሯል፡፡ ይኸ ሐዘን፣ በሁለቱ ወጣቶች መካከል የነበረው ፍቅር ምን ያህል ብርቱ እንደነበር ያሳያል፡፡ ይኸን ሁኔታ አስመልክቶ ዋናው ገጸባሕርይ ደበበ እንዲህ ይተርክልናል፡-
ሰርግ ሲሰረግና ስትዳር፣ አዛው ጎረቤቷ ነኝና አልጋዬ ውሰጥ ገብቼ ወፋፍራም ዕንባዬን አርግፌአለሁ…
የአስመሮም ሚስት ሆና ስትሄድ፣ ልሸኛት፣ ላያት፣ እንዳማረባት ላያት ሰዎች መሐል ተሸሽጌ ሳልዘፍን ሳላጨበጭብ ሳያት፣ በዐይኖቿ ፈልጋ አግኝታኝ አንገቷን ሰብራ ፊቷን በእጇ ቀብራ አለቀሰች፡፡
ማዘጋጃ ቤት የክረምት ሥራ አግኝቼ ስገባ በዛው ቋሚ ሆኜ ቀርቼ ሁለት መቶ ብር በማትሞላ ደሞዜ ሚስቴ አድርጌአት ብኖር እወድ ነበር፡፡
ሁልጊዜ እንድነካት…
ሁልጊዜ አብራኝ እንድትሆን…
ሁለታችንም ከሁለቱ አንዱ ወይም ሁለቱ አልነበሩንም፡፡ ሐሞት ወይም/እና ዕድል፡፡ በሚያዚያ ተድራ ሰፈር ለውጣ ፖፖላሬ ስትገባ መስከረም ጠባና ኢ ኤስ ኤል ሲ አልፌ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተመዝግቤ ገባሁ፡፡ ሁሉ ነገር እንደ ፈረሰ ቢገባኝም ልቤ ግን ሁሌ ያልማታል (አዳም፣ 2003፡ ገጽ 70)፡፡
የማርታ እኩይ እሳቤ፣ ዓላማው ወደ ህልውና ስንመጣ የተጎናፀፍነውን ነፃነትና ኃላፊነት በመገንዘባችን ምክንያት የሚከሰተውን ጭንቀት (anguish) መሸሽ ነው፡፡ ሳርተር እንደሚነግረን፣ እኛ ሰዎች ንቃተ ኅሊና ያለን ነፃ ፍጡራን በመሆናችን የሁሉም ተግባሮቻችን ተጠያቂዎች ነን፡፡ ታዲያ፣ ከዚህ ነባራዊ ሐቅ ጋር መላተማችን ውስጣችን ፅኑ የጭንቀት ስሜት እንዲበቅል ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም፣ እንደ ኢ-አማኙ ሳርተር፣ በዚህ ፈጣሪ አልባ ፅንፈ-ዓለም (universe) ያለ አጋዥ በባይተዋርነት የምንኖር እኛ የሰው ልጆች የቱ ድርጊት ሰናይ፣ የቱ ድርጊት እኩይ እንደሆነ የሚበይንልን አካል ፈፅሞ የለም፡፡ ይኸ እሳቤ፣ የሳርተር ፍልስፍና መደላድል ሲሆን ፍልስፍናዊ ፅንሰ ሐሳቡም ባይተዋርነት (abandonment) ይሰኛል፡፡ ይኸ የሳርተር ፍልስፍና፣ ኀልዮአዊ ሰብአዊነት (existential humanism) ተብሎ የሚጠራው  ፍልስፍናውም መነሻ ነው፡፡ እንደ ሳርተር እሳቤ፣ ሰናይና እኩይ የምንላቸው እሴቶች ብቸኛው ፈብራኪ (inventor) እኛ እያንዳንዳችን ነን፡፡ በሌላ አገላለፅ፣ የቱ ተግባር ሰናይ እንደሆነም ሆነ፣ የቱ ተግባር እኩይ እንደሆነ ቀድሞ የወሰነልን አካል ባለመኖሩ እኩይና ሰናይ የምንላቸውን እሴቶች የመፈብረኩ ኃላፊነት ጫንቃችን ላይ የወደቀ ነው፡፡ ይኸ ፈፅሞ መሸሽ የማይቻል ኃላፊነታችን ፍፁም ነፃ ፍጡራን የመሆናችንን ሐቅ የሚያስረግጥ ነው፡፡ ጭንቀት፣ ይኸ በየትኛውም መንገድ ልንሸሸው የማንችለው ሐቅ የወለደው ስሜት ነው፡፡ ከዚህ ሐቅ ጋር መጋፈጣችን ሁለት አይነት ሰብዕናዎችን ወይም ባሕርዮችን እንድናዳብር ሰበብ ይሆናል። የመጀመሪያው ባሕርይ፣ ፈፅሞ መሸሽ የማንችለውን ነፃነታችንንና ኃላፊነታችንን ሙሉ በሙሉ በመቀበል የሚገለፅ ነው፡፡ ይኸ አይነቱ ግላዊ ሰብዕና ወይም ባሕርይ እውነተኝነት (authenticity) ይሰኛል፡፡ ይኸ አይነት ሰብዕና ወይም ባሕርይ ያለው ግለሰብ፣ ለሁሉም ድርጊቶቹ ግብረ መልስ (consequence) ሌሎች አካላት (ፈጣሪ፣ ማኅበረሰብ፣ ተፈጥሮ …ወዘተ) ላይ ጣቱን ከመቀሰር ተቆጥቦ፣ የእያንዳንዱ ውሳኔው ባለዕዳ ራሱ ብቻ መሆኑን አምኖ ይቀበላል፤ ራሱንም ንቃተ ኅሊና እና ነፃነት እንደ ጎደላቸው ግዑዛን ፍጥረታት አይቆጥርም። በተጨማሪም፣ እውነተኛ (authentic) ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ የፈበረከውን የግብረ ገብ እሴትና እውነት (impersonal value system and truth) ተውሶ ኑሮውን አይገፋም፤ የራሱን እሴት ፈብርኮ ይኖራል እንጂ፡፡ ሁለተኛው፣ ባሕርይ፣ የሰው ልጅ ልክ እንደ ድንጋይ፣ ጠረጴዛ ወይም ሐውልት ነፃነት የሌለው ግዑዝ ፍጥረት ነው ብሎ ራስን በመሸንገል (dissimulation) የሚገለፅ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ይኸ አይነቱን እኩይ ሰብዕና ወይም ባሕርይ ያዳበረ ሰው በህልውናው ለተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ ብቸኛው ባለሥልጣን እሱ ራሱ የመሆኑን ሐቅ ይሸሻል፡፡  
ምንም እንኳ ማርታ፣ በእኩይ እሳቤ አማካኝነት፣ የተጎናፀፈችውን ነፃነት ለመሸሽ እንደ ስትራቴጂ ብትጠቀምበትም፣ ንቃተ ኅሊናን የተቸረች ፍጡር በመሆኗ ቤተሰቦቿም ሆነ ባሏ አስገዶም ያቀረበላትን የጋብቻ ጥያቄ ውድቅ የማድረግም ሆነ የመቀበል ምርጫዋ በእጇ ነበር፡፡ ከታሪኩ እንደምናነበው፣ እሷ ግን፣ ለውሳኔዎቿ ሁሉ ‘ከደሙ ነፃ ነኝ’ በሚል ብሂል ራሷን በመዋሸት፣ እንድታገባ የገፋፏትን ሰዎች ስትወነጅል እናገኛታለን፡፡   
ልጅነታችን የተፃፈባት ጠይም ልቧ ገና እንዳልሞተች ሁለታችንም እናውቃለን።  በፈገግታ ተያይተን ዝም አልን፡፡ ወደ ውጭ በመስኮት እያየች በምትጠልቀው ፀሐይ እንደተመሰጠች … የምትወደው ሐሳብ ውስጥ ራሷን እንደረሳች ሁሉ … እግሮቿን በመጠኑ አንፈራጣ እጆቿን ከመሐላቸው ጣል አደረገች፡፡ እስከ አሁን አልተቀመጥኩም፡፡ ገላዬና ልቤ ለየብቻ ናቸው፡፡  
ዛሬ የሆነውን ሰማህ?
ምን?
ስለ ማዘጋጃ ቤት
አዎ አዎ አይተሽዋል? ግማሹ ፈርሷል አሉ?
ማነው ግማሹ ነው ያለው? ክንፍ የሚመስለው አንደኛው የለም? መሐሉ ተቦድሷል፡፡ ጨካኞች ናቸው፡፡ እንደዚህ ያደርጋሉ? አሁን ሰው ቢሞትስ?
ሰው አልሞተም?
የሞተ አይመስለኝም
ለእኔ፣ ከድምፁ… እዚህ ድረስ ነው የተሰማው… የፈረሰ ነው የመሰለኝ
ክረምት ክረምት ማዘጋጃ ቤት ትሠራ ነበር?
አዎ ምነው?
ዛሬም እዚያ የምትሠራ መሰለኝ
ክረምት አይደለም አሁን
መሰለኝ    
እንዴት?
አንተ ላይ የፈነዳ መሰለኝ፡፡ ሞኝ ነኝ?
ዓይኖቿ ዕንባ እንዳቀረሩ ከተቀመጠችበት ተነስታ ክንዶቿን አንገቴ ዙርያ ጠመጠመች።  በሕይወት መኖሬን ካላወቀች እንዴት በር ላይ መልእክት ትተዋለች? ትዳር መያዟ እያግደረደራት ይሆን? እንዲህም ልላት አልፈለኩም፡፡
አንተ የሞትክ ሁሉ መሰለኝ … እህ … እህ… ማለት ጀመረች፡፡
አቅፌ ደግፌ ያዝኳትና ወደ አልጋው ወስጄ አስቀመጥኳት፡፡ ዓይኖቼን ማየት የፈራች አይነት አንገቷን ከሰበረችበት አላቃናችም፡፡
ተሳሳትኩ አለችኝ፡፡
ስህተቷ ምን እንደሆነ አልጠየቅኳትም፡፡ ለደቂቃዎች ያህል በዝምታ ቆየን፡፡ ወለል ወለል እያየች፣ ከነጩ ሸክላ ላይ በደንብ ያልተጻፈ የተደበቀ ቃል እንደምታነብ ሁሉ ቀስ ብላ፡
እወድሃለሁ
ቀና ብላ አየችኝ፡፡ ዐይኖቿ በከፊል ተከድነዋል፡፡ ሽፋሽፍቶቿ በዕንባዋ ዕርጥበት ተሳስረው፡፡ ምን እንደምመልስላት አላውቅም … ምን መናገር እንዳለብኝ አላውቅም፡፡
አሁን ባለትዳር ነሽ
ባልወለድ ይሻለኝ ነበር
ለምን አገባሽ? ገና ልጅ ነሽ
ጓደኞቼና ቤተሰቦቼ
ምን አደረጉሽ?
አልነገርኩህም፡፡ አለ አይደለ ‘ያገርሽን ልጅ ምናምን ካልሆነ አታገቢም፡፡ ደሞ አግብተሽም መማር ትችያለሽ’ ምናምን ሲሉኝ ትክክል የመከሩኝ መሰለኝ፡፡ ያልነገርኩህ አፍሬ ነው፡፡
እና ባልሽን አትወጂውም?
አልወደውም ግን ለምጄው ይሆናል
ምንድነው እሱ መልመድ? ሰው ለምን ትሰሚያለሽ?
መጀመሪያ አልገባኝም፡፡ ትንሽ ሲቆይ ገባኝ፡፡ ማዘጋጃ ቤት ሲፈነዳ ግን ትዝ ያልከኝ አንተ ነህ፡፡
በየዋሕነቷ ለመሳቅ ነው መሰለኝ ለትንሽ ጊዜ ፊቷን ጋርዳ ተንከተከተችና፡
ብቻ አንተ ትዝ አልከኝ፡፡
ቀና ባላ አየችኝና… ፊቷን ትከሻዬ ላይ አደረገች፡፡ አቀፍኳት፡፡ የእኔ መሆን እንዳቆመች ይገባኛል፡፡ ቀን ጠብቆ ትወልዳለች፡፡ ቀኑ ይመጣል፡፡ የሚዋዥቀው ልቧ ይረጋል፡፡ አጨብጭባ እንደ ገባች አጨብጭባ ወሙጣት እንደማትችል ታውቃለች፡፡ ምናልባት ያስፈራት ይሄ ይሆናል፡፡ የነገሩ… የትዳሩ ሳትጠብቀውና ሳታስበው ‘ፍፁም’ እየሆነ መምጣት፡፡ ትዳር ከሌሎች ወንዶች መገለል እንደሆነ በትንሹ ይገባታል፡፡ የባሏ ወዳጅ በነበረች ጊዜ የጣሟት ቀኖች ለዘላለም የሚዘልቁ መስሏት ነበር፡፡ የዘላለም ሰው የለም፡፡ የዘላለም ጣፋጭ ጣዕም የለም፡፡ እንዳጣኋት አውቃለሁ፡፡ በእኔና በእሷ መሐል ሰፊ ጥልቅ ወንዝ ይፈሳል፡፡ ያለፈውን የልጅነታችንን (ልጅነት ምንድን ነው?) እያነሳን የናፍቆት ዘገባ ከመለዋወጥ፣ ዳርና ዳር ቆመን እየተጠራራን ስለ ተፈፀመ ጉዳዳይ ከማለም የሚተርፈን ‘ምንም’ ነው፡፡ ወይስ ትዳር ባልና ሚስት የተለያየ ትርጉም ይዘው የሚሰፈሩበት እንደውጫሌ ውል የተገነባ ነገር ነው?
ለምን ጓደኞችሽ ወደዱት?
ትልቅ ሥራ አለው፤ ደሞ የአባባና የእማማ አገር ሰው ነው፡፡ እና የእሱ አባትና አባቴ ድሮ ደቀመሐሪ አብረው አፈር ፈጭተው ያደጉ ናቸው፡፡
እና፡፡ ከአስመሮም ጋር ፈጭተሻል እንዴ? የፈጨንስ እኔና አንቺ፡፡
ሂሂሂ … እኔ ላይ ክፉ አይደለም እስከ አሁን፡፡ ትንሽ ግን ይነጫነጫል፣ ይቀናል (አዳም፣ 2003፡ ገጽ 72-74) ፡፡
(ይቀጥላል)


Read 5728 times