Wednesday, 09 February 2022 10:33

በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ ከ1 ቢ. በላይ ብር ያስፈልጋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ ከ1 ቢሊዮን በላይ ብር ያስፈልጋል ተባለ፡፡ ላሊበላ፣ ሁመራ፣ ወልቃይትና ሰቆጣ አካባቢዎች አሁንም ኤሌክትሪክ እያገኙ አይደለም ተብሏል።
በጦርነቱ ምክንያት 231 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሀይል እንደባከነበትም ተቋሙ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት፣ በአማራና አፋር ክልሎች ባደረሰው ጉዳት ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ሀላፊ አቶ ሞገስ መኮንን በመግለጫው ላይ እንዳሉት፤ ህወሓት በከፈተው ጦርነት ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ንብረቶች ዘረፋና ውድመት ደርሷል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቱን ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት ቁመና ለመመለስ 23 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ 1 ቢሊዮን በላይ ብር እንደሚያስፈልም አቶ ሞገስ ተናግረዋል ።
ህወሓት በሁለቱ ክልሎች በከፈተው ጦርነት በርካታ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ከመውደሙ ባለፈ 231 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሀይል ሳይሸጥ መባከኑንም አቶ ሞገስ አክለዋል።
የህወሓት ሀይል ከአፋርና አማራ ክልሎች አብዛኛው ቦታዎች ተገዶ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ፣ አብዛኛዎቹ ቦታዎች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማድረግ ቢቻልም፣ አሁንም ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ አካባቢዎች እንዳሉም ተገልጿል።
በወልቃይት፣ በሁመራ፣ በላሊበላና በሰቆጣ አካባቢዎች እንዲሁም በአፋር ክልል ዞን ሁለት አሁንም ኤሌክትሪክ እያገኙ አይደለም ብለዋል አቶ ሞገስ።
ወልቃይትና ሁመራን መሰል አካባቢዎች ኃይል በዋናነት በሽሬ መስመር ከትግራይ ያገኙ የነበረ መሆኑ የተቋረጠውን የኃይል አቅርቦት በቶሎ ለመመለስ እንዳላስቻለም ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡
በአፋር አሁንም ጦርነት ያለ መሆኑ በተመሳሳይ መልኩ የኃይል አቅርቦቱን በቶሎ ለመመለስ እንዳላስቻለም ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በአማራና በአፋር ክልሎች ካለው የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት 53 በመቶ ያህሉ በጦርነቱ መውደሙም ተገልጿል፤ ዐልአይን እንደዘገበው፡፡

Read 4867 times