Print this page
Thursday, 10 February 2022 18:52

በ28 ብር ኤሌክትሪክ፣ 320 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ መኪና!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

•  ጃን፣ ሶላር፣ አና፣ አኪ እና ሰብሪና እየመጡ ነው

ጃን፣ አና፣ ሶላር፣ አኪ እና ሰብሪና መኪኖች ናቸው… ሁሉም ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክና በጸሐይ ብርሃን ሃይል የሚሰሩና በቅርቡ በአገራችን ጎዳናዎች ላይ እንደ ውሃ ፍስስ ሲሉ ይታያሉ የተባሉ ዘመን አፈራሽ አውቶሞቢሎች ናቸው፡፡
በተፈጥሮ ሃይል ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ግሪን ቴክ አፍሪካ የተባለው ኩባንያ፣ በቅርቡ ለገበያ ሊያቀርባቸው ያቀዳቸውን አዳዲስ መኪኖቹን ለመገናኛ ብዙኃን ባስተዋወቀበት መርሃ ግብር ላይ እንደተነገረው፣ በኤሌክትሪክና በጸሃይ ሃይል የሚሰሩት እነዚህ ዘመናዊ መኪኖች የመሸጫ ዋጋቸው ተመጣጣኝ ከመሆኑ ባሻገር፣ ከነዳጅና ከጥገና ወጪ የሚገላግሉ ናቸው፡፡
በቻይናው ዶንፊንግ ኩባንያ በአውሮፓ የጥራት ደረጃ የተመረቱት መኪኖቹ፤ በቤት ውስጥና በቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላት እጅግ አነስተኛ በሆነ ወጪ የኤሌክትሪክ ሃይል እየተሞሉና የጸሃይ ብርሃን ሃይልን እየተጠቀሙ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችሉ ናቸው፡፡
እነዚህ ዘመናዊ መኪኖች፣ ከነዳጅ ተጠቃሚ መኪኖች ጋር ሲነጻጸር፣ በእጅግ አነስተኛ ወጪ ረጅም ርቀት የሚጓዙ ሲሆን፣ ወጪው እንደ መኪኖቹ ሞዴል የተለያየ ቢሆንም፣ ለአብነት ያህል የአንደኛውን ሞዴል መኪና አቅም ብቻ እንጥቀስ፡፡
ዛሬ ማለዳ ከሃላፊዎቹ እንደተነገረን፤ ኩባንያው ለገበያ የሚያቀርበው በኤሌክትሪክ ሃይል የሚንቀሳቀስ 23 ሰዎችን የሚጭን መካከለኛ መጠን ያለው አውቶቡስ፣ በ28 ብር የኤሌክትሪክ ሃይል በአማካይ 320 ኪሎ ሜትር ያህል ሊጓዝ ይችላል፡፡
ኩባንያው መኪኖቹን በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰቡ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ በቅርቡ መሸጥ የሚጀምር ሲሆን፣ አፍሪካን ቪሌጅ ፋይናንሺያል ሰርቪስ ከተባለ የገንዘብ ተቋም ጋር በመተባበርም ለገዢዎች የብድር አገልግሎት ለማቅረብ ተዘጋጅቷል፡፡
ግሪን ቴክ አፍሪካ ከቻይና የሚያስመጣቸው እነዚህ ዘመናዊ መኪኖች፣ በካይ ጋዝ ስለማያመነጩ አካባቢን የማይጎዱ ሲሆኑ፣ ኩባንያው በቀጣይ መኪኖቹን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም ማቀዱንና ግሪን ትራንስፖርት ከተሰኘው እህት ኩባንያው ጋር በመተባበር በኤሌክትሪክና በጸሃይ ሃይል የሚሰሩ መኪኖችን ለታክሲና ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለማዋል በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ነው የተነገረው፡፡

Read 3821 times Last modified on Friday, 11 February 2022 08:44
Administrator

Latest from Administrator