Print this page
Tuesday, 08 February 2022 17:44

8 ቢ. ብር የወጣበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ በመጪው እሁድ ይመረቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ8 ቢ. ብር ገደማ አዲስ ያስገነባውን ባለ 53 ወለል ህንጻ ዋና መስሪያ ቤት በመጪው እሁድ ያስመርቃል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልና የአዲሱን ዋና መ/ቤት ምርቃት በዓልን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በ1942 ዓ.ም  በ43 ሰራተኞችና በሁለት ቅርንጫፍ ስራውን የጀመረው ባንኩ፤ የ80 አመት ጉዞውን የሚያሳይ ባለ53 ወለል ህንጻ ገንብቶ ለምረቃ ማብቃቱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፤ ፕሬዚዳንቱ።
ስምንት ቢሊዮን ብር ገደማ የወጣበትና ሰባት ዓመት የፈጀው አዲሱ ዘመናዊ ህንጻ፤በተለያዩ ቦታዎች ተበታታትነው ይሰሩ የነበሩ ከአምስት ሺህ በላይ የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ሰራተኞችን በአንድ ላይ የሚያሰባስብ ነው ተብሏል። የባንኩ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ስራ አስኪያጆችና ሌሎችም ሰራተኞች ከሁለተኛ እስከ 46ኛ ባሉት ወለሎች ላይ እንደሚደለደሉም ታውቋል፡፡
የህንጻው 47ኛ ወለል ለሬስቶራንት አገልግሎት የሚውል ሲሆን፤ 48ኛው ደግሞ ከአራቱም አቅጣጫ ከተማዋን ለማሳየት በሚያስችል መልኩ እንደገና ዲዛይን ተደርጎ ተገንብቷል። የዋና መስሪያ ቤቱ ህንጻ፤ ለ1,500 መኪኖች ማቆሚያነት የሚያገለግሉ ከምድር በታች የተገነቡ አራት ወለሎች አሉት።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲሱ ዋና መስሪያ ቤት፤ ከዋናው ህንጻ በተጨማሪ ስድስትና ስምንት ፎቆች ያሏቸው ሁለት ተደራቢ ሕንፃዎችን ይዟል። በአንደኛው ተደራቢ ህንጻ ሁለት ሺህ ሰዎች ማስተናገድ የሚችል ሰፊ የስብሰባ አዳራሽ ተገንብቷል።
ተደራቢ ህንጻው እያንዳንዳቸው 300 ሰዎች የሚይዙ ሁለት አዳራሾች እና እያንዳንዳቸው 200 ሰዎች የሚያስተናግዱ አምስት የስብሰባ አዳራሾችንም በተጨማሪነት አካትቷል። በዚሁ ህንጻ ላይ መደበኛ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥበት ቅርንጫፍ ይኖራልም ተብሏል።
ሁለተኛው ተደራቢ የህንጻ ክፍል ደግሞ፤ ለተለያዩ የንግድ ስራዎች ማለትም ለሬስቶራንቶች፣ ለንግድ ሱቆች፣ ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ፣ ለህፃናት ማቆያ የሚሆኑ ቦታዎችን የያዘ ነው። ይህ ተደራቢ ህንጻ ስድስት ያህል ሲኒማ ቤቶች በውስጡ እንደሚኖሩትም “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር”  የባንኩን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም ታደሰን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
አሁን ላይ ባንኩ ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንዳለው የገለጹት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ፤ ለግብርና፣ ለመስኖ፣ ለኮንስትራክሽን መሳሪያዎች፣ በአጠቃላይ ለወሳኝ አገራዊ የመሰረተ ልማት አውታሮች ቁልፍ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።

Read 6547 times
Administrator

Latest from Administrator